ወጣት ሠለሞን ሙላው ከአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ደባርቅ ከተማ ተነስቶ አዲስ አበባ የመጣው «ወጣቶች ለአገራዊ ለውጥና ሠላም›› በሚል መሪ ሃሳብ ከአገሪቷ የተለያዩ ክፍሎች ለተውጣጡ ወጣቶች በተዘጋጀው የሠላም ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ነው፡፡ በመድረኩ የሰላምን አደራ ይዘው ወጣቶች ለሠላም ዘብ መቆም እንዳለባቸው በእንብርክክና በእንባቸው የተማጸኑት እናቶች ልዩ ስሜት እንደፈጠሩበት ይናገራል፡፡
‹‹አሁን ላይ ቆሜ መሄዴና ከመሰሎቼ ጋር በአንድ አደራሽ ውስጥ ተቀምጬ ስለ ሠላም ማውጋት መቻሌ ሠላም ቢኖር ነው፡፡ አሊያ ግን እንኳንስ እንዲህ ተሰባስቦ መወያየት ይቅርና የምንረከባት አገር አትኖረንም፡፡አንዳንድ ጊዜ ከማን ጋር መኖር እንዳለብን ሁሉ ስጋት ይገጥመንና እንዲህ ዓይነት የሰላም መድረኮች ሲፈጠሩ ደግሞ የተስፋ ጭላንጭል ይታየናል›› በማለት በሰላም እጦት ውስጥ የተስፋ ብርሃን እንደሚጠፋ ይናገራል፡፡ለኢትዮጵያ ህልውና ወጣቶች እጅጉን እንደሚያስፈልጓት፣ሳይከፋፈሉ ኢትዮጵያዊ የሚለውን ስም በማስቀደም ለሠላም መቆም እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባል፡፡
ከትግራይ ክልል በሠላም ጉባዔው ላይ የተሳተፈው ወጣት ደጀን አብርሃ ፤‹‹ሠላም ለወጣቶች ንጹህ አየር ከመተንፈስ ያልተናነሰ ጥቅም አለው›› ይላል፡፡የሰላም እጦት መጨረሻው አገርን ማጣት እንደሆነና ከዚህ ችግር ለመውጣት ወጣቶች አገርን በሠላም በመጠበቅ ረገድ ኃላፊነትን በአግባቡ እንዲወጡ እንዲሁም ለውጡን በግለሠብ ደረጃ ከራስ መጀመር እንደሚያስፈልጋቸውም ይናገራል፡፡
‹‹እኛ ወጣቶች ጊዜን በበጎም ሆነ በመጥፎ እንደፈልግነው ልንጠቀምበት እንችላለን፡፡ ጎጂ የሆኑና ሠላምን የሚያደናቅፉ ተግባራትን በመጠየፍ የሚጠቅመንን ሠላም ማስፍን ይኖርብናል፡፡ እርስ በርስ በመረዳዳት ያሉብንን ጉድለቶች ማረም ይጠበቅብናል፡፡ ነገሮችን ሰከን ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥትም ከንግግር ባለፈ ተግባራዊ ሥራ በማከናወን የሚጠበቅበትን መፈጸም ይኖርበታል፡፡እኛም ከመንግሥት ጎን ሆነን ከሠላም በተቃርኖ የቆሙትን ልናጋልጥ ይገባናል››
በማለት ወጣቶች ግጭትና ተያያዥ ችግሮችን በመቀነስ ተሳትፏቸውን ስለሚያሳድጉበት እሴቶች ጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ ወጣቶች ለግጭትና ተያያዥ ችግሮች ያላቸውን ተጋላጭነት በመቀነስ ተሳትፏቸውን ለማሳደግ ለመብቶቻቸውና ጥቅሞቻቸው መከበር ብሎም ለአገሪቱ ዘላቂ ሠላም መረጋገጥ ተዋናይ እንዲሆኑ፤ ወጣቶች በራሳቸው አንደበት በሰላም ዙሪያ የተቀሩትን ወጣቶች በማስተማር የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጡ ለማስቻል የኢፌዴሪ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር፣ የሠላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን በጋራ ባዘጋጁት ጉባዔ በርካቶች ታድመዋል፡፡ በየክልሎቹ በመሄድ የሰላምን ዋጋ መልዕክት የሚያስተላለፉት ‹‹የሠላም አምባሳደር እናቶች›› ታዳሚውን በእንባ ያራጨና እርስ በርስ ያስተቃቀፈ የሠላም ቃልኪዳን ቃል አስፈጽመዋል፡፡
‹‹ከሀገራችን 65 በመቶ ገደማ የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል በወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ እንደመሆኑ የአገሪቷ መፃዒ ተስፋና ዕድል እጅግ አጓጊ ሆኖ ይታየኛል፡፡ በሌላ አነጋገር ኢትዮጵያ የወጣቶች ሀገር ነች ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆይ ሳይሆን፤ በርካታ ዓመታትን የሚሻገር እውነታ ነው» በማለት የተናገሩት ደግሞ የሠላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ናቸው፡፡
ይህንን አጓጊ ተስፋ ባለቤቱ ራሱ በአግባቡና በጥንቃቄ መስራት ሲችል መሆኑን ገልፀው ፤ ይህም ነገን በትውስት ወይም በውክልና ሳይሆን በባለቤትነት ማረጋገጥ እንደሚያስችል ይጠቅሳሉ፡፡«በሌላ መልኩ ዛሬ የምንኖረው በትናንትናው ትውልድ መስዋዕትነት፤ ከነገው ትውልድም ትውስታ ነው፡፡ ስለሆነም ባለ አደራም፣ ባለ ዕድልም ነን» ያሉት ሚኒስትሯ ወጣትነት በርካታ ዕድሎችና ችሎታዎች ያሉት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
እንደሚኒስትሯ ማብራሪያ፤ ወጣትነት ውስጥ የታመቀ ችሎታ፣ አዳዲስ ነገሮችን የማወቅ፣ ፈልጎ የማግኘትና የመስራት እምቅ ኃይል አለው፡፡ ይህንን እውን ለማድረግ ከግለሠብ ሠላም ጀምሮ የሀገርን ሠላም እስከማረጋገጥ የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህ ሁኔታና እውነታ የበለፀገችና የዳበረች አገር ባለቤት ለመሆን እንደሚያስችል ሁሉ የዚህ ጫፍ ደግሞ ከየትኛውም የህብረተሰብ ክፍል በላይ የሚጎዳው ወጣቶችን ነው፡፡
የወጣቱን እምቅ ኃይል በአግባቡ በመንከባከብ መምራት ከተቻለ የብልጽግና ባለቤትነትን እንደሚ ያረጋግጥ ይጠቅሳሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋስትናው ሠላም መሆኑን አመልክተው ከራስ ጋር ሠላም መሆን ለሌሎችም የስጋት ሳይሆን የደስታ ምንጭ በመሆኑ ሠላምን በመስጠት የሰላም ባለቤት መሆን እንደሚ ያስፈልግ ያስገነዝባሉ፡፡ የወጣቶች የበርካታ ችሎታ ባለቤትነት ከወጣቶች ውጭ ሌላው ጋር መገኘት አይችልም፡፡ ልዩ ፀጋ ያላቸው እንደመሆኑ ሠላምን በመገንባት ረገድ አንድም ለራሳቸው ሌላም ለተተኪው ትውልድ ድምር ኃላፊነትና ተልዕኮ አለባቸው፡፡
የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትሯ ወይዘሮ ያለም ጸጋይ በበኩላቸው፤ ያለ ሠላም መሰባሰብና መመካከር፤ ያለሰላም ማቀድና መተግበር፤ ያለ ሠላም ማደግና መለወጥ፤ ያለ ሠላም ወጥቶ መግባትም ሆነ በአንድ መወያየት የማይታሰብ ነው ይላሉ፡፡ የሰላም እጦት የሚያስከትለውን መዘዝና የሚያስከፍለው ዋጋ የከፋ መሆኑን አጎራባች አገሮች ታሪክ በመማር ነገን የተሻለ ለማድረግ ምክንያታዊ የመሆንና ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ የመፍታት ባሕል ማጎልበትና በዚያ ደረጃ ትርጉም ሰጥቶ መስራት ብልህነት እንደሆነ ነው ያስገነዘቡት፡፡
ወይዘሮ ያለም፤ በአገሪቷ ሠላምን ለማስጠበቅ በሚያስፈልግበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ቢኮንም የማህበረሰቡን ሠላም የሚያውኩ እኩይ ተግባራት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየታዩ መሆናቸውን በመግለጽ፤ ወጣቶች ያለ ሰላም ስኬትን መጎናጸፍ እንደማይታሰብ ተገንዝበው ለሠላም እጦት መንስኤ ከሆኑ ተግባራት ራሳቸውን ማራቅ እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡ ወጣትነት የአይቻልምን የአስተሳሰብ ኬላ በጥበብና በእውቀት በጣጥሶ ማለፍ የሚያስችል ፀጋና ብርቱ ተነሳሽነት በተፈጥሮ የሚቸሩበት ወርቃማ የዕድሜ ምዕራፍ እንደመሆኑ፤ይህንን ከባድ ኃላፊነት ለመወጣት የተጎናጸፏቸውን ፀጋዎች ከተፈጠረላቸው መልካም አጋጣሚዎች ጋር አዋህደው በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 12/2011
አዲሱ ገረመው