ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራና ወቅታዊ ትሩፋቶቹ

ኢትዮጵያ ለዘመናት ስትከተለው የቆየችው የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንደ ሀገር የተጠበቀውን የኢኮኖሚ እድገት ሊያስገኝ አልቻለም።በዚህም ሀገሪቱ ካለችበት ኋላ ቀርነትና ድህነት ለመውጣት ያደረገቻቸው ጥረቶች ትርጉም ያለው ለውጥ ሊያስገኙም አልቻሉም።የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከውጭ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ የተመሰረተ መሆኑ በዋነኛነት የሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ሲያዳክመው ቆይቷል ።

በአብዛኛው በውጭ ሸቀጦች ላይ የተመሰረተው ሀገራዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፤ዜጎች ሀገራዊ ጸጋዎችን ተጠቅመው አምራች እንዲሆኑና ህይወታቸውን እንዲለውጡ የሚያበረታታ እንዲሁም የሀገር ውስጥ ማኑፋክቸሪንግና ኢንቨስትመንትን የሚያነቃቃም አልነበረም።ከዚህ ይልቅ ሀገሪቱን ከፍተኛ ለሆነ እዳ የዳረጋት እንደሆነም ብዙዎች ይስማማሉ።በየአመቱም እስከ18 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ለእዳ ክፍያ እንደምታውልም መረጃዎች ያመለክታሉ።

የገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፤በ2010 ዓ.ም የሀገሪቱ አጠቃላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ብድሮችን የዕዳ መጠን ፡ እ.ኤ.አ. እስከ ማርች 2019 ድረስ ያለባት ያልተከፈለ የሀገር ውስጥና የውጭ ብድሮች ዕዳ 1ነጥብ 5 ትሪሊን ብር ወይም 52ነጥብ 57 ቢሊዮን ዶላር ነው።

ከተጠቀሰው አጠቃላይ የሀገሪቱ ዕዳ ውስጥ 26ነጥብ 93 ቢሊዮን ዶላር ወይም 769 ነጥብ 08 ቢሊዮን ብር ከተለያዩ የውጭ አበዳሪዎች ተገኝቶ ያልተከፈለ ሲሆን፣ የተቀረው 730 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወይም 25 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ደግሞ ከሀገር ውስጥ የመንግሥት ባንኮች ማለትም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክና ከብሔራዊ ባንክ ቀጥታ ብድር፣ እንዲሁም ከመንግሥት ሠራተኞችና ከግል ሠራተኞች የማኅበራዊ ዋስትና (ጡረታ) ፈንዶች ተወስዶ ያልተከፈለ ዕዳ ነው ።

ሀገሪቱ ካለባት የውጭ ዕዳ ውስጥ የማዕከላዊ መንግሥት (Centeral Government) ዕዳ 44ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር (15ነጥብ 73 ቢሊዮን ዶላር) ሲሆን፤ ቀሪው 319ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር (11ነጥብ 17 ቢሊዮን ዶላር) ደግሞ የተለያዩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መንግሥት በገባላቸው የብድር መክፈያ መተማመኛ (Loan Guarantee)፣ ሌሎች ሁለት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ደግሞ ያለ መንግሥት የብድር መክፈያ መተማመኛ፣ በራሳቸው ከውጭ አበዳሪዎች በቀጥታ ተበድረው ያልከፈሉት ዕዳ ነው።

መንግሥት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከነበሩበት ስር የሰደዱ ችግሮች እንዲወጣ በ2011 ዓ.ም ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል። ማሻሻያው በመንግሥት ከሚደገፍና የመንግሥት ቁጥጥር ካለበት ኢኮኖሚ ሀገሪቱን በማውጣት፤የግል ባለሀብቱ በስፋት የሚሳተፍበት የገበያ ኢኮኖሚ መመስረት እንደሆነ ተደጋግሞ ተነግሯል።

ኢትዮጵያ ካላት ታሪክ፣ የህዝብ ቁጥርና የተፈጥሮ ፀጋ አንፃር ስትታይ ሊለማ የሚችል ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት አላት። ይሁን እንጂ ይህንን ሀብት በሚፈለገው ደረጃ አውቆ ማልማት የሚያስችል የፖሊሲ አቅጣጫ ባለመኖሩ በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች የሚፈለገው ውጤት አልተገኘም።

የሀገሪቱ ማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ በተለያዩ ጊዜያት ካወጣቸው መረጃዎች መረዳት እንደሚቻለው ፣ ከአጠቃላይ ዜጎች መካከል 70 በመቶ የሚሆነው ከ15 እስከ 36 ዓመት ወጣትና ምርታማነትን የሚያረጋገጥ አምራች ኃይል ነው።ይህም ሆኖ ግን ይህን አምራች ኃይል አንቀሳቅሶ ወደ ምርታማነት መቀየር አልተቻለም።

ከ2011 ዓ.ም በኋላ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ይህንን ታሪክ እንደሚቀይር ተስፋ የተጣለበት ነው።ኢትዮጵያ ያሏትን ሀብቶች አውቃ እንድታለማ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ነው። ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ላይ ያተኮረ ፤የውጪ ገበያን ማእከል ያደረገ ነው ።

በከፍተኛ ወለድ ስትበደር የነበረበትን አካሄድ በማቆም በአንፃሩ የልማት አጋሮቹ ከሆኑት ዓለም አቀፍ ተቋማትና ከመንግሥታት ትብብር በአነስተኛ ወለድ ለረዥም ጊዜ በሚሰጡት ብድሮች ላይ ትኩረት አድርጎ መንቀሳቀስ የሚያስችል ነው።

በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ ከመጣበት ካለፉት አመታት ወዲህ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከ7 በመቶ በላይ እያደገ መሄዱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።በተለይም ሀገሪቱ በበርካታ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ ባለችበት በዚህ ወቅት ይህን መሰል ዕድገት ማስመዘግብ መቻሏ እንደ ሀገር ጠንካራ ሥራ መሠራቱን የሚያመላክት ነው።

ቀላል የማይባለው የሀገሪቱ ክፍል በጦርነትና በጸጥታ ችግር ውስጥ ሆኖ በቆየበት ወቅት ሳይቀር ከ6 በመቶ በላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉ ከለውጡ ወዲህ ተግባራዊ የሆነው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ፤ከዚህ የሚመነጩ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ውጤታማ መሆናቸውን የሚጠቁም ነው።

ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ሀገሪቱ ፤ በታሪኳ አይታ የማታውቀውን ሁኔታ በተከታታይ ከወጭ ንግድ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ አግኝታለች። ሀገሪቱ ፍጹም ሰላም በነበረችባቸው አመታት እንኳን ከወጭ ንግድ ሲገኝ የነበረው አመታዊ ገቢ ከ3ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ዘሎ አያውቅም።

ይህም ሆኖ ግን አሁን ያለው ሀገራዊ የልማት ፍላጎት በዚህ ብቻ የሚሳካ አይደለም። ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ግኝትና የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን የሚጠይቅ ነው። ከዚህም በላይ በሀገር ውስጥ የገንዘብ ፍሰትን ማሳለጥና የውጭ ምንዛሬን በገበያው እንዲመራ ማድረግም አስፈላጊ የሆነበት ወቅት ላይ ተደርሷል።

ይህንን ታሳቢ በማድረግ፤ ወቅቱን በሚዋጅ መልኩ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መግባት የግድ ሆኗል።ይህን መሰረት በማድረግም ከሀምሌ 22 ጀምሮ ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ገብታለች። ይህም ሀገሪቱ ለጀመረችው የኢኮኖሚ ብልጽግና ትልቅ አቅም ይሆናል የሚል እምነት ተጥሎበታል።

የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሪ ገቢ በሚያስገኙ ዘርፎች ለተሠማሩ ኢትዮጵያውያንን ይጠቅማል። እንደ ቡና፣ ሰሊጥ፣ የቅባት እህሎች፣ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ጫት የመሳሰሉ ሸቀጦችን የሚያመርቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ገበሬዎች፣ የቁም እንስሳትና ሥጋ ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ አርብቶ አደሮችና ነጋዴዎች፣ በወጪ ንግድ ዘርፍ የተሠማሩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የፋብሪካ ሠራተኞች፣ በማዕድን ፍለጋ ላይ የተሰማሩ በርካታ ዜጎችና አምራቾች፣ በሆቴልና በቱሪዝም ዘርፎች የተሠማሩ ነጋዴዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል።

በውጭ ሀገር ከሚኖሩ ዘመዶቻቸው/ጓደኞቻቸው የውጭ ምንዛሪ የሚላክላቸው በሚሊዮን የሚገመቱ የሐዋላ ተጠቃሚዎች እንዲሁም ከውጭ ገንዘብ ፈስስ የሚደረግላቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የግል ተቋማት፣ ከእነዚህም ጋር በሽርክና የሚሠሩና ምርት የሚያቀርቡ ሌሎች አካላት የዚህ የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ በማድረግ ጤናማ የገንዘብ ፍሰት እንዲኖር ያስችላል።

ከዚሁ ጎን ለጎንም የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎችን ያበረታታል፤ የማምረት ሥራቸውን እንዲያስፋፉና የገበያ ድርሻቸውን እንዲያሳድጉ ይረዳቸዋል።መመዘኛውን የሚያሟሉ የውጭ ኢንቨስተሮችም በኢትዮጵያ ስነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ (Ethiopian Securities Exchange) እንዲሳተፉ በማድረግ የውጭ ምንዛሬ ፍሰትን እንዲጨምር ያደርጋል።

በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ የሚሠሩ ኩባንያዎች የውጭ ምንዛሪ ገቢያቸውን ሙሉ በሙሉ ለራሳቸው መያዝን ጨምሮ ልዩ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም መብት የሚያጎናጽፋቸውም በመሆኑ ገንዘባቸውን በሀገር ውስጥ እንዲያፈሱ ያነሳሳቸዋል።በምትኩም በሀገር ውስጥ የውጭ ምንዛሬ ፍሰት እንዲጨምር ያደርጋል።

ከሁሉም በላይ የዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማትና ሀገራት አቋርጠውት የነበረውን እርዳታ እና ብድር እንዲለቁና ኢትዮጵያም ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የምታገኘውን ብድርና እርዳታም ቀጣይነት እንዲኖረው ያስችላል።ይህ ማለት ደግሞ በፋይናንስ ዕጥረት የቆሙ የልማት ውጥኖች እንዲተገበሩና ኢትዮጵያ የጀመረችው እድገት ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርስ ያስችላል።

ከዚሁ ጎን ለጎንም ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲው አዳዲስ ዕድሎችን ይዞ መጥቷል።ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የመዋዕለ ነዋይ ገበያ በአዲስ መልክ መጀመር ነው። የመዋዕለ ነዋይ ገበያ ለዜጎች የሀብት ክፍፍል አይነተኛ ሚና የሚጫወትና ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ የጎላ ድርሻ እንዲኖራቸው እድል የሚሰጥ ነው።

ሰሞኑንም የዚሁ የመዋዕለ ነዋይ ገበያ አንዱ ትሩፋት የሆነው የመንግሥት ግዙፍ ድርጅቶችን የተወሰነ ድርሻ በአክሲዮን መልክ ዜጎች እንዲገዙ የሚያስችል ውሳኔ ተላልፏል።ከዚህ ውስጥ የኢትዮ ቴሌኮምን 10 በመቶ ድርሻ ለዜጎች እንዲሸጥ የተደረሰበት ውሳኔ አንዱ ነው። የኢትዮ ቴሌኮም 10 በመቶ ድርሻ ወደ ህዝብ መተላለፉ የካፒታል ገበያው ጅማሬ ኢትዮጵያን ወደ ተሳለጠና ዘመናዊ የአክስዮን ገበያ ሥርዓት የሚያስገባትና የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ነው።

ዜጎች በአክሲዮን ገበያ መሳተፋቸው ኢንቨስትመንትና ቁጠባን ከማሳደጉ ባሻገር አካታች የፋይናንስ ዘርፍን በማሳደጉ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል።በሀገራቸው ኢኮኖሚ ውስጥ የጎላ ድርሻ ያልነበራቸው ኢትዮጵያውያን ንቁ ተሳታፊ በመሆን ሀብት የማፍራት እና ቁጠባን የማሳደግ እድል እንዲኖራቸው ያስችላል።የሀገራቸውን ሀብት በፍትሐዊነት የመጠቀም መብትም ይጎናጸፋሉ። በተለይም እንደ ኢትዮ ቴሌኮም አይነት 130 አመታትን ያስቆጠረ እና ግዙፍ ኢኮኖሚን የገነባ ተቋም 10 በመቶ ሀብቱ ወደ ህዝብ መተላለፉ ዜጎች ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ሀብት ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን የሚያመላክት ነው።

የምዕራፍ አንድ የአክሲዮን ሽያጩ ሰሞኑን በቴሌ ብር አማካኝነት ተጀምሯል ፤ የአንድ አክሲዮን ብር 300 ሲሆን ዝቅተኛው የአክሲዮን መጠን 33 በመሆኑ ዝቅተኛው የአክሲዮን ግዥ 9ሺህ 900 ብር መሆኑ ይፋ ተደርጓል:: በአክሲዮን ሽያጩ እያንዳንዳቸው 300 ብር ዋጋ ያላቸው 100 ሚሊዮን መደበኛ አክሲዮኖች ለሽያጭ የቀረቡ ሲሆን፤ መደበኛ አክሲዮኖች ከዝቅተኛው 9 ሺህ 900 ብር ወይም 33 አክሲዮኖች ጀምሮ እስከ ከፍተኛው 999 ሺህ 900 ብር ወይም 3 ሺህ 333 አክሲዮኖች መግዛት ይችላል፡

የአክሲዮን ሽያጩ እስከ ታኅሣሥ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ነው። ይሁንና አጠቃላይ የአክሲዮን ድርሻው መጠን ከተጠቀሰው ቀን በፊት ተሸጦ ከተጠናቀቀ እስከተገለጸው ቀን ድረስ ላይቆይ እንደሚችል ይገመታል። ኢትዮጵያውያን የተከፈተላቸውን እድል በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል። እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ሁሉ ሌሎችም ግዙፍ ድርጅቶች የተወሰነ ሀብታቸውን ለህዝቡ በአክሲዮን መልክ ለመሸጥ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውም እየተነገረ ነው።ይህ ደግሞ ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ እና የተጀመረውም የብልጽግና ጉዞ በዜጎች ተሳትፎ እውን እንዲሆን ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ዘርፍ እያደረገችው ያለው ግስጋሴ የሚበረታታ ነው። አሁን ላይ ሀገሪቱ በአፍሪካ ትልቅ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት መካከል በአምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም መረጃ ፤ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቅ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት መካከል አምስተኛ ደረጃን የያዘችው 205 ነጥብ1 ቢሊዮን ዶላር የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ገቢ(GDP) በማስመዝገብ ነው:: ከዓለም ደግሞ በ57ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።ደቡብ አፍሪካ ፣ ግብፅ፣ አልጄሪያ እና ናይጄሪያ ደግሞ በአፍሪካ ትልቅ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት ከአንድ እስከ አራተኛ ደረጃን የያዙ ሀገራት ናቸው።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You