
- ለግንባታው ከ60 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ተደርጓል
አዲስ አበባ፡- የባህርዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ የመጀመሪያው የግንባታ ምእራፍ ተጠናቆ በመስከረም ወር መጨረሻ ሥራ እንደሚጀምር የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለፀ።
የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አማረ አስገዶም በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ የፓርኩ የመጀመሪያው ምእራፍ ግንባታ በ75 ሄክታር መሬት ላይ በውሉ መሰረት በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል። በዚሁ ምእራፍ የተገነቡት የፋብሪካ ሼዶችም ስምንት ሲሆኑ፣ በመጀመሪያው ዙር ለአራት ሺ በሁለተኛው ዙር ደግሞ ለስምንት ሺ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
እንደ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ፤ በመጀመሪያው ምእራፍ የፓርኩ ግንባታ የሚያስፈልገው የኃይል መጠን ስምንት ሜጋ ዋት በመሆኑ በኃይል አቅርቦቱ ዙሪያ ጥናት ተሰርቶ ተጠናቋል። የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰጪ አካሉም የኤሌክትሪክ ምሰሶ ተከላዎችን ጀምሯል። በዚህ ወር መጨረሻም ለፓርኩ የሚያስፈልገው የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ይቀርባል ተብሎ ይታሰባል።
‹‹በቴሌኮም በኩል በፓርኩ ውስጥ የሚታዩ ችግሮች የሉም›› ያሉት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ ለዳታ ማእከል የሚረዱ እቃዎች ከውጪ እስኪገቡ እየተጠበቀ መሆኑን ገልፀዋል። የውሃ አቅርቦትን በሚመለከት በተለይ ከውሃ ጥራት ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ ችግሮችን ለመፍታት ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ባለስልጣን ጋር በመሆን የውሃ ማጣሪያ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኝ መሆኑንም ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው አመልክተዋል።
ምክትል ሥራ አስፈፃሚው እንዳሉት፤ፓርኩ እንደ ሌሎቹ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በተናጠል ለባለሃብቶች የሚሰጥ ባለመሆኑ ለአውሮፓና አሜሪካ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶችን የሚልክ አንድ የሆንግ ኮንግ ኩባንያ ሙሉ በሙሉ ፓርኩን ለመረከብ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ከሚሽንና ከፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር የጋራ መግባቢያ ሰነድ ፈርሟል።
ኩባንያው በቅርቡም በሼዶቹ ውስጥ ስልጠና ዎችን መስጠት ይጀምራል። ኩባንያው ግዙፍ ከመሆኑ አኳያና ተጨማሪ ሼዶችን የሚፈልግ በመሆኑ ማስፋፊያዎችን በራሱ ያከናውናል።
ፓርኩን ገንብቶ ለማጠናቀቅም ከ60 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጪ መደረጉን የገለፁት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ የፓርኩን ሁለተኛ ምእራፍ ግንባታ በ75 ሄክታር መሬት ላይ ለማከናወን ከባለሃብቶች ጋር ውይይት እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።
የባህርዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ CCECC በተሰኘው የቻይና የኮንስትራክሽን ኩባንያ የተገነባ ሲሆን፣ ግንባታውን ለማከናወን ዘጠኝ ወራት ፍጅቷል። ግንባታው በዚህ ወር መጨረሻ ሲጠናቀቅም በሼዶቹ ውስጥ የሚገባው ኩባንያ አጠቃላይ የቴክኒክ፣ አስተዳደርና ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ያለውን ልምድ በማካፈል ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን መስከረም 6/2012
አስናቀ ፀጋዬ