ጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ በሮም ኦሎምፒክ 42 ኪሎ ሜትር በባዶ እግሩ ሮጦ የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቅ አኩሪ ገድል የፈጸመው ከ 59 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጳጉሜን 5 ቀን 1960 ዓ.ም ነበር፡፡
አበበ በ1960ው ኦሎምፒክ ለመሳተፍ ወደሮም ከመሄዱ በፊት ከአገር ውጪ ምንም አይነት ውድድር ባለማድረጉ ለኦሎምፒኩ የመጀመሪያ ተመራጭ አልነበረም። የመጀመሪያ ተመራጩ ዋሚ ቢራቱ ውድድሩ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት በወቅቱ ልምምድ ያደርጉበት ከነበረበት ደብረዘይት በሩጫ አዲስ አበባ ዳር የሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ደርሶ ሲመለስ ሳንባውን በመታመሙ ከጉዞ ሲቀር አበበ ዋሚን ተክቶ ቡድኑን በመቀላቀል ወደ ሮም አቀና።
የኦሎምፒኩ የማራቶን ውድድር ከመጀመሩ ሁለት ሰአታት ቀደም ብሎ በውድድሩ ለአትሌቶች ጫማዎችን ሲያቀርብ የነበረው አዲዳስ ለአበበ እግር ይበቃሉ ብሎ ያቀረባቸው ጫማዎች አልሆን አሉት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በልምምድ ወቅት በአብዛኛው ያለጫማ ይሮጥ የነበረው አበበም በባዶ እግሩ ለመሮጥ ሃሳብ አቅርቦ አሰልጣኙ ተስማምተው ወደ ውድድሩ ገባ።
ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት አሰልጣኙ ኦኒ ኒስከን የአበበ ተፎካካሪ 26 ቁጥር የተጻፈበት መለያ የሚለብሰው ሞሮኳዊው ራህዲ ሊሆን እንደሚችል በመገንዘባቸው አበበን 26 ቁጥር የለበሰው አትሌት ላይ ትኩረትህን አድርግ ብለው መክረውት ነበር። በአጋጣሚ ራህዲ 10 ሺህ ሜትር ሲሮጥ የለበሰውን 185 ቁጥር የተጻፈበት ማሊያን በመልበሱ አበበ ውድድሩ እየተጋመሰ ሲሄድ 26 ቁጥር የለበሰ ሯጭ ፍልጋ ቢያማትርም ሊመለከተው አልቻለም። ራህዲ 185 ቁጥር ማሊያውን ለብሶ አብሮት በመሪነት እየሮጠ ነበር።
ማራቶኑ ሊጠናቀቅ ሶስት ኪሎ ሜትሮች ያህል እስኪቀሩት ድረስ አበበና ራህዲ ጎን ለጎን አብረው ሲሮጡ ቆይተው አበበ ፍጥነቱን በመጨመር ራህዲን በ200 ሜትሮች ያህል ቀድሞት ውድድሩን በሁለት ሰዓት ፣ ከ15 ደቂቃ፣ ከ16 ነጥብ ሁለት ሴኮንድ (2:15:16.2) በማጠናቀቅ የዓለም ክብረ ወሰንን ሰብሮ የወርቅ ሜዳሊያ አገኘ። ራህዲ ሁለተኛ ፣ ባሪ ማጊ ደግሞ ሦስተኛ ደረጃን አገኙ። ሌሎቹ ሯጮች ሲያለከልኩና ጥቂቶቹም ራሳቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ሲወድቁ፤ በባዶ እግሩ የሮጠው አበበ ስታዲየሙ ውስጥ ሲያሟሙቅና ሰውነቱን ሲያፍታታ የተመለከቱት በስታዲየሙ የተገኙ ተመልካቾችና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እጃቸውን በአፋቸው ለመጫን ተገድደዋል።
ከውድድሩ በኋላ የአበበ በባዶ እግር ሮጦ ማሸነፍ ያስገረማቸው ጋዜጠኞች አሰልጣኙን ኦኒ ኒስከንን ሁኔታውን እንዲያብራሩላቸው ሲጠይቋቸው “በባዶ እግሩ መሮጡ ምንም አያስገርምም። ልምምድ ላይ በባዶ እግሩ ሲሮጥ አንድ ደቂቃን በ98 ርምጃዎች ሲሸፍን፤ በጫማ ሲሮጥ ደግሞ አንድ ደቂቃን በ96 ርምጃዎች ሲሸፍን አይቻለሁ። እናም ብዙ ልዩነት አይኖረውም ብዬ ስላሰብኩ በባዶ እግሩ ተመችቶት እንዲሮጥ ወሰንን። ምን አልባት ጫማ በኮረኮንቻማ ቦታዎች ላይ ሊጠቅምህ ይችላል፤ ብዙ እግርህን ሊያቆስሉህ የሚችሉ ነገሮች ይኖራሉና። የሮም ጎዳናዎች ግን እንደዚያ አይደሉም። ስለዚህ አበበ ‘በባዶ እግሬ ልሩጥና ለአፍሪካ ታሪክ እንስራ አለኝ፤ እኔም ተስማማሁ።’ በጣም አርበኝነት የሚሰማው ሰው ነው” የሚል መልስ ሰጡዋቸው።
በውድድሩ ማግሥት የኢጣሊያ ጋዜጦች ‹‹ኢትዮጵያን ለመውረር የኢጣሊያ አገር ወታደር ሁሉ አስፈልጎ ነበር፤ ኢትዮጵያ ግን አንድ ወታደር ብቻ ልካ ድፍን ሮምን ወረረችው›› የሚል ጽሁፍ ይዘው ወጡ። ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሊምፒክ ውድድር አሸንፎ የወርቅ ሜዳሊያ የወሰደ ጥቁር አፍሪካዊ አበበ ቢቂላ ነው። ይህም ብዙ ጥቁር አፍሪካውያን በዓለም አቀፍ ውድድሮች እንዲሳተፉ በር ከፍቷል። አበበ የቶኪዮ ኦሊምፒክ 40 ቀናት ሲቀሩት በልምምድ ላይ እያለ ራሱን ስቶ በመውደቁ ቀዶ ጥገና ያደረገ ቢሆንም ልምምዱን በመቀጠል ከህመሙ ሳያገግም በማራቶን ተወዳድሮ ከአራት ዓመታት በፊት ሮም ከተማ ላይ ያስመዘገበውን ክብረ ወሰን አሻሽሎ አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን በማስመዝገብ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል፡፡ የኦሊምፒክ ማራቶንን በተከታታይ በማሸነፍም ከእርሱ በፊት ማንም ያላደረገውን ገድል ፈጽሟል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጳጉሜ 6/2011
የትናየት ፈሩ