ዛሬ አዲስ ዓመት ነው። የ2012 ዓ.ም የመጀመሪያ ቀን። አምና አዲስ ዓመትን ከጀመርንበት ዕለት ጀምሮ ቀናት
ቀናትን፤ ሳምንት ሳምንታትን፤ ወራትም ወራትን እየተኩ አሮጌው ዓመት ተገባዶ እነሆ የ2012 ዓ.ም አዲስ ዓመት ዛሬ ተጀመረ። ይህ
ሂደት ተፈጥሯዊ ነው። ቀናት በቀናት ሲቀየሩ የማናችንንም ጥረት አይፈልጉም። በየክፍለ ዘመኑ የነበሩ ምሁራን፣ አባቶቻችንና የአገር
ባለውለታዎች የምንላቸው በሙሉ በተለይ ደግሞ ሳይንቲስቶች ዘመናቸውን እንዴት እንደሰሩ ስንገነዘብ ዘመን በተፈጥሯዊ ሂደት በመለወጡ
ሳይሆን በከፍተኛ ትጋታቸውና አበርክቷቸው መሆኑን ልብ እንላለን።
እናስ! ዘመን ሲለወጥ በተለይ በዚህ ወቅት ያለን ኢትዮጵያውያን 2012 የምንቀበልበት ሁኔታ ዘመናችንን ለመለወጥ ወይም ለመስራት በምናደርገው ተግባርና ሚና ልንመዝነው ይገባል፤ ይህ ግን ቁርጠኝነትንም ይጠይቃል። ዘመናችንን ማደስ ከምንከተለው የአስተሳሰብ ልዕልና እና የልኬት ደረጃችን መለወጥ ሊጀምር ይገባል። ለዚህም ነው ዘመናችንን መስራት ትጋትና ልፋት ይጠይቃል የሚባለው። ዘመንን ለመስራት የዘመን መለወጥ ብቻ በቂ አይደለም፤ ተግተን መስራትና መለወጥ ይኖርብናል።
ሳንደክም ሳንለፋ ፍሬያማ ዘመን ማግኘትና መፍጠር አይቻልም። ምክንያቱም ዘመን ሁልጊዜም ይቀየራል ዓመት ዓመትን የሚተካበት ሂደት አይቋረጥም፤ ማንም ሊያሰናክለው እና ሊያቋርጠው አይችልም፤ ተፈጥሯዊ ነውና። ፍሬያማ ዘመን ደግሞ እንደ ዘመን በራሱ የሚመጣ ሳይሆን ደክመን የምንለውጠው እንጂ በተፈጥሯዊ ሂደት የምንጎናፀፈው አይደለም፤ ሆኖም አያውቅም።
በአዲሱ ዓመት በርካታ የቤት ሥራዎች አሉብን፤ ልንሰራቸው ልንቀይራቸው የሚገቡ በርካታ አስተሳሰቦች፣ ፍላጎቶች እና ጥያቄዎች አሉን። በመሆኑም አዲሱን ዓመት በትጋት ለራሳችን እንዲሁም ለመላው ሕዝባችን የሚመች አድርጎ መስራትና መለወጥ ይገባል። ስለሆነም 2012 ዓ.ም ባልተለወጠ ልብ የምንጓዝበት ሊሆን አይገባም። በአሮጌ ሀሳብ አዳዲስ ፍላጎቶችን መሻት የምንመኝበት መሆንም አይገባም። ስለዚህ ወደኋላ እየሄድን አገራችንን ወደፊት ብረሪ ስንል እያንዳንዳችን ምን የተሰራ እና የተስተካከለ ምቹ ሁኔታ ፈጥረናል ብሎ መጠየቅ ደግሞ ይገባናል። ዘመናችንን ስንሰራ ልናወልቀው የሚገባ የአስተሳሰብ ካባ አለ፤ ልንለብሳቸው የሚገቡ ወሳኝ አስተሳሰቦችንም ልብ የምንልበት ዘመን መሆን አለበት።
የዘረኝነት በሽታ አንዱ ልናወልቀው የሚገባ ክፉ አስተሳሰብ ነው። በዚህ አስተሳሰብ 2011 ምን መልክ ይዘንበት እንደነበር ማውራቱ ለቀባሪ ማርዳት ይሆናል። ኢትዮጵያ እኛን ነው የምትመስለው። ኢትዮጵያ በተለይ በ2011 ‹‹እኛን›› ምግባራችንን መስላ ነበር ጊዜውን የቋጨነው። ልክ ዱባይ የዱባይን ሕዝብ እንደምትመስለው፤ ቻይናም ቻይናውያንን እንደመሰለችው ማለት ነው። ይህን የዘረኝነት በሽታ በዚህ ዘመን እንዳይኖር ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ መትጋት ነው። ለማንም ወርውረን የምንሰጠው የቤት ሥራ አይደለም። ይህን ለማሳካት ደግሞ እንደ ሀገር እና ሕዝብ አብሮ መጓዝና መናበብ ይጠይቀናል፤ ያስፈልጋልም።
በመሆኑም ክፋት፣ ስድብ፣ ምቀኝነት ዘረኝነት ባይገባን ነው እንጂ ተሳዳቢው ወይም ፈጻሚው ሰው ነው ዋናው ባለቤት። እነዚህ ሰዎች አስቀድመው ራሳቸውን የጎዱ ናቸው። በመሆኑም ይህ አስተሳሰብም ሆነ ተግባር መርዝ በመሆኑ ልንርቀው ይገባል። መርዙን ከውስጣችን ለመውጣት ደግሞ ‹‹ክፋት ከጠላቱ ይልቅ ባለቤቱን ያጠፋል›› የሚባለው ለዚህ ነው። ዘመናችን ስንሰራ ከመርዝ የፀዳ የምናደርገው ደግሞ ራሳችን እኛው ኢትዮጵያውያን ነን።
ሌላው የምንለብሰው ካባ የእርቅ ደግሞ ለእርቅ ያለን አተያይ ነው። አስተሳሰባችንን ከለወጥን ያለፈው ጉዳት የሚያመጣብንን ስቃይ መቀነስ እንችላለን። በሌላ አነጋገር፤ ይቅርታ ያለፈውን ሁኔታ በአዲስ አስተያየት መመልከት ነው። ያለፈው አልፏል፤ ሄዷል። የተደረገው ነገር ሆኗል። ምንም አሳዛኝ ቢሆን ብንወድም ብንጠላም ያለፈውን በምንም ዓይነት መቀየር እንደማንችል አምነን መቀበል ይገባናል። የአሁኑ ሕይወታችን በተለይ አዲሱ ዓመት ያለፈው ሕይወታችን አይደለም። አዲስ ነው። በእያንዳንዱ ቅፅበት ይታደሳል። በእያንዳንዱ ደቂቃ አዲስ ሕይወት ለመጀመር ዕድል አለን። ዘመናችንን ለመስራት እንችላለን ማለት ነው።
የአሁኗን ሕይወታችንን በአዲስ መንፈስ ከኖርን የወደፊቱም ይህንን ተከትሎ ይቀጥላል፤ ይሳካልም። ስለዚህ የይቅርታ መንፈስ መሠረቱ ካለፈው ጋር በመቆራኘት ያለፈውን ሕይወታችንን የአሁኑ ሕይወታችን አናድርገው፤ ያለፈው እንዲያልፍ ከልብ እንተወው፤ እንልቀቀው። ይህ ሲሆን በእርግጥም አዲሱን ዘመናችንን እንሰራለን፤ እንዲመቸንም ማድረግ እንችላለን። እንዲህ ነው ዘመንን መስራት፤ ግጭትና ዘረኝነትን አስወጥተን ሰላም እና እርቅን ማስገባት። መልካም አዲስ ዓመት!
አዲስ ዘመን መስከረም 1ቀን 2012 ዓ.ም