አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ባለፈው አንድ ዓመት ከአንድ ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ብድር ዕዳ መክፈሏን የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ ገለጹ።
ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፤ ባለፉት ዓመታት መከፈል ሲገባው ሳይከፈል የቆየ አንድ ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር የውጭ ዕዳ ክፍያ ተፈጽሟል።
ባለፈው አንድ ዓመት የውጭ እዳ በመክፈል ረገድ የተሰራው ስራ የተከማቸ የውጭ ዕዳ ከመክፈል አኳያ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመላካች ነው ያሉት ዶክተር ኢዮብ፤ ዕዳ የመክፈል ስራው በቀጣይ ዓመታትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
እንደ ዶክተር ኢዮብ ማብራሪያ፤ በቀጣይ ሶስት ዓመታት የሚካሄደው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ኢትዮጵያ የብድር እዳዋን ለመክፈል የሚያስችል የኢኮኖሚ ቁመና ያላት ሀገር እንድትሆን ማድረግ ግብ ነው።
በአሁኑ ወቅት ከ45 እስከ 50 በመቶ የሚሆነው ከወጪ ንግድ የሚገኘው የውጭ ሚንዛሬ ግኝት ለብድር ክፍያ እየዋለ ነው። ለቀጣይ ሶስት ዓመታት የሚካሄደው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የውጪ ንግዱን ከፍ በማድረግና ብድሮችን በማሸጋሸግ ከወጪ ንግድ የሚገኘው 20 ወይም 30 በመቶ የሚሆነው የውጭ ሚንዛሬ ግኝት ብቻ ለውጭ እዳ መክፈያ እንዲውል ለማድረግ ያስችላል፤ ለዚህም በጥብቅ ይሰራል ብለዋል።
ከገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ጋር የተደረገውን ሙሉ ቃለ ምልልስ በገጽ ዘጠኝ ይመልከቱ።
አዲስ ዘመን መስከረም 8/2012
መላኩ ኤሮሴ