«የባሕር በር ጥያቄው በታሪክ አጋጣሚ የተፈጸሙ ስህተቶችን የሚያርም ውሳኔ ነው›› – አምባሳደር ሙክታር ዋሬ

– አምባሳደር ሙክታር ዋሬ በአልጄሪያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር

አምባሳደር ሙክታር ዋሬ ተወልደው ያደጉት አርሲ ስሬ ቀበሌ ነው:: የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ኃይሌ አባ መርሳ እንዲሁም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ስሬ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል:: በመቀጠልም አርሲ ጎሎልቻ በመምህርነት ሕዝባቸውን ሲያገለግሉ ቆይተዋል:: በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንዳገኙም የአርሲ ዞን አስተዳደር እና ጸጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል:: በሥራቸው ባሳዩት ትጋትም ወደ ደቡበ ምዕራብ ሸዋ ዞን በመዘዋወር የጸጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል::

በ1998 ዓ.ም ደግሞ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመዘዋወር የዲፕሎማሲ ሥራቸውን አሃዱ ብለው ጀመሩ:: የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን በተቀላቀሉ በተወሰኑ ጊዜያት ውስጥ ወደ የጅዳ ቆንስላ ጄኔራል ጽ/ቤት ኃላፊ ሆነው ተመድበው ውጤታማ ሥራዎችን አከናውነዋል:: በመቀጠልም ወደ ሱዳን በማቅናት የኢትዮጵያ እና የሱዳንን ግንኙነቶች በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ሲሠሩ ቆይተዋል:: ከሱዳን ቆይታቸው በኋላም ወደ ሎስ አንጀለስ በማቅናት ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት የተጠናከረ እንዲሆን ሙያዊ አስተዋጽኦ አበርክተዋል::

በ2015 ዓ.ም ደግሞ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር በመሆን በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን ተሹመዋል:: ከዚህ ሹመታቸው ጋር ተያይዞም የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄን ፍትሃዊነት ለማስረዳት በርካታ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል:: በኢትዮጵያ እና በሶማሊላንድ መካከል የመግባቢያ ሰነድ እንዲፈረም የበኩላቸውን ሚና ተጫውተዋል:: ሆኖም በኢትዮጵያ እና በሶማሊላንድ መካከል የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙ ያስቆጣቸው የሶማሊያ ባለሥልጣናት አምባሳደሩን በ72 ሰዓታት ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አድርገዋቸዋል:: አምባሳደር ሙክታር ሶማሊያን ለቀው ከወጡ በኋላም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ወደ ጉዳይ ፈጻሚነት ዝቅ ብሎ በማገልገል ላይ ይገኛል:: ሆኖም ሁለቱ ሀገራት በአንካራው ስምምነት ማድረጋቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ወደ ቀድሞው ደረጃው ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል::

አምባሳደር ሙክታር ከሶማሊያ ሪፐብሊክ ከተመለሱ በኋላ ለጥቂት ጊዜያት ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ካገለገሉ በኋላ ወደ አልጀሪያ በመዘዋወር በአልጀርስ የኢትዮጵያን ኤምባሲ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ:: የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም በተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአምባሳደር ሙክታር ዋሬ ጋር ቆይታ አድርጓል::

አዲስ ዘመን፡- በበርካታ ሀገራት ዲፕሎማት ሆነው እንደመሥራትዎ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ጉዞ እንዴት ይረዱታል?

አምባሳደር ሙክታር፡- ኢትዮጵያ ጥንታዊ የዲፕሎማሲ ታሪክ ካላቸው ሀገራት አንዷ ነች:: ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በሃይማኖት በባሕልና በንግድ እንቅስቃሴ ከበርካታ ሀገራት ጋር የጠነከረ ግንኙነት ያላት ሀገር ነች:: ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክም ተጠቃሽ ተሞክሮ ማዳበር ከመቻሏም ባሻገር ከንግሥት ሳባ እስከ ዘመነኛው የዲጂታል ዲፕሎማሲ ድረስ ዕምቅ ታሪክና ተሞክሮ ያላት ሀገር ነች::

በየዘመናቱ የነበሩ የኢትዮጵያ መሪዎችም ሀገሪቱን ከውጭውም ዓለም ጋር የሰመረ ግንኙነት እንዲኖራትና አልፎ ተርፎም ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር እንድትሆን ዘርፈ ግንኙነቶችን ሲመሰርቱ ቆይተዋል:: በዘመነ አክሱም የዲፕሎማሲ ዘመን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ መሠረቶች ተጥለዋል:: ከእነዚህ መካከል በንጉሥ ኢዛና ዘመን ንግድና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ ግንኙነቶች ተፈጥረዋል::

ወደ መካከለኛው ዘመን ስንመጣ የዲፕሎማሲው ዋነኛ አቅጣጫ የሀገርን ሉዓላዊነትና አንድነትን ማጽናት ነበር:: ኢትዮጵያ ከውስጥም ከውጭም የሚመጡባትን የሉዓላዊነት አደጋዎች በመጋፈጥና አንድነቷን አስጠብቆ መሄድ የዲፕሎማሲው ቁልፍ አቅጣጫ ነበር:: በዚህም ኢትዮጵያ በየዘመናቱ የሚያጋጥማትን የሉዓላዊነት ፈተናዎች በማለፍ ዛሬ ላይ ደርሳለች:: በተለይም እንደ ሀገር ለዲፕሎማሲና ለውጭ ግንኙነት ትኩረት ከተሰጠ 116 ዓመታት የተቆጠሩ ሲሆን በእነዚህ ዓመታት በርካታ ፈተናዎችንና ስኬቶችን በማስመዝገብ ኢትዮጵያን ከነሙሉ ክብሯ ለዛሬው ትውልድ ለማስረከብ ተችሏል::

117 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ዘመናዊ ዲፕሎማሲ በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት አዳዲስ ገጽታዎችን በመላበስ አድማሱን አስፍቶ ቀጥሏል:: በተለይም ለቀጣናዊ ግንኙነት የመጀመሪያውን ትኩረት በመስጠት ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የጠበቀ ዲፕሎማሲያ ግንኙነት እንዲኖራት ተደርጓል:: ዲፕሎማሲያችን ሀገራትን በወዳጅነት እና በጠላትነት ከመፈረጅ ተላቆ ከሁሉም ሀገራት ጋር መልካም ወዳጅነት መፍጠር ችሏል:: ምዕራቡንም ምሥራቁንም በወዳጅነት በመያዝ የሀገሪቱን ጥቅም የሚያረጋግጡ ውጤታማ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው::

አዲስ ዘመን፡- በጂዳ በነበርዎት ቆይታ ያከናወኗቸው ተግባራት ምን ይመስላሉ?

አምባሳደር ሙክታር፡- በጂዳ በነበረኝ ቆይታ በአብዛኛው ያከናወንኳቸው ሥራዎች ከኢኮኖሚ እና ከስደተኞች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ነበሩ:: ጅዳ በነበርኩ ጊዜ ወደ 15 የሚጠጉ ማህበራትን አቋቁሜያለሁ:: በወቅቱ ከነበረው የትግራይ ልማት ባሻገር የኦሮሚያ ልማት ማህበር፤ አፋር፤ የሶማሊ፤ ወዘተ የልማት ድርጅቶችን በማቋቋም ለሀገራቸው ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አድርጌያለሁ:: የሕዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠውም ጅዳ በነበርኩበት ጊዜ በመሆኑ ኅብረተሰቡን አስባስቤ በአንድ ቀን ብቻ ወደ 350ሺህ ዶላር በማሰባሰብ ከሁሉም ኤምባሲዎች ቀዳሚ በመሆን ለግድቡ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ችለናል:: በወቅቱ ቦንድ የመሸጥ ተግባር ባይጀመርም በራሳችን ተነሳሽነት በጅዳ የሚኖረው ኮሚኒቲ ለግድቡ መዋጮ እንዲያደርግ በሰፊው ሠርተናል:: ለሌሎች ኤምባሲዎችም ምሳሌ የሚሆን ሥራ አከናውነናል::

ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ የዜጎች መብትን በማስከበር ረገድ ቆንስላ ጽሕፈት ቤቱ ውጤታማ ሥራዎችን አከናውኗል:: የታመሙ ዜጎች ሕክምና እንዲያገኙ በማድረግ፤ የታሠሩ ሰዎችን በመጠየቅ እና አለፍ ሲልም በማስፈታት፤ በደል ለደረሰባቸው ስደተኞች ጥብቅና በመቆም ጭምር የዜግነት ግዴታችንን ለመወጣት ሞክረናል:: ሆኖም ከነበረው አስከፊ እና ስር የሰደደ ችግር አንጻር ችግሩን ከማቃለል ውጭ ዘላቂ መፍትሔ መስጠት አልቻልንም:: በተለይም አብዛኛው ዜጋ ወደ ሳኡዲ የሚያደርገው ጉዞ በሕገ ወጥ መልኩ በመሆኑ እንደ መንግሥት ጭምር የዜጎችን መብት ለማስከበር አዳጋች ሁኔታዎች ነበሩ::

አዲስ ዘመን፡- እነዚህ አዳጋች ሁኔታዎች ምን ነበሩ?

አምባሳደር ሙክታር፡- በሕገ ወጥ መልኩ የሚገቡ ዜጎች በሕጋዊ መልኩ እንደሚገባው ዜጋ የሀገሪቱ መንግሥት አያውቃቸውም:: ሕጋዊ መብትም የላቸውም:: ቢበደሉ እንኳን ፍርድ ቤት ሄደው አቤት ማለት አይችሉም:: ይልቁንም ከነበደላቸው ጭምር እስር ቤት የመወርወር አጋጣሚ ይደርስባቸዋል:: የአንዲት ኢትዮጵያዊ ስደተኛን ታሪክ እዚህ ጋር ባነሳው ደስ ይለኛል:: ኢትዮጵያዊቷ ስደተኛ ጅዳ ውስጥ ከበሯ ወጣ እንዳለች በአራት የሳኡዲ ወጣቶች ተጠልፋ ተወስዳ በአንድ ጠባብ ክፍል ውስጥ ተቆልፎባት እንድትቀመጥ ታደርጋለች:: በዚህች ጠባብ ክፍልም ወጣቶቹ እየተመላለሱ ለአራት ሲደፍሯት ይቆያሉ:: በኋላ ኢትዮጵያዊቷ እንደተናገረችውም እነዚህ አራቱ ወጣቶች ከመድፈር ባሻገር ደሟን በሲሪንጅ ይመጡ ነበር::

ሆኖም ይህቺ ወጣት ይህ ሁሉ በደል ቢደርስባትም ሕጋዊ ባለመሆኗ የሀገሪቱ ፍርድ ቤት ክሷን ሊቀበላት አልቻለም:: ይልቁንም ሕገ ወጥ ስደተኛ በመሆኗ ከነበደሏ ለወህኒ ተዳርጋለች:: የደፈርዋትንም ወጣቶች በሕግ ተጠያቂ ማድረግ አልቻልንም:: በተመሳሳይም ከራያ አካባቢ የመጣ አንድ ወጣት በመኪና ተገጭቶ ሁለት እግሩ ፓላራይዝድ ቢሆንም ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ባለመያዙ ሐኪም ቤት ገብቶ መታከም ባለመቻሉ ቁስሉን ይዞ ለረጅም ጊዜ ቆይቷል:: ሆኖም እኔ መረጃውን እንደሰማሁ የሀገሪቱ ሕግ ባይፈቅድም በድብቅ መኪናዬ ውስጥ ደብቄ አስገብቼ ሕክምና እንዲያገኝ እና እንዲድን አድርጌለሁ:: ያ ወጣት ዛሬ ድኖ ለሀገሩ በቅቷል:: ከዛም አልፎ ጤናማ ሆኖ በሀገሩ ላይ ስርቶ መኖሩ ለእኔ ከፍተኛ ደስታ ይሰጠኛል::

በርካታ ኢትዮጵያውያን ሕጋዊ ባለመሆናቸው በደል ቢደርስባቸውም ወደ ፍርድ ቤት ሄደው መብታቸውን ማስከበር አይችሉም:: ስለዚህም በራሳችን ተነሳሽነት ማህበራዊ ግልግል በማቋቋም ተበዳዮች ፍትህ የሚያገኙበትን መድረክ አቋቁመናል:: ይህ ማህበራዊ ግልግል መድረክ ኢትዮጵያዊን አብረው ሲኖሩ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለማዳኘት እና ፍትህ ለማስፈን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው:: ከዚሁ ጎን ለጎንም ኢትዮጵያውያን የጠነከረ ግንኙነት እንዲኖራቸው እና መብታቸውንም በጋራ ማስከበር እንዲችሉ በየአካባቢው የተለያዩ ኮሚኒቴዎች እንዲቋቋሙ አድርገናል:: በአጠቃላይ በሳኡዲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ እና በሰው ሀገር እንግልት እንዳይደርስባቸው የበኩላችንን ሙያዊ አስተዋጽኦ አበርክተናል::

አዲስ ዘመን፡- የሱዳን ቆይታዎትስ ምን መልክ ነበረው?

አምባሳደር ሙክታር፡– በሱዳን የነበረኝ ቆይታ በጣም ውጤታማ ነበር:: በተለይም ከሕዳሴው ግድብ ጋር በተያያዙ የሠራናቸው ሥራዎች በሱዳን ውስጥ ግድቡ ተቀባይነት እንዲኖረው መሠረት ጥለናል:: ወቅቱ የአልበሽር መንግሥት የነበረበት በመሆኑ ለሕዳሴው ግድብ አወንታዊ አመለካከት ነበራቸው:: እንደ አሁኑ የሕዳሴ ግድቡን ሲቃወሙ አይሰሙም ነበር:: ከዚሁ ጎን ለጎንም በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውን ለሕዳሴው ግድብ የገንዘብ አስተዋጽኦ እንዲበረክቱ የማስተባበር ሥራዎችን ሠርተናል፤ ከፍተኛ ገንዘብ በማሰባሰብም ለሕዳሴው ግድብ ጽ/ቤት አስረክበናል::

በወቅቱ የነበረው የሕዝብ ስሜትም ከፍተኛ ስለነበር ለሕዳሴው ግድብ ተጠይቆ ወደ ኋላ የሚል ግለሰብ አልነበረም:: ሁሉም ስደተኛ አስከፊ ሕይወትን ተጋፍጦ ካለችው ላይ ቀንሶ ለሕዳሴው ግድብ የአቅሙን ያህል አበርክቷል:: ነገ ሀገሬ ስገባ የሥራ እድል አገኛለሁ፤ ሀገሬም በልጽጋ አያታለሁ በሚል እያንዳንዱ ስደተኛ ያጠራቀማትን አራግፎ ለግድቡ አበርክቷል:: ሆኖም በኋላ ላይ የተፈጠረው መሰናክል ብዙዎቻችንን ድንጋጤ ውስጥ ከቶናል::

አዲስ ዘመን፡- ምን ነበር ድንጋጤ ውስጥ የከተታችሁ?

አምባሳደር ሙክታር፡- ትልቅ ተስፋ የጣልንበት እና ሀገሪቱን ከድህነት ያላቅቃታል ብለን ተስፋ ያደረግንበት ግድብ ሜቴክ በሚባለው ድርጅት አማካኝነት መስተጓጎሉን ስንሰማ በጣም ደነገጥን:: በሀሩር እየተሰቃየ ካገኛት ገንዘብ ላይ ለግድቡ ያዋጣው ስደተኛ የሚሰማውን ስሜት እና ተስፋ መቁረጥ ስናስበው ስሜቱን መቋቋም ተሳነን:: 10 ዲናር ጭምር የሰጡ ስደተኞች ሁሉ አሉ:: ለእነዚህ ሰዎች የሕዳሴው ግድብ ተስተጓጎለ ተብሎ ሲነገራቸው የሚሰማቸውን ተስፋ መቁረጥ መገመት ይቻላል::

የሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያውያን አልፎ የመላው አፍሪካ ኩራት ነው:: አሁን አሁን ኢትዮጵያ በሕዳሴው ግድብ መታወቅ ጀምራለች:: እኔ በተዘዋርኩባቸው በሳኡዲ ዓረቢያ፤ ሱዳን እና ሶማሊያ የሕዳሴውን ግድብ የማያውቅ የለም:: ግድቡን ከኢትዮጵያ ጋር አስተሳስሮ የመመልከት ሁኔታ ተፈጥሯል:: ይህ ሁሉ ሁኔታ ባለበት የሕዳሴው ግድብ ተስተጓጎለ የሚል ዜና ሲናፈስ ከፍተኛ የሞራል ውድቀት ይፈጥራል፤ ከዛሬ ነገ ሀገሬ እገባለሁ ብሎ ተስፋ ለሚያደርገውም ስደተኛ የሚስከትለውም የሥነ ልቦና ቀውስ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም::

ሆኖም የመንግሥት ለውጥ መምጣትን ተከትሎ ሜቴክ የሚባለው ተቋም ተወግዶ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ባላቸው ተቋማት ሥራው እንዲቀጠል መደረጉ ለብዙዎቻችን እፎይታ ሰጥቶናል:: ዛሬ ግድቡ ወደ መጠናቀቅ መድረሱ መንግሥት የወሰደው ርምጃ ውጤት ነው:: እዚህ ላይ የለውጡ መንግሥት የተከተለውን በሳል አመራርም ሳላደንቅ ማለፍ አልፈልግም::

አዲስ ዘመን፡- በሶማሊያ የነበረዎት ቆይታ እና ውጣውረድ ምን ይመስላል?

አምባሳደር ሙክታር፡- ለመጀመሪያ ጊዜ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆኜ የተሾምኩት ሶማሊያ ሞቃዲሾ ነበር:: ከተሾምኩ ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን በሚያጠናክሩ ሥራዎችን ሥሠራ ቆይቻለሁ:: ሆኖም ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የተለያዩ አማራጮችን ስትፈልግ የመጀመሪያ ተባባሪ ሆና የተገኘችው ሶማሊላንድ ነች:: ይህ ሁኔታ ደግሞ በወቅቱ በሶማሊዎች በኩል ቅሬታ ፈጥሯል:: ሆኖም የኢትዮጵያ መንግሥት ፍላጎት የሶማሊያን ብሔራዊ ጥቅም መጋፋት ሳይሆን እያደገ ያለውን የሕዝብ ቁጥሯንና ኢኮኖሚዋን የሚሸከም የባሕር በር የማገኘት ፍትሃዊ ጥያቄ መሆኑን ለማስረዳት ሞከርኩ:: ሆኖም በወቅቱ የተጋጋለ ሁኔታ ስለነበረ ሊያዳምጡኝ አልፈለጉም:: ስለዚህም በ72 ሰዓታት ውስጥ ከሞቃዲሾ እንድወጣ ትዕዛዝ አስተላለፉ፤ በመጨረሻም እኔም ሞቃዲሾን ለቅቄ ወጣሁ::

አዲስ ዘመን፡- የነበረው አለመግባባት የተፈታበትን መንገድ እንዴት ያዩታል ?

አምባሳደር ሙክታር፡- የሁለቱ ሀገራት ውዝግብ የተፈታው በቱርክ አንካራ በተካሄደ ድርድር ነው:: በአንካራው ድርድር የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ተገኝተው ውዝግብ በፈጠሩ ጉዳዮች ላይ በአግባቡ ተወያይተው ችግሮቻቸውን መፍታት ችለዋል:: ኢትዮጵያ ከአንካራው ድርድር አትርፋ ተመልሳለች:: የባሕር በር ጥያቄዋ ፍትሃዊ መሆኑ ታምኖበታል፤ ከሶማሊላንድ ጋር የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ባለበት እንዲቀጥል ተወስኗል፤ ኢትዮጵያ ለሶማሊ ሕዝብ እና መንግሥት የዋለችው ውለታ እውቅና እንዲሰጠው እና እንዲዘከር አድርጋለች:: ስለዚህም ኢትዮጵያ የተሳካ የዲፕሎማሲ ሥራ ሠርታ የሕዝቦቿን ጥቅም አረጋግጣ ተመልሳለች::

ድርድሩ በሁለቱ እህትማማቾች ሀገራት መካከል የቆየውን ማህበራዊ ትስስር ለማጠናከር እና የሀገራቱን የሁለትዮሽ ጉዳዮች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ወሳኝ ሚና ተጫውቷል:: ግንኙነቱ አሁን የተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛል::

አዲስ ዘመን፡ – የባሕር በር ጥያቄውን ተከትሎ በአንዳንድ ሀገራት በኩል የነበረውን ጣልቃ ገብነት እንዴት ያዩታል? ችግሩ በድርድር መፈታቱ የነበረውን ጣልቃ ገብነት በምን መልኩ አከሸፈው?

አምባሳደር ሙክታር፡– ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን የመግባቢያ ሰነድ ተከትሎ የኢትዮጵያን እድገት እና ለውጥ የማይፈልጉ ኃይላት ጉዳዩን ከልኩ በላይ በማጦዝ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል መቃቃር እንዲፈጠር በብዙ ሠርተዋል:: ኢትዮጵያን በጠብ አጫሪነት በመፈረጅ ለቀጠናውም ስጋት መፍትሔ ነን ብለው ተከሰቱ:: በሰላም አስከባሪነት አንድም ቦታ ተሠማርተው የማያውቁ ሀገራት ሁሉ የሶማሊያን ሰላም የምናስከብረው እኛ ነን አሉ::

እነዚህ ኃይላት ኢትዮጵያ የባሕር በር ካገኘች ትበለጽጋለች፤ በአካባቢውም ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆና ትዘልቃለች የሚል ስጋት አላቸው:: ከዚህም ባሻገር በሕዳሴ ግድብ ያጡትን ተሰሚነት በዚህኛው የማሰመለስ ህልምም ያላቸው ናቸው:: እነዚህ ኃይላት ምቹ አጋጣሚ አገኘን በሚል ስሜት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሶማሊያ ሉዓላዊነት ተጣሰ በሚል በሰላም አስከባሪነት የምረጡኝ ቅስቀሳ ሲያካሂዱ ቆይተዋል:: ሆኖም ይህ የጥፋት እሳቤያቸው በአጭሩ ተቀጨ::

በመጨረሻም በአንካራ በተደረገ ድርድር ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ከስምምነት ደረሱ:: ይህ አጋጣሚ ለሀገራቱ ትልቅ ብስራት ሲሆን ለጥፋት ኃይሎች ግን ከባድ መርዶ ነበር:: የሶስትሽ ኃይል አቋቁመን ኢትዮጵያን እናበረክካለን ብለው የተነሱት ኃይላት ሴራቸው የመከነበት እና የገነቡትም የጥፋት ምሽግ የፈረሰበት ታሪካዊ ስምምነት ነው::

የአንካራው ስምምነት አካባቢያዊ መረጋጋት የሚያመጣና ኢትዮጵያም በቀጣናው ላይ አለኝ የምትለውን የባለቤትነት ጥያቄ መልስ እንዲገኝ በር የሚከፍት ነው:: ቀጣናዊ ሰላምን በማስፈን የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የተረጋጋ እንዲሆን በር ከፍቷል:: የጣልቃ ገቦችንም ሴራ አክሽፏል::

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ያነሳችውን የባሕር በር ጥያቄን እንዴት ይመለከቱታል ?

አምባሳደር ሙክታር ፡- ኢትዮጵያ ያነሳችው የባሕር በር ጥያቄ በታሪክ አጋጣሚ የተፈጸሙ ስህተቶችን የሚያርም ውሳኔ ነው:: ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በቀይ ባሕር ላይ ይዞታ የነበራትና ቀይ ባሕርንም ስታዝበት የኖረች ሀገር ነች:: 1ሺ800 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን የቀይ ባሕር ይዞታ በቁጥጥሯ ሥራ ያኖረችና ለውጭና ገቢ እቃዎች በርካታ ወደቦችን የምታስተዳደር ሀገር ነበረች:: ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር ውጭ ቀይ ባሕርንም ከኢትዮጵያ ውጭ ማሰብ አይቻልም ነበር::

ሆኖም የኢትዮጵያን ማደግ በማይፈልጉ ኃይላት ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር እንድትወገድ ተደርጓል:: የኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆንም ከሥነ ልቦናዊ ቀውስ ባሻገር ለበርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና ሕዝቡ እንዲጋለጥ አድርጎታል:: የኢትዮጵያን ክብርና ዝና ዝቅ እንዲል ከማድረጉም ባሻገር በኢኮኖሚ ረገድም ተጎጂ እንድትሆን አድርጓታል::

ለበርካታ መሠረተ ልማቶችና ለድህነት መቀነሻ ልማቶችን ይውል የነበረውን ከ1ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ በየዓመቱ ለወደብ ብቻ በማዋል በድህነት ውስጥ እንድትማቅቅ አድርጓታል:: ኢትዮጵያ ወደብ አልባ በመሆኗ ለኪራይና ለመጓጓዣ ከፍተኛ ዶላር ስለምታፈስ የሸቀጦች ዋጋ እንዲንርና የኑሮ ውድነትም እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል:: በዲፕሎማሲ እና በተጽዕኖ ፈጣሪነትም ረገድ የኢትዮጵያ ሚና አሽቆልቁሎ ቆይቷል::

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ወደብ አልባ ከሆኑት 16 ሀገራት አንዷ ብትሆንም ወደብ አልባ የሆነችባቸው አመክንዮዎች ግን ታሪካዊም ሆነ ሕጋዊ መሠረት የሌላቸው ናቸው:: የኢትዮጵያ ሕዝብ 130 ሚሊዮን ደርሷል:: በአጠቃላይም በኢትዮጵያ የሚኖረው ሕዝብ የባሕር በር የሌላቸውን ሀገራት ሕዝብ 1/3ኛውን ይሸፍናል::

ይሄንን የሚያህል ሕዝብ ይዞ የባሕር በርና ወደብ የተነፈገ ሀገር የለም:: ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ በባሕር በር የተከበበች ሀገር ነች:: ከ60 ኪሎ ሜትር የባሕር ርቀት ላይ እየተገኙ ኢትዮጵያውያን ወደብ እና የባሕር በር እንዳይኖራቸው ተፈርዶባቸው ቆይተዋል::

በሴራ እና በተሳሳተ ትርክት ከቀይ ባሕር እንድትርቅ ከመደረጓ በስተቀር አፈጣጠሯ ለቀይ ባሕር የቀረበ ነው:: በሌላም በኩል በታሪክ ረገድም በቀይ ባሕር ላይ ለዘመናት የበላይ ሆና መቆየቷን የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች ያሏት ሀገር ነች::

ስለዚህም ኢትዮጵያ በግፍ ከይዞታዋ እንድትነቀል ከመደረጓ ውጪ ባለቤትነቷን የሚከለክላት አንዳችም ዓለም አቀፍ ሕግ የለም:: ኢትዮጵያ ወደብ አልባ የሆነችበትም ሆነ ከቀይ ባሕር እንድትወገድ የተደረገበት አካሄድ ምንም ዓይነት ሕጋዊ መሠረት የሌለው ነው::

በኢትዮጵያ አዲስ የመንግሥት ለውጥ ከመጣ ጀምሮ የባሕር በር ጉዳይ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በማመን የተለያዩ ሰላማዊ አማራጮችን በማፈላለግ ላይ ይገኛል:: የባሕር በር ጉዳይ የአሁኑ ትውልድ ብቻ ሳይሆን የመጪውን ትውልድ ዕጣ ፋንታ የሚወስን ጉዳይ ነው::

ስለዚህም መንግሥት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ለዘመናት ቁጭት ፈጥሮ የነበረውን የባሕር በር ጥያቄ በመመለስና ስብራትን በመጠገን ታሪካዊ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል:: ከ33 ዓመታት ዝምታ በኋላ የባሕር በር የምታገኝበት አማራጮችን በማፈላለግ ላይ ይገኛል:: ይህም የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር መሳካቱ አይቀርም::

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ የባሕር በር ጥያቄዋ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲያገኝ ያደረገችበትን መንገድ እንዴት ይገልጹታል?

አምባሳደር ሙክታር፡- ኢትዮጵያ ጥንታዊ የዲፕሎማሲ ታሪክ ካላቸው ሀገራት አንዷ ነች:: ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በሃይማኖት በባሕልና በንግድ እንቅስቃሴ ከበርካታ ሀገራት ጋር የጠነከረ ግንኙነት መሠረት የጣለችና በዲፕሎማሲው መስክም ተጠቃሽ ተሞክሮ ማዳበር ከመቻሏም ባሻገር ከንግሥት ሳባ እስከ ዘመነኛው የዲጂታል ዲፕሎማሲ ድረስ ዕምቅ ታሪክና ተሞክሮ ያላት ሀገር ነች::

በየዘመናቱ የነበሩ የኢትዮጵያ መሪዎችም ሀገሪቱን ከውጭውም ዓለም ጋር የሰመረ ግንኙነት እንዲኖራትና አልፎ ተርፎም ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር እንድትሆን ዘርፈ ግንኙነቶችን ሲመሠርቱ ቆይተዋል:: ኢትዮጵያ ከውስጥም ከውጭም የሚመጡባትን የሉዓላዊነት አደጋዎች በመጋፈጥና አንድነቷን አስጠብቆ መሄድ የዲፕሎማሲው ቁልፍ አቅጣጫ ነበር:: ከዚህ ባሻገር የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነትን ማረጋገጥ በየዘመናቱ የነበሩ መሪዎች ዋነኛ ትኩረት ነበር::

በዚህም ኢትዮጵያ በየዘመናቱ የሚያጋጥማትን የሉዓላዊነት ፈተናዎች ስታልፍ የቆየች ብትሆንም የባሕር በር ጥያቄን በዘላቂነት መፍታት ግን ሳይቻል ቆይቷል:: በተለይም በዘመነ ኢህአዴግ የባሕር በር ጥያቄ ዝግ ሆኖ ከመቆየቱም ባሻገር ጥያቄውን ማንሳትም በጠብ አጫርነት የሚያስፈርጅ ነበር::

በኢትዮጵያ አዲስ የመንግሥት ለውጥ ከመጣ ጀምሮ ግን የባሕር በር ጥያቄ ገንፍሎ ወጥቷል:: ሰላማዊ አማራጮችን በመከተልም የባሕር በር ጥያቄውን ገፍቶበታል:: መንግሥት የጀመራቸው ጥረቶች አካባቢያዊ መረጋጋት የሚያመጣና ኢትዮጵያም በቀጣናው ላይ አለኝ የምትለውን የባለቤትነት ጥያቄ መልስ እንዲገኝ በር የሚከፍት ነው:: ቀጣናዊ ሰላምን በማስፈን የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የተረጋጋ እንዲሆን የሚያስችል ነው::

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በተደረጉ እልህ አስጨራሽ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተቀባይነት እያገኙ መጥተዋል:: በዓለም አቀፍ መድረኮችም እውቅና ተሰጥቶታል:: የተለያዩ መሪዎችም በአንደበታቸው መስክረውለታል:: ይህም የዲፕሎማሲ ውጤት ነው::

ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለችው የዲፕሎማሲ አካሄድ በቀጠናው ተሰሚነቷን ከማሳደጉም ባሻገር የኢትዮጵያውያን የዘመናት ጥያቄ የሆነውን የባሕር በር ጥያቄ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ምላሽ እንዲያገኝ የሚያስችል ነው::

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በአልጄሪያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ ነው:: የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

አምባሳደር ሙክታር፡- የአልጄሪያ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት የተጀመረው እኤአ 1962 ጀምሮ ነው:: የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሠረትም አንድ ዓይነት አቋም በማራመድ ለድርጅቱ ምሥረታ የጋራ አስተዋጽኦ አበርክተዋል:: አልጄሪያ ከቅኝ ግዛት ከመውጣቷ በፊት በ1958 ኢትዮጵያ በህቡዕ የነፃነት ድጋፍ ትሰጥ ነበር:: ከነፃነትም በኋላ ኢትዮጵያ ዕውቅና ከሰጡ ሀገራት የመጀመሪያዋ ነች:: ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም በወቅቱ አልጄሪያን ጎብኝተዋል:: ይህንኑ መነሻ በማድረግም አልጀርስ ላይ አዲስ አበባ አደባባይ የሚባል ሰፊ አደባባይ አለ:: በአጠቃላይ አልጄሪያ ነፃ ከወጣችበት ከ1962 በፊትም ቢሆን ከአልጄሪያ ጋር ጠንካራ ግንኙነት አለን:: ከ2013 ጀምሮ ደግሞ ግንኙነታቸው ወደ ስትራቴጂክ ግንኙነት አድጓል:: በአፍሪካ ካሉ ሀገራት ብቸኛዋ የስትራቴጂክ አጋር ሀገር አልጄሪያ ነች:: ከአፍሪካ አልፎ በዓለም አቀፍ መድረኮች ጭምር እንተጋገዛለን:: በየሁለት ዓመቱም የሚንስትሮች የጋራ ስብሰባ እንካሂዳለን:: ዘንድሮም ለአምስተኛ ጊዜ ይሄው የሚኒስትሮች ስብሰባ በአዲስ አበባ ተካሂዷል::

ከአልጄሪያ ጋር አብረን የምንሠራባቸው ዘርፍ አሉ:: በፋርማሲ ዘርፍ፤ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ፤ በሥራ ፈጠራ፤ በማዕድን እና በባሕል ዘርፎች በጋራ እንሠራለን:: ከኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ባሻገርም በቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሰፊው እንሠራለን:: ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ዓረብ ሊግ ጋር ያላት ግንኙነት የተሻለ እንዲሆን አልጀሪያ ከፍተኛ እገዛ የምታደርግ ሀገር ነች:: በተለይም በዓረብ ሊግ ስብሰባ ወቅት ኢትዮጵያን የተመለከቱ ጉዳዮች በሚነሱበት ወቅት አልጀሪያ ሚዛናዊ ሆነ አስተያየት በመስጠት የዓረብ ሊግ የተሳሳተ ውሳኔ እንዳይወሰን የበኩሏን ጥረት የምታደርግ ሀገር ነች::ለተደጋጋሚ ጊዜ የኢትዮጵያ ጉዳይ በዓረብ ሊግ ስብሰባ ሲነሳ የኢትዮጵያ ጉዳይ እዚህ መነሳት የለበትም፤ ይህ አፍሪካውያን ጉዳይ ስለሆነ ፤ ለአፍሪካውያን እንተውላቸው በማለት ለኢትዮጵያ ጠበቃ የምትቆም ሀገር ነች:: ‹‹የሕዳሴ ግድብ የዓረብ ሊግ የመወያያ አጀንዳ መሆን የለበትም:: መታየትም ካለበት በአፍሪካ ሕብረት እንጂ በዓረብ ሊግ በኩል መሆን የለበትም::›› የሚል አቋም በመያዝ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያላትን ታማኝነት በአደባባይ አሳይታለች::

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ በአንባብያን ስም አመሰግናለሁ::

አምባሳደር ሙክታር ፡- እኔም አመሰግናለሁ::

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You