
ሁሉም የመንግስት ትምህርት ቤቶች ዕድሳታቸውን ጨርሰው ተውበውና አምረው ተማሪዎቻቸውን ለመቀበል ዝግጁ ሁነዋል፡፡ ተማሪዎች የደንብ ልብስ፣ ደብተር፣እርሳስና እስክሪብቶ በነጻ እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡ ተማሪዎችም በአዲሱ ዓመት ትምህርታቸውን ለመጀመር በጉጉት እየተጠባበቁ ነው፡፡ ወላጆችም የከተማ አስተዳደሩ ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁሶችንና የደንብ ልብስ በነጻ መስጠቱ የኑሮ ጫናውን እንደተጋራላቸው ደስታቸውን ይገልፃሉ።
ተማሪ ፍቅርተ ቦጃ በዳግማዊ ምኒልክ መሰናዶ ትምህርት ቤት 12ኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ የከተማ አስተዳደሩ የደንብ ልብስ፣ ሁለት ደርዘን ደብተር፣አንድ ደርዘን እስክሪብቶ፣እርሳስና መቅረጫ ለተማሪዎች በነጻ መስጠቱ ታይቶ የማይታወቅና ጥሩ ነገር ነው ትላለች፡ ፡ይህ ዕገዛም ለቤተሰቦቻችንም ሆነ ለእኛ ለተማሪዎች በጣም ደስታ የሚሰጥ ነው ባይ ናት፡፡ ትምህርት ቤቱ ታድሶ ያማረ ህንጻ መሆኑ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በትጋት ለመማር ትልቅ መነሳሳትን ይፈጥራል፡፡ የመማር ማስተማሩ ሂደት የተሻለ ያደርገዋል ስትል አስተያየቷን ሰጥታናለች።
ተማሪ ሄኖክ ደምሴም የተማሪ ፍቅርተን ሃሳብ ይጋራል፡፡ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ታድሰውና ለዕይታ ማራኪ ሆነው ለትምህርት መዘጋጀታቸው በትጋት ትምህርትን ለመከታተል መነቃቃት ይፈጥራሉ የሚል እምነት አለው፡፡
የደንብ ልብስና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁሶች ለተማሪዎች በነጻ መሰጠታቸውም የወላጆቹን ጫና እንደሚያቃልል ነግሮናል፡፡ አሁን ሁሉም ነገር ዝግጁ ነው የሚለው ተማሪ ሄኖክ ከዚህ በኋላ ተግተው የመማር ስራ የተማሪዎች ድርሻ ነው ብሏል።
ወይዘሮ ሙሉ አስማረ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ልጃቸውን የደንብ ልብስ ሊወስዱ ነው በዳግማዊ ምኒልክ መሰናዶ ትምህር ቤት የተገኙት፡፡ ልጃቸው የየካቲት 12 (መነን)ትምህርት ቤት ተማሪ ብትሆንም ትምህርት ቤቱ አዳሪ ትምህርት ቤት እንዲሆን በመንግስት በመወሰኑ ምክንያት የዳግማዊ ምኒልክ ተማሪ ሁና መመዝገቧን ነግረውናል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ከተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ደብተር፣ የደንብ ልብስ፣ እስክሪብቶ ለተማሪዎች በነጻ መስጠቱ ለእኛ ለወላጆች ትልቅ እገዛ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶቹም መታደሳቸው ተማሪዎች በአዲስ መንፈስ እንዲማሩ ያነቃቃል የሚል እምነት አላቸው።
ተማሪዎች በርትተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉና ነገ የተሻለ ደረጃ ደርሰው አገራቸውን እንዲያገለግሉ አደራ አለባቸው ያሉት ወይዘሮ ሙሉ፤ አዲስ ዓመት ለተማሪዎች የብሩህ የትምህርት ዘመን እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል፡፡
አቶ ገበየሁ ታደሰ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ ባለቤታቸው በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት መማሯን አውስተው የሂሳብ ባለሙያ መሆኗን ነግረውናል፡፡ አሁንም ባለቤታቸውን የተሻለ ደረጃ ያደረሰው ትምህርት ቤት ልጃቸውን የተሻለ ደረጃ ያደርሳታል ብለው በማመናቸው ዘንድሮ በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት እንድትመዘገብ እንዳደረጓት ነግረውናል፡፡
የስድስት ልጆች አባት እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ ገበየሁ ሁለት ልጆቻቸው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሲሆኑ፤ ቀሪዎቹ በመንግስት ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን ለመከታተል ተመዝግበዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ለተማሪዎች የደንብ ልብስ፣ እስክሪብቶና ደብተር በነጻ መስጠቱ ለወላጆች ትልቅ እፎይታ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶች መታደሳቸውም ተማሪዎችን ትምህርት ለመቀበል ያነቃቃል፤ ተማሪዎች በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት አምጥተው ቤተሰባቸውና አገራቸውን እንዲጠቅሙ ምኞቴ ነው ብለውናል፡፡››
ከዚህ በፊት የደንብ ልብስም ሆነ ሌሎች የትምህርት ቁሳቁሶችን ማሟላት የሚጠበቀው ከወላጆች ነበር የሚሉት የዳግማዊ ምኒልክ መሰናዶ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ተገኔ መንግስቱ፤ ዘንድሮ ግን በከተማ አስተዳደሩ በኩል የደንብ ልብስና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉና ወላጆች ለምዝገባ ጭምር እንዲከፍሉ አለመደረጉ ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተያይዞ ያላባቸውን ጫና ይቀንሳል ይላሉ፡፡
በትምህርት ቤቱ ለተመዘገቡት ለሁሉም ተማሪዎች አስፈላጊው የትምህርት ቁሳቁሶች እንደሚሰጣቸው ገልጸው፤ እስካሁን 820 ተማሪዎች የተመዘገቡ ቢሆንም የአስረኛ ክፍል ውጤት በቅርቡ ይፋ በመሆኑ የተማሪዎችን ቁጥር እንደሚጨምርና ወደ ትምህርት ቤቱ መጥተው ምዝገባ ለሚያካሂዱ በሙሉ ድጋፍ የሚሰጥ መሆኑን ነግረውናል፡፡
46 የመማሪያ ክፍሎች ታድሰውና ወንበራቸው ተጠግኖ ለትምህርት ዝግጁ መሆናቸውን አመልክተው፤ ትምህርት ቤቶች ታድሰው ጽዱና ማራኪ መሆናቸው ለመማርና ለማስተማር የሚመጡ ተማሪዎችና መምህራን መንፈስ የሚያነቃቃ ይሆናል፡፡በተሻለ መንፈስና መነቃቃትም ትምህርታቸውን እንዲከታተሉና እንዲያስተምሩ ይረዳቸዋል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል፡፡
ተማሪዎች ዓላማ ሰንቀው በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ተግተውና በስነ ምግባር ታንጸው ሊማሩ ይገባል፡፡ በተመሳሳይ መምህራንም ትውልድ የመቅረጽ ከፍተኛ ኃላፊነታቸውን በብቃት ሊወጡ ይገባል፡፡ አዲሱ ዓመት መልካም ውጤት የምናስመዝግብበት እንዲሆን ምኞቴ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ የ488ቱ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ዕድሳት የተጠናቀቀ ሲሆን መስከረም 12 ትምህርት እንደሚጀምሩ ይጠበቃል፡፡ ‹‹ከፍትፍቱ ፊቱ›› እንደሚባለው ያረጁት የመንግስት ትምህርት ቤቶች ታድሰው ለዕይታ ማራኪ ሲሆኑ ተማሪዎችም ሆኑ መምህራን ተደስተውና ጓጉተው ትምህርት ቤት እንዲመጡ እንደሚያደርጋቸው ተማሪዎች ይገልጻሉ፡፡ ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው፤ በአዲስ አበባ በ240 ሚሊዮን ብር ያህል ወጪ ከ450ሺ እስከ 600ሺ ለሚጠጉ ተማሪዎች የደንብ ልብስ በነጻ ይሰጣል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 5/2012
ጌትነት ምህረቴ