የነገው ቀን ትምህርት በመላ ሀገሪቱ የሚከፈትበት ዕለት ነው። ለሁለት ወራት የተለያዩ ጓደኛሞች፣ መምህራንና የትምህርት ማህበረሰቡ በናፍቆት የሚገናኝበት፤ ተማሪዎች ከመምህራኖቻቸውና ከመማሪያ ክፍሎቻቸው ጋር የሚተዋወቁበት ዕለት መሆኑም ቀኑን ልዩ ያደርገዋል።
በዚህ ወቅት የትምህርት ቤቶች ቅጥር ግቢ አረንጓዴ ሳር ለብሰው ፣ በአደይ አበባ ፈክተውና አምረው ይታያሉ። የአረንጓዴው ልምላሜና የአደይ አበባው ቢጫ ቀለም ለተማሪው ዘመኑ ብሩህ እና የተስፋ መሆኑን ያበስራሉ።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ዘንድሮ ተማሪዎቻቸውን ለመቀበል ዝግጅት ያደረጉት ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ነው። ሁሉም የመንግስት ትምህርት ቤቶች ህንፃዎቻቸው ውብ በሆነ ቀለማት አምረው፤ የጥቁር ሰሌዳውና መቀመጫ ወንበሮቻቸው ሁሉ ሳይቀሩ ታድሰውና ተጠግነው ለተማሪዎች እና ለመምህራኑ ምቹ ሆነዋል።
ለትምህርት ቤቶቹ ዕድሳት ብቻ 833 ሚሊየን ብር ወጪ ተደርጓል። እድሳት በተደረገላቸው እና በአጠቃላይ በከተማዋ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከ600ሺ በላይ ተማሪዎችን ለማስተናገድ ዝግጅቱ ተጠናቋል። ይሄም ብቻ አይደለም። ወደ ትምህርት ገበታቸው ለሚያቀኑ ተማሪዎች የከተማ አስተዳደሩ እንደወላጅ እና አሳዳጊ የመማሪያ ደብተር፣ እስክሪቢቶና እርሳስ እንዲሁም የተማሪዎች ደንብ ልብስ (ዩኒፎርም) አዘጋጅቶ ነው የሚጠባበቃቸው።
በዚህ አዲስ የትምህርት ዓመት እንደ ከዚህ ቀደሙ ችግረኛ ተማሪዎች “እኔ ከጓደኛዬ በዚህ መልኩ አነስኩ” የሚሉበት ሳይሆን ሁሉም አዲስ ዩኒፎርም ለብሰው የሚደሰቱበት እንዲሆን የተሟላ ዝግጅት ተደርጓል። ስለዚህ የተማሪዎች ዓላማ መሆን ያለበት ጥሩ ውጤት ለማምጣት ግብ አስቀምጦ መስራት፣ ብሎም ትምህርታቸውን መከታተልና ማጥናት መሆን አለበት ። የለፋና ያጠና ተማሪ ውጤቱ አስደሳች እንደሚሆን ለማንም ግልጽ ነውና።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከቁሳቁስ ድጋፉ እና የትምህርት አካባቢውን ለመማር ማስተማሩ ምቹ ለማድረግ ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎንም ተማሪዎች ምንም ሳይጎድልባቸው ሙሉ ሀሳባቸውን ወደ ትምህርት መልሰው እንዲማሩ በማሰብ ከ300ሺ በላይ ለሚሆኑና የኢኮኖሚ አቅማቸው አነስተኛ ለሆኑ ተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም በማዘጋጀት ላይ ይገኛል።
በዚህም ተማሪዎች ሳይራቡ ሀሳባቸውን ሙሉ ለሙሉ በትምህርታቸው ላይ ሰብሰብ አድርገው እንዲማሩ እና ለጥሩ ውጤት እንዲበቁ ታቅዶ የተከናወነ ነው። ለዚህ ቅንና አመርቂ ስራው የከተማ አስተዳደሩ ሊመሰገን ይገባዋል። የከተማ አስተዳደሩ ያቀደውን ይሄንን በጎ ተግባር ከግብ እንዲደርስም በአይነትና በገንዘብ ድጋፍ ያደረጉ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ጭምር ምስጋና ይገባቸዋል። ምክንያቱም የነገውን ሀገር ተረካቢ ዜጋ ከመሰረቱ በእውቀትና በስነምግባር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ላይ በእውቀት የታነፀ ትውልድ ለመፍጠር በሚሰራው ሰፊ ስራ ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል። ስለዚህ ለሁሉም ምስጋና ይገባቸዋል።
አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተማሪዎችን በትምህርትና በስነምግባር ለመቅረጽና ብቁ ለማድረግ የተዘጋጀ ነው። በዚህ መልክ ተዘጋጅቶ የቀረበውን ፍኖተ ትምህርት በብቃት፣ በታማኝነትና በሃላፊነት ስሜት መወጣት ደግሞ ከእያንዳንዱ መምህራንና የትምህርት ማህበረሰብ የሚጠበቅ ይሆናል ።
ተማሪዎች ወደትምህርት ቤት የሚመጡት የመምህሩን የራሱን ስሜት፣ የፖለቲካ ወይም የሀይማኖት አመለካከት ለመስማትና ለማወቅ ሳይሆን በየደረጃቸው መማርና ማወቅ የሚገባቸውን ዕውቀት ለመገብየት በመሆኑ መምህራን ስርዓተ ትምህርቱ የሚፈቅደውን ብቻ በማስተማር ሙያዊ ኃላፊነታቸውን መወጣትና ትውልድ የመቅረፅ ሀላፊነታቸውን በተግባር ላይ ማዋል ይጠበቅባቸዋል።
ከመምህራን ጎን ለጎንም ወላጆች፣ አሳዳጊዎች ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዴት እና በምን መልኩ እየተከታተሉ ነው? ምን አይነት ስነምግባር አላቸው? ከተማሩት ትምህርት ያገኙት ውጤቱ ምን ይመስላል? የሚለውን በቤት ውስጥ መከታተል ይገባቸዋል። እንዲሁም ከትምህርት ማህበረሰቡ ጋር በመገናኘትም መመካር ያስፈልጋል። ልጆች ትምህርት ቤት ብቻ ስለተላኩ በሚገባው መጠን ተምረዋል ወይም አውቀዋል ብሎ ማሰብ አይገባም።
መምህሩ ብቻ የሚያደርገው ክትትልና ቁጥጥር በቂ ነው ብሎ መቀመጥም የዋህነት ነው። ስለዚህ መምህሩ እና ትምህርት ቤቶች ከሚያደርጉት ክትትል ያልተናነሰ የወላጆች እና የአሳዳጊዎች ቁጥጥር ወሳኝነት አለው። ተማሪዎች አልባሌ ቦታ ላይ እንዳይውሉ፣ ወደ ሱስ አምጪ ነገሮች እንዳይሳቡ እንዲሁም በረብሻና ሁከት ውስጥ እንዳይሳተፉ መምከርና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም መገሰጽ ይገባል።
መንግስት አቅም በፈቀደ መጠን ለተማሪዎች ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ በላበት በዚህ ወቅት በሁሉም በኩል እኩል ማሰብ፣ መረዳዳት እና መቻቻል ሲኖር ነው ነገ ሀገር ተረካቢ የሆነውን መልካም ትውልድ መፍጠር የሚቻለው። ከሁሉም በላይ ግን ተማሪዎች ሙሉ ጊዜያቸውን ለትምህርቱ በመስጠትና በትርፍ ጊዜያቸው ደግሞ ቤተመጽሀፍትን በመጎብኘት ጭምር ውጤታማ ለመሆን መታተር አለባቸው።
የነገው ሀገር ተረካቢ ትውልድ፣ አደራ ተቀባይና አስተላላፊ ትውልድ መሆኑን አርቆ በማሰብም ራሱን ከአልባሌ ነገሮች ቆጥቦ ትምህርቱን መከታተልና ማጥናት ይጠበቅበታል። ለጥሩ ውጤት የሚያበቃውን ግብ አስቀምጦ መስራትንም ከዛሬ መጀመር ይገባዋል ።
አዲስ ዘመን መስከረም 4/2012