መስከረም የሚለው ቃል በኪነ ጥበብ ሰዎች ዘንድ ተደጋግሞ የሚጠራ ወር ነው። በእርግጥ ስነ ቃሎቻችንም ለመስከረም ሳያዳሉ አይቀሩም። ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም፣ መስከረም በአበባው ሰርግ በጭብጨባው፣ በመስከረም ጤፍ እርሻ ዝናብ ሲያባራ ወደ ዋሻ (የተገላቢጦሽ ለማለት ነው)፣ ያረሰማ ጎበዝ እርፍ የነቀነቀ፣ ወፍጮው እያጓራ መስከረም ዘለቀ (የቃል ግጥም)፣ መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ፣ እንኳን ሰው ዘመዱን ይጠይቃል ባዕዳ (የቃል ግጥም)፣ የመስከረም ዝናብ ካለም ቀንድ ይለያል እና የመሳሰሉ አባባሎችና የቃል ግጥሞች አሉት። የሰው ስም እንኳን ካየን መስከረም የሚባሉ (በብዛት ሴት ቢሆኑም ወንድም አሉ) ብዙ ናቸው። ይሄ ሁሉ የሆነው የአዲስ ዓመት መጀመሪያ ወር መሆኑ ነው። በሌላ በኩል ይሄ ወር የውበት ወር ነው። አበቦች ደምቀው የሚታዩበት ነው። ከያኒያን ደግሞ በአበባ ይመሰጣሉ፤ ይራቀቃሉ። እስኪ ረዘም ያለውን የሠዓሊና ገጣሚ ገብረክርስቶስ ደስታ ‹‹አንተ ነህ መስከረም›› ግጥም እንጋብዛችሁ።
አንተነህ መስከረም
ማለቂያ በሌለው ደማቅ ሰማያዊ ከሩቅ
ያለው ጋራ ተነክሮ ሐምራዊ
በዚያ ላይ ደመናው እንደ ጥጥ ተነድፎ እየተራቀቀ ሲያንጃብብ ተቃቅፎ።
አንተ ነህ መስከረም
የሐምሌን ጨለማ የነሐሴን ዝናብ የሻርከው አንተ ነህ በብርሃን ውበትህ በክረምቱ ወራት ሰማዩን ያስጌጠው የማርያም መቀነት በቀለም ያበደው ጤዛው አርሶታል መሬቱ ላይ ለቆ
በቀይና ብጫ መስኩ ተለቅልቆ
ወንዝና ጅረቱ ድንጋና አፈሩ አገሩ ውብ ሁኗል ሜዳው ሸንተረሩ። እንቁጣጣሽ አንተ ስጦታህ የበዛ
ለሰው መታሰቢያ ውበት የምትገዛ
በሽቱ መአዛክ ለውጠው ዓመቱን
ይታደስ ያረጀው ፍጥረት ሌላ ይሁን
ከምረው ዘመኑን ካበው ባመት አመት
በወሩ ደረጃ ፍጥረት ይጓዝበት።
ፍየሎች ዘለሉ ቅጠል ይበጥሱ ከተሰዱበት ወፎች ይመለሱ
ይልቀሙት እህሉን ይስሩ ቤታቸውን
የደስ ደስ ያሰሙ ንቦች ይራኮቱ
ይንጠራሩ አበቦች ይንቁ ይከፈቱ
አንበሳና ግልገል በመስኩ ይፈንጩ
ከብቶች ሳሩን ይንጩ ሕጻናት ይሩጡ ይሳቁ ይንጫጩ። ዛፎች ይተንፍሱ የነፋሱን ጠረን
ይሰራጭ በቦታው ያውደው አገሩን
አደይ አበባ ነህ የመስቀል ደመራ
ጠረንህ አልባብ ነው አየርህ የጠራ።
ያገር ልብስ አንተ ነሕ ነጭ እንደ በረዶ ሰው የሚያጌጥብህ ጥበብህን ወስዶ
ቡቃያ ነህ እሸት ጓያ የበሰለ
አረንጓዴ ልብስህ በጌጥ የተሳለ
ጥቁር አረንጓዴ ብጫ አረንጓዴ ቀለም! ቀለም! ቀለም!
የሚስተካከልህ የሚያስንቅህ የለም።
ኀዘን የምታርቅ የገነት ምሳሌ ይታደል ወለላህ ጠጁ በብርሌ
ይስከር በደስታ ሕዝቡ ይሳሳቅ
ድምጹ እየተማታ ሙዚቃው ይፍለቅ
እንቁጣጣሽ ብለን እንስጥህ ሰላምታ ይጨብጨብ ለዝናህ
ይጨብጨብ ለራስህ ይጨብጨብ ለመልክህ
አንተ ነህ መስከረም ዘመን የምታድሰ አስጊጠህ በቀለም!
ወደ ዘፈኖች ከሄድን ደግሞ በጣም ብዙ ናቸው። አንዳንዶቹ እንዲያውም ቃሉን ተጠቀሙት እንጂ ለመስከረም ወር ብቻ የሚሆኑ ዘፈኖች አይደሉም፤ ዓመቱን ሙሉ የሚዘፈኑ ናቸው። ለምሳሌ ስለአደይ አበባ ከሆነ ዘፈኑ በብዛት የሚሰማው በአደይ አበባ ወቅት ነው። የመስከረም ወር ግን አደይ አበባ ብቻ ሳይሆን ሌሎች አበቦችም ስለሚፈኩበት አበቦች ሁሉ በመስከረም ይመሰላሉ።
በዘፈናቸው ውስጥ መስከረምን የሚጠሩ ዘፋኞችም ስንፈልግ ጥላሁን ገሠሠን እናገኛለን። በነገራችን ላይ ጥላሁን ገሠሠ በመስከረም ወር የሚታወስበት ሌላም ምክንያት አለ። የተወለደው በዚህ የመስከረም ወር ውስጥ ነው። በክርስትና እምነት ተከታዮች የመስቀል በዓል የሆነው መስከረም 17 የክቡር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ የልደት ቀን ነው። ይህን ተወዳጅ ድምጻዊ ያገኘነው በዚህ በመስከረም ወር ነው ማለት ነው። እሱም ስለመስከረም እንዲህ ብሎ ዘፍኗል።
ክረምት አልፎ መስከረም ሲጠባ
የኔ ቆንጆ ተጊጣ ተውባ
አምራ ደምቃ በአበቦች ታጅባ
ያቻትና መጣች ውብ አበባ።
የመስከረም ወር አዳዲስ የኪነ ጥበብ ሥራዎችም ወደ ህዝብ የሚገቡበት ነው። ብዙ ደራሲዎች በአዲስ ዓመት አዳዲስ ሥራ ያስተዋውቃሉ።
በተከታዩ የአረጋኸኝ ወራሽ መስከረም ዘፈን ልሰናበትና የቀሩትን እናንተው አስታውሷቸው።
እሰይ አበባው እሸቱ ደርሷል
ሰፈር መንደሩ አረንጓዴ ለብሷል
ገደል ሸለቆው ታጥሮ በአበባ
አደይ አበባ እንበል መስከረም ጠባ
የሰላም የፍቅር የፍሃ አዝመራ
ሸጋ ሸጋ ታብቅል እሰይ ምድር ታፍራ
የመከራ ዘመን የያዘን ስቃይ ያብቃ
ሀብት በመስከረም ይሄው ትታይ ደምቃ
መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ
ቤት ለእንቦሳ በሏት የልቤን እንግዳ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 3/2012
ዋለልኝ አየለ