
አዲስ አበባ:- በአዲሱ ዓመት በዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊ መማር ማስተማርን እውን ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲዎች የ2011 የትምህርት ዘመንን በአስቸጋሪ ሁኔታ ማሳለፋቸውን ነው ሚኒስትር ዲኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ የተናገሩት።
ተማሪዎች በሐሳብ ልዕልና በመከራከር መተማመን ሲችሉ ከውጭ የሚነሱ ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን ምክንያት በማድረግ ትምህርታቸውን ማስተጓጎል፣ በቡድን መደባደብና መገዳደል አሳዛኝ ክስተት ነበርም ብለዋል።
“በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ታሪክ እንደ 2011 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ብዙ ልጆቻችንን ያጣንበት ዓመት ታይቶ አይታወቅም” ያሉት ፕሮፌሰር አፈወርቅ፤ ከዚህ በመማርም ከሁሉም የክልል አመራሮችና ከዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢዎች ጋር በ2012 የትምህርት ዘመን ሊወሰዱ በሚገቡ ጥንቃቄዎች ላይ ውይይት መደረጉን ገልፀዋል።
በዚህም እያንዳንዱ ወላጅ፣ ተማሪ፣ በየደረጃው ያለ አስተዳደር ለሰላማዊ የመማር ማስተማሩ ሃላፊነት ተጥሎባቸዋል ነው ያሉት።
በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ኪሮስ ጉዑሽ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ለ2012 የትምህርት ዘመን ቅድመ ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ገልፀው፤ የትምርት ጥራት ማስጠበቅ፣ የአገልግሎትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ላይ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።
ለተግባራዊነቱም ከአስተዳደርና መምህራን ጋር በጋራ ዕቅድ ላይ ውይይት በማድረግ ሁሉም ሃላፊነታቸውን እንዲወስዱ ይደረጋል ነው ያሉት።
በዩኒቨርሲቲያቸው ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንዲኖር ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር ውይይት አድርገናል ያሉት ደግሞ የኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና ናቸው።
ዩኒቨርሲቲው በ2012 የትምህር ዘመን ሰላማዊ የመማር መስተማር ሂደት እንዲኖር እያንዳንዱ የትምህርት ክፍል፣ መምህራን እና የአስተዳደር ሠራተኞች የድርሻቸውን ሃላፊነት ወስደው የሚሰሩበት ዕቅድ ማዘጋጀቱን ገልፀዋል።
“ተማሪዎች የሰላማቸው አምባሳደርና ዘብ መሆን አለባቸው” ያሉት ዶክተር ብርሃነመስቀል፤ ንብረት እንዳይወድም፣ ትምህርት እንዳይቋረጥና የተማሪ ህይወት እንዳያልፍ ከትምህርት ክፍል እስከ መኝታ ክፍል አደረጃጀት እንደሚዘረጋ አስረድተዋል።
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ተወካይ ረዳት ፕሮፌሰር ካሳሁን አቤ፤ በዩኒቨርሲቲው የ2011 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሂደት በሰላም መጠናቀቁን አስታውሰዋል ።
ለዚህም በዋናነት ዩኒቨርሲቲው የአገልግሎት መጓደል እንዳይኖር ክትትል የሚያደርግና ውጫዊው ፖለቲካዊ ጫና በዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሂደት ሥጋት እንዳይፈጥር የሚከታተል ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ እንደነበር ገልፀዋል።
የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ዲጂታል መታወቂያ መጠቀማቸው፤ ውጤት የተበላሸባቸው ተማሪዎችም ችግር እንዳይፈጥሩ ጥንቃቄ መደረጉ የዩኒቨርሲቲው ሰላም እንዲጠበቅ ተጨማሪ አቅም እንደነበረው አታውሰዋል።
የተማሪዎች ህብረት ጠንካራና ጉዳያቸውን በትኩረት መከታተሉ ለሰላማዊ መማር ማስተማሩ ሚና እንደነበረው አንስተው፥ እነዚህ ተግባራት በተያዘው ዓመትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት።
በ2011 ትምህርት ዘመን በአክሱም ዩኒቨርሲቲ በተቀሰቀሰው ግጭት ትምህርት መቋረጡና ተማሪዎች መጎዳታቸውን ያስታወሱት ዶክተር ኪሮስ፤ ዘንድሮ ችግሩ ዳግም እንዳይከሰት ከማህበረሰቡ፣ ከአካባቢው አስተዳደር እና ከተማሪዎች ጋር በመተባበር ይሰራል ነው ያሉት።
ሀገርን የሚቀይረው ትምህርት በመሆኑ ተማሪዎች ሙሉ ጊዜያቸውን ትምህርታቸውን በመከታተል፤ ከግጭትና ንብረት ማውደም እንዲቆጠቡ ዝግጅት ተደርጓል ያሉት ፕሮፌሰር አፈወርቅ፤ ተማሪዎች ለሰላማቸው ሃላፊነት የሚወስዱበት፤ የተማሪዎች ቤተሰብ በየደረጃው ካሉ የአስተዳደር አካላት ጋር ውል እንደሚገቡም አስታውቀዋል።
በዚህም በ2012 የትምህርት ዘመን ዩኒቨርሲቲዎች የደህንነትና የፀጥታ ሥጋት የሚያስወግዱበትና የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲሟላ በክረምቱ ወራት ዝግጅት መደረጉን ነው ሚኒስትር ዴኤታው መግለፃቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
አዲስ ዘመን መስከረም 4/2012