አዲስ አበባ፡- ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የወርቅ ምርትን በከፍተኛ መጠን እያሳደገ መሆኑን የማዕድን ሚኒስቴር አስታወቀ። ባህላዊ የማዕድን ቆፋሮን በማዘመን የምርት ብክነትን በመቀነስ ምርታማነትን የማሳደግ ሥራም እየተሠራ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።
የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ለኢትዮያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ መንግሥት ተግባራዊ እያደረገው የሚገኘው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የማዕድናት ምርታማነትን በተለይ የወርቅ ምርትን በከፍተኛ ሁኔታ እያሳደገ ነው።
ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በአነስተኛ ደረጃ ይመረት የነበረው የማዕድን ምርት በከፍተኛ መጠን እያሳደገው ነው፤ በተለይም የወርቅ ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ማሻሻያውን ምክንያት በማድረግ በተያዘው በጀት ዓመት ስምንት ነጥብ ስድስት ቶን ወርቅ ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል።
በዚህም ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ የእቅዱን 70 በመቶ ማሳካት መቻሉን ጠቁመው፤ማሻሻያው የማዕድናት አምራቾችን ተጠቃሚ እያደረጋቸው በመሆኑ የተሻሉ ማሽነሪዎችንና ቴክኖሎጂዎችን ገዝተው ወደ ምርት ሂደቱ እየገቡ መሆኑን ገልጸዋል።
የተሻሉ ማሽነሪዎችንና ቴክኖሎጂ መጠቀማቸውም የምርትና የጉልበት ብክነትን በመቀነስ የማዕድን ምርትና ምርታማነት በከፍተኛ ሁኔታ እያሳደገ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ሀገሪቱ ሰፊ የማዕድን ሀብት አላት፤ ያላት ማዕድን ሀብት ለማልማት የህግ ማዕቀፎችንና ፖሊሲዎችን የማሻሻል፤ ተቋማዊ ለውጦችን የማድረግ ሥራ ተሠርቷል ያሉት አቶ ሚሊዮን፤ማዕድናትን በባህላዊና በኢንዱስትሪ በማምረት ምርታማነትን የማሳደግ፤ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ማሳደግና አምራቾች ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሠራ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የማዕድን ሀብት አልምቶ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንድታገኝ ለማድረግ ባለፉት ስድስት ዓመታት ካፒታል የማከማቸት፤ አዳዲስ የልማት አቅጣጫን የመከተል ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ቀደም ሲል መንግሥት ልዩ ትኩረት ከሚሰጣቸው ዘርፎች ውስጥ የማዕድን ዘርፍ አልተካተተም ነበር፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት ግን ዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራበት ነው፤ ትኩረት በመሰጠቱም ዘርፉ እየለማና እያደገ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
እንደ አቶ ሚሊዮን ገለጻ፤ የኢትዮጵያ ማዕድን በአብዛኛው የሚመረተው በባህላዊ መንገድ ነው። በባህላዊ መንገድም በዋናነት ወርቅ፣ ጌጣጌጥና ለግንባታ የሚውሉ ማዕድናት ተመርተዋል። የማዕድን ምርትማነትን ለማሳደግ ባህላዊ የማዕድን አመራረትን የማዘመን፣ በቴክኖሎጂ የመደገፍ ሥራ እየተሠራ ነው።
የባህላዊ አምራቾች ካፒታላቸውን በማጠራቀም ቴክኖሎጂን እንዲጠቀሙ፤ ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ፤ ገቢያቸውን እንዲያሻሽሉ በማድረግ ምርትን የማሳደግ ሥራ እየተሠራ ነው፤ በተያዘው በጀት ዓመትም ስምንት ነጥብ ስድስት ቶን ወርቅ ለማምረት ታቅዷል። ከዕቅዱም ሶስት ሺህ 600 ኪሎ ግራም ያህል የሚመረተው በባህላዊ መንገድ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የባህላዊ የማዕድን ቁፋሮ ወደ አነስተኛና መካከለኛ እንዲሁም ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ እንዲያድግ እየተደረገ መሆኑን አመልክተው፤ባህላዊ የማዕድን አመራረት ዘዴ ከፍተኛ የሆነ የምርትና የጉልበት ብክነት አለው፤ የምርትና የጉልበት ብክነትን ለመቀነስ አመራረቱን የማዘመን ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ ጠቁመዋል።
ታደሠ ብናልፈው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2017 ዓ.ም