እዚያ ላይ ያለች ሸክላ ሰሪ
ድሃ ናት አሉ ጾም አዳሪ
ማን አስተማራት ጥበቡን
ገል አፈር መሆኑን!
ግጥሙ ሰም እና ወርቅ ያለው ቅኔ ነው። ግጥሙ ተደጋግሞ የሚነገረው ወርቁ በያዘው ትርጉም ቢሆንም ለዚህ ጽሑፍ የሚሆነን የሰሙ ትርጉም ነው። ሰም ማለት በግልጽ የሚታወቀው ትርጉም ማለት ነው። ይህ ግጥም የሸክላ ሰሪዎችን ጥበብ ያደንቃል። አፈር ተቦክቶ ሸክላ መሆኑን ማን ነገራቸው ሲል ይጠይቃል፤ ገል ማለት የሸክላ ስባሪ ነው። ገልን (ሸክላን) ከአፈር መሥራት እንደሚቻል ማን አስተማራቸው? ማን ነገራቸው? አፈር ተቦክቶ፣ ተጠፍጥፎ፣ እንደዚያ ዓይነት የሚያምር መገልገያ ዕቃ ይወጣዋል ብለው እንዴት አሰቡት?
ቆይ ግን ይህን የእናቶቻችንን እና የአባቶቻችንን ጥበብ እያየን ሥልጣኔን አውሮፓውያን ናቸው ያስተማሩን እንበል? ሞፈር ቀንበርን ከእንጨት መገጣጠምን አውሮፓውያን ናቸው ያስተማሩን? የሸክላ ዕቃዎችን ከአፈር መሥራት አሜሪካውያን ናቸው ያስተማሩን? እነዚያን በህብረቀለም ያሸበረቁ የስፌት ዕቃዎች ከሳር መሥራት እንደሚቻል ከኤስያ ይሆን የኮረጅነው?
በብዙ ጥናታዊ ውይይቶች ላይ እንደሚነገረው የዘመናዊ ሥልጣኔ መነሻው ባህላዊ ነገሮች ናቸው። ለጋዜጣ፣ ሬዲዮ፣ ቴሌቭዥን እና ስልክ መነሻው የድንጋይ ላይ ጽሑፍና ነጋሪት ነው። ለዘመናዊ የወንጀል ምርመራ መነሻው አውጫጭኝ ነው። ለዘመናዊ እርሻ መነሻው ሞፈር ቀንበር ነው። ለዘመናዊ ምጣድ መነሻው የሸክላ ምጣድ ነው፤ ለዚያውም ማገዶው ወደ ኤሌክትሪክ ተቀየረ እንጂ ምጣዱ አሁንም የሸክላ ነው።
ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ዕቃዎች ሥራን በማቅለል የተሻሉ መሆኑ አያከራክርም፤ ለዚህም ነው አሁን ላይ አገልግሎት ላይ እየዋሉ ያሉ ዘመናዊ ዕቃዎች ናቸው። ዳሩ ግን የሥልጣኔያችን መነሻዎች መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም። ምን ዋጋ አለው ለማዘመን ግን አልተሰራም! እነዚህ የዕደ ጥበብ ሥራዎች ሙዚየም ሲገቡ እያየን ዝም ብለናል። ጥቂት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥናት ቢሰሩባቸውም የተሰሩ ጥናቶች የመደርደሪያ ማሞቂያ ሆነው ቀሩ እንጂ ወደ ህብረተሰቡ አልደረሱም።
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በነሐሴ 2008 ዓ.ም ባሳተመው ዓመታዊ መጽሔት የሸክላ ሥራ ላይ የተሰራ አንድ ጥናት አገኘሁ። አጥኚው ገዛኸኝ ግርማ ይባላሉ። የጥናታቸው ርዕስ ‹‹የሞጎጎ›› (ምጣድ) ሥራ ትውፊታዊ የዕደ ጥበብ ዕውቀትና ክህሎት በሰለክላካ ከተማና አካባቢዋ ሰሜን ምዕራብ ትግራይ›› ይላል። ጥናቱም የተሰራው በቃለ መጠይቅ፣ በቀጥታ ማስተዋል እና በቡድን ውይይቶች ነው። ይሄ ማለት አጥኚው የዕደ ጥበብ ሥራዎችን በሚገባ አስተውለዋል ማለት ነው። ጥናቱ የተሰራው ትግራይ ውስጥ ስለሆነ ይሆናል የትግርኛ ቃላት ይበዛሉ፤ ቢሆንም ግን የአማርኛ ትርጉማቸውን በቅንፍ ውስጥ በማስቀመጥ ነው። በአማርኛው ጽሑፍ ውስጥ ያሉት አንዳንድ ሆሄያትም የትግርኛ ጽሑፍ ውስጥ የምናያቸው ናቸው። ለምሳሌ ‹‹ሓ›› የሚለውን ሆሄ የምናየው የትግርኛ ጽሑፍ ውስጥ ሲሆን በዚህ ጥናት ውስጥ በአማርኛው አጻጻፍ ውስጥ እናገኘዋለን። የቋንቋ ሰዎች እንደሚሉት ግን ትክክል ነው። ቃሉ የትግርኛ ከሆነ በአማርኛ አጻጻፍም ቢሆን በዚያው ሆሄ መጻፍ አለበት። እንግዲህ አጥኚው ይህን የዕደ ጥበብ ሥራ ሲያጠኑ የአካባቢውን ቋንቋ እንኳን ጠንቅቀው በመጻፍ ነው ማለት ነው።
የሸክላ የዕደ ጥበብ ሥራዎች ብዙ ቢሆኑም የጥናቱ ትኩረት የምጣድ አሰራር ላይ ብቻ ነው። የገዛኸኝ ግርማ ጥናት ዋቢ አድርገን ስለምጣድ አሰራር እንነገራችሁ። ምናልባት አሰራሩ ከአካባቢ አካባቢ ሊለያይ ስለሚችል የምንነግራችሁ በጥናቱ የተጠቀሰውን አካባቢ ብቻ ነው።
በመጀመሪያ ከፍ ያለ ቦታ ይመረጣል። ከዚያም ለምጣዱ መስሪያ የተመረጠው ቦታ ላይ ውሃ በማርከፍከፍ በወንፊት የተነፋ አፈር መሬቱ ላይ ይደረጋል። ለምጣድ መስሪያ የሚጠቀሙት የሸክላ አፈር ሊማ እና ሕጻ ይባላሉ። ሊማ በመባል የሚታወቀው ጥቁር ሲሆን ሕጻ የሚባለው ቀይ ነው። እነዚህ አፈሮች ከሚገኙባቸው አካባቢ በሸክም ይወሰዳሉ።
የሕጻ አፈር በዱላ እየተመታ ከደቀቀ በኋላ በውሃ በተበጠበጠ ሊማ (ጥቁሩ አፈር ማለት ነው) እየታሸ ይቦካል። መጠኑም ሕጻ ሁለት እጅ ሊማ ደግሞ አንድ እጅ ናቸው። ልዩነታቸው፤ ሕጻ ለምጣዱ ጥንካሬ የሚሰጥ ሲሆን ሊማ ደግሞ ጭቃው በቀላሉ እንዲሳሳብ ነው። የገዛኸኝ ግርማን ጥናት እንመለስበታለን፡፡ እግረ መንገድ አፈርን የመለየት የእናቶችን ጥበብ ለማስታወስ ያህል ነው።
በብዙ ገጠራማ አካባቢዎች እናቶች የአፈርን አይነት እየለዩ ለተለያየ አገልግሎት ይጠቀሙታል። ለምሳሌ አከንባሎ ለመስራት፣ ቤት ለመምረግ፣ ልብስ ለማጠብ (ልብስ በጭቃ እንደሚታጠብ ልብ በሉ) ይጠቀሙበታል። የአፈርን ቀለም እየለዩም፤ ነጩ፣ ጥቁሩ፣ ቀዩ ሲሉ ይሰማል። ነጭ አፈርን ለልብስ ማጠቢያነት ይጠቀሙበታል፤ ልብስ አይጎዳም፤ ቆሻሻም ያስለቅቃል። ጥቁር አፈር ለመምረጊያነት ይጠቀሙበታል። ሌሎች የአፈር ዓይነቶችንም እየለዩ እንደየባህሪያቸው ይጠቀማሉ። ለምሳሌ በቀላሉ የሚሰነቀጡት የአፈር አይነቶችን ለሆነ ነገር መለሰኛነት (ማለስለሻ) ይጠቀማሉ።
ወደ ጥናቱ እንመለስ ፤ ለምጣድ መስሪያነት በተዘጋጀው ጭቃ ለማጆች (ጀማሪዎች) በ60 ሴንቲ ሜትር ስፋት በክብ ቅርጽ በተዘጋጀ ብረት ውስጥ ካዘጋጁ በኋላ ብረቱን ያነሱታል። ልምድ ያላቸው ግን ምን ዓይነት ነገር ሳይጠቀሙ በግምት በ60 ሴንቲሜትር ሬዲየስ ይሰሩታል። እንዲህ ከተዘጋጀ በኋላም በፀሐይ ብርሃን እንዲደርቅ ይደረጋል። ሲደርቅም ውሃ እየተርከፈከፈ በማለስለሻ ድንጋይ ይስተካከላል። የምጣዱን ዙሪያም እየፋቁ ካስተካከሉት በኋላ የምጣዱ የታችኛው ክፍል ለ12 ደቂቃዎች ያህል በእሳት ይቃጠላል። ይህ የመጀመሪያ ዙር ምጣዱን የማቃጠል ተግባርም በትግርኛ ‹‹ምግራር›› ይባላል። እዚህ ላይ ግን ለአጥኚው አንድ ጥያቄ ልናነሳ እንችላለን። እነዚህ ሥራዎች የሚሰሩት በባህላዊ መንገድ ስለሆነ የደቂቃው ልኬታ 12 መሆኑ አሳማኝ አይመስልም። እጃቸው ላይ ሰዓት አድርገው፤ ደቂቃ እየቆጠሩ የሚሰሩት ላይሆን ይችላል።
ምጣዱ ትንሽ ፀሐይ ላይ ከቆየ በኋላ ቀይ መልክ ባለው የሸክላ አፈር ከተቀባና ከለሰለሰ በኋላ የምግብ ዘይት ይቀባና በጨሌ (እንቁይ) ይታሻል። አጥኚው የነገሩን የምጣድ ማለስለሻ የምግብ ዘይነት ቢሆንም ጉሎ የሚጠቀሙም አሉ። ጉሎ ማለት የቅባት ተክል ሲሆን በቀላሉ በማንኛውም አርሶ አደር ጓሮ የሚገኝ ነው። ምናልባት በአየር ንብረት ሁኔታ በሁሉም አካባቢ አይኖር ይሆናል። የጎመን ፍሬ የሚጠቀሙም አሉ። ጎመን አድጎ ሲዘረዝር ብዙ ፍሬ ይወጣዋል፤ ለምጣድ ማለስለሻነትም ያገለግላል። ይህኛው እንዲያውም ምጣዱ ሲዘጋጅ ብቻ ሳይሆን በአገልግሎት ዘመኑ ሁሉ ለምጣዱ ማለስለሻነት ያገለግላል (ምጣዱ እንጀራ እንዳይቆራርስ ማለት ነው)።
ወደ ጥናቱ ስንመለስ፤ የምጣዱ አዘገጃጀት አሁንም ይቀጥላል። እየተደጋገመም በእሳት ይቃጠላል። በእንጀራ መጋገሪያው በኩል ያለው የምጣዱ ክፍል በእሳቱ በኩል ይሆንና ኩበት እየተጨመረ ለ15 ደቂቃዎች ያህል በእሳት ይቃጠላል። ይህም በትግርኛ ‹‹ምጥባስ›› ይባላል። ከዚያ በኋላ መዋቢያዎችና ምልክቶች ከተደረጉበት በኋላ ለሽያጭ ይውላል።
ለገበያ የሚቀርቡ ምጣዶች በተለያየ አጋጣሚ ሊሰበሩ ይችላሉ። በቀላሉ ለሚሰበሩት ምጣዶች ግን ሰሪዎች ሁለት ምክንያት ያስቀምጣሉ። አንደኛው ምጣዱ ተዘጋጅቶ እንዳበቃ ለቅዝቃዜ ከተጋለጠ ነው። ሁለተኛው ደግሞ የተሰራበት ግብዓቶች የጥራት ጉድለት ካለባቸው ነው። የክረምት ወቅት ለምጣድ ሥራ ምቹ አይደለም (በቂ የፀሐይ ሙቀት ስለማይገኝ)።
በብዙ አካባቢዎች የሸክላ ሥራን የሚሰሩት ሴቶች ሲሆኑ አጥኚው እንደሚነግሩን በሰለክላካ አካባቢ ደግሞ ይባስ ብሎ ወንዶች እንዲሳተፉ በባህሉም አይፈቀድም (ምናልባት ስላልተጠና እንጂ በሌላውም አካባቢ ስላልተፈቀደ ይሆናል ሴቶች ብቻ የሚሰሩት)።
አብዛኞቹ የሸክላ ምርት ዕቃዎች በዘመናዊ መንገድ በሚሰሩ የፕላስቲክ ዕቃዎች ስለተተኩ በሸክላ ምርቶች ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል። እስካሁን በዘመናዊ ዕቃዎች ያልተተካው ምጣድ ብቻ ነው። ምጣድ አሰራሩን በማዘመን ኤሌክትሪክ ቢደረግም ምጣዱ አሁንም ሸክላ ነው።
ቀደም ባለው ጊዜ በሸክላ ሥራ የሚተዳደሩት የእርሻ መሬት የሌላቸው ሰዎች ነበሩ። በተለያየ መንገድም ከማህበረሰቡ የተገለሉ ናቸው። አሁን ላይ ግን እንደዚያ አይደለም። በሰለክላካ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ምጣድ የሚሰሩት ከእርሻ ሥራ ጎን ለጎን ነው። ደስ የሚለው ነገር ደግሞ በአካባቢው ማሰልጠኛ ተከፍቶ ልምድ ያላቸው እናቶች እያሰለጠኑ ነው። የትግራይ ክልል መስተዳድርም ለሙያው ትኩረት በመስጠት በሽሬ ‹‹ደሐብ ተስፋዬ›› በአዲግራት ‹‹ማርታ መብርኃቱም›› የተሰኙ ማሰልጠኛዎችን ከፍቷል። እነዚህ ማሰልጠኛዎች በቱሪስቶች ይጎበኛሉ፤ የሸክላ ሥራዎችን ይሸጣሉ።
ይህ ማሰልጠኛ የሸክላ ሥራዎችን በቴክኖሎጂ እያዘመነም ይገኛል። በባህላዊ መንገድ ይሰሩ የነበሩ የሸክላ ሥራዎች አሁን በዘመናዊ መንገድ በምጣድም በድስትም እየመጡ ነው። የኤሌክትሪክ ምድጃዎችንም ከሸክላ መሥራት እየተቻለ ነው። እነዚህን ምድጃዎች አዲስ አበባ ውስጥም እያየን ነው።
ባህላዊ የዕደ ጥበብ ሥራዎች እንዲህ መንግስታዊ ድጋፍ ቢደረግላቸው ዘርፈ ብዙ ጥቅም ይኖራቸዋል። ሥልጣኔን ያጠነክራሉ፣ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፣ በአገር ውስጥ ምርጥ በመጠቀም ወጪን ይቀንሳሉ፣ የሥራ ፈጠራ ባህልን ያዳብራሉ።
እነዚህ የዕደ ጥበብ ሥራዎቻችን ይዘምኑ ዘንድ መንግስት ተገቢውን ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል። ህብረተሰቡም የራሱ አኩሪ ባህል መሆኑን አምኖ ሊጠብቃቸው ይገባል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 10/2012
ዋለልኝ አየለ