ቄሳር የቀበረው አልማዝ

ዝነኞቹን ፍለጋ የዘመን ቁልቁለቱን ይዘን በመውረድ በሁለት ክፍለ ዘመናት መካከል ኖረው፣ ሠርተው፣ ጥበብን ከጥበብ ስጋና ደም ፈጥረው እስትንፋስ የሰጡ አንድን ሰው እናገኛለን። እኚህ ሰውም አልማዝ፣ ሥራዎቻቸውም እንቁ ነበሩ። ዳሩ ግን የፋሽስት ጥሩር ከደረቱ የታጠቀው የቄሳር መንግሥት በክፉ ዓይኑ አይቷቸው ይሁን በእንቁ ተመኝቷቸው…አልማዙን ሰው ከእምጥ ስምጥ ሰወራቸው።

ከእናት ሀገራቸው ዘርፎ፣ በገዛ አፈሯ ውስጥ ቀበራቸው። አልማዙ ሰው በአንድ ወቅት የነጋዴው ሁሉ ራስ የነበሩት ነጋድራስ አፈወርቅ ገ/እየሱስ ናቸው። ነጋድራስነቱን ከአጼው ያገኙት የሥልጣን መንገድ ቢሆንም ከዚያ ይልቅ ግን የነብስ ጥሪያቸውን መንገድ ይዘው ለጥበብ ብዙ አትርፈዋል። መቼም “ጦቢያ”ን ያህሉን መጽሐፍ የማያውቅ የለም። በሀገራችን የሥነ ጽሁፍ ታሪክ ውስጥ ዝነኛው መጽሐፍ ነው። መጽሐፍ ብቻም ሳይሆን የመጀመሪያው የሀገራችን ልቦለድም ጭምር ነው። ታዲያ ይህን የጻፉትም እኚሁ ሰው ናቸው።

ግጥም እንደመግጠምም ብለው ብዙ ስንኞችን ቋጥረዋል። በስዕል ደረጃ ስማቸው ከፍ ተደርጎ ባይወሳም ጎበዝ ሰዓሊ ነበሩ። የእኚህ ሰው ታሪክ በመሃል አገም ጠገም በዝቶበት እክል ገጠመውና እንደ ሥራቸው እንዳይነገርላቸው በመሃል ቤት ላይ ቆመዋል። ይሁንና የጋመ ፍም አመድ ቢደፋበት አይታይ ይሆናል እንጂ ማቃጠሉ አይቀርም። ሥራዎቻቸውን ጥበብ አትረሳውም። ታሪክም አይፍቀውም።

ነጋድራስ አፈወርቅ ገ/እየሱስ ሐምሌ 10 ቀን 1861 ዓ.ም በደቡባዊው የጣና ሀይቅ ዙሪያ በምትገኘው በዘጌ ስለመወለዳቸው ይነገራል። ልጅ ሆነው እንደማንኛውም የዘጌ ልጅ በመንደሯ ተሯሩጠው፣ ምናልባትም ደግሞ የከብቶችን ጭራ ተከትለው፣ ከግጦሹም አሰማርተውና ከጉድባው ላይ ዋሽንቱን ነፍተው ይሆናል። የታሪክ ማህደራቸው ግን፤ በዚያው በሚገኘው ኪዳነ ምህረት ገዳም ውስጥ በአያታቸው መምህር ድንቄ የአብነት ትምህርት ስለመቅሰማቸው ይናገራል።

ሌላው ከውልደት ሰሞን ታሪካቸው መካከል ከሚነገርላቸው አንዱ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል የስጋ ዘመድ ስለመሆናቸው ነው። ለዚህም ይሆናል አፈወርቅ የትውልድ ቀያቸውን ለቀው አዲስ አበባ፣ ከአዲስ አበባም ወደ እንጦጦው ቤተ መንግሥት ቅጥር ጊቢ ለመግባት እምብዛም ዕድሜ አልፈጀባቸውም። በመጀመሪያው አመጣጣቸው በባለሟልነት ሲያገለግሉ ጥቂት ቆዩ። በስዕል ጎበዝ ከመሆናቸውም ውስጣቸው ዕውቀትና የልጅ አዋቂነት እንዳለ ግን ለአጼ ምኒልክ ቁልጭ ብሎ ይታያቸው ነበር።

ከባለሟልነት ወደ ዙፋን አገልጋይነት፣ ከጉልበታቸው ዕውቀታቸው ይበልጥ እንደሚያስፈልጋቸው የተረዱት አጼ ምኒልክ አፈወርቅ ቢማርና ያለውን ቢያዳብር የተሻለ መሆኑን አመኑበት። የ20 ዓመት አፍላ ወጣት ሳለም ለትምህርት ወደ ባህር ማዶ ሊሰዱት አሰቡ። እናም ልጅ ቅጣውንና ጉግሳ ዳርጌን አክለው በ1880ዓ.ም ወደ ሲዊዘርላንድ ላኳቸው። አጼው በብልህነታቸው ባህላቸውን ሳያስነኩ በአውሮፓ የሥልጣኔ ቀንበጥ የተነደፉ ነበሩ። ሲወዱና ሲደፍሩ ልክ አልነበራቸውም።

ሁሉንም ማየት፣ መልካም መልካሙንም ለሀገራቸው የማድረግ ፍላጎታቸው ከፍተኛ ነበርና ይህን ለማምጣት አንድም ወጣቶችን ለትምህርት በመላክ ነበር። በዚህ እሳቤ ከተላኩት አንዱም አፈወርቅ ነበር። የላኳቸው ሦስቱ ወጣቶች ሲዊዘርላንድ ደርሰው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንደሆኑ ሲያስቡ ለነበሩት ለንጉሡ የኋላ ኋላ አንድ ነገር ደረሳቸው። አፈወርቅ ሲዊዘርላንድን ከረገጠ በኋላ ምንም ባልታወቀ ምክንያት ሹልክ ብሎ ኢጣሊያ መግባቱን ነበር። እንግዲህ “መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ” ይሉት ይሆናል እንጂ ሌላ ምንስ ሊሉት ይችላሉ።

አፈወርቅ ወደ ኢጣሊያ ካቀኑ በኋላ በቱሪን “ኢንተርናሲዮናል ደ.ቤሊ አርቲ” በተባለ ኮሌጅ ውስጥ ላቅ ያለ የሥነ ጽሁፍ ትምህርት መከታተል ጀመሩ። ምናልባትም ከሲዊዘርላንድ የመኮብለላቸው ምክንያት ሊሆን የሚችለው ይሄው ነው። የሚፈልጉትን ሳይሆን የሚፈለግባቸውን እንዲማሩ የተፈረደባቸው ስለመሰላቸው ውስጣቸው የሚላቸውን ተከትለው ራሳቸውን ነጻ ለማውጣት ይሆናል ወደ ኢጣሊያ ዞረው ይህን መምረጣቸው።

ይሁንና ከዓድዋው የፋሽስት ጦርነት ቀድመው ኢትዮጵያ የገቡት ነጋድራስ አፈወርቅ ገ/እየሱስ ነበሩ። ትዕዛዝ ጥሰው ከተላኩበት ወደ ሌላ የኮበለሉ ቢሆንም ተመልሰው ሲመጡ ግን የቤተ መንግሥቱ በር አልተዘጋባቸውም። ለዚህ ደግሞ እንደምናልባት ልናነሳት ከወደድን ኢጣሊያ ሳሉ የፈጸሟት አንዲት ግብር ነበረቻቸው። በዚያው ሳሉ ራስ መኮንን ከኢትዮጵያ ተነስተው በሥራ ጉብኝት ኢጣሊያ ገብተው ነበርና አፈወርቅ ደግሞ በአስተርጓሚ፤ ቱርጅማንነት ረድተዋቸዋል።

ራስ መኮንንም ሲመለሱ ይህንኑ ለንጉሡ ነግረው አሰርየውላቸው ይሆናል። አፈወርቅም አዲስ አበባ ገብተው የሀገራቸውን አፈር እንደረገጡ ዳግም ወደዙፋኑ ጠጋ ማለታቸው አልቀረም። ብዙ አገልግሎትም ሲሰጡ ነበር። በእንጦጦ ራጉኤልና እንጦጦ ማርያም አቢያተ ክርስቲያናት ውስጥ ቆንጆ ቆንጆ የግርግዳ ላይ ስዕሎችን የሳሉትም በዚህ ወቅት ነው። ሃሳቡን ያመጡት እቴጌ ጣይቱ ነበሩ። ቢሆንም ግን የዙፋኑ ንግሥትና ዘመዳቸው ከሆኑት እቴጌ ጣይቱ ጋር ሊስማሙ አልቻሉም። ተቀያየሙናም አፈወርቅ መልሰው ለስደት ሻንጣቸውን ሸከፉ።

በ1888ዓ.ም ወደመጡበት ኢጣሊያ ተመልሰው ሄዱ። የተማረችባቸው ኢጣሊያም እጇን ዘርግታ ተቀበለቻቸው። እሳቸውም ለእነርሱ የነበራቸው ፍቅር የዋዛ አልነበረም። ናፖሊ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የምሥራቅ ጥናት ተቋም ውስጥ የአማርኛ ቋንቋን ማስተማር ጀመሩ። በኋላም የፕሮፌሰርነትን ማዕረግም ሰጥቷቸዋል።

በሀገራችን የመጀመሪያው ልቦለድ ለመባል የበቃው “ጦቢያ”ን የጻፏት እዚያ ሳሉ ነበር። በ1908ዓ.ም በሮም ታትማ ለመነበብ በቃች። 90 ገጾች ብቻ የያዘች አነስተኛ መጽሐፍ ብትሆንም ታሪክና ክብረ ወሰኗ ግን ትልቅ ነበር። የኢትዮጵያ የዘመናዊ ሥነ ጽሁፍ አብዮት ተኳሽና መሠረት ሆና እንድትቆጠር፣ አፈወርቅም ሌላ ከፍታ ላይ እንዲቀመጡ ሆናለች። በዚህች ልቦለድ የሠበሩት ክብረ ወሰን ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ ታሪክ በሀገርኛ ቋንቋ መጽሐፍ የጻፈ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ ለመባልም ችለዋል።

ሁለት ጊዜ ከሀገር የወጡት ነጋድራስ አፈወርቅ ሁለት ጊዜ ወደ ሀገር ተመልሰዋል። ከመጀመሪያው የሁለተኛው አካሄዳቸው ላይመለሱ ቢመስልም 1922ዓ.ም እንደገና ወደ ሀገር ተመልሱ። ከዚህ በኋላም በርከት ያሉ የመጽሐፍት ሥራዎችን ለማበርከት ችለዋል። በአማርኛና ግዕዝን ጨምሮ በኢጣሊያንኛና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎች የመማሪያ መጽሀፍት አዘጋጅተዋል። “ጦቢያ” በክብሩ እንዳለም፤ ዕውቅ ከሆኑት የነጋድራስ ሥራዎች መካከል “የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽ”፣ “ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ”፣ “ሚናስ”፣ “ዘንዶ ሲነግስ”፣ “ክሊዎፓትራና ማርካንትዋን” ተጠቃሾች ናቸው። ጽፈው ለህትመቱ ያላበቋቸው ሌሎች የልቦለድ ሥራዎችም ነበሯቸው።

የ20ኛው ክፍለ ዘመን አጀማመር ለአፈወርቅ መልካምና ከእናት ሀገራቸው እቅፍ ውስጥ የሞቃቸው ይመስላል። በመጽሐፍት ሥራዎቻቸው ስመ ጥር ሆነዋል። በአጼ ምኒልክ መጨረሻና በጃንሆይ መጀመሪያ ተቀባይነትም አግኝተዋል። ከሠሩትና ካላቸው አዋቂነት የተነሳ ከዙፋኑ በታች ባሉ የሥልጣን ወንበሮችን ለማግኘትም ችለዋል። በድሬዳዋ ባለው ጉምሩክ ላይ ተሹመው “ነጋድራስ” የሚለውን ማዕረግ አገኙ።

ቀጥሎም በጊዜው በነበረው አሸማጋይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ሆነው ተቀመጡ። በሌላ ጊዜም አብዝተው ወደሚወዱት የኢጣሊያ ቀዬ መግቢያ የሥልጣን በትር ተረከቡ። የኢትዮጵያ እንደራሴ (አምባሳደር) ሆነው በሮም ተሰየሙ።

ታላቁ ሰው በቄሳር…አንዳንድ ጊዜ የማንጠብቀውን ሰው ከማንጠብቀው ሥፍራ ላይ እናገኘው ይሆናል። የነጋድራስ በቄሳር ቤት ውስጥ የመገኘት ነገር ለብዙሃኑ ውል አልባ ጉዳይ ነው። የሆነውም እንዲህ ነበር…ጊዜው ከ19ኛው ወደ 20ኛው ክፍለ ዘመን ሽግግር ተደርጎበታል። ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የፋሽስት ወረራ ዓድዋ ላይ ድል መታ ሀገር ሰላም ብላ ከተቀመጠች ድፍን ሦስት አሥርት ዓመታት አልፈዋል። ሶላቶው ግን አላርፍ ብሎ እልህ ትንፋሽ ስላሳጣው ዳግም ለወረራ በመሰናዳት ላይ ነበር።

አንድ ጊዜ እዚህ ሌላ ጊዜ ደግሞ እዚያ በማለት ውሉ የጠፋባቸው ነጋድራስ አፈወርቅ የት መሆን እንዳለባቸው ጭንቅ ጥብብ ያላቸው ይመስላል። ይሁንና ፋሽስቱ ኢጣሊያ የጦር ግሳንግሱን ሰብስቦ ወረራውን ተያያዘው። ከዚያ ቀደም የሰውየው አብዝቶ ከኢጣሊያውያኑ ጋር ሽር ብትን ማለት አዝማሚያው ያላማራቸው ወትሮም በሀሜት ጎሰም ሲያደርጓቸው ነበር። ጦርነቱ ሲጀምር ደግሞ ሀሜቱ እውነት ስለመሆኑ በብዙዎች ታመነ። በኋላም ቢሆን ለእውነታው ማስረገጫነት ሲነሳ የነበረው የቄሳር መንግሥት መልዕክተኛ ጋዜጣ ነበር።

የዚህ ጋዜጣ አዘጋጅ በመሆን መሥራት በመጀመጀመራቸው ነው። ይባስ ደግሞ ከዚያኛው ወገን የአፈ-ቄሳርነትን ማዕረግ ደረቡላቸው። እንግዲህ በዚህ መጀቦናቸው ቢሞቃቸውና ከቄሳር ለቄሳር የሚሠሩ “አፍቃሪ ቄሳር” ቢሆኑ ነው ሲል የሀገሬው ሰው አመነ። ከአህያ ጋር የዋለች ጊደር ብትማር ፈስ ነው። ከባንዳነት ሌላ ምን ሊኖራቸውና፤ ሲል ከሶላቶው ጋር ሶልተው በዚያ ወገን ስለመቆማቸው ዙፋኑም እርግጠኛ ሆነ።

በኢጣሊያና በኢትዮጵያ፣ በፋሽስትና በአርበኛው መካከል ጦርነቱ ተጧጡፎ እየከረረ ሄደ። ንጉሡም መፍትሄ ፍለጋ፣ በአውሮፓ ‘ሊግ ኦፍ ኔሽን’ አቤት ለማለት ወደ እንግሊዟ የኤልሳቤት ዙፋን ተጠጉ።

ዳሩ የመጣ ሁሉ ይሄዳል። የሄደም ይመለሳል። በመምጣትና መሄድ ተናውጣ ሥፍራዋን የማትለቅ ሀገር ብቻ ናት። ንጉሡም ከእንግሊዝ መጡ። ፋሽስቱም ጨርቅና ማቁን ሰብስቦ ወጣ። የዘውዱም ዙፋን ዳግም ጸና። ነጋድራስ ግን “የሀገሬ ጅብ ይብላኝ። አፈሯም በላዬ ይማስብኝ” ብለው ነው መሰል፤ መልቴ ከተባሉበት ከሶላቶው ጋር አብረው አልወጡም ነበር። ላይ ታች ውጣውረዱ ሁሉ አክትሞ በ1933 ዓ.ም ሀገር ነጻነቷን እንዳስመለሰች አይቀሬው የክስ ጎራዴ ተመዘዘባቸው።

“በጦርነቱ ወቅት በሀገር ክህደት ለቄሳር መንግሥት ወግነው ቆመዋልና የሞት ፍርድ ይፈረድባቸው!” ተባለ። ይህን ጊዜ ነጋድራስ ሲሰሙ፤ ምን ግጥም ገጥመው፣ እንዴት ሲሉ ጽፈውና ምን መልክ ያለውን ስዕል ስለው እንደሆን ግን እንጃ…ብቻ በባንዳነት ከመጠርጠር አልፈው፣ በፍርድ የሞት ሸንጎ ላይ ሊቆሙ ሆነ።

አሁን ሁሉም የሚጠብቀው የጃንሆይን ትዕዛዝና ፍርድ ነው። ፍርዱን አጽንቶ የመግደል፣ ሀጢያቱንም ሽሮ የማንጻት ሥልጣን የንጉሡ ነው። ግን ሀገር የከዳን ሰው ኩነኔ በምን ሊያስተሰርዩለት ይቻል ይሆን? ጃንሆይስ የቄሳርን ወይንስ የፒላጦስን ፍርድ ሊፈርዱ?

ጃንሆይ በጉዳዩ ብዙ ያሰላሰሉበት፣ አዋቂዎቻቸውንም የመከሩበት ሳይሆን አይቀርም። ግልፍ ብሎባቸው “ስቀሉት! ይህን ባንዳ” አላሉም። እልካቸውን መወጣጫ አላደረጓቸውም። ይልቁንስ ለሞት የተመዘዘውን ካራ ወደሰገባው አስመለሱት። ነጋድራስ እርጅናውም ስለተጫጫናቸው የተፈጥሮ ሞት በራሱ እየገሰገሰ ከደጃቸው መድረሱንም ጃንሆይ ተመልክተው ነበር።

ለሞት የተሰናዳውን የነጋድራስን የአንገት ገመድ ፈተው ባይሆን በሚል ፍርዱን በሌላ ለወጡት። ነጋድራስ አፈወርቅ ገ/ኢየሱስ በሀገር ላይ ክደት መፈጸማቸውን ጃንሆይም አምነው ነበርና ከሞት ፍርድ ወደ እድሜ ልክ እስራት ቀየሩላቸው። በደል ለፈጸሙባት ሀገር ሠርተው ውለታን ውለውላት ነበርና ጃንሆይም ይህንን አልዘነጉትም። የፍርዱ ለውጥ አንድም በዚሁ ነው። እናም ጉዟቸው ከመቃብር ወደ ዘብጥያ ሆነ። ከፍርድ መልስ የነበረው የነጋድራስ ሕይወት በጅማ ጅሬን እስር ቤት ውስጥ ነበር። ከዚያን በኋላ እርጅናው ላይ የጤና መጓደሎች እየታከሉባቸው በእስር ከስድስት ዓመታት በላይ ለማስቆጠር አልቻሉም።

የተፈረደባቸው የእድሜ ልክ እስራት ቢሆንም እድሜ ልካቸው ግን 6 ዓመት ብቻ ነበረች። የ79 ዓመቱ ነጋድራስ መስከረም 15 ቀን 1939 ዓ.ም ክልትው አሉ። የሰው ልጅ የፈረደባቸው እድሜ ልክ በጣት የምትቆጠረዋ 6 ብቻ ናት። እንግዲህ የምድሩ በሰማይ ቀጥሎ ይሁን ለበደሉ ተክሰው የሚያውቅ አንድዬ ብቻ ነው።

ከብዙ ሀጢያት መካከል ያለች አንዲት ጽድቅ መድሃኒት ናት። ባትሽር ባትፈውስ እንኳን እድሜን ታረዝምና ትቀጥላለች። ቢያንስ የበደልነውን የምንክስበትን የጊዜ ዕድል ትሰጠናለች። የበደሉንን ይቅር እንደማለትስ ምን ታላቅነት ይኖራል? እንኳንስ ስቶ የወደቀውን የሀገር ባለውለታን ቀርቶ ሶላቶውንስ ፋሽስት ይቅር ብለን የለም እንዴ? ከሰይጣኑ ጋር ታርቀን ሰይጣን ያሳተውን ብንኮንን አሁን ኩነኔው በኛው ላይ ነው።

ጡት ነካሽነቱን ሳናውቅለት ከነበሽታው በላያችን ላይ የሾምነው ብዙ ነውና ደርሰን አሁን ድረስ ግንፍል ብንል ራስ ማቆሸሽ ነው። ለነጋድራስም ጽድቁ ቆርቶባቸው እንኳን በሥራዎቻቸው ስለሥራዎቻቸው ስንል ልንታረቃቸው ግድ ነው። ታዲያ በአንድ ወቅት ይህንኑ በማሰብ በቴምብሩ ላይ ፎቶዋቸውን ያወጣው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር አይገጥሙ ትግል ገጥሞት ነበር። እንዴትስ ነው የአንድን ባንዳ ሰውዬ ምስል በዚህ መልክ መጠቀሙ…ሲል የደነፋው ቀላል አልነበረም።

ጣት ታመመ ተብሎ ተቆርጦ እንዴትስ ይጣላል? ለፈጸሙት ክህደት “ደግ አደረጉ!” ብለን የጀብዱ ሜዳይ ባናጠልቅላቸውም ሥራቸውን ለመካድ ግን አንችልም። በበደላቸው ከመቀጣታቸውም ሌላ አንድ ነገር እንዳስብ አደረገኝ…በጊዜው ፋሽስቱ ጓዙን ጠቅልሎ ሲወጣ ነጋድራስ በሀገር ላይ የእናታቸውን ጡት ስለመንከሳቸው በትክክል ያውቁታል፤ አሊያም ሰምተውታል። በቀጣይ ታላቁ የፍርድ ሸንጎ ላይ ሊቆሙ እንደሚችሉ መቼስ እንደሳቸው የሚያውቀውም አልነበረም።

ጌታዋን የተማመነች በግ ጅራቷን እውጭ ስታሳድር ኋላ ጌታዋ እንደሚያድናት ተማምና ነውና ስለምንስ ጌታዬ ብለው ያገለገሉትን ፋሽስት ተከትለው አልሄዱም? ቀጥሎ የሚከተላቸውን አላጡትም ካልን ሊሆን የሚችለው ጸጸት ነው። የበደልኳትን ሀገር ሸሽቼ ዳግም ከምከዳት ራሷ ትቅበረኝ ብለው ነው። እንጂማ ሳይቀድሙኝ ልቅደም ቢሉ ቤተኛ በሆኑባት ኢጣሊያ መሽሎኪያውን አያጡትም ነበር።

በደላቸውን በይቅርታ ልንሰርይላቸው የሚገባው አንድም በዚህ ተግባራቸው ነው። ሀጢያቱን አውቆ ራሱን ለቅጣት የሚሰጥ የድንጋይ ሳይሆን የስጋ ልብ ነው። ነጋድራስ ለሀገራቸው ባበረከቷት የበኩር ልቦለድ፤ በ“ጦቢያ” ገና በመጀመሪያው ገጽ ላይ ለራሳቸው ትንቢት ይሁን ይህን ጽፈው እናገኛለን “ይቅርታ ጠያቂ ያከበረ፣ ይቅርታ አድራጊውም የተከበረ ነው!” ይላል። በእርግጥ ሁሉም የተከበረ ነው። አልማዝን አቆሽሸው ከአፈር ቢቀብሩትም ያው አልማዝ ነው።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You