ቅድመ -ታሪክ
በልጅነቱ ደስተኛ ሆኖ አያውቅም። በየምክንያቱ መናደድና መቆጣት መለያው ሆኖ ቆይቷል። ብዙዎች ስሜቱን አውቀው ለመረዳት ይቸግራቸዋል። የሚቀርቡት ቢኖሩ እንኳን ቋንቋውን በወጉ የሚያውቁና በተለየ የሚያውቁት ብቻ ናቸው። ከብዙዎች በቀላሉ ያለመግባባቱ ደግሞ ለብስጭቱ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል። ሀሳቡን የሚረዳለትና የልቡን የሚሞላለት ባጣ ጊዜም ተቃውሞውን የሚገልጸው በጩኸትና በመነጫነጭ ብቻ ነበር።
ተክሉ ግደይ በተወለደ በአንደኛ አመቱ ባጋጠመው የጤና እክል ምክንያት ክፉኛ ታሞ ቆይቷል። ከህመሙ ድኖ ዕድሜው ከፍ ማለት ሲጀምር ደግሞ ሁለቱም ጆሮዎቹ መስማት እንደተሳናቸው ታወቀ።
ወላጆቹ ችግሩን ባወቁ ጊዜ ውስጣቸው በሀዘን ተመታ። አይተው ካልጠገቡት ሕጻን ልጃቸው አንደበት የተኮላተፈ ድምጽን ሲሹ በዝምታ መሸበቡ ከልብ አስከፋቸው። ውሎ አድሮ ግን ስለነገው ህይወቱ ማሰባቸው አልቀረም። ከሌሎች ልጆቻቸው ሳያንስና የበታችነት ሳይሰማው እንዲኖር ዕቅድ አውጥተው ተነጋገሩ።
ተክሉ ዕድሜው ከፍ ማለት ሲጀምር ለእሱ በተመቸ ቦታ አስመዝግበው ቀለም ሊያስቆጥሩ ትምህርት ቤት ላኩት። እሱም የመጀመሪያዎቹን ጊዜያት በሰላም ሲማርና ትምህርቱን በፍቅር ሲቀበል ቆየ። የልጅነት ጊዜውንም ከሌሎች መስሎና ከአቻዎቹ ተዛምዶ አጋመሰ።
ጥቂት ቆይቶ ግን የልጁ ባህሪ ቁጡና ነጭናጫ መሆን ጀመረ። ከጓደኞቹና ከቤተሰቦቹ ያለመግባባቱም በኩርፊያና በሀይለኝነቱ እንዲታወቅ ሰበብ ሆነ። ይህኔ የባህሪውን መቀያየር ያስተዋሉ አንዳንዶች ከድርጊቱ ተነስተው ግምታቸውን አስቀመጡ። ምንአልባት የአዕምሮ ጉዳት ገጥሞት ከሆነ በሚልም ለመፍትሄው ተማከሩ።
ወላጆች ለዚህም ቢሆን መላውን አላጡም። ሀኪም ዘንድ ቀርበው አማከሩ። ወደ አማኑኤል ሆስፒታል በተላኩ ጊዜም ራሳቸውን አበርትተው የመጣውን ሁሉ ሊቀበሉ ተዘጋጁ።
ተክሉ በሆስፒታሉ በቂ ህክምና ከተሰጠው በኋላ ጤናው ተመልሶ መልካም ጠባይን ማሳየት ያዘ። መድኀኒቱን ትቶም እንደወትሮው ሆኖ መታየት ጀመረ። ይህን ለውጡን ያስተዋሉ ወላጆቹም ፍቅር እየሰጡና በጎነትን እያሳዩ እንደባህሪው ሆኑለት።
ከአመታት በኋላ
አሁን ተክሉ የትናንት ታሪኩ ተቀይሮ በአዲስ ጎዳና ቆሟል። ቀድሞ የጀመረው ትምርት እርሾ ሆኖትም በቀለም ትምህርቱ ሊበረታ እየተዘጋጀ ነው። ያስጨንቀው የነበረ ማንነትና ከብዙዎች ያለመግባባት ችግሩ ተወግዶም ጎበዝ ተማሪ ወጥቶታል። ይህን ለውጡን ያስተዋሉ ቤተሰቦቹም ያሻው ይሆን ዘንድ ዛሬም ከጎኑ ናቸው። የበታችነት እንዳይሰማውና ህመሙ እንዳይነሳም በእጅጉ ይጠነቀቃሉ።
ተክሉ ልጅነቱን አጋምሶ የጉርምስና ዕድሜ ላይ ደርሷል። ትምህርቱን ባሰበው ደረጃ ሲገፋም ለሙያ ትምህርት ፍላጎት እንዳለው ያወቁ ወላጆቹ እንደሀሳቡ ሁሉን አመቻችተውለታል።
ጥቂት ቆይቶ ደግሞ የእንጨት ሙያ ባለቤት ሆነ። በተማረው ዕውቀት ታግዞም ራሱን ለመቻልና የሀሳቡን ዳር ለማድረስ አቀደ። ነገሮች ግን እሱ እንዳሰባቸው አልሆኑም። ሙያውን በእጁ ቢይዝም ፈጥኖ ስራ ያለማግኘቱ እውነት ያበሳጨው ጀመር።
ገንዘብ ለመቁጠር የነበረው ጉጉትና ራስን ለመቻል የያዘው ውጥን ብትን ሲልበት በሀሳብ መናወዝና መበሳጨት ጀመረ። ይህኔ ውስጡ በንዴት ግሞ የሚውለው ወጣት ባህሪ ከወትሮው መናወጥ ያዘ። እንዲህ በሆነ ጊዜም ምክርና ተግሳጽ አስጠላው። የቀድሞ ጠባዩ ምልክቶችም ይስተዋልበት ጀመር።
የአመል ግርሻ
አንድ ቀን ተክሉ ቤተሰብ ገዝቶ የሠጠው ሞተር ሳይክል በድንገት ነደደበት። ለመበሳጨት ምክንያት ይፈልግ የነበረው ወጣት ይህ አጋጣሚ ክፉኛ አበሳጨው። ንብረቱ በቀላሉ እንደማይጠገን ባወቀ ጊዜም በእጅጉ ተስፋ ቆረጠ።
ተስፋ መቁረጡ ደግሞ ከገንዘብ ማጣት ጋር ተዳምሮ ሌላ ባህረይን አስከተለ። የኪሱን ባዶነት ለመሙላት ሲልም የተቀመጠን ማንሳትና መስረቅን ልምዱ አደረገ። ይህን ክፉ አመልግን ቤተሰቦቹ ሊታገሱት አልቻሉም። ድርጊቱን ኮንነው በግልጽ ተቃወሙት።
ተክሉ በየቀኑ የሚስተዋልበት ያልተገባ አመል ከሁሉም ሊያግባባው አልቻለም። እንዲህ መሆኑ ደግሞ በእሱ ዘንድ ያለውን ትርጉም የከፋ አደረገው። ሁሌም ባይተዋርነትና የበታችነት እየተሰማውም በእልህ ከንፈሩን ሲነክስ መዋል ልማዱ ሆነ።
ከሁሉም ግን አንድ ቀን በድንገት ተነስቶ የፈጸመው ድርጊት ብዙዎችን የሚያስደነግጥ ሆነ። በመኖሪያ ቤት የነበረን ክላሽን ኮፕ መሳሪያን ጥይት አቅሞ እንዳሻው ተኮሰበት። ፖሊስ በስፍራው ደርሶ ወደ ጣቢያ እስኪወስደው ለአብዛኞቹ አስደንጋጭ ሆኖ ነበር።
ከወራት እስር በኋላ ፖሊስ ጉዳዩን መርምሮና በምክር አሳምኖ ወደቤቱ መለሰው። የእሱ ባህሪ ግን እንደ ቀድሞ ሆኖ ቀጠለ። ደጋግሞ ወደ ጣቢያ መሄድና በእስር ማሳለፍም ግድ ብሎት ቆየ።
የእስር ቤቱ ምልልስና የቤት ውስጥ አለመስማማት ለተክሉ ሰላም ማጣት ምክንያት ሆነው። የምልክት ቋንቋው መልዕክትም ብስጭቱን መግለጫ ሆነ። ስራ ያለማግኘቱና ገንዘብ ያለመያዙ በየቀኑ ሲያብከነክነው ይውላል። ይህን ስሜቱን ለመግለጽም ሰበብ እየፈለገ ይነጫነጫል።
ተክሉ ከቤተሰቦቹ ጋር ያለመግባባቱ ጉዳይ የተለመደ ሆኗል። እነሱ አመሉን የሚችሉት ናቸውና እንዳሻው ቢሆን አይከብዳቸውም። በቅርብ ጊዜ ቤተሰቡን ከተቀላቀለችው የቤት ሰራተኛ ጋር ግን በቀላሉ መግባባት የቻሉ አይምስልም። እሷ በቤታቸው በተቀጠረች ጊዜ እሱ ዘመድ ለመጠየቅ ከከተማ ርቆ ነበር። ተመልሶ ሲመጣና መኖሯን ሲያውቅም እንደሌሎች ሊግባባት ልቡ አልፈቀደም።
ትዕግስትም የእሱን የምልክት ቋንቋ በቀላሉ መረዳት አልሆነላትም። አንዳንዴ የፈለገውን እንድትፈጽም ባዘዛት ጊዜ የሚላት ሁሉ አይገባትም። ነገሮችን በግምት ላለመፈጸምም ሁሌም ዝምታን ትመርጣለች። ይህ መሆኑ ደግሞ ለተክሉ ብስጭት ፈጥሮበታል። የእሷን ዝምታም ከንቀት ቆጥሮ ቂም ይይዝባት ጀምሯል።
ወጣቷ ሰራተኛ በቤቱ የተገኘችበትን ዓላማ ጠንቅቃ ታውቀለች። ከሀገሯ አውጥቶ በዚህ ስፍራ ያቆማት የእንጀራ ጉዳይ ብቻ ነው። ስራዋን በአግባቡ ከውና ግዴታዋን ለመወጣትም ከብዙዎቹ ጋር ተግባብቶ አዳሪ ነች። ባህሪዋን የሚወዱላት አሰሪዎቿም ስለእሷ ያላቸው ክብርና ፍቅር የተለየ ሆኗል።
ተክሉ ግን ይህን መልካም ግንኙነት በበጎ ተርጉሞት አያውቅም። ሁሌም በትዕግስት ላይ ግልጽ ቅሬታውን ያሳያል። ቤተሰቦቹ በእሷ ጉዳይ ምላሽ ያለመስጠታቸውም እውነት ዘወትር ያናድደዋል።
እሱ ለምግብ ያለው አቋም የተለየ የሚባል ነው። በዚህ ጉዳይ ደግሞ ከትዕግስት ጋር የሚግባቡ አልሆኑም። እሷ አዘጋጅታ የምትሰጠው መቼም ቢሆን ጣፍጦት አያውቅም። ሁሌም ለእሱ ተብሎ የሚቀርበው ምግብ ከሌሎች ሁሉ በጣዕሙ ያነሰ መስሎ ይሰማዋል።
ይህን ስሜቱን ለመግለጽ ደግሞ ለቤት ሰራተኛዋ ማስረዳት የሚፈልገው በጩኸትና በማመናጨቅ ብቻ ሆኗል። የእሱን ቋንቋ የማትረዳው ትዕግስትም ምግቡን አቅርባ ዞር ከማለት የዘለለ ምላሽ ባለመስጠት አቋሟ ጸንታለች።
ሰራተኛዋ ከአሰሪዎቿ የሚሰጣትን አብቃቅታ ከማዘጋጀት የዘለለ ምግቡን በተለየ አጣፍጣ ለማቅረብ አይቻላትም። ይህን እውነት ለተክሉ ለማስረዳትም የንግግር ችሎታው የላትም። እናም የእሱን ጩኸትና ማመናጨቅ ችላ ዝምታን መርጣለች። ዝም…
ሰሞኑን ደግሞ ተክሉ በአዲስ ባህሪይ ተመልሷል። ‹‹አይጣፍጠኝም›› የሚለው ምግብ ጤናውን ነስቶ ለህመም እየዳረገው መሆኑን ለወላጆቹ እየገለጸ ነው። እነሱ ተክሉ የሚለውን ተረድተው እንደሁልጊዜው በዝምታ አልፈውታል። በተለይ ወላጅ አባቱ በየጊዜው ስለሚያነሳው ተቃውሞ ተሰላችተው ችላ ብለውታል። እሱ ግን አሁንም ስለሚሆነው ሁሉ ትዕግስትን ተጠያቂ እያደረገ ነው።
ለምግቡ አለመጣፈጥና ለእሱ ጤና መጓደል አሁንም ሠበቧ የቤት ሰራተኛዋ ትዕግስት ብቻ ነች። እሷ ደግሞ ተክሉ ያሻውን ቢል ከዝምታ ሌላ ምላሽ የላትም። ይህ ተደጋጋሚ ልማድ ደግሞ ተክሉን ከመቼውም ይበልጥ ያስቆጣው፣ ያ ናድደው ጀምሯል።
ህዳር 24 ቀን 2008 ዓ.ም
በዚህ ቀን ማልዶ የነቃው ተክሉ ከመኝታ ክፍሉ ሆኖ ከወዲያ ወዲህ ማለት ጀምሯል። ቁርስ ለመብላት ቢፈልግም ደፍሮ ከጠረጴዛው ለመቀመጥ ውስጡ አልፈቀደም። አሁንም ምግቡን ከበላ በኋላ ስለሚፈጠርበት ክፉ ስሜት እያሰበ ነው። ይህን ሲያስብ ደግሞ ሰራተኛዋን ያስታውሳል። በእሷ ማንነት ውስጥ ሁሌም ውል የሚልበት ዝምታም ንዴቱን ቀስቅሶ ያበሳጨዋል።
ተክሉ በሀሳብ መሀል ሳለ የቤታቸውን ተከራይ ስትገባ ተመለከታት። በምልክት ሰላም ብላው የያዘችውን ቁርስ እያስቀመጠችለት ነበር። ቁርሱን ሰርታ ለእሷ የሰጠቻት ደግሞ ሰራተኛዋ እንደሆነች አውቋል። ምግቡን ሲያይ ረሀብ ተሰማውና ለመብላት ተዘጋጀ። እጅጌውን ሰብስቦ አንዴ ሲጎርሰ ግን ፊቱ ተኮሳትሮ የግንባሩ ስር ተግተረተረ።
የቀረበለት ቁርስ ዛሬም አልጣፈጠውም። እየተበሳጨ ሰሀኑን ገፋና ሰራተኛዋን በአይኖቹ ፈለጋት። ትዕግስት ቀጣዩን ክፍል እያጸዳች ስለነበር ፊት ለፊት አልታየችውም። ያለችበትን ሲያውቅ ግን ከተቀመጠበት ተነስቶ ዋናውን በር ዘጋው። ከወጥ ቤት ገብቶም መሳቢያውን ሲከፍት የፈለገውን አገኘው።
ትዕግስት የጀመረችውን የቤት ጽዳት ለመጨረስ እየተጣደፈች ነው። ገና በርከት ያለ ስራ ይጠብቃታል። ዕቃዎቹን እያነሳች ታሰናዳለች። የተዝረከረከውን ሰብስባም መልክ ታስይዛለች። መወልወያውን ጨምቃ ዞር ስትል ግን ከተክሉ ጋር ተፋጠጠች። በእጁ ረጅም ስለት መያዙን ስታይ እየጮኸች ራሷን ለማዳን ሞከረች። እየገፈተረችም አጠገቧ እንዳይጠጋ ታገለቸው።
ተክሉ በዋዛ የሚመለስ አልሆነም። ስለቱን እንደጨበጠ ተንደርድሮ ቀረባት። ያለአንዳች ርህራሄም ከሰውነቷ እየሰካ መላ አካሏን ወጋጋት። በደም ተነክራ እንደተዳከመች የድረሱልኝ ጩኸት አሰማች። ከደጅ ሆና ጩኸቱን የሰማችው ተከራይ በሩን ለመክፈት እየታገለች ትዕግስትን ለማዳን ሞከረች። አስቀድሞ የተቆለፈው በር ግን እሷን ለማስገባት ምቹ አልሆነም። ሴትዬዋ ይህን ስታውቅ እጇን አሾልካ የበሩን ቁልፍ እንዲሰጣት ምልክት አሳየችው። ተክሉ ግን ይህን ለማድረግ አልፈቀደም።
ወይዘሮዋ በሩን እንደማይከፍት ስታውቅ በሌላ በር ዞራ በብረት ዘነዘና መስታወቱን ሰበረችው። አሁንም በሩ በቀላሉ የሚያስገባት አልሆነም። ይህኔ ሰራተኛዋን በስሟ እየጠራች በሩን እንድትከፍትላት ጠየቀች። ከውስጥ በኩል አንዳችም ድምጽ ሊሰማት አልቻለም።
አሁን ተክሉ ራሱን ለማሸሽ መላ አየፈለገ ነው። ይህን ለማድረግ ያለው አማራጭ ደግሞ ከቤቱ አንደኛውን በር ተጠቅሞ ማምለጥ ብቻ ይሆናል። በቆመበት አቅጣጫ እንቅስቃሴውን የሰማችው ሴት ቀድማ ደርሳ ቁልፉን ተቀበለችው። ወዲያው ግን እጆቹና ልብሱ በደም ተበክሎ አስተዋለች።
የፖሊስ ምርመራ
የወንጀሉን መፈጸም ሰምቶ ጉርድ ሾላ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤት የደረሰው የፖሊስ ግብረ ሀይል የሟችን አስከሬን አንስቶ የቴክኒክ ምርመራዎችን አካሂዷል። ሟች በከፍተኛ የስለት ጉዳት ህይወቷ ማለፉን አረጋግጦም ተጠርጣሪውን ለመያዝ ፍለጋውን ቀጥሏል። በመርማሪ ሳጂን አማረ ቢራራ የሚመራው ቡድን ተጠርጣሪውን አድኖ ለመያዝ ጊዜ አልፈጀበትም። ተክሉን እምብዛም ሳይርቅ በቁጥጥር ስር አውሎታል።
አሁን በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 517/08 ተመዝግቦ መረጃ የተጠናከረበት ፋይል በአግባቡ ተሰንዶ ለአቃቤ ህግ ተላልፏል። አቃቤ ህግም ተጠርጣሪውን ለክስ አቅርቦ ተገቢውን የፍርድ ውሳኔ ለማሰጠት ቀነ ቀጠሮ አስይዟል።
ውሳኔ
ሰኔ 10 ቀን 2009 ዓ.ም
በዚህ ቀን ችሎት የተሰየመው የአራዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተከሳሹን የፍርድ ውሳኔ መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት በቀጠሮው ተገኝቷል። ተከሳሹ ሆን ብሎ ሰው በመግደል በፈፀመው ወንጀል ጥፋተኛ ስለመሆኑ በበቂ ማስረጃዎችና መረጃዎች ተረጋግጧል። በመሆኑም ከድርጊቱ ይማርበት ዘንድ እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የአስራ ስድስት አመት ከስድስት ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጣ በይኖበታል።።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 10/2012
መልካምስራ አፈወርቅ