አዲስ አበባ:- የጀርመን የልማት ድርጅት ኢነርጃይዚንግ ዴቨሎፕመንት (GIZ En Dev) በኢትዮጵያ በገጠሩ አካባቢ የሚገኙ 786 የማህበራዊ አገልግሎት ሰጭ ተቋማትንና ከ555 ሺህ በላይ ሰዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረጉ ተገለጸ።
የጂአይዜድ ኢነርጃይዚንግ ዴቨሎፕመንት ፕሮግራም ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቶሎሳ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ ዘላቂነት ያለው፤ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የኃይል አቅርቦት በተለይ በገጠሩ የአገሪቱ ክፍል ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ የማህበራዊ አገልግሎት ለሚሰጡ ተቋማት፤ እንዲሁም ለጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ከታዳሽ ኃይልና ከፀሐይ ብርሃን የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ ትኩረት አድርጎ ሰርቷል። በዚህም፤ እኤአ ከ2006 ጀምሮ በዓለም መሰል ፕሮግራም ካላቸው ከስድስት ለጋሽ አገሮች በተገኘ የ34 ሚሊዮን 651 ሺህ ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ፤ በገጠሩ አካባቢ የሚገኙ 786 ማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትንና 555 ሺህ 817 ሰዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ አድርጓል።
እንዲሁም፤ ማህበረሰቡ በገበያው ውስጥ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ አገልግሎትና ቁሳቁሶች እንዲያገኝ ድርጅቱ በሰራው ሥራ አንድ ሚሊዮን 344 ሺህ 912 ሰዎች ዘመናዊ የምግብ ማብሰያ የኤሌክትሪክ ምድጃ ሲያገኙ፤ ከሁለት ሺህ 781 በላይ አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማትን ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
እንደ አቶ ሳምሶን ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ የተትረፈረፈ የታዳሽ ኃይል ጸጋ የተቸራትና የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ትልቅ አቅም ያላት ብትሆንም፤ በዓለም ላይ ዝቅተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ ከሚጠቀሙ አገር ተርታ የምትሰለፍ አገር ናት። 82 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧ በአገሪቱ የገጠር አካባቢ የሚኖር በመሆኑ፤ የኤሌክትሪክ አቅርቦት የሚያገኝበት ዕድሉ በጣም ጠባብ ነው። ስለዚህ፤ የገጠሩ ማህበረሰብ ኑሮውን በባህላዊ መንገድ ስለሚመራ እንጨትን እንደ ዋነኛ የኃይል ምንጭነት እየተጠቀመ ይገኛል።
በዚህም ደን እየተራቆተ፤ አፈሩ እየተሸረሸረ ስለሚሄድ የማህበረሰቡ ምርትና ምርታማነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነስ ኑሮው ከድጡ ወደማጡ እየሆ እንደመጣ ይናገራሉ።
በመሆኑም፤ ኢነርጃይዚንግ ዴቨሎፕመንት ፕሮግራም በዓለም መሰል ፕሮግራም ካላቸው ለጋሽ አገሮች በተበረከተለት የገንዘብ ድጋፍ፤ 13 ሺህ የሚደርሱ በፀሐይ ብርሃን የሚሰሩ ቴክኖሎጂዎችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ በማድረግ የመብራትና የሞባይል ኃይል መሙያ የኃይል አቅርቦት እንዲያገኙ አድርጓል። በተጨማሪም፤ ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ ድጋፍ በደቡብ የኢትዮጵያ የሚገኙ አምስት መንደሮችን የማይክሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች ተጠቃሚ ማድረጉን ገልጸዋል።
ድርጅቱ በ310 ጣቢያዎች ለሚገኙ 650 ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ስልጠና ሰጥቶ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራ ምድጃ በማምረት ሥራ ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ የጠቆሙት አቶ ሳምሶን፤ እነዚህ አምራች ኢንተርፕራይዞች አንድ ሚሊዮን 134 ሺህ የተሻሻሉ፤ ምርጥና ትክክል የሚባሉ የኤሌክትሪክ ምድጃዎችን አምርተው በመሸጥ ገቢ እንዳገኙ ተናግረዋል።
እንዲሁም፤ በፕሮግራሙ በተደረገ ድጋፍ አንድ ሚሊዮን 344 ሺህ 900 ሰዎች ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ምድጃ ተጠቃሚ ለመሆን የበቁ ሲሆን፤ ይሄን ያክል ቁጥር ያለው ሕዝብ ይሄንን የኤሌክትሪክ ምድጃ በመጠቀሙ በአሁኑ ወቅት በትንሹ 398 ሺህ 213 ቶን ወደ አካባቢ የሚለቀቅ የካርቦንዳ ኦክሳይድ ጋዝ ልቀትን ሲቀንስ፤ 369 ሺህ 202 ቶን የማገዶ እንጨትም በየዓመቱ ይቆጥባል ብለዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 2 ቀን 2012 ዓ.ም
ሶሎሞን በየነ