ለቴሌኮምና ዲጂታል መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ መመደቡን ኢትዮቴሌኮም አስታወቀ

 – ገቢውንም 163 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ለማድረስ አቅዷል

አዲስ አበባ፡- ኢትዮቴሌኮም በ2017 በጀት ዓመት የቴሌኮምና ዲጂታል መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ዶላር መመደቡን አስታወቀ፡፡ ገቢውን 163 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር፣ የደንበኞቹን ቁጥር 83 ሚሊዮን ለማድረስ ማቀዱም ተገልጿል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ ኢትዮቴሌኮም በ2017 በጀት ዓመት የቴሌኮምና ዲጂታል መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ መመደቡን ተናግረዋል፡፡

የዲጂታል ኢትዮጵያና የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ አስተማማኝ በሆነ የቴሌኮምና ዲጂታል መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ይደረጋል ያሉት ሥራ አስፈጻሚዋ፤ እነዚህን ማስፋፊያዎች ተግባራዊ ለማድረግ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ዶላር ተመድቧል ብለዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ አጠቃላይ የደንበኞችን ብዛት 83 ሚሊዮን ለማድረስ መታቀዱን ጠቅሰው፤ የሞባይል ደንበኞችን ቁጥር 79 ነጥብ 7 ሚሊዮን ለማድረስ ታቅዷል ብለዋል፡፡

የሞባይል ዳታና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን 47 ነጥብ 4 ሚሊዮን፣ የፊክስድ ብሮድባንድ ደንበኞችን 934 ሺህ ለማድረስ ታቅዷል ሲሉም አብራርተዋል፡፡

የቴሌብር አገልግሎት በስፋት ተደራሽ በማድረግ የደንበኞችን ቁጥር 55 ሚሊዮን ለማድረስ እንደታቀደ በመግለጽ፤ የወኪሎችን ቁጥር 275 ሺህ፣ ግብይት የሚፈጽሙ ነጋዴዎችንም 367 ሺህ ለማድረስ ታቅዷል ብለዋል፡፡

የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ ዓለም አቀፍ ስትራቴጂያዊ አጋርነትን በማስፋት፣ ተወዳዳሪ አገልግሎት በማቅረብ፣ የረሚታንስ አገልግሎት ለማሻሻል እንደታቀደ ጠቅሰው፤ በበጀት ዓመቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት መጠኑን ወደ 282 ነጥብ 85 ሚሊዮን ዶላር ለማሳደግ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

የቴሌኮም መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት አንድ ሺህ 298 አዲስ የሞባይል ጣቢያዎችን ለመገንባት መታቀዱን የገለጹት ሥራ አስፈጻሚዋ፤ የ4ጂ አገልግሎት በ500 ተጨማሪ ከተሞችና የ5ጂ አገልግሎት በ15 ተጨማሪ ከተሞችን ተደራሽ ለማድረግ ታቅዷል ብለዋል፡፡

አቅርቦትን ከማረጋገጥ አንጻር ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ የቴሌኮም መሣሪያዎችን ለግለሰብና ድርጅቶች ለማቅረብ መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ኩባንያው የቴሌኮምና የዲጂታል መሠረተ ልማቶችን በመጠቀም የደንበኛ እርካታን የሚያሳድጉ ጥራት ያለው አገልግሎቶች ለማቅረብ እንደሚሠራ ጠቅሰው፤ የቴሌኮምና የዲጂታል መሠረተ ልማቶችን በመዘርጋት፣ ለዜጎች፣ ቢዝነሶችና ተቋማት ዘመናዊ ዲጂታል መፍትሔዎች እንደሚያቀርብ ገልጸዋል፡፡

በዲጂታል መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ከመሠረታዊ የቴሌኮም አገልግሎቶች ባሻገር የድርጅት ደንበኞችን አሠራር ሥርዓት የሚያዘምኑ አሠራሮች እንደሚተገበሩ በመግለጽ፤ የመረጃና የጥሪ ማዕከል አገልግሎት፣ የቪዲዮ፣ የጌምና የሙዚቃ አገልግሎቶች፣ የዲጂታል ግብርና፣ ጤናን ጨምሮ ትምህርትና ስማርት ከተማ አቅርቦት ለማሳደግ መዘጋጀታቸውንም አስረድተዋል፡፡

የሰው ሠራሽ አስተውሎት ትግበራ የተጀመሩትን አጠናክሮ መቀጠልና በኔትዎርክ፣ የቴሌኮም ማጭበርበርን ለመከላከል ጥቅም ላይ እንደሚውል ገልጸው፤ የደንበኞችን አገልግሎት ከማሻሻል አንፃር በስፋት ለመጠቀም መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የገቢ አማራጮችንና የገቢ መጠን ከማሳደግ በተጨማሪ የኩባንያውን የወጪ ቁጠባ ስትራቴጂ ትግበራን በማጠናከር ሦስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ያህል ወጪን ለመቆጠብ መታቀዱንም ገልጸዋል፡፡

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን መስከረም 10/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You