ዲላ፦ በዞኑ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን በማልማት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ እየተሠራ እንደሆነ የጌዴኦ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የባህል፣ ታሪክ፣ ቅርስ ጥናትና ልማት ቡድን መሪ አቶ ብርሃኑ ይርባ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ የጌዴኦ የቱሪስት መስህቦች በርካታ ናቸው።ከትክል ድንጋይ መካነ ቅርሶች መካከል ቱቲፈላ፣ ጨልባ ቱቲቲ፣ የሴዴ ትክል ድንጋይ መካነ ቅርሶች ይገኙበታል፡፡
በተለይ ቀልብን ከሚስቡ የቱሪዝም ሀብቶች መካከል የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር በእጅጉ አስደማሚ መሆኑን ገልጸው፤ እነዚህን የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን በማልማት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
የዋሻ ላይ ስዕሎች፣ ፏፏቴዎች ፣ ፍልውሃ፣ የጌዴኦ የዘመን መለወጫ ደራሮ በዓል የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎችና በዓላት መሆናቸውን ገልጸው፤ በአካባቢዎቹ የመንገድ፣ የውሃ፣ የመብራትና ምቹ የማረፊያ ሥፍራዎች እንዲኖሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሠራ ነው ብለዋል።
በእነዚህ ስፋራዎች ወጣቶች ተደራጅተው የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የመስሪያ ቦታ እየተዘጋጀ መሆኑን የገለጹት አቶ ብርሃኑ፤ በባህላዊ አልባሳት፣ በቱር ጋይድ፣ በእጅ ሥራ ሙያ እና በሌሎች ተያያዥ ዘርፎች ተሰማርተው ከራሳቸው አልፈው ቤተሰባቸውን እንዲደግፉ ከክልል ቢሮ ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
የጌዴኦ መልክዓ ምድር ቅርስ የማኅበረሰቡን መስተጋብር፣ አኗኗር ከማሳየቱም ባለፈ የበርካታ አእዋፋት፣ እንስሳትና አዝርዕት መገኛ ሲሆን፤ ሰው ከተፈጥሮ ጋር እንዴት መኖር እንደሚችል የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ቅርሱን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ከ2005ዓ.ም. ጀምሮ እንቅስቃሴ ሲደረግ መቆየቱን ገልጸው፤ በሪያድ በተካሄደው 45ኛው የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ኮሚቴ የዓለም ቅርስ ሆኖ እንደተመዘገበ አቶ ብርሃኑ ይርባ ገልጸዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2017 ዓ.ም