
አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያ ብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩትን አቅም መገንባት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ሥራ መሆኑን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አስታወቁ፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር መለሰ ማርዮ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት፣ ተቋሙ
ለአገሪቱ ብዝሀ ህይወት መጠበቅ ያለው ከፍተኛ ሚና ታይቶ አቅሙ ሊገነባና ትኩረት ሊያገኝ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ ተቋሙ በቁጥርም በእውቀትም በሥራ ልምዳቸውም የተሻሉ ተመራማሪዎች ያሉት ቢሆንም ቁጥራቸው ግን ከዚህ በላይ ሊሆን ይገባል። ይህ ሲደረግም ደግሞ ላብራቶሪዎች መጠናከር አለባቸው ብለዋል። ‹‹በእርግጥ በአሁኑ ጊዜ 187 ሚሊዮን ብር ተፈቅዶ በግቢው ውስጥ ሁለት ህንጻዎችን በማሰራት ላይ ናቸው›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህ የመንግሥት ድጋፍ የሚያበረታታ መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይ ብዝሀ ህይወት ምን ማለት ነው? የሚለውን ጉዳይ በህብረተሰቡ
ውስጥ የማስረጽ ሥራ ለመስራት የሚያስችል አቅም እንዲገኝ ትኩረት መሰጠት እንዳለበትም ገልፀዋል።
በሌላ በኩልም መንግሥት ለብዝሀ ህይወት ሀብት ትኩረት ሊሰጥና አንዳንድ ጊዜ ስለጉዳዩ ባለመረዳትም የብዝሀ ህይወት ሀብትን በሚጎዳ መልኩ የሚካሄዱ የልማት ሥራዎች ሊታሰብባቸው እንደሚገባ አመልክተዋል።
“ብዝሀ ህይወት በሚፈለገው ልክ ይጠበቅ ካልን በክልል፣ በወረዳ እስከ ቀበሌ ድረስ ግንዛቤውን ማስፋት እንዲሁም ራሱን ችሎ ጠንካራ ሆኖ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ማድረግና መዋቅሩንም በደንብ ማሻሻል ያስፈልጋል” ብለዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 7/2012
እፀገነት አክሊሉ