ዳዊት ድሪምስ በአስተሳሰብ ላይ አተኩረው የሚሰሩ ባለሙያ ናቸው። እያንዳንዱ ሰው የአስተሳሰቡ ውጤት ነው። ሀገርም የዜጎቿ አስተሳሰብ ውጤት ናት የሚል አስተሳሰብ አላቸው። ዳዊት ድሪምስ ከ6 ዓመታት በፊት ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ለሀገሩ እንግዳ ለሰው ባዳ ከመሆናቸው ባሻገር አማርኛም ሆነ ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን መናገርም ሆነ መጻፍ አይቸሉም ነበር። በዚህም ላይ በእጃቸው ላይ ከ3,000 ብር በላይ ገንዘብ አልነበራቸውም። ሆኖም ግን ስድስት ዓመታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አማርኛ ከመናገር አልፈው መጽሃፍ ጽፈው ለማሳተም በቅተዋል። ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ሰዎች በአስተሳሰብ ለውጥ ዙሪያ መሳጭ ስልጠናዎችን ሰጥተዋል። ነግደውም አትርፈዋል።
ስድስት ዓመታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ይህ ሁሉ እንዴት ሊሆን ቻለ የሚለውን እንደሚከተለው በዝርዝር ይዘን ቀርበናል። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፤- አቶ ዳዊት ወይም ዳዊት ድሪምስ የተሰማራበትን ሙያ ዘርፍ ምን ብለን ልንጠራው እንችላለን
ዳዊት ድሪምስ፤- እኔ በሰዎች አስተሳሰብ ዙሪያ የምሰራ ባለሙያ ነኝ። የሰዎች አስተሳሰብ የሁሉም ነገር መፍጠሪያና ማድረጊያ ትልቅ መሳርያ ነው። እያንዳንዱ ሰው የአስተሳሰቡ ውጤት ነውና ስራዩም እንዲሁ ከሰው ልጅ ሁለንተናዊ አስተሳሰብ ጋር የተያያዘ ነው።
አዲስ ዘመን ፤- ወደ እዚህ የሙያ ዘርፍ እንዴት ልትገባ ቻልክ
አቶዳዊት፤- ከስድስት ዓመት በፊት ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የማውቀው አንድም ሰው ካለመኖሩም በላይ በእጄ ላይ ከሶስት ሺ ብር በላይ አልነበረኝም። በዚህም ላይ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው አማርኛ ቋንቋ መናገርም ሆነ መጻፍ አልችልም ነበር።
አዲስ ዘመን፤- የዛሬ ስድስት ዓመት ነው የሚሉኝ
ዳዊት ድሪምስ፤- አዎ የዛሬ ስድስት ዓመት
አዲስ ዘመን፤- አሁን ከመናገርም አልፈው ቅኔም ይቀኛሉ፤ ተረትም ይተርታሉ እኮ
ዳዊት ድሪምስ፤- ዋናው ነገር እኮ ይሄ ነው። ከፈለከው የምታጣው ነገር የለም። የሰው ልጅ ካሰበበት የማያሳካው ነገር የለም።
አዲስ ዘመን፤- እሺ ወደ ተነሳንበት ጉዳይ እንመለስ
ዳዊት ድሪምስ፤- እንደነገርኩህ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ በቂ ገንዘብም ሆነ የኔ ነው የምለው ዘመድም የለኝም። ሀገሩንም አላውቀው፤ ቋንቋውንም አልችልም። ነገር ግን ውስጤን አንድ ነገር ነገርኩት። መኖር አለብኝ። እንደ ሰው ሰርቼ መለወጥና ከራሴም አልፌ ለሌሎች የምረዳ ምሳሌ የምሆን ሰው መሆን አለብኝ ብዩ ለራሴ ቃል ገባሁ። በነዚህ ችግሮች ውስጥም ብሆን ችግሮቹ እኔን ጎትተው ሊያስቀሩኝ እንደማይገባና ያሰብኩበት ቦታ መድረስ እንደምችል እራሴን አሳመንኩት። ገቢ የማገኝበትን ስራ ለመስራት ወሰንኩ። በህይወት ለመቀጠል ከዚህ ውጭ አማራጭ አልነበረኝም። አማራጭ አለኝ ብል እንኳን በማላቀው ሀገርና፤ የእኔ ነው የምለው ስው በሌለበት ወድቆ መቅረት እንጂ የምሸሸግበት ጓዳ እንኳን የለኝም። በወቅቱ ለአንዳንድ ሰዎች ሳማክር በማታውቀው ሀገር፤ በቂ ገንዘብ ሳይኖርህና የምትግባባበት ቋንቋ እንኳን ሳታውቅ እንዴት ብለህ ነው ነግደህ የምታተርፈው ቢቀርብህ ይሻላል የሚል ምክር ለገሱኝ። እኔ ግን ውስጤን ስላሳመንኩት የሰዎቹን ምክር አልተቀበልኩም።
ስለዚህም ባለችኝ ሶስት ሺህ ብር የኮምፒውተር ቤት ለመክፈት ወሰንኩ። እንዳሰብኩትም ከፈትኩ። ብዙ ፈተናዎች ቢኖሩትም ውስጤ እርግጠኛ ስለነበረ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ሆንኩ። ነገር ግን ከነበረኝ ፍላጎትና የመለወጥ ጉጉት አንጻር በቀን ለምን አንድ ሺህ ብር አላገኝም የሚል ምኞት አሳደርኩኝ። ሳይውል ሳያድር ህልሜን አሳክቼ በቀን ያሰብኩትን እንድ ሺህ ብር ማግኘት ጀመርኩ። ይህ ሁሉ የሚሆነው ከኤርትራ በመጣሁ አንድ አመት ሳይሞላኝ ነው። ሚስጥሩ ለገባው ሰው ህልም ማቆሚያ የለውም። በአገኘው ነገር ረክቶ አይቆምም። በቀን አንድ ሺህ ብር ማግኘቴ የበለጠ ምኞትና ጉጉት አሳደረብኝ። እናም በቀን 10 ሺህ ብር ማግኘት አለብኝ ብዩ ወሰንኩ።
ህልሜንም ለማሳካት 22 አካባቢ ተከራይቼ ካፍቴሪያ ከፈትኩ። እንዳሰብኩትም በቀን 10 ሺህ ብር ማግኘት ጀመርኩ። እንዲያውም በቀን ከ15 ሺህ ብር በላይ ማግኘት ችዬ ነበር። ሚስጥሩ ስለገባኝ በቀን 15 ሺህ ብር ማግኘቴ ምንም አላስገረመኝም።
አዲስ ዘመን፤- ሚስጥሩ ስለገባኝ ሲሉ
ዳዊት ድሪምስ፤- ሚስጥሩ ምን መሰለህ። የሰው ልጆች ሲፈጠሩ ከነሙሉ ብቃታቸው ነው። አንዱ ከአንዱ አይበልጥም፤ አንዱ ከአንዱ አያንስም። መበላለጡ የሚመጣው በአስተሳሰብ ልዩነት ነው። በማንም ላይ ጥገኛ አልሆንም፤ ሁሉንም ነገር የማድረግ ብቃት አለኝ፤ እችላለሁ የሚሉ ሰዎች
ማንኛውንም ዕውቀት ና ሀብት መቆጣጠር ይችላሉ። ሁሉም ነገር ለእነሱ የተዘጋጀ እና የተመቻቸ ነው። በዙሪያቸው ያሉ ነገሮች በሙሉ ይሰግዱላቸዋል። መልካም አስበዋልና መልካም ይገጥማቸዋል። በተቃራኒው ምንም ማድረግ እንደማይችሉ የሚያስቡና ሁሉንም ነገር ከ40 ቀን ዕድላቸው ጋር የሚያያይዙ ሰዎች፤ በእንቅፋትና በጋሬጣ የተከበቡ፤ ምሬታቸው ሌላ መሬት የሚወልድ፤ ለሁሉም ነገር ሌሎችን የሚወቅሱ ስለሚሆኑ የአስተሳሰብም ሆነ የገንዘብ ድሆች ናቸው።
ወደ ተነሳሁበት ጉዳይ ልመልስህና 22 አካባቢ በከፈትኩት ካፍቴሪያ በቀን ከ15 ሺህ ብር በላይ እየሰራሁ በነበርኩበት ጊዜ በድንገት መንገዱ ለልማት መቆፈር ጀመረ። የመንገድ ቁፋሮው ለረጅም ዓመታት በመቆየቱ በአካባቢው እንኳን የንግድ እንቅስቃሴ ለማድረግ ለመዘዋወርም በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጠረ። ካፌው ስራ አቆመ። መንገዶች ባለስልጣን ሄደን ብንጠይቅም ከአንድ ዓመት በፊት ስራው እንደማይጠናቀቅ ነገሩን። አንድ ዓመት ጠበቅኩ፤ ስራው አላለቅም። ሁለት ዓመት ጠበቅኩ አሁንም አላለቀም። ሶስት ዓመት ሆነ አሁንም ስራው አላለቀም። እኔም ለሶስት ዓመታት ያህል ያለስራ ለቤት ኪራይ ከፍተኛ ወጪ በማውጣቴ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ከሰርኩ።
በዚህ ወቅት አንድ ውሳኔ ላይ መድረስ እንዳለብኝ አመንኩ። መንገዶች ባለስልጣንን እና ዕድሌን እያማረርኩ ከመኖር ካጋጠመኝ ችግር እንዴት መውጣት እንዳለብኝ ማሰብ ጀመርኩ። ያለኝ ገንዘብ በሙሉ ከስሯል። ገንዘብን ለምጄ ገንዘብን አጣሁ። የሆነ ሆኖ ህይወትን እንደ አዲስ አንድ ብዬ ለመጀመር ወሰንኩ። ከተጠቀምንበት ችግር ብልሃትን ይፈጥራልና ዛሬ የህይወቴ መሰረት የሆነውን መንገዴን በችግሬ ውስጥ አገኘሁት።
ውስጤ የነበረውን
ከራሴም አልፌ ሀገሬን ከሀገሬም አልፌ አፍሪካን የመለወጥ ህልም ፍንትው ብሎ የታየኝ በዚህ ችግር ውስጥ ሆኜ ነው። እንደበርካታ
ሰዎች በመንገዱ መፍረስ ምክንያት መንግስትን እያማረሩ ከመኖር በቁዘማ ውስጥ ህይወትን ከመግፋት ችግሩን ለሌላ ድል መወጣጫ ለማድረግ
ወሰንኩ። በነገራችን ላይ አሁንም ድረስ በመንገዱ መፍረስ ምክንያት ህይወታቸው የተናጋና መንግስትን ከመውቀስ ውጪ ሌላ ህይወት መጀመር
ያልቻሉ በርካታ ሰዎችን አውቃለሁ። የእኔ መንገድ የተለየ ስለነበረ የገጠመኝ ችግር ሌላ አዲስ ዕድል ወለደ። ዛሬ ከ1.5 ሚሊዮን
በላይ ዜጎች ተጠቃሚ የሆኑበት፤ በርካቶች ከህልማችው ጋር የተገናኙበትና ከራስም አልፎ ለሃገር ብሎም ለተቀረው ዓለም መትረፍ የሚችል
ሀሳብ የሚፈልቅበት
ማዕከል ተወለደ።‹‹ Dawit Dreams success coach›› የሚባለው ማዕከል ዕውን ሆነ። የድርጅቱ አላማ ሰዎች ትልቅ ህልም እንዲኖራቸው፣ ህልማቸውን እንዲያሳኩ የሚያስፈልጋቸውን እውቀት ማስተማር ነው። ሁሉም ሰው ትልቅ ህልም አለው። ነገር ግን ህልሙን ወደ ተግባር ለማሸጋገር ገንዘብ የለኝም፤ ዕውቀቱ የለኝም፤ ሰው ኣላውቅም የሚሉና መሰል ምክንያቶችን ሳይደረድሩ ውጤት ላይ እንዲደርሱ የበኩሉን አስተዋጽኦ የማድረግ ራዕይ ያለው ማዕከል ነው።
አዲስ ዘመን፤- ሁሉም ሰው ትልቅ ህልም አለው እንዴ
ዳዊት ድሪምስ፤- ሁሉም ሰው ትልቅ ህልም አለው። ህልሙንም ዘወትር ያየዋል። ሀብታም መሆን፤ ጥሩ መኪና ማሽከርከር፤ መማር፤ ማደግ፤ መበልጸግ የሁሉም ሰው ምኞት ነው። ህልም የሚመነጨው ከፍላጎት ነውና ሁላችንም ህልም አለን። ነገር ግን ልዩነታችን ህልማችንን ወደ ተግባር ማሸጋገሩ ላይ ነው። በመጀመሪያ በራሳችን ላይ ጽኑ እምነት የለንም፤ ባይሳካልኝስ፤ ይሄ ይቀረኛል፤ ይሄ ይጎድለኛ፤ ይሄ ያቅተናል እያልን በፍርሃት ተሸብበን በተመሳሳይ ህይወት ውስጥ እንኖራለን። በሌላ በኩል ደግሞ መስዋዕት ለመክፈል ዝግጁ አይደለንም። የያዝኳትን ይዤ ብኖር ይሻለኛል በሚል የፍርሃት ቆፈን ውስጥ ተሸሽገን ዘመናችንን እንገፋለን። ለአዕምሯችን ሁልጊዜ የምንነግረው የማይቻልባቸውን መንገዶቸ ነው። ይህን አስተሳሰብ ሰብረው የወጡት ግን ህልማቸውን በቀላሉ ማሳካት ይችላሉ።
የህልም ዓላማ ዕድገት ነው። እንደ ሰው መኪና እገዛለሁ ብሎ አልሞ መኪና ቢገዛ መኪናው ህልሙ ያስገኘለት ሽልማት እንጂ የመጨረሻው ውጤት አይደለም። ሰውዩው መኪና ስለገዛ ሂደቱን አያቋረጥም ። ደግሞ ሌላ ነገር ያልማል። አንዱን በአንዱ ላይ እያሳካ ወደ ዕድገት ምዕራፍ ውስጥ ይገባል። ስለዚህም ህልም ያላቸው ሰዎች አይቆሙም፤ በእድገት ላይ እድገት እየጨመሩ፤ ከራሳቸውም አልፈው ለሌላው ይተርፋሉ። በቁሳቁስ ብቻም ሳይሆን በአስተሳሰብም ለሌሎችም ለሀገርም ይተርፋሉ።
አንድ ሰው በወር 10 ሺ ብር የሚያገኘው አቅሙ የ10ሺ ብር ስለሆነ አይደለም። ነገር ግን አስተሳሰቡ 10 ሺ ብር ላይ ስለተገታ ነው። የሚያሰላስለው፤ አብሮ የሚያሳልፋቸው ጓደኞቹ፤ የሚያነባቸው መጽሃፎች አጠቃላይ ሁኔታው ከ10 ሺ ብር የዘለለ አይደለም። 10ሺ ብሩን ላለማጣት እንጂ፤ ይሄ ለኔ በቂ አይደለም ፤ የበለጠ ማግኘት አለብኝ ብሎ ስለማያስብ ነው በ10 ሺ ብር ተወስኖ የሚቀረው። ይህ ሰው ግን እምንቱን አስተካክሎ 100ሺ ብር ማግኘት አለብኝ ብሎ ቢነሳ ያለምንም ጥርጥር ህልሙን ማሳካት ይችላል። የሰው ልጆች የእምነታችን እስረኞች ነን። የምናገኘው የምናምነውን ነው።
አዲስ ዘመን፤- ህልም ያላቸውና ህልም የሌላቸው ሰዎች ዋነኛ መለያቸው ምንድን ነው
ዳዊት ድሪምስ፤- ሰው ህልም ሲኖረው ጠዋት ተነስቶ ወዴት እንደሚሄድ ያውቃል ምን እንደሚሰራ ያውቃል ምን መስዋዕትነት እንደሚከፍልም ያውቃል። ትልቅ ህልም ያለው ሰው ጠዋት ተነስቶ ህልሙን ለማሳካት ነው የሚሮጠው እንጂ በሌሎች ሰዎች ላይ ትኩረቱን አያደርግም። ዘወትር የሚያስጨንቀው ህልሙ ነው። ለህልሙ ስኬት ደግሞ በተሰማራበት ሙያ ሳይደክምና ሳይሰለች ቀና ደፋ ሲል ይውላል።
ህልም የሌለው ሰው ግን ጠዋት ተነስቶ ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም። ሁልጊዜም ከራሱ ይልቅ ሰዎችን ይወቅሳል። ይነጫነጫል፤ ያማርራል። ያልተሳካለት ከራሱ ጥረት ማነስ ሳይሆን ሌሎች በመንገዱ ላይ ስለቆሙ እንደሆነ ያስባል። ከጓደኛው፤ ጎረቤቱ ወይም የቅርብ ቤተሰቡ አልፎ መንግስትን አልፎም የውጭ መሪዎችንና ሀገራትን ይወቅሳል። ብሎም ያማርራል። ያልተሳካለት ያለው መንግስት ባሳደረበት ተጽዕኖ እንደሆነ ያምናል። ነገር ግን መንግስት ቢቀየርም ሰውየው ግን ተቀይሮ አታየውም። አዲስ አመት በመጣ ቁጥር ኣዳዲስ ሀሳቦችን ያቅዳል፤ ውስጡ ስላልተቀየረ ግን ዕቅዶቹ ከዕቅድ የዘለሉ አይሆኑም።
ህልም ያለው ሰው ለወሬ ለአሉባልታና ፌስ ቡክ ላይ ፖሰት ለሚደረግ ፍሬ ፈርስኪ ወሬ ቦታ የለውም። ከዛም አልፎ ሚዲያ በማዳመጥ ጊዜውን አያጠፋም።
አዲስ ዘመን፤- እንዴት፤ መረጃ አያስፈልግም እንዴ
ዳዊት ድሪምስ፤- መረጃዎች ያስፈልጉናል።
ህይወታችን በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ከመረጃዎች ጋር የተያያዘ ነው። ህልማችንም ለማሳካት ይጠቅሙናል። ነገር ግን አሁን ያሉን
ሚዲያዎች ጥላቻን የሚሰብኩ፤ ብሄርተኝነት የተጠናወታቸው፤ ከመቀራረብ ይልቅ መራራቅን የሚያወሱ፤ አብሮ ከመስራት ይልቅ ግለኝነትን
የሚያጎሉ
ሆነዋል። በሚዲያዎች የሚተላለፉ መረጃዎች በቂ ጥንቃቄ ተደርጎባቸው፤ ተበጥረውና ተለይተው ለሰው በሚጠቅም መልኩ ስለማይቀርቡ ወደ አዕምሮ ገብተው ህመምን ይፈጥራሉ። ልክ የተገኘው ምግብ እንደማይበላ ሁላ ወደ አዕምሮ የሚገባውም መረጃ በአግባቡ ተጣርቶና ታስቦበት ሊሆን ይገባል።
አብዛኞቹ ዜናዎቻችን ተስፋ የሚያስቆርጡ ናቸው። እንድ ሰው ለ30 ደቂቃ ያህል ዜና ሲያይ ካመሸ እንቅልፉ ሰላማዊ አይሆንም። ይደብረዋል፤ ይህ ሂደት ሲደጋገም ቀስ በቀስም ተስፋ ወደ መቁረጥ ይሄዳል። በተለይ በአሁኑ ወቅት በፌስ ቡክ የሚተላለፉ መረጃዎች ጥላቻንና ተስፋ መቁረጥን የሚያስፋፉ በመሆናቸው ጨርሶውኑ አልከተላቸውም። ፌስ ቡክ ስራዬ ብሎ የሚከታተል ሰው አዕምሮው ቀስ እያለ የመፍጠርና አቅሙን እያጣ ይመጣል። ከስራ፤ ከለውጥ፤ ከህልም ይልቅ ቅጽበታዊ በሆኑ አሉባልታዎችና ወቀሳዎች ለይ ስለሚያተኩር ህይወቱ እየቀጨጨ ይሄዳል።
እኔ ፖለቲካ አልወድም ነገር ግን ሀገሬን ለመቀየር ባለኝ አቅም ሁሉ እጥራለሁ። ሀገሬ ድሃ ናት። ስለሆነም ከድህነት እንዴት እንውጣ የሚለው ነው ለእኔ ቀን ከሌሊት የሚያሳስበኝ። አብዛኛው ሰው ሀገሪቱን መቀየር የዶክተር አብይ ድርሻ ብቻ አድርጎ ይወስደዋል። ነገር ግን እያንዳንዳችን ካልተቀየርን ዶክተር አብይ ሀገሪቱን ምንም ሊያደርጋት አይችልም። እናም በተለያዩ ሚዲያዎችና ፌስ ቡክ በርካታ ሰዎች አብይን ሲመክሩና ሲወቅሱ ትሰማለህ። ነገር ግን ከዛ በፊት የአንተን ህይወት ምን ያህል ለመቀየር እየጣርክ ነው ብለህ እያንዳንዱን ብትጠይቀው ምላሽ አታገኝም። ነገር ግን ህይወቴ እንዲለወጥ እኔ ነኝ መቀየር ያለብኝ፤ ሀገሬ እንድትለወጥ እኔ ነኝ መለወጥ ያለብኝ የሚል አስተሳሰብ ካልያዝን መንግስት ወይም ባለስልጣን ላይ ብቻ ጣት በመቀሰር የሚመጣ ለውጥ የለም።
አዲስ ዘመን፡- አንተ ወይም ሌሎች አንተን መሰል ሰዎች ህልማችሁ የት አድርሷችኋል
ዳዊት ድሪምስ፤- እኔ በማላውቀው ሀገርና ህብረተሰብ ውስጥ ተገኝቼ፤ በምንም መልኩ የመናገርም ሆነ የመጻፍ ችሎታ ሳይኖረኝ እና በእጄ ከ3ሺ ብር የዘለለ ገንዘብ ሳልይዝ ትልቅ ህልም በመያዜና ህልሜንም ወደ ተግባር ማሸጋገር በመቻሌ በስድስት ዓመት ውስጥ አማርኛን አቀላጥፌ ከመናገር ባሻገር ጥሩ ጸሃፊም ለመሆን በቅቻለሁ። በቅርቡም በጥሩ የአጻጻፍ ስልት የተዘጋጀ ‹‹ትልቅ ህልም አለኝ›› የሚል መጽሃፍ ለአንባቢያን ለማቅረብ በዝግጅት ላይ እገኛለሁ። ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ከ1.5 ሚሊዮን ለሚበልጡ ሰዎች በአስተሳሰብ ለውጥ ዙሪያ ስልጠናዎችን ሰጥቻለሁ። ከ5ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ውስጥ ወጥቼ ውጤታማ መሆን የቻልኩ ሰው ሆኛለሁ።
በተመሳሳይም አስተሳሰባቸው በመለወጡ አስገራሚ ሊባል የሚችል ለውጥ ያመጡ በርካታ ሰዎችን አውቃለሁ። በቅርብ የማውቃቸው ሁለት ሰዎች ኢትዮጵያን ንጹህ፤ ውብና አረንጓዴ የማድረግ አላማ ነበራቸው። ሁለቱም ያለመታከት ህልማቸውን ለማሳካት ባደረጉት ጥረት ኢትዮጵያን ውብ፤ ንጹህና አረንጓዴ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ጥሪ ውጤታማ ስራዎችን ለማከናወን ችለዋል። ሀገሪቱንም ንጹህ፤ ውብና አረንጓዴ ለማድረግ ባደረጉት ጥረትም እምነት ስለተጣለባቸው በርካታ ፐሮጀክቶች ተሰጣቸው።
የኢትዮጵያን የግብርና ትንሳኤ ለማረጋገጥ ህልም አልሞ የተነሳ አንድ ወጣትም ወደ ህልሙ የሚያቀርበው ስራዎችን እየሰራ ነው፤ በቅርቡም ውጤቱን ሁላችንም የምናየው ይሆናል። በየስፍራው ተጥለው የምናያቸው የሃይላንድ ላስቲኮች አካባቢውን ማቆሸሻቸው የሚያስቆጨውና ይህንንም ለመቀየር የተነሳ አንድ ወጣት ዛሬ ሃሳቡን ሚደግፉት አጋሮች በማግኘቱ የሃይላንድ ላስቲኮች ወደ ሀብት የሚቀየሩበት ግዜ ሩቅ አይደለም። በአጠቃላይ የተወሰኑትን ጠቀስኩልህ እንጂ በርካታ ሰዎች ህልማቸውን እውን በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ግለሰቦቹ ከህልማቸው ጋር መገናኘታቸው ደግሞ ሀገርም በእግሯ እንድትቆም መሰረት የሚጥል ነው። የበርካታ ሰዎች ህልምም ከግለሰብ አልፎ ለሀገር የሚተርፍ ነው።
በለውጥ አስተሳሰብ ውስጥ ያሉ የሚረዱት ሌሎች ግን ለመረዳት የሚቸግራቸው ነገር አንድ ሰው ህልሙን በየቀኑ ካሰበው ለማሳካትም ከቆረጠ የሚያግደው ምንም ነገር የለም። ‹‹ህልምህን በአዕምሮህ ከሳልከው፤ በልብህ እንደምታሳካው ስታምንና መከፈል የሚገባውን መስዋዕትንት ከከፈልክ ህልምህን በእጅህ ጨብጠኸዋል›› የሚል የተፈጥሮ ህግ አለ። ነገር ግን የብዙዎቻችን ህልም የተከፋፈለና ወጥነት የሌለው ነው። ውጤታማ ሯጭ ሲመለከት ሯጭ መሆን ያምረዋል፤ እግር ኳስ ተጨዋች ለመሆንም ያቅዳል፤ ወዲያውም አክቲቪስት ለመሆን ይዳዳል፤ የፌስ ቡክ አርበኛ ሆኖ ታዋቂ ለመሆን ይከጅላል። ብቻ ያየውን ለመሆን ይመኛል። እንዲህ ሆኖ ደግሞ ውጤት ላይ መድረስ አይቻልም።
አዲስ ዘመን፤- እንደ ሀገር ህልም አለን ወይ
ዳዊት ድሪምስ ፤- እኛ እኮ እንደሀገርም ሆነ ሰው ህልም የማለም ችግር የለብንም። እናልማለን ። ነገር ግን ህልማችንን ወደ ተግባር ለመቀየርና መክፈል የሚገባንን መስዋዕትንት ለመክፈል ግን ዝግጁዎች አይደለንም። በሀገር ደረጃ በየጊዜው የሚወጠኑ ህልሞችም መክነው የሚቀሩት ከዚህ አንጻር ነው።
አዲስ ዘመን፤- የአንተ ህልም ከኢትዮጵያም አልፎ በአፍሪካ ደረጃ አስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ነው። ይህንን እንዴት አሰብከው
ዳዊት ድሪምስ፤- የኔ ዓላማ ሰዎች በግል ሆነ በቤተሰብ ደረጃ ትልቅ ህልም እንዲኖራቸውና ህልማቸውም እውን እንዲሆን መርዳት ነው። ይሄ የመጀመሪያ አላማዬ ነው። በመቀጠልም የእያንዳንዱ አስተሳሰብ ሲቀየር ሀገር፤ ብሎም አህጉርና ዓለማችንም ትቀየራለች የሚል ሁለንተናዊ አስተሳሰብ ነው። በአጠቃላይ ሃሳቡ ኢትዮጵያን፤ አፍሪካን እና አለምን የሚቀይር አስተሳሰብ መፍጠር ነው።
አገራችን ሃብታም ናት። ይሁን እንጂ የአስተሳሰብ ችግር ስላለ በድህነት እየኖርን ነው። ሀብታም ሀገር ብትኖረንም አስተሳሰባችን ሀብታም ስላልሆነ እራሳችን ላይ ፈርደን በድህነት ውስጥ ለመኖር ወስነናል። ሀገራችን ሃብታም ናት፤ መሬታችን ኢትዮጵያን አይደለም አፍሪካን መመገብ ይችላል። ነገር ግን ስንዴ ከውጭ እናስመጣለን። ጥሬ ቡና ወደ ውጭ እየላክን ፕሮሰስ የተደረገ ቡና እናስገባለን። ፍራፍሬ እናመርታለን ነገር ግን ደግሞ ጁስ ከውጭ እናስገባለን። በአጠቃላይ በመሬት ስፋትና ለምነት በህዝብ ብዛት በሁሉ ነገር ሃብታሞች ነን። አእምሮችን ግን ማደግ በሚገባው ደረጃ ሰላላደገ ድሃ ሆነናል።
አሁንም ቢሆን ከአስተሳሰብ ድህነት ውስጥ መውጣት አልቻልንም። ጊዜያችንን እያባከንን ያለነው ርስበርሳችን በመጠላላት፤ በመጠላለፍ እና በመነታረክ ነው። መፍጠር የሚችለውን አዕምሯችንን ለጥፋት እናውለዋለን። ተባብረንና ተመካክረን ሀገራችንን ወደ ፊት ማራመድ ስንችል እርስ በራሳችን እየተጠላለፍን ወደ ኋላ ልንቀር ችለናል። ይሄ ችግር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን አፍሪካ ሙሉ ያለ ችግር ነው። ስለሆነም መጀመሪያ መቀየር ያለብን ራሳችን፤ ከዛ ቤተሰብ፤ ከዛ ማህበረሰቡ፤ ከዛ ቀጥሎ ሃገራችን ከዛ አፍሪካ መሆን አለበት።
አዲስ ዘመን፡ ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ
ዳዊት ድሪምስ፤- እኔም አመሰግናለሁ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 10/2012
እስማኤል አረቦ