ሠዎች በምድር ቆይታቸው ትዳር መሥርተው፣ ልጆች ወልደውና ከብደው ንብረት አፍርተው ይኖራሉ። ታዲያ የሕይወት ዑደት ነውና ሞት ሲመጣ አብረው ብቅ የሚሉ ብዙ ድብቅ ጉዳዮች የበርካቶችን በር ሲያንኳኩ ይስተዋላል። በተለይም ብዙ ጊዜ የሚነሱት የውርስ ክርክሮች በመሆናቸው እነዚህን ሁኔታዎች ተቀብሎ ማስተናገድ ትልቅ የሥነልቦና ዝግጅትንም የሚጠይቅ ይሆናል። ይህን ያነሳሁላችሁ ያለምክንያት አይደለም ይልቁንም ከጉራጌ ዞን ቄጩት ወረዳ ጮኖ ሰባብር ከተባለ ቦታ ድንገት ‹‹ሚስት ነኝ›› በማለት መጥተው ለዓመታት በላባቸው የገነቡትን ቤታቸውን ለጨረታ ሽያጭ እንዳበቁባቸው ከአንድ እናት ወደ ተቋማችን የመጣ ቅሬታን ይዘንላችሁ ስለቀረብን ነው። ጉዳዩን ሁለቱንም ወገኖች በማነጋገር፣ የሰነድ ማስረጃዎችንና የፍርድ መዝገብ ግልባጮችን በማገላበጥ እንዲሁም የሚመለከተውን አካል አነጋግረን እንዲህ ይዘንላችሁ ቀርበናል።
ከአንደበታቸው
ወይዘሮ ገነት አመርጋ እንደሚባሉ የነገሩን እናት በሰበታ ከተማ አዋስ ወረዳ ቀበሌ 01 ነዋሪ ናቸው። ለቅሬታ መነሻ የሆነው ቤት ቁጥሩ 764 መኖሪያ ቤታቸው ከባለቤታቸው አቶ ወርቁ ማሩታ ጋር በ1983 ዓ.ም እንደገዙት ይናገራሉ። በትዳር ቆይታቸውም አምስት ልጆች አፍርተው ይኖሩ ነበር። ሆኖም ማንኛውም የጋራ ሕይወት ችግር እንደሚያጋጥመው ሁሉ እርሳቸውም ሁለት ልጆች ከወለዱ በኋላ ባለቤታቸው ከሌላ ልጆች እንዳላቸው ያውቃሉ። ሲጣሉ ማስታረቅ ባሕሉ የሆነው የአገሬው ነዋሪም በሽምግልና ጉዳዩን ሲይዘው ከእርሳቸው በፊት የተፈፀመ ጉዳይ በመሆኑ ኑሯቸውን ይቀጥላሉ።
ቤታቸውን ሊያቀኑ ደፋ ቀና ብለው አረብ አገር ድረስ ተጉዘው እንደነበርም ያስታውሳሉ። በሰው አገር ሁለት መልክ አውጥተው ያገኙትን ገንዘብም የሚከራዩ ቤቶችን ሠርተውበት ቤተሠባቸውን ያስተዳድሩ ነበር። ነገር ግን ጥር 15 ቀን 2008 ዓ.ም ውሃ አጣጫቸው ከዚህ ዓለም በሞት ይለያሉ። የዓመታት የኑሮ አጋራቸው ሕልፈተ ሕይወት ሐዘን እንደ ፍም እሳት እያንገበገባቸው አርባቸው እንኳ ሳይወጣ ሚስት እንደሆኑ በመግለጽ ወይዘሮ ግዜወርቅ ኃይሌ የተባሉ ግለሰብ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ‹‹ንብረት ይገባኛል›› ብለው እንደመጡ ያስታውሳሉ።
ጥረው ግረው ባፈሩት ቤት ላይ የተነሳው የይገባኛል ጥያቄ ክርክር ወደ ፍርድ ቤት እንዳመራ የሚናገሩት ወይዘሮ ገነት፤ ጉዳዩን አሳዛኝ የሚያደርገው የቤታቸው እናት ማህደር እንዲጠፋ ተደርጎ ጎብጠው ባቀኑት፣ ልጆች ወልደው አቅፈው በሳሙበት ቤታቸው ቅምጥ መደረጋቸው እንደሆነ ዓይኖቻቸው ካቀረሩት እንባ ጋር ትንቅንቅ ይዘው ያስረዳሉ። የእርሳቸው ነዋሪነት ተሽሮ በአካባቢው የማይታወቁ ከሳሻቸው ደግሞ ነዋሪ ተደርገው ማህደር እንደተፈጠረላቸውም ነው የሚናገሩት። ወይዘሮ ግዜወርቅ የባለቤታቸው ሚስት እንደሆኑ ተደርጎ በዚሁ ቤት ላይ በሠርግ እንዳገቡ ታስቦ፤ እርሳቸው ደግሞ ቅምጥ እንደነበሩ እንዲመስል ተደርጓል።
ከወይዘሮ ግዜወርቅ የተወለዱት የባለቤታቸው ልጆች የአባታቸውን ንብረት መጠየቃቸውን ባይቃወሙም ማህደራቸው እንዲጠፋ ተደርጎ በምትኩ ሌላ ማህደር ተፈጥሮ የተወሰነው ውሳኔ ግን ፍትሕን እንዳዛባባቸው ይገልፃሉ። የልጆችን መብት እንደማይክዱም በአካባቢው የሚገኝ የባለቤታቸው የነበረ ንግድ ቤት የወይዘሮ ግዜወርቅ ልጅ ለ10 ዓመታት ያክል ይዞ ማስተዳደሩን ተቀብለው እየኖሩ እንደሆነ ያስረዳሉ። ይህንና ሌሎች ንብረቶች ከግምት ውስጥ ሳይገቡ እርሳቸው ላባቸውን አፍስሰው ያቆሙት ቤት በጨረታ እንዲሸጥ መወሰኑን ይናገራሉ። በዚህ እስከ ሰበር የደረሰው ክርክር ተቋጭቶ ድንገተኛዋ ሚስት እኩል ንብረታቸውን እንዲካፈሉ መወሰኑ፤ ብሎም ይግባኛቸው ሰሚ ማጣቱ ሐዘንን እንደፈጠረባቸው ከዓይናቸው የሚወርዱትን የእንባ ዘለላዎች በሻርፓቸው አበስ እያደረጉ ማስረጃዎቻቸውን ያሳያሉ።
በእጃቸው የሚገኙ ሰነዶች
ወይዘሮ ገነት የክርክር መነሻ የሆነውን ቤት አስመልክቶ ያሏቸውን ሰነዶች አሳይተውናል። በዚህም ለበርካታ ዓመታት ለይዞታው ክፍያ የተፈፀመባቸው ደረሠኞች፣ ማክሰኞ ጥር 28 ቀን 1983 ዓ.ም የዓለም ገና አውራጃ ፍርድ ቤት፤ አቶ ወርቁ ማሩታ በቀበሌ 01 የሚገኘውን የገዙትን ቤት ውሉ ፀድቆ በሥማቸው እንዲዛወርላቸው ጠይቀው ያሳወጁበት አዲስ ዘመን ጋዜጣ፤ እንዲሁም ይህን ተከትሎ በፍርድ ቤቱ ይዞታውን የሸጡት ወይዘሮ ሲቲና መሐመድና አቶ አባዝናብ ሸሪፍ ተጠሪዎች ሆነው አቶ ወርቁ ደግሞ አመልካች ሆነው መቅረባቸውን የሚያሳይ ሰነድ ይገኛል። በዚህም በአቤቱታው ላይ የቀረበ ተቃውሞ ስለሌለ ነሐሴ 25 ቀን 1982 ዓ.ም በተደረገው ውል መሠረት ቁጥር 764 የሆነው ከነቦታው በአቶ ወርቁ ሥም እንዲዛወር የወሰነበትን ሰነድ በማሳየት ‹‹በወቅቱ ቤቱን በጋራ ካላፈራነው ይህ ሰነድ እንዴት ከእኔ ሊገኝስ ይችላል?›› ሲሉ ወይዘሮ ገነት ይጠይቃሉ።
ጉዳዩን የሚያውቁ የአስተዳደር አካላትም የፃፉላቸውን የትብብር ደብዳቤዎች አቅርበዋል። ከእነዚህም በሰበታ ከተማ የቀበሌ 01 አስተዳደር በ29/09/2011 ዓ.ም ለኢፌዴሪ ሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በመዝገብ ቁጥር 5595/01/2011 ወጪ አድርጎ የላከው ደብዳቤ ከተመለከትናቸው ሰነዶች መካከል ይገኝበታል። በደብዳቤው የቀበሌው ነዋሪ ወይዘሮ ገነት በውርስ ንብረት ላይ መከሰሳቸውን በመግለጽ፤ ፍትህ ተጓድሎባቸው ለቅሬታ ወደ ተቋሙ ማቅናታቸውን ያብራራል። ክርክሩ ተጠናቅቆ ፍርድ ቤት ንብረት ክፍፍሉ ላይ ያሳረፈው ውሳኔ ተፈፃሚ ከመሆኑ በፊት በአጣሪ ጉባዔው በኩል የሚደረግላቸው መፍትሔ ካለ ትብብር እንዲደረግላቸው አስተዳደሩ መጠየቁን ያሳያል።
በመዝገብ ቁጥር W/M/M/S/0665/2011 በቀን 01/12/2011 የሰበታ ከተማ አፈጉባዔና ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ለአጣሪ ጉባዔው የፃፈውን ሰነድም ተመልክተናል። ጽሕፈት ቤቱ ወይዘሮ ገነት የውርስ ንብረት ክርክር ሲያደርጉ እንደነበር በመጥቀስ፤ ውሳኔው ከመፈፀሙ በፊት በጉባዔው በኩል የሚደረግላቸው መፍትሔ ካለ በሚል ደብዳቤ ፅፏል።
የፍርድ ሒደቱ ምን ያሳያል?
በመዝገብ ቁጥር 28070 በ03/11/2009 ዓ.ም በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከሳሾች ወይዘሮ እነ ግዜወርቅ ኃይሌ ተከሳሾ ደግሞ እነ ወይዘሮ ገነት አመርጋ ሆነው መቅረባቸውን መዝገብ ግልባጩ ያሳያል። በሰነዱ እንደተመላከተው፤ ከሳሾች በ22/03/2009 ዓ.ም በተፃፈ ክስ በሰበታ ከተማ አስተዳደር ቀበሌ 01 ውስጥ 11 ክፍል ያለው ቤት የቤት ቁጥር 764 በሆነው ተመዝግቦ የሚታወቀው በ374 ሜትር ካሬ ስፋት ባለው ቦታ ላይ ያረፈ ግምቱ 300 ሺህ ብር የሚያወጣ ቤት በአቶ ወርቁ ማሩታ ሥም ተመዝግቦ የሚታወቀው አቶ ወርቁ ባደረባቸው ሕመም በ15/05/2008 ዓ.ም ንብረቱን ትተው ሕይወታቸው አልፏል።
የከሳሾችን ማለትም የእነ ወይዘሮ ግዜወርቅን ጨምሮ አራት የሟች ወራሾች ቢሆኑም፤ መኖሪያ ቤቱን ተከሳሽ ወይዘሮ ገነት ምንም ዓይነት መብት ሳይኖራቸው አቶ ወርቁ ከሞቱበት ቀን ጀምሮ በአራት ክፍል ውስጥ በመኖር ሰባት ክፍል ደግሞ በማከራየት እየተጠቀሙበት ስለሆነ ቤቱ እንዲለቀቅላቸው ጠይቀዋል። በዚህም የቤቱን ኪራይ ገንዘብ 30 ሺህ 800 የሚሆን እንዲሰጣቸው እንዲወሰንላቸው በማለት መክሰሳቸውን ያብራራል።
ተከሳሽዋም በ11/04/2009 በተፃፈ መልስ አቶ ወርቁ ባለቤታቸው እንደነበሩ መናገራቸውን ያስነብባል። በአብሮነት ቆይታቸው አምስት ልጆች ማፍራታቸውንም ያሳያል። ለክርክሩ ምክንያት የሆነውን ቤትም አቶ አባዝናብ ሸሪፍና ወይዘሮ ሲቲና መሀመድ ከሚባሉ ሠዎች ነሐሴ 25 ቀን 1982 ዓ.ም በተደረገ ስምምነት ገዝተው ሌሎች ክፍሎችም ጨምረውበት እየተጠቀሙበትና ቤቱን ከባለቤታቸው ጋር ከተጋቡ በኋላ 1977 ዓ.ም ጀምሮ ያፈሩትን ንብረት አንደኛ ከሳሽ የአቶ ወርቁ ባለቤት ያልሆኑና ክርክር በሚደረግበት ቤት ላይ መብት የሌላቸው ናቸው ሲሉ ሞግተዋል። የሟች ወራሾች ከሳሽ የጠቀሷቸው ብቻ ሳይሆኑ እርሳቸው የወለዷቸውና እያሳደጓቸው ያሉ አምስት ልጆች እንዳሉ መግለፃቸውንም ያስነብባል።
አንደኛ ከሳሽ መብት የላቸውም ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ያሉት ከሳሾች ደግሞ መብት እንዳላቸው በሕጉ መሠረት አልተጣራም ተብሎ ክሳቸው ዉድቅ እንዲሆን በማለት መልስ ሰጥተዋል። ፍርድ ቤቱም በአፍ ክርክር ግራ ቀኙን ጠይቆ እንዳጣራው ከሳሽና ተከሳሽ ለሟች የወለዷቸው ልጆች የሟች ወራሾች መሆናቸውን የሚካዱ አይደለም። የክርክር ጭብጥ የሆነው ቤቱን ከሳሽ ወይስ ተከሳሽ ከሟች አቶ ወርቁ ጋር ያፈሩት? የሚለው ሲሆን፤ በማጣራት ተረድቷል። ይህን በተከራካሪዎች መካከል ያለው የመለያየት ጭብጥ ለማጣራት ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ ማስረጃ በማቅረብ አንዲሁም ከሰበታ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ኤጀንሲ የቀረበውን ማስረጃ ሰምቷል።
የከሳሽ ወይንም የወይዘሮ ግዜወርቅ ምስክሮች በሰጡት የምስክርነት ቃል ቤቱን ሟች ከአቶ አባዝናብ ሸሪፍና ከወይዘሮ ሲቲና መሀመድ ከሚባሉ ሠዎች በ1983 ዓ.ም የተገዛ መሆኑና ከሳሽ የሟች ባለቤት ሆነው አምስት ልጆች እንደወለዱ፤ ተከሳሽ ደግሞ በሆቴል ሠራተኝነት ሟች ቀጥረዋቸው አምስት ልጆች መውለዳቸውን መስክረዋል። ይህ ከሆነ ታዲያ በቤቱ ውስጥ ሲኖር የነበረው ማነው? ለሚል ጥያቄ አንደኛ የከሳሽ ምስክር ሟች ከከሳሽ ጋር ቤቱ ከተገዛበት ወቅት ጀምሮ ሲኖሩበት የነበሩ መሆኑን፣ ከሳሽ ደግሞ ደቡብ ከልል እንደነበሩ የተመሰከረ ሲሆን፤ ሁለተኛ የከሳሾች ምስከር ደግሞ በቤቱ ውስጥ ሟች ከአንደኛ ከሳሽ ጋር ሲኖሩ የነበረ መሆኑና ቤቱ ሲገዛ አንደኛ ከሳሽ አንጂ ተከሳሽ አልነበሩም በማለት የምስክርነት ቃላቸውን መስጠታቸው በመዝገብ ግልባጩ ይታያል።
የተከሳሽ ምስክሮች ደግሞ ለክርክር ምክንያት የሆነውን ቤት ሟች ከተከሳሽ ጋር በ1982 ዓ.ም በመግዛት ሲኖሩበት የነበሩና ተከሳሽ አምስት ልጆች የወለዱ መሆኑ፣ በባልና ሚስትነት ቤቱን ገዝተው በጋራ መኖራቸውን የሚያውቁ መሆኑን መስክረዋል። የአንደኛው ተከሳሽ ምስክር ቤቱን የሸጠላቸው መሆኑን መስክሯል። የሰበታ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ኤጀንሲ በሰጠው መግለጫ ቤቱ በሟች አቶ ወርቁ ተመዝግቦ የሚታወቅ መሆኑን አረጋግጧል።
ፍርድ ቤቱም መዝገቡን መርምሮ ውሳኔ ማግኘት ያለበት ጭብጥ ቤቱ ላይ አንደኛ ከሳሽ ናት ወይስ ተከሳሽ ናት መብት ያላቸው? የሚለው ጭብጥ ሃሳብ ተገኝቷል። በዚህም ጭብጡን መነሻ በማድረግ በተደረገው የመዝገብ ምርመራ ቤቱ ላይ ሟች አቶ ወርቁ ግማሽ መብት ያላቸው መሆኑ በግራና በቀኙ ቅር አላሰኘም። ይህን የሟች ድርሻም መውረስ የሚችሉት ልጆቹ ናቸው። ልጆቹ ደግሞ ከሳሾች ብቻ ያልሆኑና ሌሎችም ያሉ ስለሆነ እነሱንም ጨምሮ የውርስ ሕግ በሚለው መሠረት አጣርተው ድርሻቸውን በመለየት ሥልጣን ባለው ፍርድ ቤት በማቅረብ ተከሳሽን የማስለቀቅ መብት አላቸው በማለት መወሰኑ በሰነዱ ይታያል።
በከሳሽና ተከሳሽ መካከል ያለውን ክርክር በተመለከተ ቤቱ አቶ ወርቁ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ገዝተው ማፍራት የተቻለው ከተከሳሽ ጋር እንደሆነ አንደኛው የከሳሽ ምስክርን ጨምሮ ሁሉም የተከሳሽ ምስክሮች መመስከራቸውን ሰነዱ ያረጋግጣል። አንደኛው የከሳሽ ምስክር ሟች ከከሳሽ ጋር ገዝቷል በሚል የሰጡት የምስክርነት ቃል አስመልከቶ አንደኛው የከሳሽ ምስክር ከሰጠው ቃል ጋር የሚጋጭና በተከሳሽ ቃል የተካደ ነው። ከተከሳሽ ምስክር ውስጥ አንደኛው ምስክር ቤቱን የሸጠላቸው መሆኑን አስረድቷል። ይህ ደግሞ ፍርድ ቤቱ ማመን በሚችል ሁኔታ ቤቱ ሟች አቶ ወርቁ ቤቱን የገዙት ከከሳሽ ጋር ሳይሆን ከተከሳሽ ወይዘሮ ገነት ጋር መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።
ተከሳሽ የሟች ባለቤት መሆናቸውን የጽሁፍ ማስረጃ ውሳኔ ለፍርድ ቤት ያቀረቡና ያሰሙት የሠው ማስረጃ የሚያስረዳ መሆኑን እንዲሁም ወይዘሮ ግዜወርቅ ቤቱ በ1983 ዓ.ም ጀምሮ ተጠቅመውበት የማያውቁና በንብረቱ ላይ መብት እንዳላቸው የሚያሳይ ነገር እንዳሌለም ሰነዱ ያመለክታል። በመዝገብ ውስጥ ያለው ማስረጃ የሚያስረዳው ተከሳሽ ወይዘሮ ገነት ከሟች ጋር በባልና ሚስትነት አብረው ሲኖሩ ንብረቱን ያፈሩ መሆናቸውን የሚያስረዳ ነው። ከሳሽ ወይዘሮ ግዜወርቅ አስተዳድረውትም ሆነ ተጠቅመውበት የማያውቁትን ብሎም ለፍተውበት ያላፈሩትን ንብረት ድርሻቸውን በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይዘው እየተጠቀሙበትና የሚተዳደሩበት መሆኑን ማስረጃው አስረድቷል። እርሳቸውም ይህንኑ እያወቁ ተከሳሽ ለብዙ ዓመታት ይዘው በውስጡ ለሟች ልጆች ወልደው እየተዳደሩበት ያሉትን ሳይጠይቁ መቅረታቸው መብት የሌላቸው መሆኑን የሚያስረዳ ነው በማለት ያስረዳል።
በሌላ በኩል ከሳሽ በጉልበትና በገንዘብ ከሟች ጋር ባፈሩት ጥሪት ቤቱ መገዛቱን አላስረዱም። ተከሳሽዋ ግን ቤቱን ከሟች ጋር ማፍራታቸውንና ሲጠቀሙበት እንደነበረ ከከሳሽ በላይ እንዳስረዱ መዝገብ ግልባጩ አስፍሯል። ስለሆነም በተካሄደው ምርመራ ቤቱ ከግማሹ
ድርሻ ወይም መብት ያለው ተከሳሽ አንኳ ተከሳሽ ወይዘሮ ገነት እንጂ ከሳሽዋ አይደሉም ሲል የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ መስጠቱ በሰነዱ ይነበባል። በዚህም ከሳሽ ወይዘሮ ግዜወርቅ በቤቱ ላይ መብት የላቸውም በማለት ክሳቸው ውድቅ መደረጉን ትዕዛዝ ያስተላልፋል። በተያያዘ ከሳሽና ተከሳሽ ከሟች የወለዷቸው ልጆች የሟችን ንብረት የሚደርሳቸው ድርሻ አጣርተው በመለየት በውርስ ሕግ መሠረት የመካፈል መብት እንዳላቸው ትዕዛዝ ማሳረፉን ሰነዱ ያስነብባል።
የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፍትሐብሔር ችሎት በመዝገብ ቁጥር 266745 በ4/4/2010 ዓ.ም መዝገብ ግልባጭ፤ ይግባኝ ባዮች እነ ወይዘሮ ግዜወርቅ መልስ ሰጪ ደግሞ ወይዘሮ ገነት መሆናቸውን ያሳያል። መዝገቡ ተከፍቶ ለችሎት ሊቀርብ የቻለው የውርስ ሀብትን በተደረገ ክርክር የቀረበውን አቤቱታ በማየት የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ በመቃወም በ30/12/2009 በቀረበ ይግባኝ መነሻ እንደሆነም ያብራራል።
ይግባኝ ባዮች ወይም የስር ከሣሾች በ23/3/2009 ዓ.ም በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባቀረቡት ማመልከቻ የመልስ ሰጪ ባለቤታቸውና የልጆቻቸው አባት የሆኑት አቶ ወርቁ በ15/5/2008 ዓ.ም ሕይወታቸው ስላለፈ በሰበታ ከተማ ውስጥ የሚገኝ 11 ክፍል ቤት ቁጥሩ 764 የሆነ እና በ347 ሜትር ካሬ መሬት ላይ የሚገኘውን በግምት ብር 300 ሺህ የሚያወጣ አንደኛ ይግባኝ ባይ ወይዘሮ ግዜወርቅ ከሟች ጋር አፍርተው ግማሹ የሚስትነት ድርሻ ሲሆን፤ ቀሪው ደግሞ የሟች ልጆች ድርሻ ስለሆነ መልስ ሰጪ ወይዘሮ ገነት ከሕግ ውጪ ከያዙት ውስጥ ሰባት ክፍል ቤት እያንዳንዱን በወር ብር 400 እያከራዩ ስለሚጠቀሙ የቤቱን ኪራይ ሟች ከሞተ ጊዜ አንስቶ እያከራዩ የቆዩትን በአንድ ላይ 30 ሺህ 800 ብር በመክፈል ቤቱን ለቀው በቀበሌው አስተዳደር በኩል የባለቤትነት ማረጋገጫው በሥማቸው እንዲዞር እነ ወይዘሮ ግዜወርቅ ክስ ማቅረባቸውን መዝገቡ ያስታውሳል። .
ተከሣሽ በ11/4/2009 ዓ.ም በሰጡት ምላሽ፤ ቤቱን ከሟች ባለቤታቸው ጋር በ1977 ዓ.ም ከተገናኙ በኋላ መስከረም 25 ቀን 1982 ዓ.ም ከአቶ አባዝናብና ወይዘሮ ሲቲና ላይ ገዝተው በዘሁ ቤት አምስት የሟች ልጆችን እንዳፈሩ እንዳስረዱ ሰነዱ ያስረዳል። በዚህም አንደኛ ይግባኝ ባይ ወይም ከሣሽ መብት የላቸውም፣ ከሣሽ የሟች ባለቤት አይደሉም፣ የሟች ባለቤት ቢሆኑ ወይዘሮ ገነት ከሟች ጋር 30 ዓመት አብረው ሲኖሩ ወይዘሮ ግዜወርቅ ፍቺ አይጠይቁም ነበር ወይ? በሚል ምላሽ መስጠታቸውን አስፍሯል።
ከሣሽ ወይዘሮ ግዜወርቅ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ጉራጌ ዞን ችሃ ወረዳ እንጂ ሰበታ ከተማ እንዳልኖሩም በምላሻቸው ለፍርድ ቤቱ ማሳወቃቸው በሰነዱ ይነበባል። የሟች ልጆችም ከሣሽ ያቀረቧቸው ብቻ እንዳልሆኑና የእርሳቸው ልጆች የወራሽነት መብት እንዲጠበቅላቸው ያነሳሉ። ለክርክሩ መነሻ የሆነው ቤትም የሚኖሩበት እንጂ አከራይተው የሚጠቀሙበት ከባለቤታቸው ጋር ከ20 ዓመት በፊት ለፍተው ካፈሩት ሀብት ላይ መብት ስለሌላቸው ውድቅ እንዲደረግ መጠየቃቸውን ያሳያል።
የስር ፍርድ ቤትም ከሣሽ ወይዘሮ ግዜወርቅ የሟች ባለቤት መሆናቸውን በሰነድና በሠው ማስረጃ ቢያስመሰክሩም ነዋሪነታቸውን ያደረጉት ግን በደቡብብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በመሆኑ በ1988 ዓ.ም ጀምሮ ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ይዞታ ተጠቅመውበት እንደማያውቁ ከሟች ጋርም ያላፈሩት መሆኑ ስላረጋገጡ ከንብረቶቹ ውስጥ የባለቤትነት ድርሻ ያላቸው ተከሣሽ ወይዘሮ ገነት እንጂ ከሣሽ መብት የላቸውም በማለት በመዝገብ ቁጥር 28070 ላይ በ3/11/2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት ፍርድ ሰጥቷል።
በዚህ ችሎት ይግባኝ ባዮች ወይም የስር ከሣሽም የስር ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ይግባኛቸውን በቀን 30/12/2009 ዓ.ም ማቅረባቸውን ሰነዱ ያትታል። ከሟች ጋር በ1970 ጋብቻ ፈጽመው ሆቴል ቤት ውስጥ በመነገድ ባገኙት ገቢ በ1983 ዓ.ም ቤቱን መግዛታቸውን ማስረዳታቸውን አስፍሯል። መልስ ሰጪ ደግሞ የሆቴሉ ሠራተኛ ሆነው የተቀጠሩ እንጂ በባልና ሚስትነት ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ቤት አለማፍራታችውን በምስክር ተረጋግጦ ከሟች ባለቤታቸው ጋር ባፈሩት ንብረት ላይ መብት የላቸውም በማለት የስር ፍርድ ቤት የሰጠው ፍርድ ስህተት ነው ተብሎ እንዲሰረዝላቸው መጠየቃቸው በሰነዱ ይታያል ።
የመልስ ሰጪ ምስክር ከአቶ ወርቁ ጋር መቼ እንደተጋቡ እንደማያውቁና ጋብቻ መፈፀም አለመፈፀማቸውን እንደማያውቁ መስክረው ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ንብረት አብረው ማፍራታቸውን በማስረጃ ሳያረጋግጡ ከሟች ጋር በገንዘባቸው መግዛታቸው ተረጋግጦ ሳለ መብት የላቸውም በማለት የተሰጠው ፍርድ ውድቅ ተደርጎ መልስ ሰጪ ከየካቲት ወር 2008 ዓ.ም ጀምሮ ቤቱን የያዙባቸው መሆኑና በገንዘባቸው የገዙት መሆኑ የተረጋገጠ ነገር ሳይኖር የስር ፍርድ ቤት የሰጠው ፍርድ ትክክል አይደለም ተብሎ እንዲሻር ሲሉ ፍርድ ቤቱን መጠየቃቸው መዝገብ ግልባጩ ያስነብባል።
የመልስ ሰጪ ልጆች በጋብቻ ውስጥ ስለመፀነሳቸው በማስረጃ ሳይረጋገጥ የይግባኝ ባዮችን ድርሻ የማግኘት መብት በሚያሳጣ መልኩ የተሰጠ ውሳኔ ስህተት ስለሆነ መልስ ሰጪ ለክርክሩ መነሻ በሆነው ቤት ላይ መብት የላቸውም ተብሎ የሚስትነትና ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ላሉት ይግባኝ ባዮች ወይንም የሟች ልጆች ንብረቱን ለቀው የተጠቀሙበትን እንዲከፍሏቸው በማለት የይግባኝ ቅሬታ ማቅረባቸውን ያብራራል። ፍርድ ቤቱም የቀረበውን ይግባኝ ተቀብሎ በመመልከት ወራሾች ድርሻቸውን ማግኘት የለባቸውም ወይ? የሚለውን ነጥብ ለማጣራት መዝገቡን አስቀርቦ ግራና ቀኙን በቃል እንዳከራከረ ያትታል። የይግባኝ ባዮች ጠበቃ ሐሳቡን አጠናክሮ ያቀረበ ሲሆን፤ መልስ ሰጪ ጠበቃ በበኩሉ ባሰማው የቃል ክርክር ወይዘሮ ገነት በቤቱ ውስጥ እየኖሩ የነበሩ መሆናቸው ጠቅሶ ይግባኝ ባይ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ቸሃ ወረዳ ውስጥ ንብረት እያላቸው መብት በሌላቸው ቤት ላይ አቶ ወርቁ ሕይወታቸው ሲያልፍ ከብዙ ዓመታት በኋላ በ2008 ዓ.ም በመምጣት መጠየቃቸው አግባብ እንዳልሆነ መሟገታቸውን ሰነዱ ያሳያል። በመሆኑም የስር ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ ትክክል ስለሆነ እንዲፀና ጠይቀዋል።
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ካደመጠ በኋላ አንደኛ ይግባኝ ባይ የሟች ባለቤት መሆንዋ በምስክር የተረጋገጠ ሲሆን፤ ለክርክሩ መነሻ ከሆነው ቤት ላይ መብት የላቸውም በማለት የተሰጠው ፍርድ ትክክል ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ሐሳብ እንደጭብጥ በመያዝ የቀረበውን ይግባኝ፣ በፍርድ ቤቱ የተካሄደውን የቃል ክርክር እንዲሁም የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሣኔ በማገናዘብ መዝገቡን እንደመረመረ ሰነዱ ያስረዳል። በዚህም ከመዝገቡ መረዳት እንደሚቻለው አንደኛ ይግባኝ ባይና ሟች አቶ ወርቁ በጋብቻ ውስጥ አምስት ልጆች ወልደው ጋብቻቸው ፀንቶ ሟች ሕይወታቸው እስካለፈበት ዕለት ድረስ የቆየ መሆኑን በማስረጃ እንደተረጋገጠ ያትታል። ቤቱ ውስጥም አብረው ሲኖሩ እንደነበረና ይግባኝ ባይ ወደ ገጠር ሲሄዱ እንደያዙት መስክረዋል። በሌላ በኩል ደግሞ መልስ ሰጪ በማንኛውም የጋብቻ ስርዓት ከሟች ጋር ጋብቻ መፈፀማቸው አልተረጋገጠም።
ለክርክሩ መነሻ የሆነውን መልስ ሰጪና ሟች ብቻ አብረው ያፈሩት መሆኑ እንዳልተረጋገጠ መዝገብ ግልባጩ ያብራራል። እንዲሁም ቤቱ መጀመሪያ የተገዛው ከንግድ ሥራ ሻይ ቤት አንደኛ ይግባኝ ባይና ሟች በባልና ሚስትነት አብረው እያሉ የተገዛ ሲሆን፤ መልስ ሰጪ በወቅቱ ሠራተኛ ቢሆኑም በኋላ ግን ከሟች ጋር እንደ ባልና ሚስት አብረው ሲኖሩ በቤቱ ላይ ክፍል ጨምረው መሥራታቸው ተረጋግጧልም ይላል። እንዲህ ከሆነ የይግባኝ ባይ ጠበቃ እንደተከራከሩት መልስ ሰጪ በቤቱ ላይ መብት የላቸውም የሚያስብል አይደለም በማለት ሐሳቡን ውድቅ ያደርገዋል። በተጨማሪም የስር ፍርድ ቤት እንደወሰነው ይግባኝ ባይ የሚስትነታቸውን ድርሻ ለክርክሩ መነሻ ከሆነው ቤት ላይ የላቸውም የሚያስብልም አይደለም።
በአጠቃላይ ለክርክሩ መነሻ የሆነው ቤት በፊት ይግባኝ ባይና ሟች በትዳር እያሉ ተገዝቶ መልስ ሰጪ ከሟች ጋር እንደ ባልና ሚስት አብረው ሲኖሩ ተጨምሮ የተሠራ ስለሆነ ይግባኝ ባይ ከሟች ጋር በጋብቻ ሲኖሩና ሟችና መልስ ሰጪ እንደ ባልና ሚስት አብረው ሲኖሩ ያፈሩት ስለሆነ የይግባኝ ባይ የመልስ ሰጪና የሟች የጋራ ሀብት መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ ያብራራል። በዚህም በቤቱ ላይ እኩል መብት አላቸው። ክፍፍሉ ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ሦስተኛ ድርሻቸው መሆን ሲገባው በዚህ ችሎት ይግባኝ ባይ መብት የላቸውም በማለት የስር ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ ስህተት ያለበት ነው ይላል። የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 28070 ላይ በቀን 38/11/2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠው ፍርድ መሻሩንና የቤቱ አንድ ሦስተኛ ይግባኝ ባይ፣ አንድ ሦስተኛ መልስ ሰጪ ድርሻቸውን ከወሰዱ በኋላ የቀረውን አንድ ሦስተኛ ደግሞ የሟች 10 ልጆች እኩል በዓይነት እንዲካፈሉ መወሰኑን መዝገቡ ያሳያል። መግባባት ካልቻሉም አቅም ያለው ወገን ግምቱን በመክፈል እንዲያስቀር በዚህም ካልተስማሙ ደግሞ ቤቱ በጨረታ ተሽጦ ገንዘቡን እንዲካፈሉ ትዕዛዙን ማስተላለፉን ሰነዱ ያሳያል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር መዝገብ ቁጥር 158956 በቀን 25/10/2010 ዓ.ም አመልካቾች እነ ወይዘሮ ገነት ተጠሪዎች ደግሞ እነ ወይዘሮ ግዜወርቅ መሆናቸውን አስፍሯል። ለችሎቱ በቀን 23/9/2010 ዓ.ም በተፃፈ አቤቱታ በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 279907 በ11/07/2010 ዓ.ም የተሰጠ ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት አለበት በማለት ጉዳዩ በሰበር እንዲታይ ማመልከቻ መቅረቡን ያሳያል። በቀረበው ጉዳይ ላይም መሠረታዊ የሕግ ስህተት ተሠርቷል ለማለት አልተቻለም። መዝገቡም ለሰበር አይቀርብም በሚል መወሰኑን አስፍሯል።
በመዝገብ ቁጥር 310227 በቀን 06/09/2011 ዓ.ም ጉዳዩ በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቀርቦ እንደነበር የመዝገብ ግልባጩ ያመላክታል። በሰነዱ እነ ዮሴፍ ወርቁ አመልካቾች ተጠሪዎች ደግሞ እነ ግዜወርቅ መሆናቸው ይነበባል። ችሎቱ መዝገቡን መርምሮ ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን፤ ጥያቄው ለሰበር ሊቀርብ የቻለበትን ምክንያትም ያስረዳል። በዚህም የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መካከለኛ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 266745 በቀን 24/08/2011 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠው ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት አለበት በማለት ፍርዱ እንዲስተካክል በቀን 03/09/2011 ማመልከቻ መቅረቡን ያትታል።
አንድ ጉዳይ ለሰበር ችሎት ሊቀርብ የሚችለው ቅሬታ የቀረበበት ፍርድ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ካለው ብቻ በመሆኑ አቤቱታውን መነሻ በማድረግ በስር ፍርድ ቤቶች ከተሰጡት ፍርዶች ጋር ምርመራ ተደርጓል። በዚህም በጉዳዩ ላይ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል ለማለት የሚያስችል ነጥብ አልተገኘም። መዝገቡም ለሰበር ችሎት አይቀርብም በሚል መወሰኑን መዝገብ ግልባጩ ያስረዳል።
የመዝገብ ቁጥር 266745 በቀን 24/08/2011 ዓ.ም የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መዝገቡን መርምሮ የሰጠውን ፍርድ የሚያሳይ መዝገብ ነው። በሰነዱ እነ ወይዘሮ ግዜወርቅ ይግባኝ ባይ ሆነው መቅረባቸውንና እነ ወይዘሮ ገነት ደግሞ መልስ ሰጪ እንደነበሩ ተመላክቷል። ለፍርድ መነሻ አመልካቾት በቀን 6/3/2011 ዓ.ም ባቀረቡት ይግባኝ በተደረገው ክርክር በዚሁ መዝገብ ቁጥር በፍርድ ቤቱ የተሰጠው ፍርድ ሳያውቁ ጥቅማቸውን የሚነካ በመሆኑ ፍርዱ ተሽሮ ወደ ክርክሩ ገብተው እንዲከራከሩ መጠየቃቸው ሰፍሯል።
ይግባኝ ባዮች ለፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በወይዘሮ ገነት ላይ ባቀረቡት አቤቱታ የአንደኛ ይግባኝ ባይ ወይም ወይዘሮ ጊዜወርቅ ባለቤትና በመዝገብ ግልባጩ ከሁለተኛ እስከ አራተኛ የተቀመጡት አባት አቶ ወርቁ በ2008 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን በመግለጽ፤ በሰበታ ከተማ ቀበሌ 01 ውስጥ የሚገኝ 374 ሜትር ካሬ ላይ ሰፍሮ የሚገኝ መኖሪያ ቤት ተከሣሿ /ወይዘሮ ገነት/ የአንደኛ ይግባኝ ባይ የሟች ባለቤት /ወይዘሮ ግዜወርቅ/ ወይም ልጆቻቸው አባት ከሞቱ በኋላ ከሕግ አግባብ ውጪ በመያዝ ለግል ጥቅም ማዋላቸውን ያብራራል።
ወይዘሮ ገነት፤ ያለአግባብ ከያዙት መኖሪያ ቤት ውስጥ አራት ክፍሉን እየኖሩበት ሰባቱን ክፍል ደግሞ አከራይተው እየተጠቀሙበት በመሆኑ ቤቱን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ ያለው የቤት ኪራይ ብር 30 ሺህ 800 እንዲከፍሉ መጠየቃቸውን መዝገቡ ያስረዳል። በዚህም ክርክር ካስነሳው ቤት ውስጥ ግማሹ ይግባኝ ባይ የሆኑት ወይዘሮ ግዜወርቅ የሟች ባለቤት በመሆናቸው ግማሹ የሟች ድርሻ ደግሞ ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ያሉት ወራሽ ልጆች ስለሆነ ቤቱን እንዲለቁ በማለት ጠይቀው እንደነበር ሰነዱ ያሳያል።
በችሎቱ መልስ ሰጪ የነበሩት ወይዘሮ ገነት በሰጡት ምላሽ፤ ከአቶ ወርቁ ጋር በ1977 ዓ.ም መገናኘታቸውን እንዳቀረቡ ሰነዱ ያሳያል። ከተገናኙ በኋላ ክርክር ያስነሳውን ቤት በግዥና ሽያጭ ውል በ25/12/1982 አቶ አባዝናብ ሸሪፍና ወይዘሮ ሲቲና መሐመድ ከተባሉ ሠዎች መግዛታቸውንም ይገልፃሉ። በዚሁ ቤት ውስጥ ከሟች ጋር አምስት ልጆች አፍርተው ይኖሩ እንደነበር መልስ ሰጥተው እንደነበር ያትታል።
ይግባኝ ባይ ወይንም ወይዘሮ ግዜወርቅ በቤቱ ላይ ምንም መብት የላቸውም በማለት፤ ነዋሪነታቸውም በደቡብብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ጉራጌ ዞን መሆኑን ለችሎቱ ማቅረባቸውን ሰነዱ ያስነብባል። ክርክር በሚደረግበት ቤት ላይም ተጠቅመው እንደማያውቁና ከሟች ጋር ቤቱን እንዳላፈሩ የሟች ወራሾችም ተከሣሽ ያቀረቧቸው ልጆች ብቻ ሳይሆኑ የልጆቻቸው የወራሽነት መብት እንዲጠበቅላቸው መጠየቃቸው በሰነዱ ይነበባል።
ከፍተኛው ፍርድ ቤትም ግራ ቀኙን ካከራከረ በኋላ ጉዳዮን በግራ ቀኙ ምስክሮች በማጣራት ወይዘሮ ግዜወርቅ /የስር ከሣሽ/ ክርክር ባስነሳው ቤት ተጠቅመው የማያውቁ መሆናቸውን ከሟች ጋርም ማፍራታቸው ያልተረጋገጠ በማለት ያቀረቡትን የባለቤትነት ድርሻ ተቀባይነት የለውም በማለት ፍርድ ሰጥቶ እንደነበር መዝገብ ግልባጩ ያብራራል። በከፍተኛ ፍርድ ቤት የተሰጠውን ፍርድ በመቃወም እነ ወይዘሮ ግዜወርቅ ቅሬታቸውን ያቀረቡ ሲሆን፤ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቅሬታቸውን ካከራከረ በኋላ በቀን 4/04/2011 ዓ.ም በዋለው ችሎት ጉዳዩን ተመልክቷል።
የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክርክር ያስነሳው ቤት ወይዘሮ ግዜወርቅ ከሟች ጋር በትዳር እያሉ በተገኘ ገቢ መገዛቱን፣ ከተገዛ በኋላ ወይዘሮ ገነትና ሟች እንደ ባልና ሚስት አብሮ ሲኖሩ የተጨመረበት ቤት መኖሩን በመግለጽ ሁለቱም የባለቤትነት ድርሻ እንዳላቸው በመግለጽ፤ የቤቱ አንድ ሦስተኛ የይግባኝ ባይ የወይዘሮ ግዜወርቅ ድርሻ አንድ ሦስተኛ የመልስ ሰጭ ወይዘሮ ገነት የሚስትነት ድርሻ የቀረው አንድ ሦስተኛ ደግሞ የሟች ድርሻ ሆኖ ይግባኝ ባይ ከሟች የወለዱት አምስት ልጆችና መልስ ሰጪ የወለዱት አምስት ልጆች ባጠቃላይ ወራሾች 10 ሠዎች የሟችን ድርሻ እንዲካፈሉ በማለት የይግባኝ ባይ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ አሻሽሎ ፍርድ ሰጥቷል።
እነ ወይዘሮ ገነት፤ የተሰጠው ፍርድ ጥቅማቸውን የሚጎዳ ስለሆነ ፍርዱ ተሽሮ ወደ ክርክር ለመግባት ማመልከቻ ማቅረባቸውን ሰነዱ ያሳያል። የመቃወሚያው ይዘትም ወይዘሮ ግዜወርቅ ወይንም አንደኛ ይግባኝ ባይ ፍርድ የተሰጠበት ቤት ላይ ምንም ዓይነት መብት ሳይኖራቸው የሚስትነት ድርሻ አንድ ሦስተኛ አንዲካፈሉ መወሰኑ አግባብ አለመሆኑን፣ በሰበታ ከተማ በሟች አባታቸው ሥም ተይዞ የሚገኘውን የንግድ ቤት በወይዘሮ ግዜወርቅ እጅ ያለ ስለሆነና ሌሎች ንብረቶችም በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ ንብረቱ ተጣርቶ ፍርድ መሰጠት ስላለበት ክርክር ባስነሳው ቤት ላይ ብቻ ፍርድ መሰጠቱ ስህተት ስለሆነ ወደ ክርክሩ ጉበተው መብታቸውን ለማስከበር በሚል በማመልከቻ መጠየቃቸውን መዝገብ ግልባጩ ያብራራል።
ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን የሠው ምስክር እንዲያቀርቡ በማዘዝ ሰምቷል። የመልስ ሰጭ ምስክሮች ክርክር ያስነሳውን ቤት ሟች ከወይዘሮ ገነት ጋር ገዝተው እየኖሩበት የነበረ መሆኑን ተናግረዋል። በሌላ በኩል የይግባኝ ባይ ምስክሮች በበኩላቸው ወይዘሮ ግዜወርቅና ሟች በ1970 ዓ.ም በሰርግ መጋባታቸውን ብሎም ክርክር ያስነሳውን ቤት በ1983 ዓ.ም መግዛታቸውን በመግለጽ፤ ቤቱ ሲገዛ ወይዘሮ ገነት የሟችና የአንደኛ ይግባኝ ባይ ቤት ሠራተኛ መሆናቸውን ቀርበው መስክረዋል።
የመዝገብ ግልባጩ፤ የጉዳዩን አመጣጥ ክርክር ባስነሳው ቤት ላይ ቀድሞ የተሰጠውን ፍርድ ጭብጦች ከነበረው ክርክር ጋር በማገናዝብ መመርመሩን ያትታል። በዚህም ቤቱ ላይ ወይዘሮ ግዜወርቅ መብት ሳይኖራቸው የሚስትነት አንድ ሦስተኛ ድርሻቸውን ይውሰዱ መባሉ አግባብ አይደለም የሚል ሆኖ አንደኛ ይግባኝ ባይ ከአመልካቾች አባት ጋር ጋብቻ ፈጽመው ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ አብረው መኖራቸው አላከራከረም ይላል። በዚህም ሰበታ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የመኖሪያ ቤት ሟችና ይግባኝ ባይ ጋብቻ ፀንቶ ባለበት ጊዜ መገዛቱ በምስክር ቃል ተረጋግጧል። በሌላ በኩል ተቃዋሚዎችም ወይዘሮ ግዜወርቅ ቤቱን አስመሥልክቶ ምንም አስተዋፅዖ የላቸውም ከማለት ባለፈ ወይዘሮ ገነትና ሟች ብቻ ማፍራታቸውን የሚገልጽ ነገር የለም። ይህ ከሆነ ደግሞ በአንደኛ ይግባኝ ባይ ጋብቻ ውስጥ የተፈራው ንብረት የመልስ ሰጪና የሟች የግል ንብረት ነው የሚያስብል ነገር የለም በማለት ያብራራል። ስለሆነም በኦሮሚያ የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 78/1/ እና 79 መሠረት የአንደኛ ይግባኝ ባይ የጋራ ንብረት መልስ ሰጭና የሟች ነው መባሉ ጉድለት ያለበት አይደለም። በሌላ መንገድ ሟች ከሁለቱም ሴቶች 10 ልጆች መውለዳቸው በምስክር ተረጋግጧል። ፍርድ ቤቱም የሟች አንድ ሦስተኛ ድርሻ ለወራሾች እንዲካፈል በማለት የሰጠው ፍርድ የተቃዋሚዎች መብት ተነክቷል የማያስብል በመሆኑ የቀረበው መቃወሚያ ተቀባይነት ያለው ሆኖ እንዳልተገኘም አስፍሯል።
ሌላው በግራ ቀኙ ክርክር ወቅት የተነሳው ጭብጥ ፍርድ ያላረፈበት ንብረት ላይ ተቃዋሚዎች ያቀረቡት መቃወሚያ የሕግ ድጋፍ አለው ወይስ የለውም? የሚለውን በተመለከተ የመቃወሚያ አቤቱታቸው ሌላ የውርስ ሀብት እያለ በሰበታ ከተማ በሚገኘው መኖሪያ ቤት ላይ ብቻ ፍርድ መሰጠቱ አግባብ አይደለም የሚለውን በተመለከተ መጀመሪያውኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 358 መሠረት የመቃወም አቤቱታ በፍርድ ላይ የሚቀርበው ፍርድ ባገኘ ጉዳይ ላይ እንደሆነ ይታወቃል። ፍርድ ቤቱም በተጠየቀው ዳኝነት ላይ ብቻ ነው ፍርድ የሚያስተላልፈው እንጂ የንግድ ቤቱንና ሌሎች በአንደኛ ይግባኝ ባይ እጅ የሚገኝ የዚህ መዝገብ አካል ስላልሆነ የመልስ ሰጪ አመልካቾች ያነሱት አቤቱታ ተቀባይነት እንደሌለው ያብራራል። በዚህም አመልካቾች ያቀረቡት አቤቱታ ውድቅ መደረጉንና በቀን 4/04/2010 ዓ.ም በዋለው ችሎት በዚህ መዝገብ ላይ የሰጠው ፍርድ መጽናቱን ትዕዛዝ እንዳስተላለፈ መዝገቡ ያሳያል።
በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር መዝገብ ቁጥር 177469 አመልካቾች እነ ዮሴፍ ወርቁ ማለትም የወይዘሮ ገነትና የሟች ልጆች እንዲሁም ተጠሪዎች ደግሞ እነ ወይዘሮ ግዜሽወርቅ መሆናቸው ይታያል። መዝገቡ ግንቦት 13 ቀን 2011 ዓ.ም በተፃፈ ቃለ መሃላ መነሻነት ቀርቦ መመርመሩንና የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 312227 በቀን 06/09/2011 ዓ.ም የተሰጠ ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት አለበት በማለት ጉዳዩ በሰበር እንዲታይ ማመልከቻ ቀርቧል። ችሎቱም በየደረጃው በየፍርድ ቤቶቹ የተደረጉትን ክርክሮችና ውሳኔዎች አግባብ ካለው ሕግ ጋር መርምሯል። ይሁን እንጂ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ተሠርቷል ለማለት እንዳልተቻለ በመግለጽ መዝገቡ ለሰበር ችሎት አይቀርብም በሚል እንደዘጋው ሰነዱ ያመለክታል።
ሌላው ወገን
የክርክር መነሻ በሆነው ቤት ላይ ሌላኛው ተከራካሪ የሆኑት እነ ወይዘሮ ግዜሽወርቅ ኃይሌን ለማነጋገር አቀናን። ሆኖም ሁለተኛ ልጃቸው ወጣት አበበ ወርቁን ነው ለማግኘት የቻልነው። እናቱ በሕመም ምክንያት ፀበል እንደገቡ ነግሮን፤ ስለቤቱ የሚያውቀውን አስረድቶናል።
እንደ አበበ ገለፃ፤ እናቱ ወይዘሮ ግዜሽወርቅ የአባቱ አቶ ወርቁ የመጀመሪያ ሚስት በመሆናቸው ክርክር ሲደረግበት የነበረውን ቤት አብረው ነው ያፈሩት። ሆኖም አባታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ በቤቱ ላይ ክርክር ተደርጓል። ጉዳዩ ፍርድ ቤት ከመድረሱ በፊት በሽምግልና እንዲያልቅ ቢጠየቅም ወይዘሮ ገነት ግን ፈቃደኛ አልነበሩም። የመጨረሻው የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ቤቱ በሐራጅ ተሸጦ እንዲካፈሉ ተወስኗል። ይህም የሟችን ሁለቱንም ቤተሰቦች ከግምት ውስጥ ያስገባ ቢሆንም፤ ከንብረቱ በላይ ግን የአባቶቻቸው ልጆች ዝምድናና ወዳጅነት እንደሚበልጥባቸው ነው የሚናገረው።
አስተዳደሩ
በሰበታ ከተማ የቀበሌ 01 አስተዳደር ሊቀመንበር አቶ ብዙአየሁ በቀለ፤ ጉዳዩን እንደሚያውቁት ይናገራሉ። ቅሬታ አቅራቢዋ ሲመላለሱ እንደነበር በማስታወስ፤ ከሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ጋርም እንደተወያዩበት ይገልፃሉ። ባለቤታቸው ሲያርፉ የመጀመሪያ ሚስታቸው እንደመጡና በወይዘሮ ገነት ሥም የነበረ ማሕደር ጠፍቶ ሌላ ማሕደር እንደተከፈተ ቅሬታ እንደቀረበም ይገልፃሉ። አስተዳደሩም ጉዳዩን ለማጥራት ጥረት አድርጓል። ሆኖም ግን የማሕደሮች አቀማመጥ ለዚህ መሠል ችግሮችና ብልሹ ሥራዎች በር ከፋች በመሆናቸው ችግሩን የፈጠረውን አካል ይዞ ተጠያቂ ለማድረግ አልተቻለም ይላሉ።
ጉዳዩ ፍርድ ቤት ሲደርስ አስተዳደሩ የማያውቅ በመሆኑ እንጂ የአካባቢው የቀበሌ ማኅበረሰብ ሸንጎ አባላት በወይዘሮ ገነት ሥም ማህደር እንደነበር እንደሚያውቁ እንደገለፁላቸው ያስታውሳሉ። ነገር ግን ማህደሩ እንዴት እንደሆነ ባልታወቀ ሁኔታ እንዲጠፋ ተደርጓል። የመዝገብ ቤት ሠራተኛዋም ለወሊድ ፍቃድ በወጣችበት ወቅት ካልጠፋ በስተቀር ማህደሩ እንደነበረ መናገሯንም ይገልፃሉ። ማህደሩ በደንብ ቢፈለግም እንኳ ሳይገኝ መቅረቱ ሆነ ተብሎ የተፈፀመ እንደሆነም ያመለክታል ይላሉ።
በየቀኑ ወደ ቢሯቸው እያቀኑ ስለሚያለቅሱም አስተዳደሩ የሚችለውን ለመደገፍ ጥረት አድርጓል። በዚህም በኢኮኖሚ አቅማቸው ደካማ በመሆናቸው ለሰበታ ከተማ ፍትሕ ቢሮ በመጻፍ ነፃ ጥብቅና የሚቆምላቸው የሕግ ባለሞያ እንዲያገኙ ተደርጓል። በአሁኑ ወቅት ግን ፍርድ ቤት ውሳኔ በማሳረፉ አስተዳደሩ ጣልቃ ገብቶ ሊያደርግ የሚችለው ነገር የለም። ሆኖም ግን የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አጣሪ ጉባዔ ጉዳያቸውን ተመልክቶ መፍትሔ ከሰጣቸው በሚል የትብብር ደብዳቤ እንደላኩላቸውም ይናገራሉ። በቀጣይም መፍትሔ እንዲያገኙ ወይዘሮ ገነትን ለመርዳት አስተዳደሩ ዝግጁ እንደሆነ ያመላክታሉ።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጳጉሜ 6/2011
ፍዮሪ ተወልደ