
-ለውሃ ቆጣሪ 14 ሚሊዮን ብር ከፍሏል
-በዓመት 2ነጥብ5 ሚሊዮን ደንበኞችን አስተናግዷል
አዲስ አበባ፡- የፍል ውሃ አገልግሎት ድርጅት ደንበኞች በዓመት ከሚጠቀሙት 262 ሚሊዮን 800ሺ ሊትር ውሃ በቴክኖሎጂ እጥረት የተነሳ ከአንድ ጊዜ እጥበት ሌላ ጥቅም ላይ ማዋል አልተቻለም። ከከርሠ ምድር የሚወጣውን ፍልውሃ ለማባረዝ ከአዲስ አበባና ውሃ ፍሳሽ ባለሥልጣን በመስመር ለሚጠቀመው ውሃ በዓመት 14 ሚሊዮን ብር ለመክፈል ተገዷል።
የፍልውሃ አገልግሎት ድርጅት የውሃ አቅርቦት ስርጭት ኢንጅነሪንግ ዳይሬክተር ኢንጅነር ጌትነት ዘነበ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደገለፁት፤ የፍል ውሃ አገልግሎት ድርጅት መታጠቢያ ክፍሎቹን ባለፉት ሦስት ዓመታት ወደ 400 ክፍሎች ማሳደጉን ጠቁመዋል።
በእነዚህም ክፍሎች ከፍተኛ የሆነ የውሃ ፍጆታ መኖሩን አስገንዝበዋል። አንድ ሰው በአማካይ 120 ሊትር እንደሚጠቀምና በቀን እስከ 6000 ደንበኞች እንደሚስተናገዱ አብራርተዋል። ለዚሁ አገልግሎት በዓመት 262 ሚሊዮን 800ሺ ሊትር ውሃ ጥቅም ላይ ይውላል። ይህ ውሃም ከአንድ ጊዜ በላይ አገልግሎት እንደማይሰጥና በቀጥታ በቆሻሻ መልኩ የሚወገድ ነው።
በሌላ መንገድ ደግሞ ከከርሠ ምድር የሚወጣው ፍልውሃ ከፍተኛ ሙቀት ያለው በመሆኑ ውሃውን ለማባረዝ ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ በየዓመቱ 2ሺ173 ሜትር ኪዩብ ውሃ ይጠቀማል፤ ለዚህም 14 ሚሊዮን ብር ድረስ ዓመታዊ የቆጣሪ ክፍያ ለመፈፀም ተገዷል። ይሁንና በአሁኑ ወቅት ከተጀመረው ሸገርን ማስዋብ ከሚለው ፕሮጀክት ጋር ይህን ውሃ መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል ንድፈ ሃሳቦች መኖራቸውንና በጥናት ላይ የተመሰረተ ሥራ መኖሩን አስገንዝበዋል።
በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ የሚፈለገውን ያህል ውሃ ለማቅረብ አለመቻሉን ከማሳወቁም በተጨማሪ በከተማዋ ካለው የውሃ እጥረት አኳያ ሌላ ዘዴ መጠቀም መጀመሩንም አብራርተዋል። ድርጅቱ በቀን ከሚጠቀመው 2ሺ173 ሜትር ኪዩብ ውሃ ውስጥ 30 ከመቶ መቀነሱንና ይህንንም ተቋሙ በራሱ ግቢ ውስጥ በቆፈራቸው ጥልቅ የጉድጓድ ውሃ መተካት እንደቻለ አስረድተዋል።
ኢንጂነር ጌትነት እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት የፍል ውሃ አገልግሎት ድርጅት ከደንበኞች ፍላጎት አኳያ በቂ አገልግሎት እየሠጠ ባለመሆኑ ሌላ መላ ለመዘየድ ታስቧል። በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የፍል ውሃ ሥፍራዎችን ለማስተዳደርና ለማልማት ለከተማ አስተዳደሩ ጥያቄ መቅረቡን ገልፀዋል።
ለአብነትም በጎሮ አካባቢ የፍል ውሃ መገኘቱን ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅት በግለሰቦች እጅ ከመሆኑም በተጨማሪ በበቂ ደረጃ እየለማ አይደለም። ሥፍራውን በማልማት የአካባቢውን ነዋሪዎች ቀዳሚ ተጠቃሚ ማድረግና ለሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎችም እንዲጠቀሙበት ጥናት ተካሂዶ ከከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ እየተጠበቀ ነው።
የፍልውሃ አገልግሎት ድርጅት የገበያ ጥናት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ማሻሻያ ዳይሬክተር አቶ ከበደ ወርቁ በበኩላቸው፤ ድርጅቱ ከሰኞ እስከ ሐሙስ 6ሺ125 ከአርብ እስከ እሁድ ባለው ጊዜ ደግሞ 7000 ደንበኞችን እያስተናገደ ይገኛል።
በዚህም መሠረት በ2011 በጀት ዓመት በቀዝቃዛ ውሃ አቅርቦት ከፍተኛ ችግር የነበረ ቢሆንም በተቋሙ የቴክኒክ ዲፓርትመንት የተጠናከሩ ሥራዎች በመከናወናቸው ችግሮችን ተቋቁሞ 2ነጥብ5 ሚሊዮን ደንበኞችን አስተናግዶ በዓመቱም 153 ሚሊዮን ብር አግኝቷል። በ2012 በጀት ደግሞ 3ነጥብ2 ሚሊዮን ዜጎችን ለማስተናገድ ወጥኗል። ድርጅቱ በቀጣይ ‹‹ስፓ ቪሌጅ›› ለመገንባት ማቀዱንም አስረድተዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ ከደንበኞች ፍላጎት አኳያ ድርጅቱ እየሰጠ ያለው አገልግሎት በቂ አይደለም። በተለይም ለማስፋፊያ የሚሆን ክፍት ቦታ ባለመኖሩ ደንበኞችን በተፈለገው መጠን ማስተናገድ አልተቻለም።
ከ56 ዓመት በፊት በአንድ የእስራኤል ካምፓኒ የተገነቡት በርካታ መታጠቢያ ክፍሎች ቅርስ በመሆናቸው ማፈረስ የማይቻል ሆኗል። በአሁኑ ወቅት ያለው ቦታ ውስን በመሆኑ ማስፋፊያ ቦታ እንደሚያስፈልገው አሳስበዋል።
ድርጅቱ በአዲሱ በጀት ዓመት አዳዲስ አሠራሮችን ቀይሶ እንደሚንቀሳቀስ በተለያዩ አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ማሻሻያ በማድረግ ደንበኞችን ለመሳብ ማቀዱን አቶ ከበደ ጠቁመዋል።
የፍልውሃ አገልግሎት ድርጅት ከ56 ዓመት በፊት በአፄ ኃለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ግንባታው ተከናውኖ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ልማት ድርጅት ሆኖ የተመዘገበ መሆኑ ይታወቃል።
አዲስ ዘመን መስከረም 3/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር