ዜና ሐተታ
ጅግጅጋ የአንድነት ማኅተማችንን በምክክር እናፅና የሚለውን ክተት ለማስተናገድ ሽር ጉድ ብላ ተሳታፊዎች ተቀብላለች፡፡ብዕር ይዞ በአመክንዮ መሞገት፤ ሃሳብ አንስቶ በልዕልና መርታት ነው የምክክሩ ዓላማ።ይህም የኢትዮጵያን ልጆች ከግጭት እና ከንትርክ አዙሪት ይታደጋል ተብሎ የታመነበት ክተት ነው፡፡
ሀገራዊ ምክክር ሂደቱ በጣም ጥሩ እና ውጤቱም መልካም እንደሚሆን የሚጠበቅ ነው ይላሉ ከአዋሬ ወረዳ የተገኙት የማኅበረሰብ ተወካይ አቶችቢን አሕመድ ሀሰን።
ከልብ ከተመካከርን የምክክር መድረኩ ጥሩ ውጤት ያመጣል ብለው እንደሚያምኑ የሚናገሩት የማኅበረሰብ ተወካዩ፤ ወንድማማቾች ሆይ እርስ በራሳችሁ ተጋገዙ እንጂ አትገዳደሉ ማለት እፈልጋለሁ ሲሉ ይመክራሉ፡፡
ጥላቻ እና ግጭት ሀገሪቱንም ሆነ ክልሎቹን ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን በመጥቀስ፤ ችግሮች በግጭት የሚፈቱ ቢሆን ሶማሌ ክልል ከዚህ ቀደም የነበሩ ግጭቶች ሁሉ ቀድሞ መፍታት ይችል እንደነበር ያጣቅሳሉ።
ችግሮችን በግጭት መፍታት እንደማይቻል በማመን ክልሉ በአሁኑ ጊዜ ሰላማዊ ምክክሮችን ምርጫው እያደረገ መምጣቱን በመናገር፤ በግጭት ውስጥ ያሉ ክልሎች ከሶማሌ ክልል ሊማሩ ይገባል ይላሉ።
በግጭት ውስጥ ለሚገኙ ክልሎች “በጥላቻ እና በግጭት ወንድ ይሞታል እንጂ ወንድ አይወለድም” ማለት እፈልጋለሁ ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
በግጭት ውስጥ ያሉ ክልሎች ሀገርን ሲያስተዳድሩ የነበሩ እና ጥሩ ልምድ ያላቸው መሆናቸውን በመጥቀስ፤ ችግሮችን በምክክር መፍታት ከእነዚህ ክልሎች የሚጠበቅ እንደሆነ ያስገነዝባሉ።
ሀገራዊ ምክክር በተለይ በክልሎች መካከል ያለውን ግጭት የሚፈታ እንደሚሆን እንደሚያምኑ በመግለጽ፤ ከዚያም አልፎ መንግሥት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እንዲከተል ያደርጋል።እያንዳንዱ ዜጋም በዜግነቱ ኮርቶ የሚኖር እንጂ የሌላ ሀገር ናፋቂ እንዳይሆን ዕድል ይፈጥራል በማለት ያስረዳሉ፡፡
መንግሥት ከሀገራዊ ምክክሩ የሚመነጩትን ውጤቶች ተግባራዊ እንዲያደርግ አፅንዖት መስጠት እፈልጋለሁም ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
እኛ የሀገራዊ ምክክር ዘማቾች በሕዝብ ውክልና ሀገራችንን ለማፅናት እየታገልን እንገኛለን ያሉት ተወካዩ፤ ከውስጥና ከውጭ ገንዘባቸውን እና ንብረታቸውን ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚያዋጡ ኃይሎች አንድ ሀገር ብቻ እንዳላቸው አውቀው ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ሲሉ ይመክራሉ፡፡
ሌላው አቶ አብዱሰላም መሐመድ ከፋፈን ዞን ጉርሱም ወረዳ የመንግሥት ሠራተኞችን ውክልና የያዙ የምክክሩ ተሳታፊ ናቸው።
ከምክክሩ ኢትዮጵያም ሆነች የሶማሌ ክልል ሕዝብ ተጠቃሚ ነው የሚሉት አቶ አብዱሰላም፤ ከዚህ በፊት ባልነበረ መልኩ የሶማሌ ክልል ሕዝብ እንዲህ ተሰብስቦ የኢትዮጵያን ችግር አንድ ላይ ሆነን እንፍታ በማለት ምክክር መጀመሩ እጅግ አስደስቶኛል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
የምክክር ሂደቱ በራሱ የኢትዮጵያ ችግር የሶማሌ ክልል ሕዝብ ችግር፤ የሶማሌ ሕዝብ ችግርም የኢትዮጵያ ችግር መሆኑን አመላካች ነው በማለት፤ ለመፍትሄውም በጋራ በመቆም ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ያስችላል ብለዋል።
ከዚህ በፊት በሌሎች ክልሎች ስለተካሄደው ምክክር መስማታቸውን በማንሳት ትንሽ ትልቅ ሳይል ሁሉን አሳታፊ ምክክር መካሄዱ ለምክክሩ ስኬት ወሳኝ መሆኑንም ነው የሚገልጹት።ሌሎች ክልሎች ላይ ምክክሩን በማካሄድ አንድነትን ማረጋገጥ ይገባልም ይላሉ፡፡
ውይይቱ ለሀገራዊ አንድነት እና ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ፋይዳ እንዳለው በመግለጽ፤ በምክክር የየግል ሃሳባችን ተደምሮ ወደ ማኅበረሰብ አድጎ እና በክልል ደረጃ ተዋቅሮ መምጣቱ በቀጣይም በሀገር አቀፍ ደረጃ ተጨምቆ የሚቀርብ መሆኑ ኢትዮጵያ ተስፋ ያላት ሀገር መሆንዋን ያመላክታል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
ውይይት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑን ከዚህ ምክክር መገንዘብ ይገባል ያሉት አቶ አብዱ ሃሰን፤ ችግር ካለም ጠረጴዛ ላይ ቁጭ ብለን በመመካከር መፍታት ልማዳችን ሊሆን ይገባል ነው ያሉት፡፡
ቀደም ሲል በንግድ ሥርዓቱ ላይ ጥያቄዎች ነበሩን የሚሉት ደግሞ ከኪቲባ ቀብሪበያህ የመጡት የነጋዴዎች ተወካይ አቶ አሕመድ መሐመድ ናቸው።
በተፈጠረው ዕድል ያሉንን አጀንዳዎች ማሰባሰብ ችለናል የሚሉት አቶ አሕመድ፤ ምክክሩ የሶማሌ ክልልን እንደ ክልል ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ እና አንድነትን ለመገንባት የሚረዳ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ነጋዴ በመሆኔ የወደብ ጉዳይ ያሳስበኛል ብለውም፤ የወደብ ጥያቄም ሊመለስ የሚችለው እኛ ኢትዮጵያውያን በመጀመሪያ አንድነታችንን ማረጋገጥ ስንችል ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከምክክሩ ብዙ እናተርፋለን፤ በጥቂቱ ካተረፍን እንኳን ሰላም፣ አንድነት፣ ወንድማማችነት በድምሩም ሀገራዊ መግባባት ላይ እንደርሳለን ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
በተሳተፍንበት ምክክር ላይ እንደተመለከትኩት የምክክሩ ሂደትና አሳታፊነት የሚደነቅ ነው፤ ሆኖም ቀሪ ክልሎች ሊሳተፉ ይገባል ብለዋል።ቀሪ ክልሎች ሲሳተፉ ሀገራችን ሙሉ ሰላም ታገኛለች ብዬ አስባለሁ ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ውብሸት ሰንደቁ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2017 ዓ.ም