አጥፊ ሳይሆን አላፊ ስለመሆን በጠቅላላው
እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
ያለጥፋት ካሣ የመክፈል ጉዳይ “አንድ ሰው ምንም ጥፋት ባላደረገበት ሁኔታ እንዴት ተጠያቂነት ይኖርበታል?” የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። እርግጥ ነው በእለት ተዕለት የሕይወት ገጠመኞቻችን አላፊነትና ጥፋተኝነት የተሳሰሩ መሆናቸውን ነው የምንገነዘበው። አንድ ሰው አጥፊ ከሆነ ለጥፋቱ አላፊ ሆኖ ይጠየቅበታል። ይሁንና ሕግ አላፊነትን በጥፋት ብቻ ሳይሆን ያለጥፋትም የሚመጣ ስለመሆኑ ይደነግጋል። ጥፋት ሳይኖር አላፊ መሆንን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሰዎች በሚያጠፉት ጥፋት ሁሉ ሳይቀር ሕግ “ንጹሁን” ሰው ጥፋተኛ ነህ ብሎ አላፊ የሚያደርግበት ሁኔታ አለ።
ጥፋት ሳይኖር አላፊ የመሆን ጉዳይ ከውል ውጭ የሚመጣ አላፊነት አንዱ መገለጫ ነው። ከውል ውጭ አላፊነት ደግሞ በሰዎች መካከል ምንም ዓይነት የውል ግንኙነት ሳይኖር በሌላው ሰው ላይ ለሚደርስ ጉዳት ተጠያቂነትን የሚያስከትል የፍትሐብሔር ግዴታ ነው። ከውል ውጭ የሚደርስ አላፊነት ከሶስት ሁኔታዎች ይመነጫል። እነዚህም በራስ ጥፋት በሌላ ሰው ላይ ጉዳት በማድረስ፤ አጥፊ ሳይሆን አላፊ በመሆን እንዲሁም በሌሎች ሰዎች ጥፋት በሌላው ሰው ላይ ጉዳት ሲደርስ (ለምሳሌ አካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ ለሚፈጽመው ጥፋት ወላጆች ወይም ሞግዚትና አሳዳጊዎቹ) አላፊ መሆን ናቸው።
በዚህ ጽሁፍ ታዲያ ከውል ውጭ ለሚደርስ አላፊነት ሁለተኛው ምንጭ የሆነውን ያለጥፋት አላፊ የመሆንን ጉዳይ እንመለከታለን። ያለጥፋት አላፊ መሆን አንድ ሰው በራሱ ጥፋት ባይሰራም እንኳን በአንዳንድ በሕግ ተለይተው በተጠቀሱ አድራጎቶች ወይም በንብረቶቹ አማካኝነት በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ቢደርስ ጥፋተኛ ሆኖ የሚጠየቅበት ነው።
ንጋቱ ተስፋዬ “ከውል ውጭ አላፊነትና አለአግባብ መበልጸግ ሕግ” በተሰኘው መጽሐፉ እንደሚያብራራው አንዳንድ ምሁራን አንድ ሰው ምንም ጥፋት ሳይሰራ አላፊ የሚሆንበትንና ሌላ ሰው ለሚፈጽመው ጥፋት አላፊ የሚኮንባቸውን ሁኔታዎች እንደ ማህበራዊ ፍትህ መጓደል አድርገው ይቆጥሯቸዋል። ይባስ ብለውም አንድን ሰው ያለጥፋቱ አላፊ ማድረግ እና ሌሎች ለሚፈጽሙት ጥፋት ካሳ እንዲከፍል ማስገደድ በወንጀል ጉዳይ ንጹህ ሰውን ከመቅጣት ጋር ተመሳሳይ መሆናቸውን በመግለጽ ይነቅፋሉ። ይህም ከውል ውጭ አላፊነት ሕግ ዋነኛ ዓላማ ከሆነው በደል እንዳይፈጸም ከመከላከል፣ አጥፊን ከመቅጣት እና ካሳ ከማስከፈል እሳቤ ያፈነገጠ ነው ሲሉም ይደመጣሉ።
ይሁንና ያለጥፋት አላፊነት በአንዳንድ ልዩ ሁኔታዎችም ሊኖር እንደሚገባ ከአገራችን ሕግ እና በየጊዜው እየተከሰቱ በፍርድ ቤቶች እልባት ከሚያገኙ ክርክሮች መገንዘብ ይቻላል። ከውል ውጭ የሚመጣ አላፊነት ሕግ ዋና ዓላማ ግለሰቦች ለሚደርስባቸው ጉዳት ዋስትና እንዲኖራቸው (ካሣ እንዲያገኙ) ማድረግ ነው። እንጂ አጥፊዎችን መቅጣት አለመሆኑ ብዙዎችን የሚያስማማ ነው። ይልቁንም ሰዎች ለሚያደርሱት ጥፋት የመቅጣትና የማስተማር ዓላማን ሰንቆ የወጣው የወንጀል ህግ ነው። ይህ ሲባል ግን አጥፊው ለሚፈጽመው ጥፋት በፍትሐብሔር አይቀጣም ማለት ሳይሆን ይልቁንም ለተጎጂው የሚከፍለው ካሣ በራሱ እንደ ቅጣት የሚቆጠር ነው ማለት ነው።
ከውል ውጭ አላፊነት ሕግ ተቀዳሚ ዓላማው ግለሰቦች ለሚደርስባቸው ጉዳት ካሣ ማስከፈል ነው ሲባል ታዲያ ሊሰመርበት የሚገባ መሰረታዊ ጉዳይ አለ። ሕጉ ካሣ የማስከፈል ዓላማ ነው ያለው ሲባል ያለበቂ ምክንያት ሰዎች አላፊ እንዲሆኑ ያደረጋል ማለት አይደለም። ጥፋት ባያደርጉም እንዲሁም ሌሎች እነርሱ አላፊ የሚሆኑላቸው ሰዎች በሚያደርሱትም ጥፋት ቢሆን እንዲጠየቁ ማድረግ ቅቡልነት ያለው አመክንዮ ስለመሆኑ መናገር ይቻላል።
አንድ ሰው አጥፊ ሳይሆን በህጉ ላይ እንደተመለከተው ተለይተው በተቀመጡ አድራጎቶች ወይም ንብረቶች አማካኝነት በሌላ ሰው ላይ ለሚደርስ ጉዳት ተጠያቂ የሚሆነው በሕግ ተለይተው በተቀመጡት የተወሰኑ ጉዳዮች ብቻ ነው። እነዚህም አንደኛ በሌላ ሰው ላይ ጉዳት የሚደርሰው በሰዎች አድራጎት ሲሆን፤ ሁለተኛ ጉዳት የሚደርሰው በንብረት አማካኝነት ሲሆን ነው። ሶስተኛው በተሰሩ እቃዎች ለሚደርስ ጉዳት አላፊ መሆን ነው። ከዚህ የምንረዳውም ሕጉ ሰዎችን ያለጥፋታቸው አላፊ የሚያደርገው በተወሰኑና በተመረጡ ምክንያቶች ብቻ መሆኑን ነው።
በሶስቱም ሁኔታዎች አላፊነቱ የሚመጣው ያለጥፋት ሲሆን፤ ካሣ እንዲከፍል የሚከሰሰው ሰው ጥፋተኛ አለመሆኑን በማስረዳት ከኃላፊነት አይድንም። ይልቁንም የተጎጂው ጥፋት መኖሩን እና የውል ግንኙነት መኖሩን በማሳየት ከአላፊነት መዳን ይችላል። በተጨማሪም ውል ባይኖርም እንኳ ካሳ ጠያቂው ሰው ጉዳቱ በደረሰበት ጊዜ ለንብረቱ ባለቤት ወይም ጠባቂ ክፍያ ሳይፈጽም ጉዳት ባደረሱበት ንብረቶች ይገለገል ከነበረም ይህንኑ አንስቶ በመከራከር ከአላፊነት መዳን ይቻላል። በሌላ በኩል ካሣ ለማግኘት ደግሞ ጉዳት መድረሱንና መንስኤውን ማስረዳት ብቻ በቂ ነው ማለት ነው።
አንድ ሰው አጥፊ ሳይሆን ካሣ የሚከፍልባቸውን እነዚህን ሶስት ጉዳዮች ነው እንግዲህ በዝርዝር የምንመለከተው።
ያለጥፋት አላፊነትን የሚያስከትሉ አድራጎቶች
ያለጥፋት አላፊነትን የሚያስከትሉ ድርጊቶች ተብለው በሕጉ በግልጽ የተመለከቱት ጉዳዮች ሶስት ናቸው። እነዚሁም በፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 2066፣ 2067 እና 2069 የተገለጹት ናቸው። ያለጥፋት አላፊነትን ከሚያስከትሉት ሶስት ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ የአስፈላጊ ሁኔታ ነው። አስፈላጊ ሁኔታ የሚለውን ሕጉ ሲደነግግ አንድ ሰው ራሱን፣ ሌላን ሰው፣ ሃብቱን ወይም የሌላውን ሰው ሃብት በእርግጥ ሊደርስበት ከሚችል አደጋ ለማዳን ሲከላከል በሌላው ሰው ላይ ሆነ ብሎ ጉዳት ካደረሰ (በተጎጂው ጥፋትና ምክንያት ካልሆነ በቀር) ተጠያቂ ነው ይላል።
በአስፈላጊ ሁኔታ ውስጥ በሌላ ሰው መብት (ንብረት) ላይ ጉዳት የደረሰው ሆነ ብሎ በተፈጸመ አድራጎት ቢሆንም ከአደጋው ለማምለጥ ሌላ አማራጭ ስለሌለ አድራጎቱ እንደ ጥፋት አይቆጠርም። ይሁን እንጂ አድራጎቱ ጥፋት ባይሆንም የድርጊቱ ፈጻሚ ላደረሰው ጉዳት ካሣ የመክፈል አላፊነት አለበት። መኖሪያ ቤቱ በእሳት ሲቃጠልበት በድንገት የደረሰ ሰው የጎረቤቱን በር ገንጥሎ በመግባት የእሳት ማጥፊያ መሳሪያ አውጥቶ እሳቱን ቢያጠፋ ድርጊቱ እንደ ጥፋት ባይቆጠርበትም በጎረቤቱ ንብረት ላይ ላደረሰው ጉዳት ግን አላፊ ነው።
“ከውል ውጭ አላፊነትና አለአግባብ መበልጸግ ሕግ” የተሰኘው የንጋቱ ተስፋዬ መጽሀፍም እንደሚያብራራው የአስፈላጊ ሁኔታን መነሻ በማድረግ አንድ ሰው ያለጥፋቱ አላፊ እንዲሆን ህጋችን የደነገገበት መነሻ ከማይፈለጉ ሁለት መጥፎ ነገሮች አነስተኛውን ለመምረጥ በማሰብ ነው። ከአደጋው የሚተርፈው እና በሰውየው አድራጎት ጉዳት የሚደርስበት መብት ሲነጻጸሩ ከአደጋው የሚድነው መብት የበለጠ መሆን አለበት። አለበለዚያ ግን አድራጎቱ ጥፋት መሆኑ አይቀሬ ስለሚሆን አላፊነቱም ያለጥፋት ሳይሆን በጥፋት ላይ የተመሰረተ አላፊነት ይሆናል ማለት ነው።
እዚህ ላይ የአስፈላጊ ሁኔታን ጉዳይ ከወንጀል አላፊነት አንጻርም አየት አድርጎ ማለፉ ጠቃሚ ነው። የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 75 አስፈላጊ ሁኔታ የሚለውን የፍትሐብሔር ሕጉን አገላለጽ “አስገዳጅ ሁኔታ” በሚል ተክቶት እናገኛለን። ያም ሆነ ይህ አገላለጹ ቢለያይም ቅሉ በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ ግን ተመሳሳይ ናቸው። በወንጀል ሕጉ እንደተመለከተው የራስን ወይም የሌላውን ሰው መብት በቅርብ ከሚደርስ ከባድ አደጋ ለማዳን የተፈጸመ ድርጊት፤ አደጋውን በሌላ መንገድ ለማስወገድ የማይቻል ከሆነና አድራጊው ከሁኔታው ጋር ተመጣጣኝ የሆኑ ዘዴዎችን የተጠቀመ ከሆነ አያስቀጣም። ከዚህ የምንረዳው አስገዳጅ ሁኔታ የወንጀል ቅጣትን እንደማያስከትል ነው። መኖሪያ ቤቱን ከደረሰበት የእሳት ቃጠሎ ለማዳን የጎረቤቱን በር ገንጥሎ የእሳት ማጥፊያ የወሰደ ሰው በሌላ ሰው ንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ ወንጀል አይቀጣም ማለት ነው።
ያለጥፋት አላፊነትን የሚያስከትል ሌላው አድራጎት በሰው አካል ላይ ጉዳት ማድረስ ነው። በፍትሐብሔር ህጉ ቁጥር 2067 ላይ እንደምናነበው አንድ ሰው በሰራው ሥራ በሌላ ሰው አካል ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ አላፊ ነው። ይሁንና ይህንን ጉዳት ያደረሰው ሥራ በሕግ የተፈቀደና የታዘዘ እንደሆነ ወይም ሥራው የተፈጸመው ራስን ለማዳን በሚገባ ሲከላከል እንደሆነ ወይም ደግሞ አደጋው ሊደርስ የቻለው በተበዳዩ ጥፋት ምክንያት ብቻ እንደሆነ በአድራጊው ላይ አላፊነት እንደማይኖርበት ሕጉ አስቀምጧል።
በሌላ ሰው አካል ላይ ጉዳት በማድረስ የሚመጣ አላፊነት ጋር በተያያዘ ግንዛቤ ሊያዝበት የሚገባው ጉዳይ በስፖርት ጨዋታ ወቅት የሚደርስ የአካል ጉዳት ነው። አንድ ሰው በስፖርት ላይ ሳለ በስፖርቱ ተካፋይ የሆነውን ወይም ተመልካቹን ቢያቆስለው የስፖርቱን ስነ ሥርዓት የሚመለከተውን ደንብ በግልጽ ካልጣሰ ወይም የተንኮል ሥራ ካልፈጸመ በቀር በአላፊነት እንደማይጠየቅ መገንዘብ ያስፈልጋል።
ሶስተኛው ያለጥፋት አላፊነትን የሚያስከትል አድራጎት አደገኛ ሥራ ነው። በህጋችን አደገኛ ሥራ ተብለው የተመለከቱት የሚፈነዱ ወይም መርዛማ ነገሮችን መጠቀም፣ ማከማቸት እንዲሁም ከፍተኛ ጉልበት ያለው የኤሌክትሪክ መስመር መዘርጋት፤ የመሬትን የተፈጥሮ አቀማመጥ መለወጥ እና አደገኛ የሆኑ የኢንዱስትሪ ሥራዎችን ማካሄድ ናቸው። እነዚህን ስራዎች ማከናወን በራሱ ጥፋት ባይሆንም ሥራው በሌላ ሰው ላይ አደጋ (ጉዳት) ካደረሰ ግን በእነዚህ ሥራዎች ላይ የተሰማራ ሰው ካሣ የመክፈል አላፊነት አለበት ማለት ነው። በእነዚህ ሥራዎች ላይ የተሰማራ ግለሰብም ይሁን የተፈቀደለት የመንግስትም ሆነ የግል መስሪያ ቤት ለጉዳቱ አላፊ ይሆናል። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው የኤሌክትሪክ ኃይል መስሪያ ቤት አላፊነት ነው።
የያኔው የሼል ኢትዮጵያ አንድ የነዳጅ ማደያ እና የመንግስት ቤቶች ኮርፖሬሽን ንብረት የሆነ ቤት በአንድ የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ በጉርብትና ይኖራሉ። አንድ ቀን ታዲያ ነዳጅ የጫነ መኪና ነዳጅ በሚያራግፍበት ወቅት በነዳጅ ማደያው ላይ በተነሳ እሳት የቤቶች ኮርፖሬሽን ቤት ላይ ጉዳት ይደርሳል። ሼልም ቤቱን አድሶ ያስረክባል። ይሁንና ኮርፖሬሽኑ በእድሳቱ ምክንያት ቤቱ በመዘጋቱ የኪራይ ገቢ ማጣቱን በመግለጽ ያጣውን ገንዘብ እንዲከፍለው በሼል ላይ ክስ ይመሰርታል። ሼል ደግሞ ቤቱን አድሶ ማስረከቡን ሳይክድ ለአደጋው አላፊነት ያለበት ነዳጅ አጓጓዥ የነበረው አሽከርካሪ ነው በማለት ተከራክሯል። ጉዳዩ የቀረበለት የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም ሼል አላፊነት የለበትም ሲል በነጻ አሰናበተው። በይግባኝም ውሳኔው ጸና።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ደግሞ የቀረበለትን የሰበር አቤቱታና ምላሹን ከመረመረ በኋላ ነዳጁ ሲራገፍ የነበረው ሼል ስራውን በሚያከናውንበት የነዳጅ ማደያ መሆኑንና አላፊነቱም የሚመነጨው ከሚያከናውነው ከዚሁ አደገኛ ሥራ መሆኑን በመግለጽ በማደያው ሥራ ላይ ለሚከሰተው አደጋ ሼል አላፊነት እንዳለበት ድምዳሜ ላይ ደርሷል። እናም የነዳጅ ማደያ ሥራ ጥንቃቄ የሚያስፈልገውና በቀላሉ የመቀጣጠል ወይም የመፈንዳት ባህርይ ያለው አደገኛ ስራ በመሆኑ ለሚደርሰው አደጋም ባለማደያው አላፊነት አለበት ሲል የሥር ፍርድ ቤቶችን ውሳኔዎች ሽሯቸዋል። ይህም በአደገኛ ስራ ምክንያት በሌላ ሰው ላይ አደጋ የደረሰ እንደሆነ ሥራውን የሚያከናውነው አካል ለጉዳቱ ካሳ የመክፈል አላፊነት ያለበት መሆኑን ያስገነዝባል።
በንብረት አማካኝነት ለሚደርስ ጉዳት አላፊ መሆን
በንብረት አማካኝነት ለሚደርስ ጉዳት አላፊ መሆን ያለጥፋት አላፊነትን ከሚያስከትሉ ድርጊቶች በመቀጠል ሰዎች ያለጥፋታቸው አላፊ የሚሆኑበት ሁለተኛው ምክንያት ነው። በሕጋችን ያለጥፋት አላፊነትን የሚያስከትሉ ንብረቶች ተብለው በልዩ ሁኔታ የተዘረዘሩት እንስሳት፣ ሕንጻዎች፣ ማሽኖችና ባለሞተር ተሽከርካሪዎች ናቸው። ንጋቱ ተስፋዬ በመጽሃፉ እንደሚያስረዳው ሕጉ እነዚህን ንብረቶች መርጦ ያለጥፋት አላፊነት እንዲኖር ያደረገበት ምክንያት በባለቤት በኩል ምንም ጥፋት ሳይኖር መሳሪያዎቹ አደጋ/ጉዳት የማድረስ ችሎታ ስላላቸው ነው።
የአንድ እንስሳ ባለቤት እንስሳው ጉዳቱን ያደረሰው በድንገት በማምለጥም ቢሆን ያደርጋል ተብሎ ያልታሰበውንም ጉዳት አድርሶ ቢገኝ እንስሳው ባደረሰው ጉዳት አላፊ ነው። የእንስሳው ጠባቂ በሚል በሕጉ የተገለጸውም ቢሆን ማለትም ለግል ጥቅሙ እንዲያውለው የሌላ ሰው እንስሳ በእጁ የሚገኝ ሰው፤ እንስሳውን በኪራይ፣ በተውሶ፣ ለመጠበቅ፣ ለመቀለብ፣ ወይም በማናቸውም ሁኔታ የተረከበ ሰው እንስሳው ለሚያደርሰው ጉዳት አላፊ ነው። ነገር ግን እንስሳውን በታዛዥነት እንዲጠብቅ (ለምሳሌ እረኛ) ወይም እንስሳውን ለባለቤቱ ወይም ለሌላ ሰው ጥቅም የሚሰራበት ሰው (ለምሳሌ ጋሪ የሚሰራ) እንስሳው ጉዳቱን ያደረሰው በእሱ ጥፋት ካልሆነ በስተቀር አላፊ እንደማይሆን መረዳት ያስፈልጋል።
ከእንስሳት በተጨማሪ የአንድ ህንጻ (ቤት፣ አጥር፣ ድልድይ፣ ሐውልትን የመሰሉ ማናቸውም ግንባታዎች) ባለቤት ወይም ባለይዞታ ህንጻው ሊያደርስ ይችላል ተብሎ ያልታሰበ አደጋ ቢያደርስ እንኳ ለሚደርሰው ጉዳት አላፊ ይሆናል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ታዲያ ባለቤቱ ህንጻውን የገነባውን ወይም በህንጻው ውስጥ የሚገኘውን ወይም ህንጻው ባደረሰው ጉዳት አጥፊ የሆነውን ሰው የመጠየቅ መብት አለው። ሌላው መሰረታዊ ነጥብ በአንድ ህንጻ ውስጥ የሚኖር ሰው ከህንጻው እየወደቁ ጉዳት በሚያደርሱ ተንቀሳቃሽ ነገሮች አላፊ የመሆኑ ጉዳይ ነው። ከሌላ ሰው ህንጻ ላይ ጉዳት ይደርስብኛል ብሎ የሚሰጋ ሰው ደግሞ የህንጻው ባለቤት ጉዳቱ ከመድረሱ አስቀድሞ አስጊው ነገር እንዲወገድለት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ሊጠይቅ መብት አለው።
ከእንስሳትና ከህንጻ በተጨማሪ ያለጥፋት አላፊነትን የሚያስከትሉ ንብረቶች የሚባሉት ማሽኖችና ባለሞተር ተሽከርካሪዎች ናቸው። የአንድ ማሽን ወይም ባለሞተር ተሽከርካሪ ባለቤት የሆነ ሰው አደጋው የደረሰው ማሽኑን ለማንቀሳቀስ ወይም ባለሞተር ተሽከርካሪውን ለመንዳት ባልተፈቀደለትም ሰው ቢሆን እንኳ ማሽኑ ወይም ባለሞተር ተሽከርካሪው ባደረሰው ጉዳት አላፊ ይሆናል። ይሁንና ማሽኑ ወይም ባለሞተር ተሽከርካሪው አደጋውን ባደረሰ ጊዜ የተሰረቀበት መሆኑን ማስረዳት ከቻለ አላፊነት እንደማይኖርበት ልብ ይሏል። ከዚህ ውጭ ግን ልክ እንደ እንስሳት ሁሉ ለግል ጥቅም ሊገለገል የወሰደ ሰው ለአደጋው አላፊ ሲሆን፤ በታዛዥነት የሚሰራ ሰው ደግሞ በራሱ ጥፋት ካልሆነ በስተቀር አላፊ እንደማይሆንም መገንዘብ ያስፈልጋል።
በተሰሩ እቃዎች ለሚደርስ ጉዳት የሚመጣ አላፊነት
ይህ አላፊነት በንብረት አማካኝነት ለሚደርስ ጉዳት እና ያለጥፋት አላፊነትን በሚያስከትሉ ድርጊቶች ከሚደርስ ጉዳት በመቀጠል ሰዎች ያለጥፋታቸው አላፊ የሚሆኑበት ሶስተኛው ምክንያት ነው። ትርፍ ለማግኘት ሲል ዕቃዎችን የሚሰራና ለሕዝብ የሚያቀርብ ሰው በእቃዎቹ በሚገባ ሲጠቀምባቸው በነበረ ሌላ ሰው ላይ (ወንበርን ለመቀመጫ፣ አልጋን ለመኝታ ወዘተ) እቃዎቹ ጉዳት ቢያደርሱ አላፊ ነው። ነገር ግን ዕቃው በልማድ እንደሚደረገው ተመርምሮ ቢሆን ኖሮ ጉዳቱን ያመጣው የእቃው ጉድለት ሊታወቅ የሚችል ከሆነ አምራቹ ምንም አላፊነት የለበትም።
በተሰሩ እቃዎች ለሚደርስ ጉዳት በአላፊነት የሚጠየቀው ባለቤት ወይም ጠባቂ ሳይሆን አምራቹ (ሰሪው) ነው። የእቃው ተጠቃሚ እቃውን ከቸርቻሪ የገዛ ወይም ከገዥው የተከራየ ወይም የተዋሰ ሊሆን ይችላል። እቃውን የገዛው ከአምራቹ ከሆነ ግን ግንኙነቱ በውል ላይ የተመሰረተ ስለሚሆን ከውል ውጭ አላፊነት አይኖርም። አምራቹ በተሰሩ እቃዎች ለሚደርስ ጉዳት በአላፊነት ከውል ውጭ የተከሰሰ ከሆነ ደግሞ ማቅረብ ያለበት መከራከሪያ አንድም ተጠቃሚው እቃውን በተገቢው መንገድ አልተገለገለበትም ወይም እቃውን ከቸርቻሪ ሲገዛ በልማድ እንደሚደረገው ተገቢውን ምርመራ አድርጎ ቢሆን ኖሮ ጉዳቱን ያስከተለውን ጉድለት ሊያውቀው ይችል ነበር የሚል መሆን አለበት።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 7/2012
ከገብረክርስቶስ