በኢትዮጵያውን የዘመን አቆጣጠር ቀመር መሰረት ዓለም ከተፈጠረ፣ ዘመን ከተቆጠረ ነገ መስከረም 1 ቀን 2012 ዓ.ም 7512 ዓመት ይሞላዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ የመጀመያዎቹ 5500 ዓመታት የመጀመሪያው ሰው፣ አዳም የፈጣሪውን ትዕዛዝ ባለማክበሩ የተነሳ በደረሰበት እርግማን የሚሞቱ ሰዎች ሁሉ ድኅነት የማያገኙ በመሆናችው “ዓመተ ፍዳ” በመባል ይቆጠር ነበር፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከተወለደ ወዲህ ያሉትን ዓመታት ደግሞ ፈጣሪ የፈጠረውን ሰው መልሶ ይቅር ያለበትና ምህረት ያደረገበት በመሆኑ “ዓመተ ምህረት” እያልን እየቆጠርናቸው እነሆ ነገ መስከረም አንድ ላይ 2012ኛውን ዓመተ ምህረታችንን በምህረት እንቀበላለን፡፡ እናም አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር “አዲስ ዓመት” ብቻ ሳይሆን “አዲስ ነገር” መመኘትና መፈለግ የሁሉም ሰው ባህርይ ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ አዲስ ነገር መፈለግ ያለብን ሦስት መቶ ስልሳ አምስት ቀናት ጠብቀን አዲስ ዓመት ሲመጣ ብቻ አይደለም፡፡ ማንም ሰው በባህርይው ሁሌም አዲስ ቢሆንና አዲስ ነገር ቢያገኝ አይጠላም፡፡ እናም የቻለ አዲስ ዓመት ጠብቆ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ጊዜ አዲስ ነገርን ሊፈጥር ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ አዲስ ዓመትን ጠብቆ ለለውጥ፣ ለአዲስ ህይወት፣ ለአዲስ ስኬት መነሳሳትም ነውር ነው የሚል አመለካከት የለኝም፡፡
በበኩሌ ‹‹አዲስ ዓመት የሚባል ነገር የለም›› ከሚሉ ሰዎች ጋር አልስማማም፡፡ ምክንያቱም የ86ሺ አራት መቶ ሴኮንዶች ትርታዎችን ሰምቶ፣ ደቂቃዎችን ቆጥሮ፣ ሰዓቶችን ተመልክቶ፣ ሃምሳ ሁለት ሳምንታትን ሰንብቶ፣ አስራ ሁለት ወራትን ቆጥሮ፣ ሦስት መቶ ስልሳ አምስት (ዘንድሮ ሦስት መቶ ስድሳ ስድስት) ሌሊቶችንና ቀኖችን አምሽቶና አንግቶ ወደ አዲስ የህይወት መቁጠሪያ “አውደ ዓመት” መሸጋገር ዕውነትም አዲስ ነው፡፡ አዎ ይህ ለዕኔ ሕይወትን እንደ አዲስ እንደመጀመር ነው፡፡ ስለሆነም ሰው አዲስ ዓመትን ጠብቆ አዲስ ነገር ለመፍጠር ቢያቅድ ስህተት ሊሆንበት አይችልም፡፡ ምክንያቱም በአዲስ የጊዜ መቁጠሪያ አውድ ውስጥ ሆኖ አዲስ ህይወት፣ አዲስ እንቅስቃሴ ማድረግ የበለጠ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ በአሮጌ አቁማዳ አዲስ ወይን አይጠመቅምና!
ማንም ሰው ከአቅሙ በላይ የሆነ ችግር ካላጋጠመው በቀር ዛሬ ላይ ሆኖ ትናንትን መኖር አይፈልግም፡፡ ዘንድሮ በአዲሱ ዓመት ላይ ሆኖ የአምናውን ወይም የካቻአምናውን ተመልሶ አይኖርም። እንደዚያማ ቢሆን ኖሮ ወይም አዲስ ዓመት ዋጋ ባይኖረው ኖሮ ልጅነት፣ ወጣትነት፣ ጉልምስና፣ ሽምግልናና ሞት ባልኖሩም ነበር፡፡ ያኔ በህጻንነታችን ስናደርግ እንደነበረው ዛሬም አፈር እየፈጨንና ውሃ እየተራጨን እንገኝ ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር ሰው ህጻን ሆኖ ተወልዶ ህጻን እንደሆነ ይሞት ነበር። ዳሩ ግን ዘመን ወይም ዓመት የጊዜ መለኪያ ብቻ ሳይሆን የህይወትም መለኪያ ነውና ቀናት በቀናት፣ ወራት በወራት እየተተኩ፣ ዘመን በዘመን እየተለወጠ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ዕድሜያችን እየጨመረ ይመጣል፤ ዕድገታችንም እንዲሁ ፡፡ አዲስ ዕድሜ አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ ድርጊት … አዲስ ነገር ይዞ ይመጣል። ይህ እገሌ በተባለ ሰው የተቀመረ ፅንሰ ሃሳባዊ ትወራ አይደለም፡፡ ሁልጊዜም ዑደቱን ጠብቆ የሚካሄድ የማያቋርጥ ተፈጥሯዊ ህግ ነው፡፡
እንዲህ ከሆነ እንግዲህ ውድ አንባቢያን ሆይ … እኔም ሆንኩኝ እናንተ በ2012 ዓ.ም፣ በአዲሱ ዓመት እንዲኖሩን የምንፈልጋቸው አዳዲስ ነገሮች ይኖራሉ ማለት ነው፡፡ መቼም ሰው የሌለውን እንጂ ያለውን ነገር ለማግኘት አይፈልግምና የሁላችንም ፍላጎት ይለያይ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ቤት የሌለው በአዲሱ ዓመት ቤት መግዛት ወይም መስራት ይፈልግ ይሆናል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ቤት ኖሮት መኪና ስለሌለው በአዲሱ ዓመት መኪና ለመግዛት ያሰበ ይኖራል፡፡ ቤትም መኪናም ተሟልቶለት ላጤ የሆነ ሰው ደግሞ ትዳር የመያዝ ዕቅድ አውጥቶ ይሆናል … ብቻ ብዙ ነው፡፡ በምግብ ራሱን ያልቻለ የኔ ቢጤ ምስኪን የምግብ ዋስትናውን ለማረጋገጥ፣ መተዳደሪያ ሥራ የሌለው ሥራ ለመያዝ፣ ልጆቹን በአውሮፓና በአሜሪካ ማስተማር የሚፈልግ፣ በቦሌና በዱባይ ለመኖሪያ የምትሆን ትንሽዬ ቪላ መቀለስ የሚፈልግ እንዲሁም ስልጣን የመያዝ ምኞት ያለው ሰው ይኖራል፡፡
እኔ ግን ለዛሬው በአዲሱ ዓመት ቤት ከሚፈልጉት መካከል ራሴን ልመድብና ስለ ቤት ያለኝን የግሌን ዕይታ ላካፍላችሁ፡፡ በእርግጥ ይች የቤት ነገር የመላ ኢትዮጵያውያን በተለይም ደግሞ የሁሉም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ጥብቅ ፍላጎት ለመሆኗ በአገሪቱ ያሉ የመገናኛ ብዙሃን አንዳቸውም ሳይቀሩ በየጊዜው የሚናገሩት ነው፡፡ ወደ ጉዳዬ ልለፍ፡፡
በአሁኑ ጊዜ በጣም እየከፉ ከመጡ ማኅበራዊ ችግሮች መካከል አንደኛውና ዋነኛው የመኖሪያ ቤት ችግር ነው፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን በእጅጉ ከሚያሳስቧቸው ችግሮች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚወሳው የመኖሪያ ቤት ችግር ነው፡፡ ለኑሮ ተስማሚ ካልሆኑት ጎስቋላ መንደሮች አንስቶ በተለያዩ የኮንዶሚኒየም ሳይቶች በኪራይ ቤቶች መከራቸውን እያዩ እስካሉ ዜጎች ድረስ መንግሥት በስፋት አቅዶ በተለያዩ ፕሮጀክቶች እየገነባቸው ያሉ ቤቶችን በተስፋ ቢጠብቁም ጉም የመዝገን ያህል ሆኖባቸዋል፡፡ በ1996 ዓ.ም. የተጀመረው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ ላለፉት 12 ዓመታት ባደረገው አዝጋሚ ጉዞ ከመቶ ሺሕ በላይ ቤቶች ተገንብተው ለዕድለኞች ተላልፈዋል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ፍላጎትና አቅርቦት አልተጣጣሙም፡፡
የመኖሪያ ቤት ችግር ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የሚወጡ የነገ ሃገር ተረካቢ ወጣቶችንም ጭምር የሚፈታተን የዘመኑ ተግዳሮት እየሆነ መጥቷል። በወጣትነታቸው ቤተሰብ ላይ ሸክም የሆኑ ዜጎች እየበዙ ነው፡፡ ፍቅረኞች በመኖሪያ ቤት ዕጦት ምክንያት ትዳር መመሥረት ተስኗቸዋል፡፡ ብዙዎቹ የመንግሥትና የግል ድርጅት ሠራተኞች ከወር ደመወዛቸው ከግማሽ የሚበልጠውን ለመኖሪያ ቤት ኪራይ ለመክፈል ይገደዳሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ በኮንዶሚኒየም ቤቶች ላይ ቆጠራ ከተደረገ ወዲህ፣ በበርካታ ሳይቶች በአንድ ቤት ላይ ከአንድ ሺ እስከ ሁለት ሺ ብር የሚደርስ ከፍተኛ ጭማሪ መደረጉን ተከራዮች ተናግረዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው ቤቶች እየተመለሱ ጥገኝነት እየጠየቁ ነው፡፡ በቆጠራው ሳቢያ ሕገወጥ ድርጊቶች ቢጋለጡም፣ ለዓመታት ተገናኝተው የማያውቁ አከራዮች በደላሎች አማካይነት ባደረጉት ግንኙነት ያለምንም ምክንያት በተከራዮች ላይ ውርጅብኝ ፈጽመዋል፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ አስመራሪ ድርጊት ምክንያት ተከራዮች ካላሰቡት ዕዳ ጋር ለመጋፈጥ ተገደዋል፡፡ ይህ አነስተኛ ማሳያ የወቅቱን የመኖሪያ ቤት ጉዳይ አንገብጋቢነት የሚያመላክት ነው፡፡
አንገብጋቢ የሆነውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት መንግሥት ዋነኛው አካል ቢሆንም፣ ይመለከታቸዋል የሚባሉ ባለድርሻ አካላት በሙሉ ከዕቅድ ጀምሮ እስከ አፈጻጸም ድረስ ተሳትፎ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ መንግሥት የተቆጣጣሪነት ኃላፊነቱን እየተወጣ የግንባታውን ሙሉ ኃላፊነት በጨረታ አማካይነት ብቃት ላላቸው የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች መስጠት ይኖርበታል፡፡ በመላ አገሪቱ እየተገነቡ ያሉትንና የነበሩትን መንገዶች ለአገር ውስጥና ለውጭ ኩባንያዎች በሰጠው አሠራር መሠረት፣ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታም በዚህ መንገድ ካልተመራ ችግሩ ቀውስ ያስከትላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ መንግሥት ለመኖሪያ ቤቶች ግንባታ የተለያዩ ግብዓቶችን እያቀረበ በሥራ ተቋራጮች የሚያስገነባበት አሠራር ወጪ ቆጣቢ ካለመሆኑም በላይ ለሙስና የተጋለጠ ነው፡፡ ከፍተኛ የሆነ የጥራት መጓደልም ይፈጠራል፡፡ ይህም በተግባር እየታየ ነው፡፡ በመሆኑም በብዛት ቤቶችን ገንብተው መጠቀም የሚፈልጉ ኩባንያዎች በጥንቃቄ ተመርጠው ሥራ ይሰጣቸው፤ ለዚህም ጠቃሚ ልምዶች ይገብዩ፤ በዘርፉ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ዕድሉ ይሰጣቸው የሚሉት የዘርፉ ባለሙያዎች የሚመክሯቸው ምክረ ሃሳቦች ናቸው፡፡
የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ አሁን ባለው አዝጋሚ ጉዞው የሚቀጥል ከሆነ፣ ተመዝግበው ወረፋ የሚጠብቁትን ብቻ ሳይሆን ነገን በተስፋ የሚጠባበቁ ታዳጊዎችንም ጭምር ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ወገኖች ደግሞ ከኪራይ ብዝበዛ የተነሳ ኑሮን መቋቋም ሲያቅታቸው ቀውስ አይፈጠርም ብሎ አለመስጋት በራሱ አጠያያቂ ነው፡፡ በቅርቡ ለባለ ዕድለኞች በመተላለፍ ላይ የሚገኙ ቤቶች በሚገባ ባለመጠናቀቃቸው ሳቢያ ተጨማሪ ወጪ እያስወጡ ነው፡፡ እንዲያው ለመሆኑ ከኑሮ፣ ከቤት ኪራይ፣ ከቁጠባና ከመሳሰሉት ወጭዎች ምን ተርፎ ነው በአግባቡ ተጠናቆ መረከብ የሚገባን ቤት ለተጨማሪ ወጪ የምንዳረግበት? ይህ ዓይነቱ አሠራር በቀጠለ መጠን መሸማቀቁም አብሮ ይቀጥላል፡፡ በሌላ በኩል ቤቶቹ በኩባንያ ቢገነቡ ግን ከዕቅድ፣ ከዲዛይን፣ ከወጪ ቆጣቢነት፣ ከጥራት፣ ከተጠያቂነትና ከመሳሰሉት አንፃር ብርቱ ቁጥጥር ስለሚኖር ይህ ዓይነቱ አካሄድ ተመራጭ ይሆናል፡፡ ይህም አንዱ የመፍትሔ አመላካች ነው፡፡
በአጠቃላይ መንግሥት በቤቶች ልማት ፕሮጀክት አማካይነት የተጀመረው ጥረት በበጎ ቢወሳም፣ ስትራቴጂውን እየፈተሸና እየከለሰ ተመራጭ መፍትሔዎችን ካልፈለገ በመኖሪያ ቤት ችግር እየተፈተኑ ያሉ ዜጎችን በአጭር ጊዜ ሊደርስላቸው አይችልም። በተጨማሪም ከአቅም በላይ እየሆነ የመጣውን የኑሮ ጫና እየተጋሩ ያሉ ዜጎች፣ በአከራዮቻቸው ማናለብኝነት የሚደርስባቸው ግፍ ከመጠን እያለፈ በመምጣቱ አገራዊ ቀውስ እንዳይፈጠር አማራጮችን በቅን ልቦና ማየት ያስፈልጋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በአራቱም አቅጣጫዎች የሚሰማው የመኖሪያ ቤት ችግር አድማጭ ይፈልጋል፡፡ መንግስት አሁንም ለመኖሪያ ቤት ጉዳይ ልዩ ትኩረትና ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል፡፡
ቤት ከመኖሪያነትና ከመሰረታዊ ፍላጎትነት ባሻገር
የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች የሚባሉት ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ወይም ቤት ናቸው። ‹‹መሰረታዊ ፍላጎት›› ማለት ደግሞ ዋና፣ ሊታጣ የማይገባ፣ ለመኖር የግድ አስፈላጊ የሆነ የሚል ትርጉም ይኖረዋል፡፡ ታዲያ መሰረታዊ ፍላጎት ማለት የሰው ልጅ በህይወት ለመኖር ሊያጣው የማይገባው አንዱ ቤት ከሆነ “መኖሪያ” የሚለው ትርጓሜ ለምን ለ“ቤት” ብቻ ተለይቶ ተሰጠ? ምግብና መጠለያ ለመኖር የግድ የሚያስፈልጉ “መኖሪያ” አይደሉምን?
በእኔ ዕይታ ይህ የሆነበት ምክንያት እንደተባለው ምግብና መጠለያ “ለመኖር የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ፍላጎቶች” ሲሆኑ ቤት ግን “ለመኖር የሚያስፈልግ” መሰረታዊ ፍላጎት ከመሆኑም በላይ “መኖሪያ” ጭምር በመሆኑ ነው፡፡ እዚህ ጋር “ለመኖር የሚያስፈልግ” የሚለው ሃረግና “መኖሪያ” የሚለው ቃል ከፍተኛ የትርጉም ልዩነት አላቸው፡፡ ሰው ለመኖር ምግብና ልብስ ያስፈልጉታል መኖሪያ ሊሆኑት ግን አይችሉም። ለሰው አስፈላጊም፣ መኖሪያም ሊሆን የሚችለው ቤቱ ብቻ ነው፡፡ አዎ ሰው ለመኖር ቤትም ያስፈልገዋል፤ ከአስፈላጊነቱም በላይ ግን ቤት ለሰው መኖሪያው ነው። እናም ሰው በህይወት ለመቆየት ምግብ ይበላል፤ ልብስም ይለብሳል መኖሪያ ከሌለው ግን ምን ዋጋ አለው? የጠጣው ውሃ ፣ የተመገበው ምግብ ፣ የለበሰው ልብስም ከችግር አያድኑትም፤ ያፈራውን ንብረት ሌቦች ይዘርፉታል፤ ከነአካቴውም አውሬ ሊበላው ይችላል – መጠለያ፣ መኖሪያ ቤት የለውምና! እናም ቤት የሌለው ሰው (የኪራይ ቤትም ቢሆን) ምንም እንኳን ምግብና ልብስ ቢያገኝም በህይወት መቆየት እንጂ በህይወት መኖር ያዳግተዋል፡፡
ለዚህም ይመስላል ጥንታዊው ሰው ለልብስ ብዙም ግድ የለውም ነበር፡፡ ምግቡን ብቻ ተከትሎ በየቦታው እየዞረ ከመኖር በአንድ አካባቢ ረግቶ፣ ቤት ሰርቶ ቋሚ ኑሮ መስርቶ መኖር ከጀመረ በኋላ ወደ ተሻለ የአዕምሮ ዕድገት ደረጃና የኑሮ ዘይቤ (ስልጣኔ) የተሸጋገረው፡፡ ጥንት የሰው ልጅ በህይወት ለመቆየት አስፈላጊ ሆኑትን መሰረታዊ ፍላጎቶች በተለይም የሚበላው ምግብ ካገኘ ስለ መኖሪያ ብዙም አይጨንቀውም ነበር፡፡ በየዛፉ ስርና በየዋሻው በጊዜያዊነት እየተጠለለ ያሳልፍ ነበር፡፡ ትንሽ ቆይቶ አዕምሮው እያደገ ሲመጣ ግን ከመሰረታዊ ፍላጎትም በላይ መሰረታዊ የሆነውን፤ ለመኖር የሚያስፈልገውን ብቻ ሳይሆን “የሚያኖረውን” ዋነኛውን የኑሮ ቁልፍ “መኖሪያውን” መርሳቱን ተገነዘበ፡፡ በሂደትም በቋሚነት የሚኖርበትን ቤት ወደ መስራት ተሸጋገረ፡፡ ከቦታ ቦታ መንከራተት በመተው ቋሚና የተረጋጋ ህይወት መኖር ጀመረ፡፡ ህይወቱ በፍጥነት እየተሻሻለ፣ ዕመርታዊ ለውጥ እያሳየ መጣ፤ ወደማያቋርጥ የስልጣኔ ጉዞ ገባ፡፡ እነሆ አሁን ላለበት ታላቅ የዕድገት ደረጃ በቃ፡፡
ቤት፣ አዕምሮና አገር
ቤት የሚያስፈልገው ለመኖር ብቻ ሳይሆን የተሻለ ህይወትም ለመኖር ጭምር መሆኑን አመላካች ነው፡፡ የዚህ መሰረታዊ ምክንያቱ የአዕምሮ ዕድገት ከተረጋጋ ህይወት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስላለው ነው፡፡ የሰው ልጅ ታላላቅ ነገሮችን ማከናወን የሚችለው አዕምሮው በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ሲሆን ወይም የአዕምሮ ሰላም በሚያገኝበት ጊዜ መሆኑን የሥነ ልቦና ሊቃውንት ይመሰክራሉ፡፡ በተረጋጋና በሰላማዊ ሁኔታ ውስጥ ለመሆን ደግሞ ዜጎች አዕምሯቸው ሰላም የሚያገኝበት፣ ተረጋግተው የሚያስቡበትና የሚኖሩበት “መኖሪያ” ቤት ያስፈልጋቸዋል፡፡
ያኔ አዕምሮ በተረጋጋ ህይወት ውስጥ ሲሆን ሥራውን በአግባቡ ያከናውናል፡፡ ክፉውን ከበጎ መለየት ይችላል፤ ለራስም፣ ለሰውም፣ ለፈጣሪም የሚበጁ መልካም መልካም ነገሮችን ያስባል፤ ያመዛዝናል፤ ይፈጽማል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሰው የሚያስበው ስለ ሰላም፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ ዕድገትና ስለ ብልፅግና ብቻ ይሆናል፡፡ አገር ማለት ህዝብ፤ ህዝብ ማለት ደግሞ የእያንዳንዱ ሰው ውህደት ውጤት ስለሆነ ስለ ሰላም፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ ዕድገትና ብልፅግና የሚያስቡ ግለሰቦች ባሉባት ምድር ፍቅርና መተሳሰብ የነገሰባት ሰላማዊና የበለፀገች አገር ትፈጠራለች ማለት ነው፡፡
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጳጉሜ 6/2011
ይበል ካሳ