ከስምንት ወራት በፊት በኢትዮጵያ የጀመረው የለውጥ ጉዞ አሁን ላይ ርምጃውን ጠንከር አድርጎ ቀጥሏል:: ተቋምን መልሶ የማደራጀት ሥራው መከላከያ ሰራዊቱንም አካቷል፡፡ በእርግጥም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የአገሪቱን ሁኔታ ባገናዘበና የዓለም አቀፉን እውነታ ከግምት ባስገባ መልኩ እንደአዲስ ማደራጀቱ ተገቢ ነው፡፡
የመከላከያ ሠራዊቱ አቅሙንና ጥንካሬውን በበርካታ የአፍሪካ አገሮች የተከሰቱ የርስበርስ ግጭቶችን ለማስቆም የተሰጠውን የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በብቃት በመወጣት ያስመሰከረ ቢሆንም በርካታ ችግሮች እንደነበሩበት ግን አይካድም፡፡ እንደተቋምም በብዙ መሰናክሎችና ችግሮች ተተብትቦ ቆይቷል፡፡ ሙያው ራሱን የቻለ ዕውቀትና ፍልስፍና ያለው መሆኑ ቢታወቅም ከዚህ አንጻር የተማረ የሰው ሃይል እጥረትም ነበረበት፡፡
በሃገር መከላከያ ተቋም ውስጥ የከፍተኛ ትምህርት መሐግብር የሚሰጥበት ብቸኛው ተቋም የቀድሞው የሐረር ጦር አካዳሚ ነበር፡፡ አካዳሚው ከመላ አገሪቱ በፈተና የመለመላቸውን ተማሪዎች ለአምስት ዓመታት በመደበኛ የቀለም ትምህርት፤ በወታደራዊ ሳይንስና ስልጠና፤ በህግና በስነምግባር አንጾ በምክትል መቶ አለቅነት ማዕረግ ያስመርቅ ነበር፡፡
ይህ ዓይነቱ አሰራር ከቀረ ከ40 ዓመታት በላይ ተቆጠሩ፡፡ ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ውትድርናም በጎዶሎ ፍልስፍና መመራት ጀመረ፡፡ የእውቀትና የጥበብ ድርቅም መታው፡፡ መሪዎቹ በአብዛኛው ከግንባር የሽምቅ ውጊያ ትግል የተገኙ በመሆናቸው ተቋሙ ከወገንተኝነት አልፀዳም፡፡ የፖለቲካ ፍላጎት ማስፈጸሚያ፤ የቡድኖች ስልጣን መቆያ መሣሪያም ሆኖ ቆየ፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በ1980ዎቹ መጨረሻ እንደገና በአዋጅ ሲደራጅ፤ መሰረቱ የኢፌዴሪ ሕገመንግስት አንቀጽ 87 ነበር፡፡ ይህ አንቀጽ፤ የሠራዊቱን የብሔር፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተዋፅኦ ሚዛናዊነት፤ ሠራዊቱ በማናቸውም ጊዜ ለሕገመንግስቱ ተገዥ ስለመሆኑ፤ እንዲሁም ተግባሩን ከፖለቲካ ድርጅቶች ወገናዊነት ነፃ ሆኖ እንደሚያከናውን ያትታል፡፡ ይሁን እንጂ፤ ይህ ተግባራዊ ሲሆን አልታየም፡፡
የአሁኑ የመከላከያ ሠራዊትን የእንደገና መገንባት /ሪፎርም/ ሥራ በእርግጥ የሀገራዊው ሪፎርም አንድ አካል አንደሆነ ይታወቃል’ ሪፎርሙም በተቋሙ ውስጥ ከላይ እስከታች ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ማስፈን፤ ተዋጽኦው ኢትዮጵያን እንዲመስል ማድረግ፣ በወታደራዊ ሳይንስ የተቃ‚ና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ሠራዊት መፍጠር፤ ግዳጅ መፈጸም የሚያስችል ብቃት መገንባት የሚሉ መርሆዎች ያሉት መሆኑ ተገልጿል’ ይህ መሠረታዊ የሪፎርም ሥራም ተጀምሯል’ ሪፎርሙ ቅድሚያ ሰጥቶ ባከናወነው ተግባርም ከዕዝ አመራሮቹ ጀምሮ የብሔር ተዋጽኦውን ሚዛናዊ የማድረግ ሥራ ስለመሰራቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተገልጿል’ ስብጥሩም ባለፈው ሳምንት መጨረሻ መግለጫ በሰጡት የጦር ኃይሉ አመራሮች ታይቷል’ አደረጃጀቱም በምድር ሀይል፤ በአየር ሀይልና በባህር ሀይል እንደሚሆን ታውቋል፡፡
የመከላከያ ሠራዊት ዋናው ሥራው ውትድርና ነው፡፡ ውትድርና ደግሞ ሳይንስ ነው፤ በዘመናዊ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ የበለጸገ፤ ውትድርና ጥበብ ነው፡፡የላቀ መምራትና የመመራት ሥርዓት የሚታይበት እንዲሁም የጸጥታና የደህንነት ስትራቴጂ የሚተገበርበት ክቡር ተግባር ነው፡፡ የሀገር ፍቅር የሚታይበት፤ የሕዝብ አገልጋይነት የሚገለጽበት፤ የህይወት መስዋዕትነትን የሚያስከፍል ታማኝነት መገለጫው የሆነ ሥነምግባር የነገሰበት ሙያም ነው፡፡ እናም፤ የመከላከያ ሠራዊት አባል ሆኖ ወደምድር ሀይል፤ ባህር ሀይልና አየር ሀይል የሚቀላቀል ዜጋ መነሻውም መድረሻውም ሰላምና ብልፅግና፤ እንዲሁም የሕዝቦች ልዕልና ነው፡፡ ሊያውቀው የሚገባውም ይህንን ሳይንስና ጥበብ መሆን አለበት፡፡
ግዳጅ መፈጸም የሚስችል ብቃት የሚጎለብተው በእውቀትና በጥበብ ነው፡፡ እናም በየደረጃው ያሉ የሠራዊቱ አመራሮችም ሆኑ አባላቱ አግባብ ያለው የውትድርና ሳይንስ ሊማሩ፤ ዘመን ያፈራውን ቴክኖሎጂ ሊቀስሙና ሊጠቀሙ፤ እንዲሁም አግባብነት ያለው የውትድርናና የውጊያ ጥበብ ሊካኑ ይገባል’ በቀጣይ ወደሠራዊቱ የሚቀላቀሉ ወጣቶችም ሙያውን በፍቅር የሚመርጡት እንዲሆን መስራት ያስፈልጋል’ ለዚህም ተቋማዊ ቁመናውና አሰራሩ ግልጽነት የተላበሰና ተጠያቂነት የሰፈነበት ሊሆን ይገባል’
ይሁን እንጂ፤ ሪፎርሙ በአገር መከላከያ ተቋም ብቻ መወሰን የለበትም’ ይልቁንም የፌዴራል ፖሊስንና የክልል ፖሊስን ያካተተ፤ በለውጥ ላይ ያለውን የሀገር ደህንነት መሥሪያ ቤት ጨምሮ ሁሉንም የአገሪቱን የፀጥታ ዘርፍ ያጠቃለለና የተቀናጀ መሆን ይኖርበታል’ በዚህ ረገድ በክልሎች የሚታየውንም የተዘበራረቀ የፖሊስ ኃይልና የጸጥታ አካል አደረጃጀት መልክ ማስያዙ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ተግባር ነው፡፡
ለዚህ ደግሞ መንግሥት እንደለውጥ መሪነቱ አስተዋይነትን የተላበሰ መሪነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡ አስፈላጊ ናቸው በሚላቸው ጊዜያትና ጉዳዮች ላይ የሚመለከታቸውን አካላት ማወያየት፤ ሀሳባቸውንም በሆደ ሰፊነት መቀበል ይጠበቅበታል፡፡ ሕዝቡና ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶችም፤ መከላከያ በአንድ በኩል የውጭ ሥጋትን በብቃት ለመቋቋም፤ በሌላ በኩል የውስጡን አገራዊ ሰላም ለማስጠበቅ በሚያስችል መልኩ ራሱን ለማብቃት የሚደርገውን መልሶ ግንባታ በንቃት ሊከታተሉና በሁሉም መስክ ሊደግፉት ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2011