ከዓለም እስከ አህጉር፣ ከአህጉር እስከ ሀገር፣ ከሀገር እስከ ማህበረሰብ ብሎም እስከ ግለሰብ፣ ከትልቅ እስከ ትንሽ በእግር ኳስ ልቡ ያልተሳበና ለእግር ኳስ ፍቅር ያልተንበረከከ የለም። በርካቶች «በማራኪነቱ፤ በልብ ሰቃይነቱ፤ በአስፈንዳቂነቱም ሆነ በአሳዛኝነቱ ወደር አይገኘለትም» ሲሉ የሚመሰክሩለት እግር ኳስ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅጉን ተቀባይ የሰላምና የፍቅር ስፖርት መሆኑንም ሳያቅማሙ ይስማሙበታል።
እንደ ሌሎች የስፖርት አይነቶች ሁሉ ተወዳጁ እግር ኳስም በዳኞች ውሳኔ ላይ እምነት ያሳደረና ውሳኔያቸውም ከበሬታና ሙሉ ሥልጣን የተሰጠው ነው። ዳኝነት በጣም ከባድ ሙያና ከባድ ሃላፊነት ይጠይቃል። ለስፖርቱ ሳቢነት፣ ማራኪነት ተወዳጅነት፤ እንዲሁም በጨዋታ ለሚገኘው ውጤት የዳኞች ጨዋታን የመምራትና የውሳኔ አሰጣጥ ብቃት እጅግ ወሳኝ ነው። ዳኞች በቅፅበታዊ ውሳኔና ፍርድ እግር ኳስን ሊገድሏትም ሆነ ሕይወት ሊዘሩባት ይችላሉ።
ለተወዳጁ ስፖርት እንደ ወይን እየጣፈጠ ዓመታትን መቀጠልም የዳኞች ሚና በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም። አፍቃሪ እግር ኳሶችም በሜዳው ላይ ፍልሚያ ቀልባቸው የሚሳበው፤ በስፖርቱ ፍቅር የሚንበረከኩት አሊያም የሚዝናኑት፤ በማይታመኑ፣ በማይጠበቁ ልብ ሰቃይ፤ አስፈንዳቂና አሳዛኝ ክስተቶች ውጤቶች ብቻ አይደለም። በዳኞች ውሳኔ አሰጣጥ ጭምር ነው።
ቀደም ባሉት ዘመናት የጨዋታ ሕግ ማስከበሪያ መሣሪያ ባለመኖሩ ዳኞች የሜዳ ላይ ክስተቶችና በጨዋታው መሃል የሚፈጠሩ ክስተቶችን ተመርኩዘው ውሳኔ የሚሰጡት አስገራሚ በሆነ መልኩ ነበር። ጥንት የእግር ኳስ ውድድር ሲደረግ ዳኞች አማካይ የሆነ ቦታ ተፈልጎላቸው በትሪቡን መሐል ተቀምጠው ይዳኙ ነበር። ይሁንና በዚህ ዓይነት ጨዋታን መምራት ጥፋቶች ለመመልከትና ለመቆጣጠር ምቾት የሚሠጥ አይደለም በመባሉ ዳኞች ሜዳ ገብተው ጨዋታን እንዲመሩ ተደርጓል።
በዘመኑም ዳኞች ውድድሮችን የሚመሩት በፊሽካ በመጠቀም ሳይሆን በማጨብጨብ፣ በመጮህና ጨዋታውን አስቁመው በመጣራት ሲሆን፤ ይህ ዓይነቱ ዳኝነትም አስቸጋሪና አድካሚ በመሆኑ ተለውጦ ቃጭል ወይም ትንሽ ደውል በማንቃጨል ጨዋታውን መምራት እንደ አማራጭ ሆኖ ቀርቧል። ይህን አማራጭ በመከተል ዳኞች ጨዋታን በመምራት ሂደት ጥፋትን ጨምሮ ሌሎችን ውሳኔዎችን ለማሳለፍ እየተሯሯጡ በትንሽ ደውል ቃጭል ቢያንቃጭሉም ሰሚ ግን አልነበራቸውም።
ይሁንና በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ እንግሊዛዊው ጆሴፍ ሁድሰን ፊሽካን ለዓለም ማስተዋወቁን ተክተሎ በትንሽ ደውል ቃጭል እያንቃጨሉ እግር ኳስን የመምራት ታሪክ ተቋጨ። በእርግጥ ቀደም ባሉት ዓመታት ዘመናዊም ባይሆን ፊሽካዎች መኖራቸው አይካድም።
ይሁንና የፊሽካ ግልጋሎት በተለይ ከጥንታዊው የግሪክ ሥልጣኔ ጀምሮ የዘውድ ቤተመንግሥት ወይንም ከተማ ጠባቂዎች ድንገተኛ ጠላት በሚታያቸው ወቅት ሠራዊትና ሕዝቡን ለማንቃት፤ ለማስጠንቀቅ ብሎም ለማስታጠቅ ይጠቀሙበት እንጂ የእግር ኳስን ሕግ ለማስከበር ጥቅም ላይ አልዋለም።
ምስጋና «የፊሽካው ፈጣሪ» የሚል ስያሜን ላገኘው ጆሴፍ ሁድሰን ይሁንና ፊሽካ በእንግሊዝ ሀገር በርሚንግሃም የእግር ኳስ ዳኞች የጨዋታ ሕግ ማስከበሪያ መሣሪያ ለመሆን በቅቷል። ለመጀመሪያ ጊዜ እግርኳስ ጨዋታን ለመምራት ጥቅም ላይ የዋለውም እኤአ 1878 /79 የውድድር ዓመት በተካሄደው በፉትቦል አሶሴሽን ካፕ በኖቲንግሃም ፎረስት እና በሼፊልድ ክለቦች ጨዋታ ስለመሆኑ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።
የእግር ኳስን ሕግ ለማስከበር ጥቅም ላይ ከዋለው ፊሽካ የምትወጣው ይህች ድምፅ አስደንጋጭም፣ አስደሳችም አሳዛኝም ናት። በርካቶችን ልባቸው ቀጥ እስኪል ባሉበት እንዲቀሩ ምክንያት ሆናለች። አንዳንዶችን በድንጋጤ አድርቃ እስከ ወዲያኛው ላይመለሱ ሸኝታለች። ይህች ድምፅ ጥቂት የማይባሉትን ደግሞ በሕይወት ዘመን አንዴ ከሚከሰትና ከማይደገም ጮቤ ጋር ውላ አሳድራለች።
በአሁኑ ወቅት ግልጋሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት የፊሽካ አይነት ዲዛይኖች ይፋ የሆኑት እኤአ 1884 በጆሴፍ ሁድሰን አማካኝነት ነው። ቀደም ሲል ከተሠራው በድምፅም ሆነ በጥራት ዘመናዊ የሆነውን ይህን ፊሽካም ዜግነቱ የኒውዝላንድ የሆነው ዊሊያም አታክ የተባለ ግለሰብ እኤአ 1884 በተካሄደ በራግቢ ጨዋታ ላይ ተጠቅሞታል።
ይህም ግለሰብ ዘመናዊውን የእግር ኳስ ፊሽካ በመጠቀም ስፖርታዊ ጨዋታን በመምራት በታሪክ የመጀመሪያው ዳኛ አድርጎታል። በአሁኑ ወቅት ትንሽየዋ ክብ መሳይ ከብረት፤ ከፕላስቲክ አሊያም ከእንጨት የምትሠራው ፊሽካ በማምረት Fox 40 የተባለን ድርጅት የሚስተካከሉት ይቆጠሩ ቢባል ከአንድ እጅ ጣት አይበልጡም።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2017 ዓ.ም