ተማር ልጄ——ተማር ልጄ
ወገን ዘመድ የለኝ ሀብት የለኝም ከጄ፤
ስማኝ ልጄ——– ሌቱ ፀሃይ ነው፤
ላልተማረ ሰው ግን ቀኑ ጨለማ ነው!———-
እነዚህ ስንኞች በአንድ ወቅት በአገራችን አንጋፋ የሙዚቃ ሰው በአለማየሁ እሸቴ የተቀነቀኑ ናቸው። በነዚህ ስንኞች ውስጥ ደግሞ በርካታ ቁምነገሮች አሉ። በአንድ በኩል የሀብትና የብርሃን ምንጩ ትምህርት መሆኑን የሚገልፅ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ አለመማር የጭለማ ጉዞ መሆኑን ያስረዳናል።
አዎ! ለአንድ አገር እድገት መሰረታዊ ከሚባሉ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ትምህርት ነው። አሁን ለደረስንበት የስልጣኔ ዘመን ዋነኛው መሰረትም ትምህርት መሆኑ እሙን ነው። የአገራችን የዘመናዊ ትምህርት ታሪካዊ ዳራ የሚጀምረው በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ሲሆን ተደራሽቱ ግን እስከቅርብ ጊዜ ድረስ አነስተኛ ነበር።
ዘመናዊ ትምህርት በመጠኑ በተስፋፋበት የአፄ ኃይለስላሴ ዘመንም ቢሆን ትምህርቱ የሚሰጠው ለተመረጡ የመኳንንትና የባላባት ልጆች በመሆኑ ለብዙኃኑ ድሃ ማህበረሰብ የተፈቀደ አልነበረም። ቢፈቀድም ብዙም እንዲገፉበት አይፈለግም ነበር።
በአንፃራዊነት ትምህርትን ተደራሽ ከማድረግ አንጻር የደርግ መንግስት ቀደም ሲል ከነበሩት ስርዓቶች የተሻለ መንገድ ተጉዟል። በተለይ ሁሉም ዜጋ ከመሃይምነት ተላቆ የተሻለ ግንዛቤ እንዲያገኝ በመሰረተ ትምህርት ላይ የተደረገው ርብርብ በርካታ ዜጎችን ከመሃይምነት ያላቀቀ ነበር።
ያም ሆኖ ግን በመላው አገሪቱ የትምህርት ተቋማት ባለመስፋፋታቸውና በዘርፉም በቂ መምህራን ባለመኖራቸው የተማረ የሰው ሃይል ለማፍራት የተሰራው ስራ የሚፈለገውን ያህል መሆን ሳይችል ቀርቷል።
በአንጻሩ ባለፉት 28 አመታት በትምህርት ዘርፉ የተገኘው ለውጥ ከፍተኛ እመርታ የታየበት ነው። በተለይ የትምህርት ተደራሽነትን ከማዳረስ አንጻር ሰፊ ጥረት የተደረገበትና ስኬትም የተመዘገበበት ነበር። ለምሳሌ ከአጠቃላይ ትምህርት አንጻር ከ24 አመታት በፊት በአገራችን የነበሩት 4 ሺ የመጀመሪያ ደረጃና 278 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብቻ ሲሆኑ የተማሪዎች ቁጥርም ከ2 ሚሊዮን ያልበለጠ ነበር።
በአሁኑ ወቅት ግን ከ39 ሺ በላይ የመጀመሪያ ደረጃ እና 3300 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ። የተማሪዎች ቁጥርም ከ28 ሚሊዮን በላይ ደርሷል። ይህ ቁጥር ከአብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት አጠቃላይ የህዝብ ቁጥር የላቀ ነው። 16 የነበሩት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ቁጥርም 1546 የደረሰ ሲሆን፤ ሁለት የነበሩት የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችም 46 ደርሰዋል። ተጨማሪ 178 የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም በስራ ላይ ይገኛሉ።
ይሁን እንጂ የትምህርት ተቋማትና የተማሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ቁጥር ቢያድግም ከትምህርት ጥራት አንጻር ከፍተኛ ተግዳሮት እንዳለ መገንዘብ ተገቢ ነው። በዚህ የተነሳ በአሁኑ ወቅት የትምህርት ጥራቱ ከፍተኛ አደጋ ውስጥ መውደቁ ይነገራል። ይህንን ችግር ለማስተካከልም መንግስት የትምህርት ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ በዘንድሮ አመት ወደ ስራ ለመግባት ዝግጅቱን አጠናቋል።
ይህ የትምህርት ፍኖተካርታ በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆንና የወደቅንበት የትምህርት ጥራት ችግርም ተስተካክሎ የአገራችን የትምህርት አሰጣጥ ደረጃውን የጠበቀና ብቁ ዜጎች የሚፈሩበት እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል።
በተለይ ተማሪዎች መማር ከምንም በላይ ዋነኛ ተግባራቸው መሆኑን መረዳትና ለዚህ ስኬት መስራት ይኖርባቸዋል። የአገር ሁለንተናዊ እድገት ከሚለካባቸው መንገዶችም አንዱ በትምህርት በመሆኑ በዚህ ረገድ ተማሪዎች በየትኛውም ዓለም ላይ ተወዳዳሪና አሸናፊ ሆኖ ለመገኘትና ራሳቸውንም ሆነ አገራቸውን ለመጥቀም ዛሬን በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል።
ለትምህርት ዘርፉ ተገቢውን ትኩረት ያልሰጠ አገር ለማደግ የሚኖረው ተስፋ የመነመነ ነው። በተለይ አሁን በደረስንበት የቴክኖሎጂ ዘመን ዓለም ወደአንድ መንደርነት የተለወጠችበት ሁኔታ እየተፈጠረ በመሆኑ ውድድሩ ከመላው ዓለም ጋር መሆኑን መረዳትና ለዚያ የሚያበቃ እውቀትና ክህሎት ለመጨበጥ ጥረት ማድረግ ከእያንዳንዱ ዜጋ ይጠበቃል።
እነሆ አሁን የምንገኝበት የመስከረም ወር ደግሞ ተማሪዎች ከእረፍት ተመልሰው ትምህርታቸውን “ሀ” ብለው የሚጀምሩበት ወር ነው። በመሆኑም ስለትምህርት ጥራት የምንጨነቅ ከሆነ ከዛሬ ጀምሮ አእምሮአችንን ለትምህርት መስጠትና ትኩረት ሰጥቶ መከታተል ተገቢ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በ2012 የአዲስ አመት ዋዜማ ልዩ መርሃግብር ላይ እንደገለፁት የ2012 አዲስ አመት ማለት 365 ገጾች እንዳሉት ያልተፃፈ መፅሃፍ ይቆጠራል። በዚህ መፅሃፍ የተሻለ ቁምነገር ሰርቶ ለማለፍ ደግሞ እያንዳንዷን ቀን መጠቀም ተገቢ ነው። ከነዚህ ገጾች መካከል አንድ ገጽ እንኳን ቢጎድል ታሪኩ ሙሉ ሊሆን አይችልም። ስለዚህ የተሟላ ታሪክ እንዲኖረን ከዛሬ ጀምሮ እያንዳንዷን ቀን እንስራባት መልዕክታችን ነው!
አዲስ ዘመን መስከረም 5/2012