አንድን ቤት ለሁለት በከፈለው በኢትዮ ኤርትሪያ ጦርነት መንግስት ያደረገውን ጥሪ ተቀብለው በባድመ ግንባር ሲዋጉ መቆየታቸውን የዛሬው የፍረዱኝ ባለጉዳያችን ወታደር አያልነህ አበባው የኋሊት በትዝታ ነጉደው ያስታውሳሉ። በጦርነቱ አንደኛው ወገን አሸናፊ ነው የሚል የጀግና መጠሪያ ይሰጠው እንጂ፤ ዳሩ ግን ሁለቱም ወገን ተሸናፊ መሆናቸው እሙን ነው። ምክንያቱ ደግሞ ካገኙትና ከሚያገኙት በላይ ያጡት፣ ወንድማማቾች የተዋደቁበትና ሕይወታቸው ያለፈበት፣ በርካቶች ለአካል ጉዳት የተዳረጉበትና ጥይትና ጠባሳ በሰውነታቸው ውስጥ ይዘው እንዲኖሩ አድርጓቸው ማለፉ በቂ ማሳያ ነው። ወታደሩም በ1993 ዓ.ም በውጊያው በሸንበቆ ግንባር ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በጉዳታቸው ወቅት በታጠቅ ማገገሚያ ቢቆዩም፤ የደረሰባቸው የአካል ጉዳት መጠን ዳግም ወደ ሠራዊቱ ለመቀላቀል እንደማያስችላቸው በመረጋገጡ የሕክምና ውጤታቸው ለቦርድ ቀርቦ እንዲሰናበቱ መደረጉን ይናገራሉ። ያለማንም አስገዳጅነት የአገራቸውን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ዘምተውና ቆስለው ቢመለሱም ለእርሳቸው የመርዶ ያክል የከበደው ከሰራዊቱ መሰናበታቸው በደብዳቤ ተገልፆ መጓጓዣ ተሰጥቷቸው መሸኘታቸው ነበር። ከሰራዊቱ ከተሰናበቱ በኋላ በክልላቸው ተጠቃሚነታቸው እንደሚረጋገጥ የተነገራቸው ቢሆንም እንደተባለው ሳይሆን ይቀርና ምላሽ ሳያገኙ ዓመታት ይነጉዳሉ።
ስንብታቸው እንደ ማንኛውም የሠራዊቱ አባል የካሳና ጡረታ መብታቸውን ያስከበረ ሳይሆን ችግርን ያስከተለ እንደሆነ የሚገልጹት ወታደሩ፤ መብታቸው ሳይከበርላቸው በመቆየቱ ሲጠይቁ፣ ምላሽ ለማግኘትም ሲወጡና ሲወርዱ ይቆያሉ። በዚህ መልኩ ጥያቄያቸው ምላሽ ሳያገኝ በእንግልት 20 ዓመታት ሊያስቆጥሩ መሆኑ ትውስ ሲላቸው ‹‹ እኔ ኢትዮጵያዊ አይደለሁምን ?›› የሚል ጥያቄን እንደሚያጭርባቸውም ዓይናቸው በእንባ ተሞልቶ በሲቃ ይናገራሉ።
በአካላቸው ላይ የደረሰውን ጉዳት በልብስ ሸፍነው ተስፋ ባለመቁረጥ ምላሽ ለማግኘት ከላይ ታች የሚሉት ወታደር አያልነህ፤ ለሁለት አሥርት ዓመታት ያልተፈፀመ ጉዳያቸውን መፍትሔ ናፍቀው መኖሪያቸውን ምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ ካደረጉበት ሥፍራ የቀን ሥራ እየሰሩ ያጠራቀሟትን ገንዘብ ቋጥረው ከአንድ ወር በፊት አዲስ አበባ መግባታቸውን ነው የሚናገሩት። ሆኖም ግን ምንም እልባት ባለማግኘታቸው ያጠራቀሟት ጥቂት ገንዘብ ከኪሳቸው በማለቋ በአሁኑ ወቅት በረንዳ ለማደር መገደዳቸውን ያስረዳሉ። ጎዳና ላይ አጥንት ዘልቆ የሚሰማው የክረምቱ ቅዝቃዜም የኖረ ቁስላቸውን ቀስቅሶ ለሳል ዳርጓቸዋል። ታመው በመንገድ ላይ የሚያያቸው ለነፍሱ ያለ ከሚተባበራቸው ባለፈ ማደሪያም ሆነ ጊዜ የማይሰጠውን ሆድ ዝም የሚያስብሉበት ምንም ገንዘብ እንደሌላቸው ነው የሚናገሩት። እኛም ጉዳዩን በተመለከተ ከራሳቸው አንደበት ያደመጥነውን፣ የሰነድ ማስረጃዎችንና የሚመለከተውን አካል አነጋግረን ያቀናበርነውን ዘገባ እንዲህ ይዘንላችሁ ቀርበናል።
እንዴት?
ወታደሩ እንደሚናገሩት፤ ወደ ክልሉ ከተላኩ ደብዳቤዎች መካከል አንዱ በሚገኙበት አካባቢ የጡረታ ዋስትና እንዲረጋገጥላቸው የሚል ነው። ነገር ግን የተሰጣቸው ያልሆነ ተስፋ ለዓመታት ሳይፈፀም እንዲንከራተቱ አድርጓቸዋል። ጉዳያቸውን የሕዝቡን እንባ ለማበስ ለተቋቋሙ ተቋማት ሁሉ ቢያሳውቁም በተመላለሱባቸው ዓመታት የሥራ ኃላፊዎቹ ከመቀያየር ባለፈ በእርሳቸው ሕይወት ላይ ግን ጠብ ብሎ የተቀየረ ነገር የለም። ደብዳቤያቸው ምላሽ ባያገኝም፣ በየዓመቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እስከ እንባ ጠባቂና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ተቋማት ሁሉ ጠይቀዋል። በቅርቡም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ለመከላከያ ሚኒስቴር ጽፎላቸው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ደብዳቤውን አስገብተዋል።
ደብዳቤውን እንዳስገቡ ስህተቱ የተፈጠረው በሐኪሞቹ ነው የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ይናገራሉ። የተፈጠረውን ስህተት ለማረምም ወደ በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የጤና ዋና መምሪያ የጦር ኃይሎች ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በማቅናት የህክምናውን ጉዳይ ሲጨርሱ ለሚኒስቴሩ ሠው ሀብት መምሪያ እንደሚመራላቸው ይነገራቸዋል። ሐኪሞቹም በቀጥታ ለቅበላና ሽኝት ማህደሩ መላክ እንዳለበትና ተያይዞ ለሆስፒታሉ የሕክምና ቦርድ ጉባዔ እንዲቀርብ ይጽፋሉ። በዚህ መሠረት ማህደራቸውን በመፈለግ ለቦርድ ያቀርባቸዋል። ቦርድ ጉባዔውም በማህደሩ መሠረት 35 በመቶ ካታጎሪ አራት ተሰጥቷል በሚል ወደ ቅበላና ሽኝት ኬዝ ቲም ደብዳቤ ይጽፍላቸዋል። ደብዳቤያቸውን በመያዝ ወደ ጡረታ ክፍል ቢያቀኑም ‹‹እንዴት ድጋሚ ይታይ ተባለ›› በሚል ክፍሉ ጥያቄ ያነሳባቸዋል። እርሳቸውም ‹‹ደሜ ውሃ ነውን?›› በማለት እንደ ማንኛውም ዜጋ ጥቅማ ጥቅም ማግኘት እንደሚገባቸውና ከሌሎች በተለየ ሁኔታ ጉዳያቸው ያልተፈፀመበትን ምክንያት መጠየቃቸውን ይናገራሉ።
የጡረታ ክፍሉ፤ ደብዳቤውን ቢቀበላቸውም ማህተም ያላረፈበት በመሆኑ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ይገልጽላቸዋል። እርሳቸውም አጭበርባሪ እንዳልሆኑና ጉዳዩን ለማጣራት ሆስፒታሉ እንዲሁም የሠው ሀብቱ ሩቅ ባለመሆኑ በቀላሉ ማጣራት እንደሚቻል ይናገራሉ። ከብዙ ክርክር በኋላም ተመልሰው እንዲመጡ ይገለጽላቸዋል። ሆስፒታሉም ዳግም ለሠው ሀብት አስተዳደር ይጽፍላቸዋል።
ጉዳያቸውን ጨርሰው ለሠው ሀብት እንደላኩላቸውና ተከታትለው እንዲያስጨርሱ ይነገራቸዋል። ሆኖም ግን በቦታው ሲሄዱ ማህደራቸው እንዳልመጣ ይገለጽላቸዋል። በ8/12/2011 ዓ.ም እንደመጣ ገልፀው በዚህ መነሻ ሲፈለግ ከሌሎች ለተመሳሳይ ችግር ተጋላጭ ከሆኑ 24 ሠዎች ጋር ማስረጃቸው አብሮ ይገኛል። ችግራቸው ታይቶ ውሳኔ እንደሚያገኙ አንድ እርምጃ እንደተራመዱ ቢያስቡም ዳሩ ግን ጡረታው እንዴት ይሠራ? የሚለው ደግሞ ሌላ ጥያቄ ሆኖ ይቀርባል። በዚህም ቀድሞ የእርሳቸው ደመወዝ 200 የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ማደጉ ይገለጽላቸዋል። እንደ ደረጃው ታይቶ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ ቢወሰንላቸውም ‹‹አይሰጥም›› በሚል ተወስኖባቸዋል። ‹‹ሐኪም የወሰነው እንዲፈፀም ቢሆንም ሙያዊ ዕውቀት የሌለው አካል በሕክምና የተረጋገጠን ሰነድ አልቀበልም የሚል ከሆነ ታዲያ ሆስፒታሉስ ሆነ የሕክምና ባለሙያዎቹ ስለምን አስፈለጉ ?›› ሲሉም ይጠይቃሉ።
መንግስት ያደረገውን ጥሪ ተቀብለው ለአገራቸው ዳር ድንበር መከበር ቢቆሙም ‹‹የችግሩ ቀን ሲያልፍ አገልግሎቱ እንዳለፈበት ዕቃ መጣሌ ያሳዝነኛል። እኔ የተለየ እንድጉላላ የተደረገበት ምክንያቱስ ምንድን ነው? መብቴ የታፈነበት ያላወኩት ጥፋቴስ? ኢትዮጵያዊ አይደለሁምን? ወይስ ሌላ ዜጋ ነኝ? የእኔ ደም ውሃ ሆኖስ ይሆን ደሜን የሚተካ ካሳ ያላገኘሁት?›› ሲሉም በሁኔታው ምን ያክል ስነልቦናቸው እንደተጎዳ ይገልፃሉ። የሕክምና ባለሙያዎች ያረጋገጡትን ግለሰቦች ተፈፃሚ እንዳይሆን ማገዳቸው ተገቢነት የጎደለው ተግባር ነውም ባይ ናቸው።
‹‹በውጊያ ላይ ባጋጠመኝ ጉዳት ለወታደራዊ አገልግሎት ብቁ አይደለህም ተብዬ ከሠራዊቱ በቦርድ ውሳኔ ስሰናበት ጡረታ መብቴ እንዲከበርልኝ ቢወሰንም ለማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ባለመላኩ ግን ለሁለት አስርት ዓመታት ለእንግልት ተዳርጌያለሁ። በውሳኔው ክፍያውን በምኖርበት ምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ እንዳገኝ ቢወሰንም ተፈፃሚ ባለመሆኑ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር ጽሕፈት ቤት ሳይቀር ለአገር መከላከያ ሚኒስቴር ሌሎች ተመሳሳይ ችግሮች እንዳሉ ጠቅሶ ጠይቆ ነበር። ሆኖም ምንም ዓይነት ምላሽ ሳላገኝ ቆይቻለሁ።›› በማለት የሚመለከተው አካል ጉዳያቸውን እንዲመለከትላቸው ይጠይቃሉ።
ዘላቂ ጡረታ እንዲያገኙ በአካባቢያቸው የማህበራዊ ዋስትና እንዲሰጥ በማለት ቢወሰንም መብታቸው ተነፍጎ እየተጉላሉ መሆናቸውን በመግለጽ፤ በዚህ ሳቢያ የሕክምና እርዳታ እንኳ እንደማያገኙ ይናገራሉ። እንደ ማንኛውም ወታደር ጥቅማ ጥቅማቸው ሊከበር እንደሚገባና ጤነኛ ናቸው ከተባለም ወደ ሥራ መመለስ እንዳለባቸው ያነሳሉ። ለአገር የደሙ መሆናቸውን በማንሳትም በተነፈጉት መብታቸው ሳቢያ ችግራቸው ተባብሶ የአገር ሸክም ከመሆናቸው በፊት አስፈላጊው እገዛ እንዲደረግላቸው፤ ለዚህም መከላከያ ሚኒስቴር ያሉበትን ሁኔታ እንዲረዳና መፍትሔ እንዲሰጣቸውም ይጠይቃሉ።
በእጃቸው የሚገኙ ሰነዶች
ወታደር አያልነህ ቅሬታቸውን በተለያዩ ወቅቶች በጽሁፍ ማመልከቻ ማስገባታቸውን የሚገልጹ ደብዳቤዎች አሳይተውናል። ከዚህ ውጪም የአገር መከላከያ ሚኒስቴር የምድር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ በቀን 4/03/1993 ዓ.ም ለማህበራዊ ዋስትና ባለሥልጣን የላከው ሰነድ በእጃቸው ከሚገኙ ማስረጃዎች ውስጥ አንዱ ሆኖ ተመልክተነዋል። ሰነዱ በሚኒስቴሩ ከታቀፉት የተለያዩ ኃይሎች ውስጥ በማገልገል ላይ እያሉ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው አባላት የጡረታ አበል መጠየቂያ ፎርም እንደሆነ ያሳያል። በዚህም መለያ ቁጥር 05032691 መሆኑና የነበሩበት ኃይል ወይንም ክፍል ታጠቅ ማገገሚያ ማዕከል እንደነበር ያመለክታል። የቅጥር ዘመናቸው የካቲት 1 ቀን 1991 ዓ.ም ሲሆን፤ የሚከፈላቸው ደመወዝ 220 ብር ሆኖ የጡረታ አበል የተወሰነበት ምክንያት ሕመም ተብሎ ሰፍሯል። ከታኅሳስ 1 ቀን 1993 ዓ.ም ጀምሮ የጡረታ አበሉ ተወስኖ ለባለመብት እንዲሰጥም ማሳሰቡ በደብዳቤው ይታያል።
በኢፌ.ዴ.ሪ የምድር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ በቁጥር መ/ፋ.8.3/ሐ2/25077/7/93 በቀን 26/07/1993 ዓ.ም ለምድር ኃይል ሎጅስቲክስ ዘርፍ ፋይናንስ መምሪያ የኋላ ቀሪ ደመወዝ ጥያቄ ምላሽን በተመለከተ ጽፎ የላከው ደብዳቤ ነው። በደብዳቤው በመለያ ቁጥር 0503291 ወታደር አያልነህ በታጠቅ ማገገሚያ ማዕከል ሕክምናቸውን በመከታተል ላይ እንደነበሩ ያስቀምጣል። የሕክምና ቆይታውን አጠናቅቀው የቦርድ ውሳኔ አግኝተው የተሰናበቱ አንደሆኑና ግንቦት ወር 1991 ዓ.ም የኋላ ቀሪ ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው በጠቅላይ መምሪያው በኩል ተጣርቶ ለፋይናንስ መምሪያው ምላሽ እንዲሰጥ መጋቢት 20/07/93 በደብዳቤ ቁጥር መኃ5/ሐ2/ተ/19/790 እንደፃፈላቸው ያስታውሳል። ሆኖም ግን አባሉ የኋላ ቀሪ ደመወዝ ለማጣራት በተደረገው ሙከራ የኋላ ቀሪ ደመወዝ ተመላሽ ሥም ዝርዝር ሊገኝ ባለመቻሉ ወደ ፋይናንስ መምሪያው የላኩት መሆኑንና ከተመላሽ ሰነድ ጋር ተመርምሮ እንዲከፈላቸው ያሳስባል።
የኢፌዴ.ሪ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ለሚኒስቴሩ የሠው ሀብት አመራር ዋና መምሪያ ጽሕፈት ቤት በቁጥር ዕንባ/ዘ9-አአ/1345/1 መጋቢት 2005 ዓ.ም የወታሩን አቤቱታ አስመልክቶ የላከው ደብዳቤ ከሰነዶቻቸው መካከል ይታያል። በደብዳቤው እንደሰፈረው፤ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በአዋጅ ቁጥር 211/92 በተሰጠው ሥልጣንና ተግባር መሠረት ዜጎች
እንደተፈፀመባቸው የሚያቀርቡትን አስተዳደራዊ በደሎች ተቀብሎ በመመርመር ተገቢውን የመፍትሔ ሃሳብ እንደሚያቀርብ ያትታል። በዚህም ወደ ተቋሙ አቤቱታቸውን ለማሰማት ያቀኑት ወታደር አያልነህ መጋቢት 8 ቀን 1991 ዓ.ም በባድመ ግንባር ውጊያ ላይ እያሉ በደረሰባቸው የአካል ጉዳት መሠረት ለወታደራዊ አገልግሎት ብቁ እንዳልሆኑ ተገልፆ ከሠራዊቱ በቦርድ ውሳኔ በ09/04/93 ዓ.ም መሰናበታቸውን ያትታል። ይሁን እንጂ ከሠራዊቱ ከተሰናበቱ በኋላ የሙያ ተግባር የምስክር ወረቀት (የክብር ደብዳቤ) እንዳልተሰጣቸው መግለፃቸውንና የደረሰባቸውን ጉዳት አስመልክቶ ለማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ መረጃ ስላልተላለፈላቸው በሕጉ አግባብ ሊከፈላቸው ይገባ የነበረው ክፍያ ሳይከፈላቸው መቅረቱን ጠቅሰው ቅሬታ ማቅረባቸውን ያብራራል።
እንደ አመልካቹ አቤቱታ በደረሰባቸው ጉዳት የተነሳ ከሠራዊቱ ከተሰናበቱ በኋላ አንደ ጉዳታቸው መጠን ሊከፈላቸው የሚገባው ክፍያ ወይንም ዘላቂ የጡረታ ክፍያ ለማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ማስረጃ ባለመላኩ የተነሳ ሊከፈላቸው ያልቻለበትን? ለኤጀንሲው ማስረጃዎችን መላክ ያልተቻለበትን? ወይም በሌላ ምክንያት ከሆነ እንዲሁም የሙያ ተግባር የምስክር ወረቀት ያልተሠጠበትን ማስረጃ በማያያዝ ደብዳቤው በደረሳቸው በ10 ቀናት ውስጥ በፅሁፍ ምላሽ እንዲሰጡ ማሳሰቡን ያሳያል።
የምዕራብ ጎጃም አዊ አካባቢ ጽሕፈት ቤት ቋሪት ቅርንጫፍ ለቋሪት ወረዳ አስተዳደር ምክር ቤት በቀን 10/08/2005 ዓ.ም በቁጥር አ.ብ.ቁ.ተ/ቋ/17/257/05 ወታደሩን አስመልክቶ የፃፈው ደብዳቤ ሌላው የተመለከትነው ሰነድ ነው። በደብዳቤው ወታደር አያልነህ የጡረታ ክፍያ በቅርንጫፉ ጽሕፈት ቤት እየተከፈላቸው አለመሆኑን ማረጋገጣቸውን አስፍሯል።
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የርዕሰ መስተዳደር ጽሕፈት ቤት ለክልሉ ማሕበራዊ ዋስትና ባህር ዳር ቅርንጫፍ በቁጥር አብመ03/571/መ/ተ-1 በቀን 22/9/05 ወታደሩን አስመልክቶ የላከው ማስረጃ ተመልክተናል። በዚህም ወታደር አያልነህ ከመከላከያ ሠራዊት በ1993 ዓ.ም በክብር የተሰናበቱ አባል መሆናቸውንና የጡረታ ክፍያ ያልተከፈላቸው ስለሆነ ዘላቂ ጡረታ እንዲሰጣቸው ከምዕራብ ጐጃም ዞን የተሰጣቸውን ማሰረጃ በቁጥር 1956/ጽ/ቤ-18 በቀን 12/9/2005 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ እንደተላከ ያስረዳል። ስለሆነም በቅርንጫፉ በኩል ከመመሪያ አንፃር ታይቶ የወታደሩን የዘለቂ ጡረታና መቋቋሚያ ጥያቄ እንዲመለስላቸው በመግለጽ ለአፈፃፀሙ የሚረዳ የምዕራብ ጐጃም ዞን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ለርዕሰ መስተዳደር ጽሕፈት ቤት የላከውን ማስረጃ አያይዞ መላኩን ደብዳቤው ያሳያል።
በቀን 2/11/2011 ዓ.ም በሚኒስቴሩ የጤና ዋና መምሪያ የጦር ኃይሎች ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕክምና ጉባዔ ቦርድ ቀርበው ውሳኔ ያገኙ የሠራዊት አባላት ወደ ክፍላቸው መመለሻ ፎርም ላይ ለመከላከያ ሠው ሀብት መምሪያ ወታደሩን አስመልክቶ ሞልቶ የላከው መረጃ ሌላው ሰነድ ነው። በፎርሙ ላይ ወታደር አያልነህ በሆስፒታሉ ለሕክምና ቦርድ ቀርበው እንደነበር በመጥቀስ፤ ከጉዳቱ በኋላ ሥጋ በሥጋ ምትና የቆየ የአዕምሮ ችግር በመኖሩ ምክንያት ውሳኔው እንደተሰጠ ተመልክቷል። የአካል ጉዳት መጠኑም 35 መሆኑና ካታጎሪ አራት መሆኑን አብራርቷል።
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት በቁጥር አብክመ 11.8/663/ል-1/2011 በቀን 17/05/2011 ዓ.ም ለአገር መከላከያ ሚኒስቴር የላከው ደብዳቤ ከሰነዶቹ መካከል ይገኛል። ደብዳቤው በክብር የተሰናበቱ ሠራዊት አባላትን በተመለከተ እንደሆነም ያትታል። በተለያየ ጊዜ በክብር የተሰናበቱና የጡረታ ጊዜያቸው የደረሰ የሠራዊት አባላት በክልሉ ውስጥ ከፍተኛ መጉላላት እየደረሰባቸው እንደሆነ ጥያቄ እያቀረቡ እንደሚገኙም ያብራራል። ከእነዚህ መካከል በ1993 ዓ.ም በክብር የተሰናበቱት ወታደር አያልነህ አንዱ እንደሆኑና ግለሰቡ የጡረታ ጥያቄ እያቀረቡ የሚገኙ በመሆናቸው በተቋሙ መፍትሔ እዲሰጣቸው የላኳቸው መሆኑን በማሳወቅ ለሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮችም በምን መልኩ መፍትሔ መስጠት እንደሚቻል ማብራሪያ እንዲሰጥበት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ጽሕፈት ቤት ጠይቋል። መሠል ችግሮች በየደረጃው በስፋት እየቀረቡ የሚገኙ ጥያቄዎች በመሆናቸው ተገቢ ትኩረት እንዲሰጠውም ክልሉ እንዳሳሰበ በደብዳቤው ይነበባል።
አስተዳደሩ
በመከላከያ የሠው ሀብት ጡረታና ስንብት ቡድን ክፍል ኃላፊን በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡን አነጋግረናቸው ነበር። መጀመሪያ ፈቃደኛ ሆነው በጉዳዩ ላይ ምላሻቸውን ሊሰጡን ቢስማሙም ቃላቸውን ሊጠብቁና መረጃውን ሊሰጡን ግን አልቻሉም። ለተወሰኑ ደቂቃዎች በነበረን የሥልክ ምልልስ፤ በጉዳዩ ላይ ምላሽ መስጠት እንደሚቸግራቸው ጠቅሰው ነበር። ግለሰቡ ከሠራዊቱ ከተሰናበቱ ቆየት ያሉ መሆኑን በመግለጽም፤ ተመልሰው ቦርድ መጠየቅ እንደማይችሉ ነበር የነገሩን። በመሀል የነበረን ቆይታ የስልክ ቆይታ ተቋርጦ ነበር። ጋዜጣው ለሕትመት መላኪያ ሰዓቱ ሲደርስ ኃላፊው ኮሎኔል ስልክ ደውለው በቀጣዩ ቀን የተሟላ ምላሽ ሊሰጡን ቃል የገቡ ሲሆን፤ ዝግጅት ክፍሉም የተቋሙን ምላሽ በመስከረም 14 ዕትሙ ይዞ እንደሚቀርብ ከወዲሁ እናሳውቃለን።
አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 7/2012
ፍዮሪ ተወልደ