
- ጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር)- በኢትዮጵያ የሥርዓተ ምግብ ሽግግርና ኒውትሪሽን ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና አስተባባሪ
ኢትዮጵያ የዜጎቿን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የተለያዩ መርሃ ግብሮችን ቀርጻ እየሠራች ትገኛለች፡፡ በተለይም ደግሞ የግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ከማጎልበት ጎን ለጎን እያንዳንዱ ዜጋ የተመጣጠነ ምግብን በበቂ ሁኔታ እንዲያገኝና አጠቃላይ ሥርዓተ ምግብ ሽግግሩን እውን ለማድረግ እየተተገበሩ ባሉ ሥራዎች አበረታች ውጤቶች እየተገኙ ነው፡፡ ከእርሻ እስከ ጉርሻ በሚል መርሆ በምግብ ሥርዓት ሰንሰለቱ ውስጥ ያሉትን ሥራዎች በተቀናጀና በተናበበ መልኩ እንዲያካሄድ በማድረግ ረገድ መንግሥት ከፍተኛ ቁርጠኝነትን አሳይቷል፡፡
በሌላ በኩል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ2030 ሀገራት ዘላቂ ልማት ግቦች ማሳካት ያስችላቸው ዘንድ የሥርዓተ ምግብ ሽግግር መርሃ ግብር ቀርፀው እንዲተገብሩ በሰጠው አቅጣጫ መሠረት ኢትዮጵያም የመንግሥታቱ ድርጅት አባል እንደመሆኗ ይህን የቤት ሥራ ወደ ሀገር ቤት በማምጣት ከተባበሩት መንግሥታት የምግብ ሥርዓት ማሕቀፍ እና ከዘላቂ ልማት ግቦች ጋር የተጣጣመ አጠቃላይ የምግብ ሥርዓት እና ኒውትሪሽን Ethiopian Food System and Nutrition (EFSN) ፍኖተ ካርታ አዘጋጅታ በመተግበር ላይ ትገኛለች፡፡
ይህ ፍኖተ ካርታ የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚጠቅም በንጥረ-ምግብ የበለፀገ፣ ተደራሽ እና ተፈጥሯዊ የምግብ አሠራርን ለማጎልበት ያለመ ነው። ለኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ትግበራ እና ስኬታማነት በቅርቡ የተቀላቀለውን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርን ጨምሮ 16 ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን የያዘ ምክር ቤት ተቋቁሞ የሥራ ድርሻ የተከፋፈሉ ሲሆን ምክር ቤቱን የግብርና እና የጤና ሚኒስቴር በጋራ ይመሩታል፡፡ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ደግሞ የምክር ቤቱ ሴክሬታሪያት ሆኖ እየሠራ ይገኛል፡፡ እንደ ሀገር ሽግግሩን ለማፋጠን እየተሠራ ስላለው ሥራ ከሴክሬታሪያቱ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና አስተባባሪ ከዶክተር ጌታቸው ድሪባ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በቅድሚያ ጽሕፈት ቤቱ የተቋቋመበት አላማ ምንድን ነው ?
ጌታቸው (ዶ/ር)፡- የተቋቋመበት ዋና ዓላማው ዘላቂ የልማት ግቦች አንዱ የሆነው የምግብ ሥርዓት ሽግግርን ለማሳለጥ ነው። እንደሚታወቀው ከዚህ ቀደም እ.ኤ.አ 2015 ዘላቂ የልማት ግቦች የሚባል መርሃ-ግብር በዓለም ላይ ተዘርጎቶ ኢትዮጵያ ተቀብላ እየተገበረች ትገኛለች። በዚህ እሳቤ መሠረት 17 የልማት ግቦችና 169 ዓላማዎች ያሉ ሲሆን የሚያጠነጥነውም ማንም ሀገር ፤ አንድም ሰውም ቢሆን ወደ ኋላ እንዳይቀር ማድረግ፤ ድህነትና ረሃብን ማስወገድ ላይ ነው። የተፈጥሮ ሀብታችንን መጠበቅ፣ የሕዝብና የሀገርን ብልፅግና እውን ማድረግና ሰላምን ማረጋገጥ ከዋነኛ ትኩረቶቹ መካከል የሚጠቀሱ እናም በጋራ መሥራት የሚባሉ ቁልፍ ጉዳዮችን የያዘ መርሃ ግብር ነው።
ነገር ግን ረሃብ ከመጥፋት ይልቅ እየጨመረ ነው የሄደው። በመላው ዓለም ጦርነት አለ፤ ኮቪድ መጣ፣ የኢኮኖሚ ቀውሱ በከፍተኛ ደረጃ በርካታ ሀገራትን ችግር ውስጥ አስገባ፤ ስለዚህ ይሄ የታሰበው ዘላቂ የልማት ግብ እንዴት አድርገን እናፋጥን የሚለው እሳቤ መጣ። ይሄ ጥያቄ ሲጠየቅ በተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊው ሥርዓተ ምግብ በሚል መርሃ-ግብር እንዲተገበር ፀደቀ። በነገራችን ላይ ሥርዓተ ምግብ ሲባል ከእርሻ እስከ ጉርሻ ያለውን ሰንሰለት የያዘ ነው። እናም በመካከሉ ያሉትን የማምረትን፣ የማከማቸትን፣ ወደ አግሮ ኢንዱስትሪ የማስገባት፣ የማጓጓዝ፣ ለሰው ልጅ ደህንነት ሊመጥን በሚችል ደረጃ ለምግብነት ማምጣት ነው።
የሥርዓተ ምግብ ሽግግር ማምጣት የሚለው እሳቤ የተፈጠረው እነዚህ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማፋጠን ነው። በተቀናጀና በተናበበ መልኩ ሀገራት እንደ መንግሥት የማስተባበሪያ መዋቅር ሠርተው፤ በተፋጠነ ሁኔታ ግቡን ለማስፈፀም እንዲችሉ ነው። ይህንን ለማስፈፀም ከአራት ዓመት በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት የሥርዓተ ምግብ እሳቤን በመውሰድ ግብርና ሚኒስቴርና ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን በመወከል የማስተባበር ኃላፊነት ተሰጥቷቸው በጥምር እንዲመሩ ተደርጓል። በተለይም 17ቱን የልማት ግቦች ለመተግበር በሚያስችል መልኩ መርሃ ግብሩ እንዲጀመር ተደረገ። በዚህ መሠረት 16 ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ያሉበት መዋቅር እንዲፈጠር ተጠየቀና እሱም ፀድቆ በሥሩ የማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት እንዲፈጠር ተደረገ። ይህም ለጊዜው በግብርና ትራንስፎርሜሽን ውስጥ ሆኖ እንዲሠራ በማድረግ የሥርዓተ-ምግብ ሽግግርና ኒውትሪሽን ጽሕፈት ቤት ተቋቁሟል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ምንም እንኳን ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ብትሆንም በተደጋጋሚ የድርቅ አደጋ ያጋጥማታል። ሀብቷን ተጠቅማ ዜጎቿን ከአደጋ መከላከል ያልቻለችባቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
ጌታቸው (ዶ/ር)፡– እኛ የሥርዓተ-ምግብን ንድፍ ስናዘጋጅ እንደ ኢትዮጵያ ለይተን ያወጣናቸው 18 መሠረታዊ ችግሮች አሉ። እነዚህም ከምርትና ምርታማነት ጋር የተያያዙ ማነቆዎችን የመፍታት፣ ከፖሊሲ፣ ከቴክኖሎጂ፣ ሜካናይዜሽን ጋር የተያያዙ ማነቆዎች፣ ከገበያና ከገበያ ትስስር ጋር፣ ከተፈጥሮ ሀብት ጋር በተያያዘ እንዲሁም የአፈር ለምነቱ ተሸርሽሮ በጣም በከፍተኛ ደረጃ ለምርት የማይበቃበት ሁኔታ ላይ የደረሱ ቦታዎችን አይተን 24 ቁልፍ የመፍትሔ ሃሳቦች አወጣን።
ከጠየቅሽው ጥያቄ አንፃር ከእነዚህ ችግሮች ለመላቀቅ በመሠረታዊ እሳቤዎች ላይ መግባባት ያስፈልጋል ባይ ነኝ። እንደተባለው ለብዙ ዘመን ያቆየናቸው ችግሮች አሉ። በተለይ ዘመናዊ እሳቤ ውስጥ ያለመግባታችን፣ የዛሬ 10 ሺህ ዓመት የተፈጠረው የበሬ እርሻ ዛሬም ድረስ በበሬ ማረሳችንና ከእነዚህ ጋር ተያይዞ ወደ ዘመናዊ አስተሳሰብ እና ዘመናዊ ሥርዓት ውስጥ አለመግባታችን፤ የአየር ንብረት ለውጡ ለብዙ ጊዜ ሲጎትተን ነው የቆየው። በዚህ ምክንያት በየዓመቱ ረሃብ አለ፤ ድርቅ፤ ጎርፍ፤ እና የመሳሰሉትን ችግሮችን እንዴት እንሻገር የሚለው ነው የሥርዓተ ምግብ ሽግግር የሚያካትተው ነው።
በተለይ የአየር ንብረት ለውጥና ሥርዓተ ምግብ ሽግግሩን አናበን መሥራት የምንችልባቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደርጋል። እንደምናስታውሰው የአየር ንብረት ለውጡ ባስከተለው ጦስ በቅርቡ ቦረና ላይ የነበረው የከብት እልቂት ከፍተኛ የሚባል ነው። ሱማሌና አፋር ክልልም ላይ እንደዚሁ በሚሊዮን የሚቆጠር ሀብት ነው የወደመው። በየጊዜው የሚደርሰውን አደጋ ለመቋቋም ዘላቂ መፍትሔ ያስፈልጋል። የአየር ንብረቱ ለውጥ በኢኮኖሚያችን፣ በሕዝባችን ላይ ከፍተኛ ማነቆ ስለሆነ መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል የሚል ዕሳቤ ተይዞ ነው እየተሠራ ያለው። ይህንን ከ24ቱ ቁልፍ የመፍትሔ ሃሳቦች ጋር እንዲሁም ከኢትዮጵያ 10 ዓመት መሪ እቅዱ ጋር እንዲናበብ፤ ቅድሚያ እየተሰጣቸው እንዲተገበሩ እየተደረገ ነው።
ከዚህ አንፃር በአሁኑ ወቅት በመንግሥት በከፍተኛ ደረጃ እየተሄደበት ያለው የስንዴ ምርትና ምርታማነት መስኖ ለማስፋት አንዱ ቁልፍ የመፍትሔ ሃሳብ ብለን ይዘን የምንሄደው ነው። የሌማት ትሩፋትም፤ የአረንጓዴ ዐሻራና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራችንም እዚህ ውስጥ ይገባሉ። ስለሆነም መንግሥትም ሆነ ሕዝቡ ተባብሮ ይህንን ችግር የምንወጣበትን መንገድ መፈለግ የግድ ይለዋል። ሌላው መሠረታዊ ቁልፍ የሆነው የፖሊሲ ማነቆዎች ነው። ከዚህ አንፃር ለምሳሌ መሬትን በተመለከተ ገበሬው በጣም የተበጣጠሰ፤ ከግማሽ ሄክታር በታች ነው መሬት አለው የሚባለው። ዘመናዊ እሳቤ ውስጥ ለመግባት፣ ትራክተር ለመጠቀም፣ የማዳበሪያ ዋጋ በየጊዜው እየጨመረ ቢመጣም ለመጠቀም ብዙ የሚቸገር ሕዝብ ነው። ስለዚህ የክላስተር እርሻ ሲስፋፋ ግብዓት ለማቅረብና ቴክኖሎጂን በቀላሉ ለማቅረብና ምርታማነትን ለማሳደግ ይቻላል። እንደ አጠቃላይ ሕዝብና ሀገርን ከአደጋ መከላከል ልማትን ማስቀጠል ወሳኝ ጉዳይ ነው። ይህም መንግሥት፣ የሕዝብ፣ የግል ዘርፍ የጋራ ጥረትና መሥራትን መናበብን ይፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አኳያ ታዲያ ኢትዮጵያ በተለይም ባለፉት ሶስት ዓመታት ሥርዓተ ምግብ ሽግግርን ለማምጣት እየከወነች ያለችው ሥራ ምን ያህል ውጤታማ ነው ማለት ይቻላል?
ጌታቸው (ዶ/ር)፡- በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ሥርዓተ ምግብ ሽግግር ከውጭ የመጣ ባዕድ ነገር አይደለም። እንደ አሁኑ ስያሜ ተሰጥቶት አይከናወን እንጂ ከዚህ ቀደምም በተለያዩ መርሃ ግብሮች የሀገሪቱን የምግብ ሥርዓት ለማሻሻል ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። በመሠረቱ የኢትዮጵያ ሥርዓተ ምግብ ሽግግር ሃሳብ ነው፤ ግን ደግሞ በቁርጠኝነት መሥራት ይጠይቃል። ከዚህ አንፃር ሲታይ የአረንጓዴ ልማት ዐሻራ በኢትዮጵያ ሥርዓተ ምግብ ሽግግር አንዱ ትልቁ ምሰሶ ነው፤ የተፈጥሮ ሀብትን በመንከባከብ፣ የስንዴው፣ የሌማት ትሩፋትና ሌሎችም የልማት ሥራዎች የኢትዮጵያ ሥርዓተ ምግብ ሽግግር አውታሮች ናቸው።
በማህበራዊ ደግሞ ብንወስደው የአደጋ ጊዜ መከላከል ሥራ፣ የትምህርት ቤት ምገባ፣ የገጠርና ከተማ ሴፍትኔት መርሃግብሮች ሁሉ የኢትዮጵያ ሥርዓተ ምግብ አካሎች ናቸው። በተለይ ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ሽግግሩን ለማፋጠን የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች ስናከናውን ቆይተናል፤ በዚህም ብዙ አመርቂ የሆኑ ውጤቶች ታይተዋል። በሌላ በኩል አርሶ አደሩ መሬቱ በጣም የተበጣጠሰ ነው፤ ይህ በመሆኑ ለቴክኖሎጂና ለግብዓት አጠቃቀም አይመችም። በዚህ ምክንያት ምርቱም ውጤታማ የሚባል አልነበረም። ሆኖም እነዚህን የተበጣጠሱ መሬቶች በክላስተር በማጣመር፤ የቴክኖሎጂ፤ የግብዓትና የባለሙያ ድጋፍ ጭምር እየተደረገላቸው ምርታማነት በእጅጉ ጨምሯል። የአርሶ አደሩም ተጠቃሚነት እየጎለበተ መጥቷል።
በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችው ሥርዓተ ምግብ ሽግግር አምስት ዋና ዋና መሠረታዊ መርሃ ግብሮች ያሉት ሲሆን፤ አንዱ ሰውን ማዕከል ያደረገ ሥራ ነው። ምክንያቱም ልማት ብቻውን ምንም ዋጋ የለውም፤ ዋናውና ትኩረት ልናደርግበት የሚገባው ጉዳይ የሰውን ሰብዕና ሉዓላዊነቱን ለማስከበር የሚደረጉ ጥረቶች ናቸው። ሁለተኛው ትልቁ ሥራ የተፈጥሮ ሀብትና ምድርን መጠበቅ ነው። በዚህ ረገድ የሚሠሩ ሥራዎች እጅግ በርካታ ናቸው። ከዚህ ውስጥ ደግሞ የአረንጓዴ ዐሻራ አንዱ ሆኖ ከዚህ ቀደም ምርት የማይሰጡ፤ አፈራቸው ተሸርሽሮ አሲዳማ መሬት ያላቸው አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ ለማድረግ ትልቅ ሥራ ተሠርቷል።
ሌላው ሰላም ነው፤ የሥርዓተ ምግብ ሽግግሩ ዋናው እሳቤ ሰው በልቶ እንዲያድርና ሰላም እንዲፈጥር ማድረግ ነው። ለሰላም ትልቅ ጋሻ መሆን አለበት፤ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ወደ ሥራ መግባት አለበት። ሀገሬ ነው፤ እኖራለሁ፤ ተስፋ አለኝ፤ ለእኔና ለልጆቼ ወይም ለመጪው ትውልድ ተስፋ አለኝ ብሎ የሚሠራበትና በሰላም የሚኖርበትን ሁኔታ መፍጠር አንዱ መሠረታዊ ጉዳይ ነው። በመሠረቱ የሰላም እጦት መነሻው በበቂ ደረጃ መብላት አለመቻል ወይም ምግብ አለማግኘት ነው። ስለዚህ እኛ የኢትዮጵያ የተቀናጀ የልማት እሳቤ ለሀገር እድገት ትልቅ ሚና ይጫወታል ብለን ነው እየሠራን ያለነው።
ሌላው ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ሀብት መፍጠር ነው፤ በሀገራችን ለብዙ ጊዜ ስንሰማ የኖርነው ስለ ድህነት መቀነስ፣ ረሃብን ማስቀረት ሥራዎች ነበሩ። በእኔ እምነት እነዚህ ሥራዎች ጥሩና የሚደገፉ ናቸው። ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ግን በተለየ አቀራረብና አካሄድ እንደ ሀገርም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ሀብት የመፍጠር ግብ ተጥሎ ሲሠራ ቆይቷል። በዋናነትም ከነበርንበት አዙሪት ወጥተን፤ ትልቅ ምኞት ይዘን ሀብትና ብልፅግናን ለመፍጠር ነው የሚለውን እሳቤ በመያዝ የተቀናጀ የኢትዮጵያ ሥርዓተ ምግብ ሽግግር እየተከናወነ ነው። ከዚህ ባሻገር ቅንጅት መፍጠር የሚል ሲሆን እንደሚታወቀው ደግሞ በእኛ ሀገር በቅንጅት መሥራት እጅግ ፈተና የበዛበት ጉዳይ ነው። ሰዎችን፣ ተቋማትን ማደራጀት፣ ማቀናጀት ከባድ ሥራ ነው። ማቀናጀት ወይም መደመር የሚለው እሳቤ ውስጥ የማስገባቱ ጉዳይ ላይ ተቋማት በየፊናቸው ገንዘብን ተከትሎ ወይም ዘርፍን ብቻ ተከትሎ ብቻ የተናጠል ሥራ መሥራትን ነበር ምርጫቸው የሚያደርጉት። በሚሠሩት ሥራ ውጤታማነት ላይ ቆም ብሎ አለማየትን፣ በጋራ እሳቤ ያለ መሄድ ችግርም በስፋት ይስተዋል ነበር።
ምንም እንኳን ቅንጅቱ የብዙ ጊዜ የአስተሳሰብ፣ የባሕል፣ የትርክት ለውጥ የሚያስፈልግ ቢሆንም እስከ ዛሬ ባለው ሂደት አበረታች የሚባል ለውጥ እየመጣ ነው። ለዚህም አብነት አድርገን መጥቀስ የምንችለው በፌዴራል ደረጃ 16 ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ለመጀመሪያ ጊዜ በሚባል ሁኔታ ለሥርዓተ ምግብ ሽግግሩ እውን መሆን በአንድ ላይ የሚሠሩበት እድል መፈጠሩ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ተጨባጭ የሚባል ሥራ ለማከናወን ያስችል ዘንዳም ማስተባበሪያ መዋቅር የተፈጠረለት ሲሆን ማረቂያ ተደርጎለታል። ይህም ትልቅና በሌላ ሀገር ያልተለመደ አሠራር ነው። ምክንያቱም በዚህ ደረጃ ይህንን ያህል የፖለቲካ ቁርጠኝነት የታየበት፤ ከፍተኛ ሀብት የተመደበበት፤ የፖለቲካ አመራሮች በንቃት የሚሳተፉበት ሁኔታ በሌላ ሀገር ባለመኖሩ ነው።
በዚህ ረገድ እያንዳንዱ ክልል ላይ የክልሉ ፕሬዚዳንት የሚመሩት ካውንስል ተፈጥሮ በዚያ ደረጃ እየሄደ ነው። እኛም እያገዝን ሃሳብ፣ አቅም አፈፃፀም ላይ አዳዲስ ሃሳቦችን በመውሰድ እየረዳን ነው የምንገኘው። ይሄ ትልቅ የማስተባበሪያ መዋቅር ነው። ሶስተኛው የልማት አጋሮችን የተበጣጠሰ ነገር እንዳይሠሩ በኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ሽግግር እሳቤ ላይ ተሰባስበው ወጥ የሆነ እገዛ እንዲያደርጉ እነሱንም የማስተባበር ሥራ ይሠራል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ እንደ አውታር ሆኖ እንዲወጣ እየሠራን ያለነው የግል ዘርፉን ነው። በርግጥ የግሉን ዘርፍ መጀመሪያ ላይ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ይሳተፋል ብለን አስበን ነበር ስናየው ግን እንዳሰብነው ሊሆን አልቻለም። የግል ዘርፉን ራሱን የቻለ የራሱ ፈተና ያለበት፣ የራሱን ሚና የሚጫወትበት ትልቅ ዘርፍ ነው። እናም እንዴት አድርገን ብናደራጀው ውጤታማ የሆነ አስተዋፅኦ ሊያበረክት እንደሚችል ብዙ ትኩረት አድርገን ሥንሠራ ቆይተናል። በቅርብ ጊዜ ብሔራዊ የግሉ ዘርፍ መድረክ ለመፍጠር ዝግጅት ላይ ነው የምንገኘው።
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ ግሎባል አሊያንስ ፎር ኢምፕሮቭመንት ኒውትሪሽ የተባለ ዓለም አቀፍ ተቋም አማካኝነት በምግብ ሥርዓቱ ሽግግር ሥራ ያተኮረ ጥናት ይፋ መደረጉ ይታወሳል። በፌዴራል ደረጃ በቅንጅት እየተሠራ ያለውን ያህል ወደ ክልል ሲወርድ ቅንጅቱ የሚላላበትና ትኩረት ያለመስጠት ሁኔታ መኖሩን ተገልጿል። በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
ጌታቸው (ዶ/ር)፡- በመሠረቱ ኢትዮጵያ በእድገት ሂደት ላይ ያለች ሀገር ናት፤ እንደ መንግሥት ትልቅ ግብ ይዞ በቁርጠኝነት እየተሠራ ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃና ፍጥነት በሁሉም አካል ይሠራል ማለት አይደለም። ይህም ቢሆን ግን በግልፅ የመጡ ለውጤቶች የሚያሳዩት ፈጣንና አበረታች ልማት እየመጣ ስለመሆኑ ነው። ኢትዮጵያ ሥርዓተ ምግብ ሽግግር ለማሳለጥ በጊዜ የለንም መንፈስ እየሠራች ትገኛለች። ያለፋታም እየተጋች በመሆኑም ውጤቶቹን በተጨባጭ እያየነው ያለነው። ከዚህ አንፃር የጠቀስሽው ጥናት የሚያሳየው በተቀናጀ የምግብ ሥርዓት ሽግግር ጉዞ ውስጥ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል ምን ምንድን ነው የሚለው ነገር ነው እየታየ ያለው።
ይህም የሚያመለክተው የት ቦታ ነው ጠንክረን መሄድ የሚያስፈልገን? እነማንን ብናስተባብር ነው ውጤት የምናገኘው? የሚለውን ነው እንጂ የድካም ማሳያ አይደለም። እንዴት አድርገን ክልሎችና ፌዴራል ተቋማት በምን መልኩ ትስስር ተፈጥሮላቸው መተጋገዝ እንደሚችሉ ለማመላከት ታስቦ የተዘጋጀ ጥናት ነው። ዋናው ጥረታችንም በተሻለ መልኩ የሥርዓተ ምግብ ሰንሰለቱን ተከትሎ እንዲሄድ ማድረግ ነው። ብዙዎቹም አስተያየት የሰጡት ያንን ነው። የእሴት ሰለንሰለት ተከትሎ እንዲሄድ ማድረግ ሲባልም አምራቹ፣ ነጋዴው፣ አቀነባባሪውም፣ ቸርቻሪውም፣ መሪው፣ ገዢው አብሮ እንዲጓዝ ለማድረግ ነው። የተነሱት ጉዳዮች አዳዲስ እይታ እንዲኖረን፣ እንድናሳትፍ፤ እንዳንዘናጋ ነው ያደረጉን። ለምሳሌ የሃይማኖት ተቋማትና እንደ እድር ያሉ አደረጃጀቶችን የመሳሰሉ የሸማቹ ማኅበር መብቶች ሁሉ የሥርዓተ ምግቡ ተዋናይ ናቸው። እንዴት አድርገን እንደምናሳትፋቸው አቅደን የምንሠራው ይሆናል።
አስቀድሜ እንደገለጽኩልሽ ቅንጅት ባሕላዊ ለውጥ ይፈልጋል፤ የትርክት ለውጥ ይፈልጋል፣ አሁን ያለንበት ወቅት ዓለም አቀፉ ራሱ ወደ ውስጥ ጉዳዩ የገባበት ሁኔታ መኖሩን እነዚህን ጉዳዮች ከግምት ውስጥ ያስገባ እይታና የተለየ አካሄድ ይጠይቃል። ካለፈው ሁለትና ሶስት ወራት በፊት ዓለም አንድ መንደር ሆኖለች ሲባል ነበር አሁን ግን በንግድም ሆነ በሁሉም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ሁሉም ወደ የራሱ እየዞረ ነው። ኢትዮጵያም ከውጭ የምትጠብቃቸው ርዳታዎች በተለይ በአንዳንድ ሀገሮች ሙሉ ለሙሉ ተቋርጠዋል። አንዳንዶቹም ለመውጣት ዝግጅት እያደረጉ ነው። ስለዚህ በራሳችን በውስጥ አቅማችን ነው መሥራት ያለብን። ሀብትን፣ እውቀትን ልምድን አቀናጅተን መሥራት አለብን። ምክንያቱም ደግሞ ምርጫ ስለሌለን ከዚህ በኋላ ርዳታና ድጋፍ ሳንጠብቅ መሥራት ይገባናል።
አዲስ ዘመን፡- በተመሳሳይ ለምግብ ሥርዓቱ ሽግግር እንደ እንቅፋት ሆነው በጥናቱ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል የፋይናንስ እጥረት አንዱ ነው። በተለይ ደግሞ ክልሎች ይህንን ሥራ ታሳቢ አድርገው ያለ መበጀታቸው እንደ ችግር ተነስቷል። ይህንን ችግር ለመፍታት ምን ታስቧል?
ጌታቸው (ዶ/ር)፡- በመሠረቱ ገንዘብ ሁልጊዜም ቢሆን በቂ አይደለም። በግለሰብም፣ በቤተሰብም ሆነ በሀገር ደረጃ በቂ ሆኖ አያውቅም። ጥያቄው ስለገንዘቡ መብቃት ወይም አለመብቃት አይደለም። ጥያቄው ያለንን እንዴት ውጤታማ በሚሆን መንገድ እንጠቀም የሚለው ነው። መታየት ያለበት ይሄ ነው። ኢትዮጵያ ያለችበት ወቅት በጣም ብዙ ሕዝብ ያለባት ብትሆንም በአንጻሩ ደግሞ የበርካታ ወጣቶች ሀገር ናት። ይሄ ወጣት የሥራ እድል ይፈልጋል፤ በልቶ ማደር ይፈልጋል፤ ለራሱና ለቤተሰቡ ሀብት መፍጠር ይፈልጋል።
ስለዚህ ያለን እድል ይህንን ትኩስ ኃይል ይዞ መሥራት ነው። ሁልጊዜ ገንዘብ ብቻ በቂ አይደለም። ለመፍጠር ገንዘብ ብቻውን አይፈጥርም፤ ፈጠራ ከጭንቅላት ነው የሚነሳው። እናም ይህንን ነው እንጂ ማሰብ ያለብን ገንዘብማ ሁልጊዜ ያንሳል። ግን ያለንን ሀብት በአግባቡ ከመጠቀም ውጭ ምርጫ የለንም። በዚህ ረገድ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ተቀናጅተንና ተባብረን መሥራት ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን፡- ከፍተኛ የትምህርትና የምርምር ተቋማት በየጊዜው የሚያወጡትን የምርምር ሥራ መሬት ላይ በማውረድ ለምግብ ሥርዓቱ ሽግግር መሳለጥ የሚገባቸውን ያህል ሚናቸውን እንዳልተወጡ እንደ ክፍተት ተነስቷል። በዚህስ ረገድ ምን መሠራት አለበት ይላሉ?
ጌታቸው (ዶ/ር)፡- እኛ እንደ ማስተባበሪያ መዋቅር የምርምር ተቋማት የፈጠራ ማዕከሎች በጣም እያነሳሳን ነው። ለኢትዮጵያ ሥርዓተ ምግብ ሽግግር ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲመጣ ሁሉ አቀፍ የሆነ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል። ስለዚህ እዚህ ጉዳይ ላይ ገለፃ እያደረግንና እያቀናጀን የተሻለ ውጤት ለማምጣት ጥረት እያደረግን እንገኛለን። ያለፈው የት ነበር ካልሽኝ እሱ የታሪክ ጉዳይ ነው የሚሆነው። ዛሬ ያለንበት ሁኔታ አቅደን እየሠራን ያለነው ሥራ ጊዜ የሚሰጥ አይደለም።
ለዚህ ሥራችን መሳካት ተመራማሪዎች እጅግ ወሳኝ ሚና አላቸው። በመሆኑም ዩኒቨርሲቲዎችን፣ የምርምር ተቋማትንና የዓለም አቀፍ በምርምር ላይ የሚሠሩ ድርጅቶችን እናሳትፋለን። ስለዚህ የልማት ድርጅቶችም ገንዘብ ተሰጥተው እንዲህ ዓይነት ጥናት የማስተባበሪያ መዋቅሩ ምን ይመስላል? ባለድርሻ አካላት እንዴት ነው የሚያዩት የሚለውን ምላሽ እንዲሰጡን ሁሉንም እናሳትፋለን። በቀጣይም በዚሁ መልክ ነው የሚሄደው።
አዲስ ዘመን፡- የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ2030 ለማሳካት ካቀዳቸው የልማት ግቦች መካከል የታዳጊ ሀገራት የምግብ ሥርዓት ሽግግር ማምጣት አንዱ እንደመሆኑ ኢትዮጵያ ከዚህ አንፃር ያለችበት ቁመና ምን ይመስላል?
ጌታቸው (ዶ/ር)፡– ኢትዮጵያ ግቡን ለማሳካት የሚበረታታ ጥረት እያደረገች ነው ያለችው። ታታሪ ሀገር ናት፤ በዚህም በዓለም እይታ ውስጥ ገብታለች። ለዚህም ነው ለመጀመሪያ ጊዜ አፍሪካ ውስጥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ኢትዮጵያ እንድታዘጋጅ የተመረጠችው። ይህም በራሱ የእኛን ታታሪነት ያሳየ ነው። የኢትዮጵያ እርሻ 10 ሺ ዓመት የፈጀ ነው። የኢትዮጵያ ባሕልም እንደ ሀገሪቷ ታሪክ ረጅም ጊዜ ያለው ነው። ለብዙ ዘመናት ያቆየነው የቤት ሥራ ዛሬ በምግብ ሥርዓት ሽግግርን ለማሳለጥ እንቅፋት የሆኑ ችግሮች በአንድ ጊዜ ይቀረፋሉ ማለት አይደለም። ሂደቱ አስቀድሜ እንደገለፅኩት በተለያዩ መለኪያዎች በጣም ብዙ ነው። ሀገር በቀል የፖሊሲ አቀራረጽ ላይ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት ያለው የመንግሥት ቢሮክራሲ፣ የሚፈጀውን ጊዜ ለመቀነስ ብዙ ጥረት ይደረጋል።
ጥረቱ እንዳለ ሆኖ አሁንም ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል። ግን እንደ መንግሥት እንደ ሀገር ጥረቱ አለ፤ ግን የሕዝቡን የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ ላይ አሁን እየተከናወነ ካለው ሥራ በላይ መሥራት ይገባናል። ያንን ለማሟላት ኢትዮጵያ ብዙ ርምጃዎች ይቀራታል። የጋራ ትብብር፤ የጋራ ጥረት ይጠይቃል። ደግሞም ድህነት መለኪያው ብዙ ነው፤ ዓለም ባንክ ካስቀመጠው ሁለት ዶላር ከ25 ሳንቲም መለኪያ ሲወሰድ በጣም ብዙ ሕዝብ ነው ደሃ የሚባለው። ከ23 እስከ 25 በመቶ ይደርሳል። ይህም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ደሃ ከሚባሉት ጎራ ውስጥ ነው ያሉት።
በመሆኑም በጣም ብዙ ጥረት ማድረግና ብዙ አቀበት መውጣት አለብን። ለዚህም ደግሞ በዋናነት ሰላም መኖር አለበት። ስለምንሠራና ስለምናርስ ብቻ በቂ አይደለም፤ እያንዳንዳችን በሰላም መኖርን ማወቅ አለብን። አሁን ላይ ጦርነት ያለባቸው፣ ሰላም የታጣባቸው አካባቢዎች ማረስ አይችሉም፣ ምግብ እንደ ልብ አያገኙም፤ በነፃነት ተንቀሳቅሰው መሥራት አይችሉም። ይህን ሁኔታ መቀየር ካልቻልን ልማት ብቻውን የሚያመጣው ለውጥ ስለማይኖር ይህንንም ታሳቢ አድርገን መሥራት ይገባናል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ጌታቸው (ዶ/ር)፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም