‹‹ያለግሉ ዘርፍ ተሳትፎ የሚሠራ ሥራ በአንድ እጅ እንደማጨብጨብ ነው›› ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር)

ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ

ኢትዮጵያ በጥበበኛ እጆች ታንፀው ከቆሙና የቀደመ የስልጣኔ ታሪክ ካላቸው የዓለም ሀገራት መካከል ቀዳሚ ስለመሆንዋ አያጠያይቅም፡፡ ለዚህም ደግሞ ዛሬም ድረስ የስሪታቸው ምስጢር ለዓለም ጠበብታት እንቆቅልሽ ሆነው የቆዩት የአክሱምና የላሊበላ ሕንፃ ግንባታን መጥቀሱ በቂ ነው፡፡ ዳሩ በነበሯት ጥበቦችና ጥበበኞች የሙያተኞችን ሥራ ከመዘከር ባለፈ ኢትዮጵያውያን እውቀትና ክሕሎት ከትውልድ ትውልድ ማሻገር ባለመቻሉ ለኢኮኖሚያዊ እድገቷ ወደኋላ መቅረትም ሆነ ለቀደመ የስልጣኔ ዝናዋ መደብዘዝ በምክንያት ይነሳል፡፡

በተለይ ደግሞ አጉልና ሥራ ጠል የሆኑ ብሒሎች እየጎለበቱ ከመሄዳቸው ጋር ተያይዞ የሚሠሩ ጥበበኞች እንደወንጀለኛ አንገታቸውን የሚደፉባት፤ የማይከበሩባትና የሚገለሉባት ሀገር መፈጠሯንም በድፍረት የሚናገሩ አሉ፡፡ ይህ ጎጂ አመለካከትና ባሕል ታዲያ በሙያ ነክ ትምህርቶች ላይም ቀላል የማይባል አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ እንደሀገር ነባር እውቀቶችን ለጥቅም እንዳናውል ከማድረጉም ባሻገር በላቡ በወዙ ለፍቶ አዳሪው የማደግ ተስፋው ላይ ያስከተለው የጎንዬሽ ጉዳት በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ግን በዓለም ያሉ የበለፀጉ ሀገራት የማደጋቸው ሚስጢር ለሀገር በቀል እውቀትና ክህሎት የላቀ ሥፍራ መስጠታቸው፤ ተዋናዮቹንም በመደገፋቸው ጭምር እንደሆነ እሙን ነው፡፡

እንደ ሀገር ምንም እንኳን ለሥልጣኔ ቀደምት ብንሆንም የኃያሉ ሀገራት ቴክኖሎጂ ማራገፊያ ከመሆን ያላለፍንበት ሚስጢርም ይኸው ነው፡፡ መንግሥት ይህንን የታሪክ ስብራት መቀየር ያስችል ዘንዳ ከትምህርት ስርዓቱ ጀምሮ እስከ ኢንዱስትሪው፤ ከቤተሰብ እስከ መንግሥታዊ ተቋማት ድረስ ከፍተኛ የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት ፖሊሲና የሕግ ማዕቀፎችን ቀርፆ እየሠራ ይገኛል፡፡

በተለይም ደግሞ ለክህሎት ትልቅ ስፍራ በመስጠት እያንዳንዱ ዜጋ ሁለትና ከዚያ በላይ የሙያ ባለቤት የሚያደርግ ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ በዚህና በሌሎችም ሥራዎች ዙሪያ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) ጋር ቆይታ አድርገናል፤ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በቅድሚያ ስለ ክህሎት ምንነት ያብራሩልንና ውይይታችንን እንጀምር?

ተሻለ (ዶ/ር)፡- ክህሎት ለሁሉም ሥራ መግቢያ በር ነው። የክህሎት ሥራ እንደዋና ማርሽ ቀያሪ ሥራ ነው ተብሎ ነው የሚወሰደው። የትኛውም ወደ ሥራ የሚሰማራ ዜጋ ከህሎት አግኝቶ ወደ ሥራ ቢሰማራ ያ ሥራ ዘላቂና ውጤታማ አልያም ወደ ኋላ የማይቀለበስ ይሆናል። በአሠሪና ሠራተኛ መካከል ድልድይ ሆኖ የሚያስተሳስራቸውም በክህሎት የሚገኝ ምርታማነት ነው። ሠራተኛው ምርታማ ወይም በሥራው ውጤታማ ካልሆነ ከአሠሪው ጋር ያለው ግኑኝነት የመበላሸት ዕድሉ ሰፊ ነው። የኢንዱስትሪ ሰላም የሚረጋገጠው አንዱ ሁለቱም አሠሪና ሠራተኛ ምርታማነትን ማዕከል አድርገው ሲነጋገሩ ነው። ሠራተኛውም ይሄ ተቋም የእኔ ነው ብሎ ምርታማነቱን አሳድጎ፤ አገልግሎት አሰጣጡን አሻሽሎ ሲሠራ አሠሪው ለሠራተኛው ማድረግ የሚገባው እያደረገ ሁለቱም ታግዘው ይሄዳሉ የሚል አጠቃላይ አቅጣጫ ነው ያለው።

ክህሎት ስንል ጠቅለል ያለ ነገር ነው፤ ግን በውስጡ እውቀት አለው፤ አመለካከት አለው፤ ሥራ የምንሠራበት ደግሞ የተለየ ችሎታ አለው። ስለዚህ እነዚህን ነገሮች የተጎናፀፈ ሰው ነው በባህሪው ምስጉን የሆነ፤ ሥራ ወዳድ የሆነ ሰው ማለት ነው። በሚሠራው ሥራ ላይ በቂ እውቀት ሊኖረው ይገባል።

በአጠቃላይ አዕምሮውን እና እጁን በአግባቡ የሚጠቀም ሊሆን ይገባል። በተለይ እጅ ለክህሎት ሥራ ወሳኝ ነው፤ አንዱም ልዩ ባህሪያችን እሱ ነው። ከምንም በላይ እጁንም አዕምሮውን እንዲያንቀሳቅስና ሥራ ወዳድ እንዲሆንና ለውጥ እንዲያመጣ የሚያደርገው ደግሞ ልብ ነው። ምክንያቱም ለሥራ ዝግጁ ካልሆነ፤ ለመማር ዝግጁ ካልሆነ ውጤታማ የመሆን እድሉ ዝቅተኛ ነው። በ21ኛው ክፍለ ዘመን እውቀት ሞልቷል፤ ከኢንተርኔትም ሆነ ከተለያዩ ቦታዎች በቀላሉ የሚገኝ ነው። የልብ ዝግጅት፤ ሥራን መውደድ፤ ከባህሪ ጋር የተገናኙ ውጤታማ የሚያደርጉ ነገሮች ግን ከልብ ዝግጅት የሚመጡ ናቸው።

የሰውን አዕምሮ፣ እጁንና ልቡን አቀናጅቶ መሥራት የሚችል ዜጋን በመፍጠር የኢትዮጵያን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ነው የእኛ ዋና ዓላማ። እንደሚታወቀው በእኛ ሀገር ያለው ምርታማነት በቂ አይደለም። ስለዚህ የሶስቱንም ዘርፎች የሚያስተሳስረውና እንደድልድይ ሆኖ የሚያገለግለው የክህሎት ልማት ሥራ ነው። የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከሚሠራቸው ዋና ዋና ሥራዎች አንዱ የክህሎት ልማት ነው። ስለዚህ ሥራና ፈጠራ ሥራው በክህሎት መመራት አለበት የሚል አቅጣጫ ይዘን ነው እየሠራን ያለነው። የሥራ እድል ፈጠራውም ቢሆን በክህሎት እንዲመራ ነው ታቅዶ እየተሠራ ያለው።

አዲስ ዘመን፡- በክህሎት ልማት ረገድ የሀገራት ተሞክሮ ምን ይመስላል?

ተሻለ (ዶ/ር)፡– የክህሎት ልማት በእኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ያሉ ሀገራት የተቀየሩት ክህሎታቸውን ማሳደግ በመቻላቸው ነው። እኛ ብዙውን ጊዜ ልምድ የምንወስድባቸው የአውሮፓ ሀገራት ጭምር የእድገታቸው ሚስጥር ክህሎት ነው። ግን ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያደጉ የኤዢያ ሀገራት ዋነኛ ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ ሀገራት ከልማታቸው ጀርባ ስላለው ሚስጢር ምንነት ብዙ ጽሑፎች ወጥተዋል። ሌሎች ነገሮች ቢኖሩም በዋናነት ግን የሰው ኃይላቸው ላይ የሠሩት ሥራ ነው። ለምሳሌ የኮሪያ በአጭር ጊዜ ውስጥ መቀየር፤ የሲንጋፖር፣ የማሌዢያና መሰል በፍጥነት እያደጉ ያሉ ሀገራት ከጀርባቸው ያለው ትልቁ ነገር ለሰው ልጅ ክህሎት የሰጡት ትኩረት ነው።

እነዚህ ሀገራት የዜጎቻቸውን ምርታማነት አሳድገው፤ (አንዳንዶቹ ሀገራት እንዳውም በቂ የተፈጥሮ ሀብትም አልነበራቸውም)፤ የሰው ኃይላቸውን በማብቃታቸው ምክንያት ከሌሎች ሀገራት የተፈጥሮ ሀብት በማስገባት እሴት ጨምረው ትልቅ ላኪ ሀገራት የሆኑ አሉ። ለምሳሌ ብረት የማያመርቱ ሀገራት ብረትን በጥሬው ከሌላ ሀገር በማስገባት እሴት ጨምረው መልሰው የሚልኩ አሉ። የግብርና ምርቶችም እንደዚሁ ለምሳሌ ቡና ሊሆን ይችላል፤ የተለያዩ እሴቶችን በመጨመር በዓለም ላይ ታዋቂ የሆኑበት ሁኔታ አለ። ስለዚህ አንድን ሀገር ከሌላ ሀገር፤ አንድ አካባቢ ከሌላ አካባቢ ተወዳደሪነት እንደትልቅ ማርሽ ቀያሪ ተደርጎ የሚወሰደው ክህሎት ነው።

አዲስ ዘመን፡- የቀደሙ አባቶችና እናቶችን ሀገርን ገንብተው ለትውልድ ያስረከቡ ቢሆንም የዚያኑ ያህል ኋላቀርና በጎጂ ባሕላዊ የአመለካከት ችግር ምክንያት ለሙያተኞች በቂ ትኩረት ሳይሰጥ በመኖሩ ሀገሪቱን ከእድገት ወደ ኋላ እንደጎተታት ይጠቀሳል፤ በዚህ ላይ የእርሶ ምልከታ ምንድን ነው?

ተሻለ (ዶ/ር)፡– በነገራችን ላይ ስለዚህ ጉዳይ ብዙ ጊዜ ማውራትም፤ መፃፍም ያስደስተኛል። እንግዲህ አስቀድሜ እንዳልኩት ሀገራት የተቀየሩት በእውቀት፤ በክህሎት ነው። ቴክኖሎጂ ማፍለቅ፤ መጠቀም የሚችል ያንን ደግሞ በቀጣይነት ማድረግ የሚችል ትውልድ ገንብቶ ነው እንጂ እንዲሁ ያደገ ሀገር የለም። ስለዚህ በእኛ ሀገር ሁኔታ በምንመለከትበት ጊዜ ለክህሎት ያለን ነገር ከአክሱምና ላሊበላ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የተሠሩ ሥራዎች ኢትዮጵያኖች በክህሎት የተካኑ ጀግኖች እንደነበሯት ማሳያ ነው። የልሂቃንና የጥበበኞች ሀገር መሆንዋም ግልፅ ነው። ሕንፃን ወደ ላይ ሳይሆን ወደ ታች መገንባት የሚችሉ ጥበበኞች ማሕፀን ነች። ብዙ ጊዜ በዓለም ላይ የተለመደው ወደ ላይ መሥራት ነው። እነ ላሊበላና አክሱም ከአንድ ድንጋይ ወደ ታች ሠርተዋል። ይሄ እስከዛሬ ድረስ እንዴት ተሠራ የሚለው ተመራምረንም እስካሁን አልደረስንበትም።

በሌላ በኩል ያንን ጥበብ ከትውልድ ትውልድ ያሸጋገርንበት፤ ያሳደግንበት፤ ያወደስንበት መንገድ በቂ አልነበረም። በሂደት ሙያንና ሙያተኛን የምናይበት መንገድ የተስተካከለ አልነበረም፣ የተሳሳተ ነበር። ለምሳሌ እነዚያን ሥራዎች የሰሩ ጠቢባን፤ የተለያዩ ስያሜዎችን በመስጠት የማንቋቋሽ ባሕል ነው ያዳበርነው። እስከዛሬ ታሪካዊ ተብለው የሚጠቀሱ ትልልቅ ሥራዎችን የተለያዩ ስያሜዎችን በመስጠት ክህሎታቸውን ማድነቅ ሲኖርብን፤ ያንን ወስደን ከዘመናዊ እውቀት ጋር አሁን ከደረሰበት እውቀት ጋር አዋህድን መሄድ ሲኖርብን ባለሙያን የማናናቅ፤ ከሙያ ሥራ ይልቅ ለቢሮ ሥራ ቦታ መስጠት፤ የቆሸሸ ልብስና እጅ ይዞ ከሚሰራ ይልቅ ቢሮ ውስጥ የሚሠራ ሰው የሚከበርበት ባሕል ፈጠርን።

በመሰረቱ አንዱ ሥራ ከሌላው አይበልጥም፤ አንዱ ሌላውን አይተካም። ስለዚህ ሰው ሁሉ ሲያድግ፤ ሲማር ቢሮ ውስጥ ለመግባት ብቻ ነው የሚያስበው። ለሙያ ሥራ የምንሰጠው ቦታ ዝቅ እያለ መጣ። በዚያ ምክንያት እነዚህ ሙያተኞች ሙያቸውን በምንፈልገው ደረጃ ማሳደግ አልቻሉም። አንዳንዶቹ እውቀታቸውን ወደ ቀጣይ ትውልድ በማሻገር ከዚህ ዓለም በሞት የሄዱበት ሁኔታ አለ። ይህንን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) በመጽሐፋቸው ቁልጭ አድርገው ጽፈውታል። እነዚህ ሙያተኞች የሠሯቸው ጥበቦች ከተራ ዜጋ ጀምሮ እስከ ቤተመንግሥት እንዲሁም እስከቤተክህነት ድረስ ጥቅም ላይ የሚውሉ ናቸው።

ቤተክህነት ውስጥ ለቅዳሴ ወይም ለተለያየ አምልኮታዊ ዓላማ የምንጠቀምባቸው እቃዎች በባለሙያ የተሠሩ ናቸው። ከበሮ፣ ፅናፅል፣ መቋሚያውና ሌላውም ሁሉ የተሠራው በባለሙያ ነው። መሣሪያዎችን እንጠቀምባቸዋለን፤ ሆኖም ለባለሙያዎቹ የምንሰጣቸው ቦታ በቂ አልነበረም።

በቤተመንግሥት እንደዚሁ የምንበላባቸው፤ የምንቀመጥባቸው፤ የምንተኛባቸው እቃዎች በሙሉ በባለሙያ የተሠሩ ናቸው። እነዚህን የባለሙያ ውጤት እየተጠቀምን ለባለሙያ ግን የምንሰጠው ክብር ዝቅ ያለ ነው። ከዚህም አልፎ ከሌላው ማሕበረሰብ እንዲገለል አድርገነዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ አንጥረኛ ወይም ሸክላ ሠሪ ሰው ትዳር ለመያዝ እንኳን የሚቸገርበት ዘመን ሩቅ አይደለም። እንደዚህ አይነት ጎጂ አስተሳሰቦች ምንም እንኳን በፖሊሲ የማይደገፉ ቢሆንም፤ አሁን ላይ ብዙ የተቀየሩ ነገሮች ቢኖሩም የቀደመው ኋላቀር ምልከታ ተፅዕኖ ቀላል አይደለም። ዘመን ተሻጋሪ ሆኖ እስከዛሬ ድረስ የሙያን ነገር እንደ ሁለተኛ ነገር እንዲሆን አድርጎታል። ያንን ለመቀየር ነው እንደሚኒስቴር መሥሪያ ቤት እየሠራን ያለነው።

አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አኳያ አሁን ላይ ለክህሎት የተሰጠው ትኩረት ምን ይመስላል?

ተሻለ (ዶ/ር)፡– አስቀድሜ እንደገለጽኩት ኢትዮጵያኖች ወደ ቤተሰብ መሸጋጋር የሚችል ሰፊ ክህሎት ነበሯቸው። ያንን በዘመናዊ ትምህርትና መንገድ እንዲሰፋና በትምህርትና ሥልጠና ስርዓት ውስጥ ገብቶ እንዲሄድ ለማድረግ የተሞከረው ሙከራ በንጉሱ ዘመን ነው። ንጉሡ ለሙያ ትምህርት ትኩረት ሰጥተው ስለነበር በዚያ ጊዜ ተግባረድ የሚባለውን ተቋም በ1934 ዓ.ም ገንብተዋል። እሱን ተከትሎ ሌሎችም ተቋማት ተገንብተዋል።

እነዚህ ተቋማት ለሙያ በተለይ ለእጅ ሥራ፣ ለኢንዱስትሪ ሥልጠና ምቹ ተደርገው ነው የተገነቡት። በኋላ ደግሞ አሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር ያለው የንግድ ሥራ ኮሌጅ የቢዝነስ ሥራዎችም ሆነ ተቀጥሮ መስራት የሚችልበትን ጥበብና ክህሎት እንዲኖረው ለማድረግ ጥረት አድርገዋል።

ተቋማቱ ከተገነቡ ረጅም ዕድሜ ያስቆጠሩ ቢሆንም ቀጣይነት ባለው መልኩ ትኩረት ሰጥቶ ሰፋ ባለ መንገድ የክህሎት ልማት ሥራን በዚያ ደረጃ ተሰርቷል ተብሎ አይታሰብም። ባለፉት 20 ዓመታት ግን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መንግሥት ሠርቷል። አሁን ደግሞ በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው ያለው። ለመጀመሪያ ጊዜ በፖሊሲ ተካቶ፤ ስትራቴጂ ወጥቶለት፣ የሙያ ትምህርት ሥልጠና የማስፋፋት ሥራዎች ተሰርተዋል። ዛሬ በየትኛውም የሙያ አካበቢዎች ብትሄዱ ስፋትና ጥልቀቱ የተለያየ ሊሆን ይችላል በርካታ የክህሎት ማሠልጠኛ ተቋማት አሉ። ከዚህ ቀደም ከተሞች አካባቢ ታጥረው የነበሩት አሁን ገጠር አካባቢዎችም እንዲስፋፋ ተደርጓል። በዚያ መሰረት እንግዲህ ዛሬ ላይ በመንግሥት ብቻ ከ700 በላይ የመንግሥት የቴክኒክና ሙያ ተቋማት አሉ። የግል ደግሞ ከዚያ በላይ አሉ። ይህም የሚያሳየው መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ነው።

ማስፋፋቱ ላይ ብቻ ሳይሆን በተለይ ከለውጡ በኋላ ጥራትን ለማምጣት መሥራት አለብን ተብሎ እየተሰራ ነው። ምክንያቱም የጥራት ጉዳይ አንዱ ስብራት ስለሆነ እሱን በሚጠግን መንገድ ሥራዎች እየሠራን እንገኛለን። ከዚህ ትኩረት የተነሳ ዛሬ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በመደበኛና መደበኛ ባልሆነ መንገድ በየዓመቱ በእነዚህ የክህሎት ማሠልጠኛ ተቋማት ውስጥ ገብተው ይሠለጥናሉ። ይሄ ትልቅ ቁጥር ነው። እሱ ብቻም ሳይሆን ደግሞ ዜጎች ወደ ሥራም ከመሰማራታቸው በፊት አስቀድሜ እንዳነሳሁት ክህሎት መታጠቅ አለባቸው የሚል እሳቤ እንዲስፋፋ፤ ሰው በዘልማድ ሥራ መሥራት የለበትም፤ ቢዝነስም ቢሆን በእውቀት መሠራት መቻል አለበት ብለን እየሠራን እንገኛለን።

እንደሚታወሰው ከሁለት ዓመት በፊት ያፀደቅነው የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ለክህሎት ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቶልናል። እሱን ተከትሎ ስትራቴጂ የወጣ ሲሆን የብቃት ማዕከል ደንብ ወጥቷል። ስለዚህ መንግሥት በርካታ የሕግ ማሕቀፎችን አውጥቶ መንግሥት እየሠራ ነው የሚገኘው። እነዚህን ተቋማትን ደግሞ በሀብት እንዲደገፉ፤ መሰረተ ልማታቸው እንዲያድግ፤ ወቅቱ ከሚጠይቀው አንፃር የዲጂታል መሰረተ ልማትም እንዲሟላላቸውና ሥልጠናው ጥራት እንዲኖረው ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን እየተሠራ ይገኛል።

እኛም እንደሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ምንም እንኳን አብዛኞቹ ተቋማት በክልል የሚገኙ ቢሆንም በመምህራን ሥልጠና፣ በመሰረተ ልማት ግንባታ እንዲሁም በፖሊሲ ቀረፃና በካሪኩለም ቀረፃ ላይ በሰፊው እየሰራን እንገኛለን። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ተደማምረው አሁን ላይ እየተሻሻለ የመጣ ነገር አለ።

እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቢያንስ የአንድ ሙያ ባለቤት እንዲሆን መሥራት ያስፈልጋል። በዚህ ዓመት ሚኒስቴሩ ‹‹አንድ ሙያ ለአንድ ዜጋ›› የሚል ኢኒሼቲቭ ቀርፆ እየሠራ ነው ያለው። ይህ ኢኒሼቲቭ በዋናነት ኢትዮጵያኖች ብዙ ነን፤ ሁላችንም ትምህርት ቤት ገብተን ልንማር አንችልም። መደበኛ ትምህርት 12ኛ ክፍል የጨረሱ ወደ ማሠልጠኛ ተቋማት ሊኖሩ ይችላሉ፤ ይሄ አንድ መንገድ ነው። ሁለተኛው ደግሞ እንደገበያው ፍላጎት አጫጭር ሥልጠናዎችን በመስጠት በቀላሉ ወደ ሥራ እንዲሰማራና ውጤታማ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል የሚል አቅጣጫ ነው።

በተጨማሪም በጣም ብዙ ሰው ጋር መድረስ እንችላለን ብለን ያሰብነው ኢኮኖሚው ውስጥ በልምድ ሙያ አግኝተው የሚሰሩ ሰዎች ግን ደግሞ ሰርተፍኬት የሌላቸውና እውቅና ያላገኙትን የሕብረተሰብ ክፍሎች በስፋት ለመድረስ ነው የታቀደው።

ለምሳሌ በአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት ሥራ ላይ ከኮንሶና ከሐረር አካባቢ የመጡ አርሶአደሮች፤ ወጣቶች አሉ። እነዚህ አርሶአደሮች ወንዝ ዳር ልማት እየሰሩት ያሉት ሥራ እጀግ ጥበብ የተሞላበትና ሀገር በቀል እውቅና መሰረት በማድረግ ነው። ስለዚህ ይህንን ሀገር በቀል እወቀት በዘመናዊ እውቀት ማዳበር ያስፈልጋል። በልምድ የተገኘውን ክህሎት እውቅና የመሰጠት ሥራ ጀምረናል። በሁሉም ክልል ሰርተፍኬት የመስጠት ሥራ ይሰራል።

በተመሳሳይ በኮንስትራክሽን፤ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ በጣም ሰፊ ማሕበረሰብ በልምድ ነው የሚሰራው። በተለይ የሆቴል አገልግሎታችንን በምናይበት ጊዜ ብዙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ሠርተናል፤ ግን አገልግሎታችን ገና ነው። በመሆኑም በተሠሩት መዳረሻዎችና ሆቴሎች ሀገር ተጠቃሚ እንድትሆን ከተፈለገ በዘርፍ ያለው የሰው ኃይል መብቃት መቻል አለበት፤ ክህሎት ሊኖረውና የተመሰከረለት ለሆን ይገባል። ከዚህ አንፃር አርሶአደሮቻችንንም ጭምር በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ ያሉትን የማብቃትና ሰርቲፋይድ ማድረግ ያስፈልጋል። አርሶአደሮቻችን ለረጅም ዓመት ሰርተዋል፤ የቀለም ትምህርት አልተማሩም ማለት እውቀት ወይም ክህሎት የላቸውም ማለት አይደለም። በግብርና ሥራ ላይ ለዓመታት በልምድ ያካባቱት እውቀትና ክህሎት ባለቤት ናቸው። ይህም ሲባል የማያውቁት ነገር ሊኖር ይችላል፤ ስለዚህ ይህንን ሞልቶ ሰርተፍኬት እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል።

ይህ ሲሆን አርሶአደሮቻችን ለምግብ ብቻ ሳይሆን ለወጭ ንግድም የሚያመርቱበት ሁኔታ መፍጠር ይቻላል። እናም አጠቃላይ ዜጋውን የመቀየር ሃሳብ ይዞ ነው እየተሠራ ያለው። አንድ ሰው የሁለትና ከዚያ በላይ ሙያ ሲኖረው አንድ በር ሲዘጋበት ሌላውን ማንኳኳት የሚችልበትን ዕድል ይፈጥርለታል። እዚህ ላይ መተጋገዝ ይኖርብናል። ሰው ክህሎቱን ማሳደግ ከቻለ በእርግጠኝነት ኢትዮጵያ ታድጋለች። ያለብንን የምርታማነት ስብራት መጠገን እንችላለን። በመሆኑም የቴክኒክ ክህሎት ብቻ ሳይሆን የአዕምሮ ብልጽግናም፤ የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ ከሠራን ይቀየራል ብዬ አስባለሁ።

አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ሰፊ የሥራ አጥ ቁጥር የመኖሩን ያህል በተቃራኒው ደግሞ ኢንዱስትሪውም የሰለጠነ ሰው ኃይል እጥረት እንዳለበት በተደጋጋሚ ይነሳል። ከዚህ አንፃር በሁለቱ መካከል ያለውን ከፍተት ለመሙላት ምን እየተሰራ ነው?

ተሻለ (ዶ/ር)፡– ትክክል ነው፤ አንቺም እንዳነሳሽው የፍላጎትና የአቅርቦት አለመጣጣም አለ። በመሰረቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እያለ የሚሠራ ሰው ጠፍቷል ቢባል ማንም ሊያምን አይችልም። በአቅርቦቱና በፍላጎቱ መካከል ያለው ያለመጣጣም ነው፤ ወይም ‘አልተገናኝቶም’ ልንለው እንችላለን። ይህም ሲባል ኢንዱስትሪው የሚፈልገው የሰው ኃይልና ተቋማት ደግሞ የሚያሰለጥኑትና የሚያቀርቡት የሰው ኃይል መካከል አለመጣጣም አለ። ይሄ የሚፈጠረው ተቀራርቦ ካለመሥራት ነው። የእኛ ተቋማት ደሴት ሆነው ከተቀመጡ፤ ኢንዱስትሪው ጋር የማይሄዱ ከሆነ፤ መምህራኖቻቸውንና ሠልጣኞቻቸውን ወደ ኢንዱስትሪው የማይወስዱ ከሆነ፤ በየጊዜው ካሪኩለም ሲቀረፅ ኢንዱስትሪው ምን ይፈልጋል የሚለውን ነገር ዝም ብሎ ተቋማት አጥንቶ መክፈት ብቻ ሳይሆን ኢንዱስትሪውን ማሳተፍ ያስፈልጋል።

የግል ዘርፉ ከካሪኩለም ቀረፃ ጀምሮ በሥልጠናውም፤ መጨረሻ መዝኖ ለእሱ የሚሆነውን ሠልጣኝ እስከመረከብና ወደ ሥራ እስከመሰማራት ድረስ መሳተፍ መቻል አለበት። ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ የግልና የመንግሥት ተሳትፎ የሚፈለገው ደረጃ አልደረሰም። ብዙውን ሥራ መንግሥት ብቻውን ተሸክሞ ነው እየሄደ የቆየው። ያለግሉ ዘርፍ ተሳትፎ የሚሠራ ሥራ በአንድ እጅ እንደማጨብጨብ ነው፤ የፈለገውን ያህል መንግሥት ቢሠራ የግሉን ዘርፍ ሚና ሊተካ አይችልም። የግሉ ዘርፍና መንግሥት በጋራ አብሮ ማቀድና አብሮ መሥራት መቻል አለባቸው። በሌላው ዓለም በተለይ በአውሮፓና በኤዢያ የግሉ ዘርፍ በጣም ይሳተፋል፤ የግሉ ዘርፍ ፋይናንስም ያደርጋል። ይህንን የክህሎት ልማት ፋይናንስ አድርጎ፤ ትምህርት ስርዓቱን (ካሪኩለሙን) ራሱ ቀርፆ፤ ራሱ ሥልጠናውም ላይ ተሳትፎ፤ አስተያየቱን ሰጥቶ የዚህ ሥራ አካል ሆኖ ነው የሚሰራው።

ለምሳሌ በጀርመን የግሉ ዘርፍ ራሱ ‘የሀገሪቱ ተወዳዳሪነት የሚረጋገጠው የሰው ኃይሉ ላይ ከሠራን ነው’ ብሎ ያምናል። የጀርመን ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪ ነው፤ ብዙ ቴክኖሎጂዎችን በዓለም ገበያ ላይ ይሸጣል፤ የግሉ ዘርፍ በርካታ ምርቶችን ወደ ውጭ ይልካል። በተለይ ወደ አፍሪካ ከጀርመን ብዙ ቴክሎጂዎች ይመጣሉ። እነዚህ የቴክሎጂ ምርቶች መኪኖችን ጨምሮ በዓለም ላይ የታወቁ እነማርቼዲስ፤ ቢ.ኤም.ደብሊውን ጨምሮ ከዚያ ነው የሚመጡት። የእነዚህ ኩባንያዎች ተወዳዳሪ መሆን የቻሉት የሰው ኃይሉ ብቃት በማረጋገጣቸው ነው። ቀጣይነት ባለው መንገድ ኢንደስትሪው የሰው ኃይል ብቁ ሲሆን ነው የሚል እምነት ይዟል። በማመናቸውም ይሳተፋሉ፤ ገንዘብም ኢንቨስት ያደርጋሉ፤ ልማትን ይደግፋሉ፤ ያልተሟላ ነገር ካለ ከእግር እግር ተከታትለው አብረው ይሰራሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥም ምንም እንኳን የእኛ ሀገር የግል ዘርፍ ገና ጅምር ቢሆንም ባህሉን ግን መድፈር አለብን ብለን አብረን እየሠራን ነው ያለነው። ብዙ አደረጃጀቶችን እየፈጠርን ነው ያለነው። በቅርቡም ለምሳሌ በግብርናው ዘርፍ የግሉና መንግሥት አብሮ እንዲሠራ የዘርፍ ክህሎት ካውንስል አቋቁመናል፤ ቦርድ አለው፤ ከገበያ ፍላጎት፣ ከካሪኩለም ከመቅረፅ መምህሩን ከመመልመል ጀምሮ ሠልጣኞችን አሰልጥኖ ለገበያው እስከማቅረብ ድረስ በግብርናው ዘርፍ በተለይ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ከግብርና ጋር ተቀናጅቶ የሚሰራ ካውንስል ነው።

የኢንዱስትሪ አማካሪ ቦርድም አለ፤ ከኢንዱስትሪ የተውጣጡ አካላት የተደራጁበት ነው። ይህም ሃሳባቸውን እየሰጡበት መንግሥትም እየመከረበት እዚህ አካባቢ የሚፈጠረውን ክፍተት እንዲሞላ ለማድረግ እየሠራን ነው። ከሌሎችም አደረጃጀቶች ጋር አብረን እንሠራለን። ለምሳሌ የንግድና የዘርፍ ማሕበራት ዘርፍ ከእነሱ ጋር በቅርበት እንሠራለን። ምክንያቱም እነሱ ስር በርካታ የንግድ ድርጅቶች አሉ፤ እነዚያ የንግድ ድርጅቶች ለክህሎት ቦታ እንዲሰጡ፤ ሠራተኞቻቸቸውን እንዲያሰለጥኑና ተመዝነው ሰርቲፋይድ እንዲሆኑና የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ለማድረግ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ ነው።

አዲስ ዘመን፡- በዚህ ረገድ ታዲያ የግሉ ዘርፍ ተነሳሽነት ምን ይመስላል?

ተሻለ (ዶ/ር)፡– አስቀድሜ እንዳልኩት እንደዚህ አይነት ነገሮች እንደባሕል ግንባታ ነው የሚታዩት። በመሆኑም የሥራ ባሕል፤ ተቀራርቦ የመሥራት ባሕል ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚመጣም ብቻ አይደለም። ቀጣይነት ያለው ሥራ መሥራት ይጠይቃል። ለምሳሌ የአውሮፓን ተሞክሮ ብናይ ከሁለተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ጊዜ ጀምሮ ፋብሪካዎች ገና መቋቋም ከሚጀመሩበት ጊዜ የግሉ ዘርፍ በራሱ በፋብሪካው ውስጥ የሥልጠና ተቋማትን እዛው እያቋቋመ የራሱን ሠራተኞች እያሠለጠነ ነው የቆየው። ትምህርት ቤቶቹ የተፈጠሩትም በራሱ በኢንዱስትሪው ነው። በእኛ ሀገር ከዚህ በተቃራኒው ነው። የግሉ ዘርፍ ገና በጅምር ደረጃ ያለ ነው፤ መንግሥት ትምህርት ቤቶቹን አቋቁሞ አሁን ኢንዱስትሪዎቹን ለማምጣት ነው እየሠራን ያለነው። ስለዚህ የታሪክና የባሕልም ልዩነት አለ።

አሁን ላይ ግን የግሉ ዘርፍ ተባባሪ እየሆነ ነው ያለው። እኔም በዚህ ዘርፍ ብዙ እንደቆየ ሰው ያለፉት 10ና 15 ዓመታት ተሞክሮ ስናይ ከጊዜ ወደ ጊዜ የግል ዘርፍ ለክህሎት ወይም ለሰው ኃይል ልማት የሚሰጠው ቦታ እየጨመረ መጥቷል። የሚፈለገውን ያህል ግን አይደለም። ምክንያቱም ከመንግሥት በላይ ሆኖ ያገባኛል ብሎ መሥራት አለበት። ምክንያቱም በዋናነት የእሱ ምርታማነት ነው የሚያድገው። በመሆኑም አሁን ላይ ከሚፈለገው አንፃር ገና ነው። በግል ደረጃ በደንብ በራቸውን ከፍተው ከሥልጠና፤ ከሙያ ተቋማት ጋር የማይሠሩ ኢንዱስትሪዎች ይኖራሉ። ይሁንና በማኅበር ወይም በተቋም ደረጃ የተደራጁ የግሉ ዘርፍ አንቀሳቃሾች በሙሉ ከመንግሥት ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት ፍላጎት አላቸው። አሁን ከዚህ በኋላ እጅ ለእጅ ተያይዘን ተናበን ከሠራን ይለወጣል።

አዲስ ዘመን፡- ዘርፉን ዲጂታላይዝድ በሆነ መንገድ እንደሚመራ ለማድረግ እየተሰራ ስላለው ስራ ያብራሩልን?

ተሻለ (ዶ/ር)፡– የክህሎት ወይም የሙያ ሥልጠና ከሌሎች ሥልጠናዎች የሚለየው ተግባር ተኮር መሆኑ ነው። የሙያ ደረጃው በሚዘጋጅበት ጊዜ ኢንዱስትሪው ላይ ያሉትን ተግባራት ቆጥሮ ወደዚህ በማምጣት ዜጎች ሥራን ነው የሚሰለጥኑት፤ ንድፈ ሃሳብ አይሰላም። ይሄ ሥልጠና ከዚህ በፊት ልማዳዊ በሆነ መንገድ ነበር ሲሰጥ የነበረው። ወርክሾፕ በመገንባት ፤ ሰልጣኞችን ወርክሾፕ ውስጥ ወስዶ የገፅ ለገፅ ስልጠናዎች ነበሩ ሲሰጡ የነበሩት። ይህ አይነቱ ሥልጠና ጥሩ ቢሆንም በቂ አልነበረም። በዚህ ዘመን የትም ሆኖ ስልጠና መውስድ የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል። የግድ ትምህርት ቤት መጥቶ ሳይሆን ቤቱም ሆነ ሥራ ቦታ ሆኖ መሠልጠን የሚችልበትን እድል መፍጠር ይገባል።

ስለዚህ ገፅ ለገፁ እንዳለ ሆኖ በቀጥታ የሚሰጥ የመረጃ መረብ (የኦን ላይን) ትምህርት ሊጨመርበት ይገባል ብለን እየሠራን ነው ያለነው። በተለይ ከኮቪድ በኋላ ይህንን በስፋት እየሠራን ነው። በወቅቱ የቴክኒክና ሙያ ሥርዓቱ ዝግጅት ስላልነበረውና በዲጂታል መሰረተ ልማት ግንባታ ዙሪያ ብዙ ስላልሠራን ሥልጠናውን ማስቀጠል አልቻልንም። ስለዚህ በፍጥነት በሠራነው ሥራ በአሁኑ ሰዓት ሁሉም ክልሎች በሚባል ደረጃ እኛም ከፌደራል ሀብት መድበን በመደገፍ ሁለቱንም ያማከለ አቀራረብ ነው የምንከተለው። ምክንያቱም በቀላሉ ሌላ ዓለም ያለውን ሀብት አምጥቶ ልጆቻችን መማር የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር ነው። በገጠርም ሆነ በከተማ ያለው ዜጋ ተመሳሳይ የሆነ እውቀትና ክህሎት የሚጨብጥበትን ሁኔታ ለመፍጠር ያግዛል።

ይህም ሁለት ነገር ነው የሚፈልገው፤ አንዱ መሰረተ ልማት ሲሆን ብዙ ወጪ የሚጠይቅ ነው። መሰረተ ልማት ዝርጋታው በእነዚህ ሁሉ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ የአይ.ሲ.ቲ መሰረተ ልማቶችን የመዘርጋት ሥራ እየሠራን ነው ያለነው። በዋናነት ግን ሰው ላይ መሥራት ያስፈልጋል። መምህራኖቻችንን ሥልጠና ሲሰጡ ከዚህ በፊት የጀመሩት አይነት አቀራረብ አለ። ስለዚህ ወደ አዲሱ እሳቤ መምጣት ያስፈልጋል። ለዚያ የሚሆን የማስተማሪያ መሣሪያ እንዲያዘጋጁ አስተማሪዎችን ማዘጋጀት ይገባል።

ስለዚህ መሰረተ ልማት ላይ እየሰራን ነው፤ በቀጣይ በቴክኒክና ሙያ ሥርዓቱ ሁለቱንም እያመጋገብን የምንሄድበት ሁኔታ ነው የሚኖረው። እንደተባለው ግን ትልቅ ሃብት የሚጠይቅ በመሆኑ፤ በቅርብ ጊዜ የጀመርነው ስለሆነ በሚፈለገው ደረጃ ደርሷል ማለት አይቻልም። ክልሎችም ሆነ እኛም በጀት እየመደብን ተጋግዘን እየሠራን ነው፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚቀጥሉት ሁለትና ሶስት ዓመታት መቶ በመቶ የቴክኒክና ሙያ ሥርዓቱ ዲጂታላይዝድ የማድረጉን ሥራ እንሰራለን። በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ደረጃ ‘ቲቬት ዲጂታላይዜሽን’ የሚባል ፕሮግራም አለን፤ የተለያዩ አጋሮችም ሃሳብ እየሰጡበት ያለ ነው። መንግሥትም ሀብት እየመደበበት ያለ ነው። በዚህ ፕሮግራም መሰረት በሚቀጥሉት ሁለት ሶስት ዓመታት ሙሉ ለሙሉ ዲጂታላይዝድ የማድረግ ሥራ እንጨርሳለን ማለት ነው።

የዲጂታላይዜሽን ሥራው በተሳካ ሁኔታ መከናወን እንደሀገር ሁለት ነገር ነው የሚያመጣው በዋናነት ተደራሽነቱን ያሰፋዋል። አስቀድሜ እንዳልኩት ሕንፃ በመገንባት፤ ብዙ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት፤ ማሽኖችን በመግዛት ልናደርስ የነበረውን በቀላሉ በዚህ በዲጂታል ቴክኖሎጂ በገጠርም በከተማም እንዲስፋፋ ያደርጋል። ይህም የተደራሽነቱን ችግር ይፈታዋል። ሁለተኛ ጥራት ያመጣል። አስቀድሜ እንደገለፅኩት የክህሎት ሥልጠና በባህሪው በጣም ውድ ነው። ብዙ ቴክኖሎጂ፣ ካፒታል ይፈልጋል። ይህንን በቀላሉ ተቋሞቻችን ማሽነሪ ገዝቶ፣ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን አሟልተው መስጠት የማይችሉትን በቀላሉ በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመጠቀም በአውሮፓም ሆነ በየትኛውም ሀገር የሚሰጠውን ስልጠናና ትምህርት በቀላሉ እኩል እንዲያገኙትና እንዲጠቀሙበት ያደርጋል። ሌላው ይቅርና በገጠርና በከተማ መካከል ያለውን ፍትሓዊነት የማሻሻል ትልቅ አቅም አለው።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።

ተሻለ (ዶ/ር)፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You