ለአማርኛ ቋንቋ ሥነጽሑፍ እድገት ከፍ ያለ አስተዋፅኦ ያበረከቱት ደራሲ ፣ ባለቅኔና ዲፕሎማቱ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ህይወታቸው ያለፈው ከ81 ዓመት በፊት በዚህ ሳምንት መስከረም 9 ቀን 1931 ዓ.ም ነበር።
ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ በ1871 ዓ.ም ሰሜን ሸዋ መርሐ ቤቴ አውራጃ በታች ቤት ወረዳ ረመሸት ቀበሌ ደን አቦ ገዳም በተባለ ሥፍራ ከአባታቸው ከአቶ ወልደስላሤና ከእናታቸው ወይዘሮ ወለተማሪያም ተወለዱ። ሲወለዱ የተ ሰጣቸው ስም ገብረመስቀል የሚል ነበር። እንጦጦ ራጉኤል ደብር መጥተው የመጻሕፍትን ትርጓሜ ከደብሩ ሊቃውንት በሚማሩበት ወቅት አንድ መምህራቸው «ጎንደር በነበርኩ ጊዜ መምህሬ ስለሚወዱኝ ኅሩይ እያሉ ይጠሩኝ ነበር።ወደ አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ ግን በዚህ ስም እየተጠራሁኝ አይደለም።አንተ የቀለም ቀንድ ስለሆንክና በምግባርህም የተወደድክ ስለሆንክ ኅሩይ የተባለውን ስሜን ትጠራበት ዘንድ ሸልሜሃለሁ!» ሲሏቸው እርሳቸውም በደስታ ተቀበሉ።
ብላቴን ጌታ ኅሩይ በእንጦጦ ራጉኤል ደብር የመጽሐፍ ትርጓሜን በሚገባ ተምረው አጠናቀዋል።አዲስ አበባ ስውዲሽ ሚሽን ትምህርት ቤት ገብተው እንግሊዝኛ ቋንቋ ተምረዋል። ከእንግሊዝኛ ቋንቋ በተጨማሪ አረብኛ ቋንቋ ለመማር ጥረት ቢያደርጉም ኅሩይ ሰለመ የሚል አሉባልታ ስለሰሙ ትምህርቱን ለማቆም ተገደዋል።በኋላም ከፈረንሳያውያን ሐኪሞች ፈረንሳይኛ ቋንቋን ተምረዋል።
ብላቴን ጌታ ኅሩይ በንግስት ዘውዲ ቱና በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን የታወቁ ፖለቲከኛና የቤተ ክህነት ምሁር ነበሩ።ራሳቸው የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ብለው በሰየሙት መስሪያ ቤት ዋና ጸሐፊና ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል።ከ1912 እስከ 1913 ዓ.ም የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ከንቲባ ሆነው አገልግለዋል። በብላቴን ጌታ ማዕረግ የልዩ ፍርድ ቤት ዳኛ በመሆንም ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል።አጠር ላለ ጊዜም በጃፓን የኢትዮጵያ መንግስት ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው ሰርተ ዋል። በ1919 ዓ.ም ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዳይሬክተር ጀነራል ሆነው ተሹ መዋል።
ብላቴን ጌታ ኅሩይ ከማይጨው ጦርነት መልስ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ተከትለው ወደ ውጭ ተሰደዋል።ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በጄኔቫ የዓለም መንግሥታት ማህበር ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ ስለፈጸ መችው የግፍ ወረራ ሲገልጹ ኅሩይ ከጎና ቸው ነበሩ። በስደት ላይ እንዳሉም በጠና ታመው መስከረም 9 ቀን 1931 ዓ.ም አርፈው ለንደን ውስጥ ተቀበሩ።ከ ዘጠኝ ዓመታት በኋላ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጥረት አፅማቸው ከለንደን ወደ አዲስ አበባ መጥቶ መስከረም 11 ቀን 1940 ዓ.ም. በቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን እንዲያርፍ ተደርጓል።
ሥርዓተ ቀብራቸው መስከረም ዘጠኝ ቀን እዚያው እንግሊዝ አገር ሲፈጸም ንጉሠ ነገሥቱ የሚከተለውን ንግግር አድርገው ነበር።
“አሁን የአዳምን ልጆች ወግ ሲቀበል የምታዩት ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ በአገራችን ሥርዓት በመልካም አያያዝ ያደገ ከኢትዮጵያም ከፍ ካሉት ሊቃውንት የሚቆጠር ነው። ብልሃቱንና ትጋቱንም ለመልካም ሥራ የሚያገለግሉ መሣሪያዎች ስላደረጋቸው በመንግሥታችን ሥራ ለመመረጥና ወደ ታላቁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ለመድረስ በቃ። በየጊዜው የጻፋቸው ከፍተኛ ባህሪውን የሚገልጹ መጻሕፍት፤ ይልቁንም በቤተ ክህነትና በታሪክ እውቀት በዓለም ሊቃውንት ዘንድ የታወቀና የተከበረ አደረጉት። ለምታውቁት ሰው ከታሪኩ ከዚህ የበለጠ ልነግራችሁ የሚያስፈልግ አልመሰለኝም። በአጭሩ ከጠባዩ ትልቅነት የሚሰማኝን ለመናገር ሳስብ ጊዜውን ሁሉ ቁም ነገር በመሥራት ማሳለፉ፤ ከራሱ ይልቅ የተቸገሩትን ለመርዳት መጣሩ፤ እውነትን፣ ፍር ድንም ማክበሩና በአገር ፍቅር መቃጠሉ ትዝ ይሉኛል።
“አገልጋዬና ወዳጄ ኅሩይ! በተቻለህ ስለአገርህ ሥራህን በሚገባ ፈጽመህ በምትሰናበትበት ጊዜ ታላቅ ነህ ሳል ልህ ብቀር ሥራዎችህ ቀድመውኝ ይናገራሉ። በክፉ አድራጊዎች የሚገፋ የዓለምን ፀጥታ የሚያናውጥ ነፋስ ምንም ቢያንገላታህና በታላቅ ፈተና ላይ ቢጥልህም ሊያሸንፍ አልቻለም። ታላቅና ቸር በሆነው ጌታ በተመደበው ሕግ ግን መታዘዝ ግድ ሆነብህ። ይህም ለያንዳንዳችን የሚደርሰን ዕድል ነው። አንተም እስከ መጨረሻ ከታገልክ በኋላ ዛሬ ደከመህ፣ አንቀላፋህም። በሥጋ ብትለየንም ስምህና ሥራህ በመካከላችን ይኖራሉ። ኅሩይ! እግዚአብሔር ሲያስበን አጥንቶችህና መንፈስህ የሚሰፍሩበትን ቦታ እስኪያዩና ከአባቶችህ እስኪቀላቀሉ ድረስ በእንግድነት በመጣህበት በዚህ ሥፍራ በሰላም እረፍ።”
ብላቴን ጌታ ኅሩይ በተደጋጋሚ ወደ ውጭ አገራት መጓዝ ችለዋል።እንግሊዝ፣ አሜሪካን፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያንን እና ግብጽን የመሰሉ አገራትን የመጎብኘት ዕድል የገጠማቸው ኅሩይ የአገራቸውን ኋላ መቅረት በአውሮፓውያኑ ሥልጣኔ መነጽርነት ባስተዋሉ ቁጥር ቁጭታቸውን ባገኙት አጋጣሚ ይገልጹ ነበር።በአንድ አጋጣሚ ጣሊያን ሀገርን ሲጎበኙ በኢንዱስትሪው አማካኝነት የሚከናወነውን ድንቅ ሥራ ተመልክተው በመደመም ተከታዩን ሀሳብ አስፍረው ነበር።
“ለሀገራችን ለኢትዮጵያ የልብስና የእርሻ መኪና በግድ ያስፈልጋል።ኑሯችን ሁሉ ሸማ ለብሰን ነው እንጅ እንደ አውሮፓዎች የበግ ጠጉርና ሐር ዘወትር አንለብስምና አገራችን ጥጥ ለማብቀል የተመቸ ነውና ስለዚህ የሸማ መኪና ያስፈልገናል።ምግባችንም እህል ነው እንጅ እንደ አውሮፓዎች ሥጋና ዓሣ አትክልት ሁልጊዜ አናገኝምና አገራችንም አሳምሮ እህል ያበቅላልና ስለዚህ የእርሻ መኪና ያስፈልገናል።ይህንንም አስቀድሞ መንግሥት ገዝቶ ፋብሪካውን ቢያቆም መኳንንቱና ያገር ባለፀጎች ሁሉ እንደ ኩባንያ ገንዘብ እያዋጡ አንድ አንድ መኪና እየገዙ ፋብሪካ ያቆሙ ነበር።ከዚህም በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም ያገኙበት ነበር።”
ዓለማዊ ችግርን ለመፍታት ዕጣፋንታ ወይም መለኮታዊ ኃይል ምንም ሚና የለውም። ፈጣሪ የሚያዝ ንብን የሰጠንን ጸጋ የገጠሙንን ችግ ሮች ለመፍታት ማዋል ሲሳነን ነው በማለትም ግላዊ አተያያቸውን እንደ ሚከተለው ገልጸዋል።
“እግዚአብሔር ይጠብቀኛልብሎ ቤት ሳይሠሩ፣ አጥር ሳያጥሩ፣ እህል ሳይዘሩ መንደር ለመንደር ሲዞሩ ቢሞቱ እግዚአብሔርን መፈታተን ነው።ንጉሥም እግዚአብሔር ይጠብቀ ኛል ብሎ ጋሻ ጦሩን፣ ሰይፉን፣ መድፉንና ጠመንጃውን ሳያዘጋጅ ቢቀ መጥ ድንገት ጠላት መጥቶ እርሱን ገድሎ መንግሥቱን ቢወስድበት እግዚአብሔርን መፈታተን ነው። ጉልበታችሁን ተማምናችሁ እግዚአብ ሔርን አትርሱ።”
ብላቴን ጌታ ኅሩይ በርካታ መጽሐፍት ጽፈዋል።የአጼ ዮሐንስ ታሪክ ባጭሩ (1910 ዓ.ም)፣ የልዕልት መነን መንገድ በየሩሳሌምና በምስር (1915 ዓ.ም) ፣ ወዳጄ ልቤ (1915 ዓ.ም) ፣ መጽሐፈ ቅኔ (1918 ዓ.ም) ፣ በአማርኛ ቋንቋ የተጻፉ መጽሐፍት ካታሎግ (1920 ዓ.ም)፣ ማህደረ ብር ሃን ሀገረ ጃፓን (1924 ዓ.ም)፣ ዋዜማ (1926 ዓ.ም)፣ ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሠ-ነግሥት ዘኢትዮጵያ (1955 ዓ.ም)፣ ድርሳኖች (1983 ዓ.ም)፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል (1999 ዓ.ም) እና ሌሎችንም ጨምሮ ታሪክ፣ የጉዞ ማስታወሻ፣ ሃይማት፣ ልብወለድ፣ ግጥምና የጠቅላላ ዕውቀት መጽሐፍትን አበርክተዋል።
ብላቴን ጌታ ኅሩይ በአጠቃላይ ከሃያ በላይ መጻሕፍትን ደርሰዋል።ኅ ሩይ ገና በለጋነት ዕድሜያቸው ከወይዘሮ ሐመረ እሸቴ ጋር ትዳር መስርተው ስድስት ልጆችን ወልደ ዋል። ብዙ የልጅ ልጆችንም ለማየት በቅተዋል። የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ከኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ጋር በመተባበር ጳጉሜን 2 ቀን 2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ የአራት ቀደምት ደራሲያንን ምስል የያዙ ቴምብሮች አስመርቆ ገበያ ላይ ሲያውል ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ምስላቸው በቴምብር ላይ ከተቀረጸላቸው ደራሲያን አንዱ ነበሩ። ጉለሌ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚም ያስገነባውን የስነ ጥበባት ማዕከል በስማቸው እንዲጠራ አድርጓል።በቅርብም የህይወት ታሪካ ቸው “የብላቴን ጌታ ህሩይ ወልደ ሥላሴ ታሪክ 1871 – 1931 ዓ.ም” በሚል ርዕስ በፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ተዘጋጅቶ ታትሟል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 7/2012
የትናየት ፈሩ