ለበዓል ወደ ቤተሰብ በሄድኩበት አጋጣሚ አንድ ጓደኛዬን አገኘሁት። ይህ ጓደኛዬ አብረን የተማርን ሲሆን እሱ እዚያ የተማርንበት ትምህርት ቤት ውስጥ መምህር ሆነ። በተገናኘን ቁጥር ያለፈ ትዝታችንን እያነሳን እንጫወታለን። በዚህ ዓመትም ተገናኝተን ተጫወትን።
በጨዋታችን ውስጥም ያው ‹‹ሥራ እንዴት ነው?›› የሚለው በሁለታችንም በኩል ተነሳ። በተገናኘን ቁጥር የሚነግረኝ ነገር የተማሪዎችን ጎበዝ አለመሆን ነበር። እኔም የቅርብ ጓደኛዬ ስለሆነ ‹‹መምህሩ ጎበዝ ሲሆን ነው ተማሪ ጎበዝ የሚሆን›› እያልኩ በቀልድም በቁም ነገርም እነግረዋለሁ።
እሱም ‹‹ስላላየኸው ነው የምትፈርድ! ምንም ማንበብና መጻፍ የማይችልን ተማሪ ከየት ጀምሮ ነው ጎበዝ ማድረግ የሚቻል›› እያለ ይሞግተኛል (እሱ የሚያስተምረው ሁለተኛ ደረጃ ነው)። ይሄም ከታች ክፍል ያሉ መምህራን ችግር ነው እየተባባልን እንከራከራለን።
በዚህ ዓመት የነገረኝ ነገር ግን ከዚህም ከበድ ያለ ሆነ። ‹‹ተማሪዎችን ‹ምን መሆን ትፈልጋላችሁ?› ብትላቸው፤ እንደ ድሮው ‹ዶክተር፣ ኢንጂነር..› የሚሉ እንዳይመስልህ! ምኞታቸው፤ ሴቶች ወደ አረብ አገር፣ ወንዶችም ወደ ወርቅ ቁፋሮ ነው የሚሉህ›› አለኝ። ምኞታቸው ብር የሚያገኙበትን አጋጣሚ ማመቻቸት ነው። ትምህርት የማይማሩ ጓደኞቻቸው ሄደው የመጡበት አካባቢ መሄድ ነው ፍላጎታቸው። ወላጆችም ገንዘብ ካመጡልን በማለት ብዙም አይቆጧቸውም፤ እንዲያውም ይባስ ብሎ የሚፈቅዱላቸውና ሂዱ የሚሏቸውም አሉ። ቁጥራቸው በዛ ያለው ከ5ኛ ክፍል በታች ያሉት ናቸው። እነሱም ዕድሜያቸው ገና ለመሄድ ስላልደረሰ ነው።
ይሄ የመሄድ ፍላጎት ገና በልባቸው ሲጠነሰስ ለትምህርቱ ትኩረት አይሰጡም። መሄድ ሳይችሉ ቢቀሩ እንኳን ፈተና አያልፉም። እንኳን ሀገር አቀፍ ፈተናዎች ላይ የክፍል ውስጥ ፈተና እንኳን የሚያመጡት ውጤት ዝቅተኛ ነው።
ከዚህም በላይ አሳዛኙ ደግሞ የተማሪዎች ብቻ ሳይሆን የመምህራኑም ተስፋ መቁረጥ ነው። ‹‹ምክንያቱ ምን ይሆን›› ያልኩት ጓደኛዬ እንደሚለው የብዙ መምህራን ቅሬታ ከደመወዝና ጥቅማጥቅም ጋር፣ ከሥራ መሰላቸት ጋር የመጣ ነው። የሥራ መሰላቸቱንም ያመጣው ከኑሮ ውድነት ጋር የሚከፈለን ክፍያ አይመጣጠንም በሚል ቅሬታ ነው።
ይሄ ነገር ትውልድ መግደል ነው። መምህራን መንግስት ላይ ያላቸውን ቅሬታ የሚገልጹት ተማሪ ላይ ከሆነ ይሄ የእውቀት አባትነት ሳይሆን ጨለማን ማውረስ ነው። እርግጥ ነው የሚከፈለው ክፍያ በቂ ነው ማለት አይደለም። በቂ አለመሆኑ ግን የተማሪዎችና የወላጆች ችግር አይደለም፤ የመንግስት ችግር ነው። ያንን ከመንግስት ጋር ነው መነጋገር። እልሃቸውን ተማሪ ላይ አይደለም መወጣት ያለባቸው። የጠየቁት ጥያቄ ካልተመለሰ ወይም በውይይት መፍትሔ ላይ ካልደረሱ ሥራውን መልቀቅና የተሻለ ካለ መፈለግ ነው!
በነገራችን ላይ ይሄ ችግር የሚታየው መምህራን ላይ ብቻ አይደለም። በብዙ የመንግስትም ሆነ የግል ተቀጣሪ ሰራተኞች ላይ የሚታይ ነው። የግል ላይ ቢዝረከረክ በነገታው እንደሚባረር ስለሚያውቀው ማንም አይዝረከረክም። የመንግስት ተቋማት ላይ ግን ይሄ ነገር ጎልቶ ይታያል። ብዙ ጊዜ የታዘብኩትን ነገር ልንገራችሁ።
የመንግስት መስሪያ ቤቶች ሾፌር ይቀጥራሉ። ሹፌሮችም ሰራተኞችን ወደ ሥራ ቦታ ይወስዳሉ። ይህ ሲሆን ታዲያ ሾፌሮች በለቅሶና በጭቅጭቅ ነው። ከመስሪያ ቤት ሲወጡ አለቃቸው ያዘዛቸውን ‹‹እሺ›› ብለው ይወጣሉ። ከዚያ በኋላ ከሠራተኛው ጋር ጭቅጭቅ ይፈጥራሉ። ‹‹እዚህ ቦታ አልሄድም፣ በዚህም አልሄድም፣ እዚህ አልጠብቅህም›› ይላሉ። ይባስ ብሎ በፉከራ ‹‹ማን አባቱ ነው የሚያዝዘኝ፣ እስኪ ማን እንዲህ አድርግ እንደሚለኝ አያለሁ!›› እያሉ ፉከራ!
የቅሬታቸውን ምክንያት ሲናገሩም፤ ‹‹በዚህ ደሞዝ አልሰራም! አንተ ይህን ያህል እየተከፈለህ እኔ ልፈጋልህ ነው!›› እና ታዲያ ሥራውን ለቆ የተሻለ ካለ መፈለግ ነዋ!
ወደ መምህራኑ ስንመለስ የእነርሱ ደግሞ ከዚህም ይከፋል። የእነርሱ ማኩረፍ እንደሌላው ማኩረፍ አይደለም። ትውልድ ላይ ነው እየሰሩ ያሉት።
የተማሪዎች ተስፋ መቁረጥ ግን የመምህራን ችግር ብቻም አይደለም። ይሄ የወላጆችም ችግር ነው። አለፍ ሲልም የትምህርት ዋጋ ማጣት ነው። ከእነርሱ በፊት የተማሩ ሲያማርሩ ከሰሙ ከታች ያሉት ተስፋ ይቆርጣሉ። ተምሮ ሥራ የለም፤ በደመወዝ መኖር ከባድ ነው፣ ሥርዓተ ትምህርቱ ሀገር በቀል እውቀት ላይ ያተኮረ አይደለም… የሚሉ ቅሬታዎች ተደጋግመው የሚሰሙ ናቸው። ታዲያ ይሄን እየሰሙ ይሆን?
የትምህርት ነገር ገና ብዙ ያልተስተካከለ ነገር አለው። አዲስ በወጣው የትምህርት ፍኖተ ካርታ ላይ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ ዲግሪ ያለው ይሆናል ተብሏል። ይሄ ጥሩ ነገር ነው። የመምህራን ብቃትና ቆራጥ ውሳኔም አንዱ አጠያያቂ ነገር ስለነበር። ከ10ኛ እና ከ12ኛ ክፍል ውጤት ያልመጣለት ተማሪ ነበር እኮ መምህር የሚሆነው! ከዩኒቨርሲቲ የተመረቀውም ቢሆን ብዙም የተሻለ አይደለም። ባዮሎጂ፣ ኬሚስትሪ፣ ፊዚክስ ትምህርት ክፍል የሚመደቡት ከ12ኛ ክፍል ዝቅተኛ ውጤት ያመጡት ናቸው። እነዚህ ወሳኝ እና ለሁሉም የትምህርት ክፍል መሰረት የሆኑት የትምህርት አይነቶች ‹‹ኮምፒቴሽናል ሳይንስ›› በሚለው ውስጥ ናቸው። ይሄ ዘርፍ ማለፊያ ነጥቡን ብቻ ያመጡ ተማሪዎች ሳይመርጡት የሚመደቡበት ነው። እንደ ህክምና፣ ምህንድስና፣ ጤና፣ መሬት አስተዳደር፣ የመሳሰሉ የትምህርት ክፍሎችን መርጠው የሞሉ ተማሪዎች ያንን ካላገኙ የሚመደቡት ‹‹ኮምፒቴሽናል›› እና ‹‹አዘር ሳይንስ›› የሚባለው ውስጥ ነው። መምህር የሚወጣው ደግሞ ከዚህ ዘርፍ ውስጥ ነው። ብቻ ጠለቅ ብሎ ላሰበው ሰው የትምህርት ነገር ብዙ ትኩረት ይፈልጋል!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 10/2012
ዋለልኝ አየለ