ፍርድ ቤቱ ፈጣን እልባት ለመስጠት የሚያስችል አሠራር መዘርጋቱን ገለጸ

አዲስ አበባ:- የተቀዱ ክርክሮችን ወደ ጽሁፍ ለመቀየር የሚያስችል ሶፍት ዌር በማበልጸግ ወደ ተግባር በማስገባቱ የሥራ ጫና መቀነሱን፣ መዝገቦች በተያዘላቸው ጊዜ እልባት እንዲያገኙ ማገዙን የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ገለጸ።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ እና የ2017 ዓ.ም እቅድ ትውውቅ መርሀ ግብር ትናንት ባካሄደበት ወቅት፤ የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሌሊሴ ደሳለኝ፤ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግ የዳኝነትን አገልግሎት ቅልጥፍና ለማሳደግ እና ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

ከአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ጋር በመተባበር የተቀዱ ክርክሮችን ወደ ጽሁፍ ለመቀየር የሚያስችል ሶፍት ዌር በማበልጸግ ተግባራዊ የተደረገው አሰራር የዳኝነት አገልግሎት ቅልጥፍናን ማሳደግ መቻሉን ጠቁመዋል።

የሥራ ጫናን መቀነስ አስችሏል፣ መዝገቦች በተያዘላቸው ጊዜ ዕልባት እንዲያገኙ በማድረግ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።አሠራሩ ሳይዘረጋ በመቆየቱ ተገልጋዮች በቃል ያደረጓቸው ክርክሮች ወደ ጽሁፍ እስኪገለበጡ ብዙ ጊዜ ለመጠበቅ ይጉላሉ እንደነበርም ነው የጠቆሙት፡፡

በ2017 ዓ.ም ስድስት ችሎቶች ላይ ስማርት ችሎቶችን ለማደራጀት ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ በመጠቆምም፤ ለተግባሩ ምቹ የማድረግ ሥራ መሠራቱንም ወይዘሮ ሌሊሴ ተናግረዋል።

ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የዳኝነት አገልግሎት ተደራሽነትን ማሳደግ ትኩረት ይደረግበታል ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ በቪዲዮ ኮንፈረንስ የሚሰጥ የዳኝነት አገልግሎት ማጠናከር፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ድምጽን ወደ ጽሁፍ የመቀየር አገልግሎት ማስፋፋት፤ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ዘመናዊ የመረጃ አያያዝን ሥርዓት ማጠናከር ከትግበራዎቹ መካከል እንደሚጠቀሱም ነው የገለጹት።

ዳኞች መደበኛ የሥራ ጊዜ ዝግ በሆነበት ነሐሴና መስከረም ወራቶች በዕረፍት ጊዜያቸው በመጠቀም ለሁለት ሺህ 485 መዛግብት እልባት መስጠት መቻላቸውንም ነው የጠቆሙት።

የዳኞችን ነጻነት እና ገለልተኝነትን የሚሸረሽሩ ተግባራትን ለመከላከል ትኩረት መደረጉንም ወይዘሮ ሌሊሴ አመልክተዋል። የዳኝነት ነጻነት ሊሸረሽሩ የሚችሉ ህጎችን በተመለከተ የዳሰሳ ጥናት ለማከናወን መታቀዱም ተጠቅሷል።

ለፍርድ ቤቱ አገልግሎት የሚመደበው በጀት ፍላጎትን ያሟላ አለመሆኑ፤ በግልጽ ችሎት ለማስቻል በቂ የቢሮና የማስቻያ አዳራሽ አለመኖር፤ ያሉ የችሎት አዳራሾች በእድሜ ብዛት (በእርጅና) ምክንያት ለተገልጋዮችና ለዳኞች ምቹ አለመሆንና በአፋጣኝ እድሳት የሚፈልጉ መሆናቸው ካጋጠሙ ተግዳሮቶች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የዳኞችና የመዝገብ ጥምርታ አለመመጣጠንና የዳኞች እጥረት፤ የአስተዳደር ሠራተኞች አለመሟላት፣ በአንዳንድ ዳኞችና ሠራተኞች ተቀራራቢ አመለካከት፣ እውቀት፣ ክህሎትና በቁርጠኝነት የመፈጸም ውስንነት መኖር ፈተና እንደነበርም ነው የተገለጸው።

የ2016 በጀት ዓመት 30 ሺ መዛግብትን ለመፈጸም ታቅዶ እንደነበር አስታውሰዋል። ሆኖም የዳኞች ቁጥር በቂ ባለመሆኑ ምክንያት እቅዱን በመከለስ 20 ሺ 784 መዝገቦች እንዲሠሩ ታቅዶ 24 ሺ 853 መዛግብት ላይ እልባት ተሰጥቷል ብለዋል። ወደ ተያዘው በጀት ዓመት የተሻገሩ ሰባት ሺህ 136 መዛግብት መኖራቸውንም አመልክተዋል።

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You