ህግ፣ ደካማው እንዳይሰጋ፤ ብርቱው ደግሞ እንዳይታበይ የሚያደርግ ከለላ ነው። ዜጎች ከአቅማቸው በላይ የሆኑ ሰዎች ሲያስቸግሯቸውና እንደማይቋቋሟቸውም ሲረዱ ‹‹በህግ አምላክ›› ሲሉ ህግን ጥላ ከለላ በማድረግ ድምፃቸውን ያሰማሉ፤ ብሎም ለሚመለከተው አካል ህግን መሰረት አድርገው ቅሬታቸውን ያቀርባሉ። በሁለት በተጋጩ ግለሰቦች መካከል ስለተፈጠረውም ጉዳይ በህግ ይጣራል፤ በህግም ውሳኔ ይሰጣል።
ህግ ካለና የሚከበር ከሆነ ሰዎች በየትኛውም ስፍራ ተንቀሳቅሰው የእለት ጉዳያቸውን መከወን ይችላሉ። በሰላም ወጥቶ መግባት፣ ዘርቶ ማጨድ፣ ነግዶ ማተርፍና ተምሮ መመረቅ የሚቻለውም ህግ ሲኖርና ሲከበር ብቻ ነው! ህግ ባለበትና በሚከበርበት አገር በሰላም ወጥቶ ለመግባት አንዳች የሚያሰጋ ነገር አይኖርም። የህግ የበላይነት ሲረጋገጥ ዜጎች ያለስጋት መስራትና የልፋታቸውንም ፍሬ ማጣጣምም ይችላሉ።
ይሁንና አንዳንዴ ይህ ቀረሽ የማይባል ህግ ወጥቶ ተግባራዊ በማድረጉ በኩል በሚኖር ቸልተኝነት ብቻ ዜጎች ሲጎዱ ይስተዋላል። አንዳንዴም ደግሞ የወጡ ህጎች ነፃ ከማድረግ አሊያም ፍትህ ከማስገኘት በተቃራኒ መልሰው አሳሪና አሸማቃቂ ሲሆኑም ይታያሉ። አገርም እንደ አገር በልማት ጎዳና ላይ እንዳትሆን አንቀው የሚይዟት ህጎችም ይኖራሉ።
እንዲህ አይነቱ ችግር ሲያጋጥም ደግሞ አላሰራ እያለ ማነቆ የሚሆነውን ህግ፣ ሊያሰራ በሚችል መቀየር አግባብነት ያለው ተግባር ነው። እንደሚታወቀው ለዜጎች የተሻለች አገርን ለመፍጠር ያስችላት ዘንድ አገራችን ኢትዮጵያ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ብቻ በርካታ ህጎች እንዲሻሻሉ አድርጋለች።
ይህንንም ስታደርግ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል የተውጣጣና በተለይ ደግሞ ከሙያ ዘርፉ በእውቀታቸውም ሆነ በስነ ምግባራቸው እንዲሁም በልምዳቸው የተሻሉ የሚባሉ 13 አባላት ያሉት በጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ስር ያለ አማካሪ ጉባኤ በማቋቋም ነው። በዚህ አማካሪ ጉባኤ ስር ደግሞ ከመንግስት ውጭ የሆኑ ከመቶ በላይ የህግ ባለሙያዎች ተሰባስበው ህጎችን በማሻሻል ሂደት ውስጥ ተሳትፈዋል።
ከተሻሻሉ በርካታ ህጎች መካከልም የንግድ ህግ፣ የፀረ ሽብር፣ የበጎ አድራጎት፣ የምርጫ፣ የጥላቻ ንግግር እና ሌሎች የሚጠቀሱ ሲሆን፣ ይህም መልካም ነገር ነው። ይሁንና የተለያዩ ህጎች በመውጣታቸው ብቻ ግን ህጉን ጥሩ ህግ ነው ሊያሰኙት አይችሉም። ዋናው ነገር መሻሻሉ ሳይሆን ተግባራዊ መደረጉ ላይ ነው።
ለተግባራዊነቱ ደግሞ ከአንድ ወገን የሚደረግ እንቅስቃሴ መጠበቅ የለበትም። ተግባራዊነቱን የሚያረጋግጡት የፍትህ አካላት ናቸው ተብሎም ወደእነርሱ ብቻ መግፋትም ተገቢ አይደለም። ምክንያቱም የህግ የበላይነት መረጋገጥ ለሁሉም ዜጋ ወሳኙ ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም ለተግባራዊነቱ ቁርጠኛ ሊሆን ግድ ይላልና።
በዛሬው ቀን ‹‹እኔ ለህግ ተገዢ ነኝ›› በሚል መሪ ሐሳብ የፍትህ ቀን ይከበራል። የወጡ ህጎች ያለምንም መሸራረፍ ሊተገበሩ የሚገባውና የሕግ የበላይነት ሊረጋገጥ የሚችለው ልክ እንደ ዘንድሮው መሪ ቃል ሁላችንም ለተቀረፀው ህግ ተገዢዎች መሆን ስንችልና ለተግባራዊነቱም ስንታትር ብቻ ነው።
ለህግ ተገዢዎች የምንሆነው ደግሞ ሰዎች አዩኝ አላዩኝ በሚል ይሉኝታ ሳይሆን ለህሊናችን በመታመን ሊሆን ይገባል። የፍትህ ቀንም በዓመት አንዴ ጳጉሜን አምስት ብቻ ተከብሮ የሚያበቃ ስላልሆነ ሁሌም ቢሆን ፍትህ እንዲረጋገጥ ለህግ የበላይነት መገዛታችንን ማቋረጥ አይኖርብንም።
በእርግጥ ህግ ይረጋገጥ ዘንድ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ ይታወቃል። ከዚህም መካከል አንዱ የወጡ ህጎች ተግባራዊ ስለመሆናቸው የሚፈተሽ አካሄድ ዛሬን ጨምሮ ከሁለት ቀን በኋላ በምንይዘው አዲሱ ዓመት ተግባራዊ ሊሆን ስለመቻሉ የተሰራው ስራ ይበል የሚያሰኝ ነው።
የወጡ ህጎች በሌሎች የመንግስት አካላት እየተፈፀሙ ነው ወይ? ምንስ ችግር አለባቸው? የሚለውን ነገር በአግባቡ ለመፈተሽ ይረዳ ዘንድ በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ አንድ ዳይሬክቶሬት ተቋቁሞ ተቋማትን ኦዲት ለማድረግ መታሰቡ ከፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የወጣ መረጃ አመልክቷል።
የዚሁ ተቋም መረጃ እንደሚያሳየው፤ በአዋጅ ደረጃ የወጣ ህግ ከአንድ ሺ በላይ ሲሆን፣ የወጡ ደንቦችም ሆነ መመሪያዎችም የዚያኑ ያህል ናቸው። አንዳንዱ ህግ አባት ህግ ነው፤ ለምሳሌ አዋጅ ከወጣ በኋላ ያንን አዋጅ ተከትሎ የሚወጣ ደንብ፣ መመሪያም ሆነ አስራር ሊኖር ይገባል። እነዚህ ነገሮች አሉ ወይ? የሚለውን ነገር ለማጣራት በተቋቋመው ዳይሬክቶሬት አማካኝነት አምስት ተቋማት ተመርጠው ኦዲት ለማድረግ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።
በተጨማሪም የመንግስት ተቋማት የሚሰጡት ውሳኔዎች ህጋዊ ስለመሆናቸውና ህግን መሰረት አድርገው ስለመሰጠታቸው እንዲሁም በህገ መንግስታችን ላይ መንግስት ለህዝቡ ስራው ግልፅ መሆን አለበት የሚለውም ሲታይ ብዙውን ጊዜ ወደተቋማት ሲኬድ ‹‹ይህ መመሪያ ይከለክለኛል››፣ ‹‹ያኛው ደግሞ ያግደኛል›› የሚሉ ነገሮች ይበዛሉና እነዚህ ኦዲት መደረግ አለባቸው ተብሎ አንድ የአስተዳደር አዋጅ መዘጋጀቱም መልካም ጅማሮ ነው ማለት ይቻላል። በአጠቃላይ ህግ ማውጣት ብቻም ሳይሆን ተፈፃሚ ስለመሆናቸውም ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑ እሰይ የሚያስብል ነው።
የህግ ጥሰት ካለ ትናንት እንደሆነው ሁሉ ሰብዓዊ መብት ይጣሳል። ጉልበተኞች አይለው ደካማዎቹ ደግሞ አንገታቸውን ይደፋሉ፤ አልፎ ተርፎም ከአገር ይሰደዳሉ። በአንፃሩ ደግሞ ወንጀለኞች ያልደከሙበትንና ያልለፉበትን ሀብት በማን አለብኝነት ያጣጥማሉ። ይህ እንዳይሆን ግን ሁሉም ዜጋ ለህግ የበላይነት መረጋገጥ የተቻለውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅበታል።
የህግ የበላይነት በአገራችን ተከበረ ማለት ኢትዮጵያችን ወደ ብልፅግናው እንዲሁም ወደ እድገቱና ልማቱ ተሸጋገረች ማለት ነው፤ ስለዚህም የፍትህ አካላት ብሎም መንግስት ለህግ የበላይነት መረጋገጥ ብርቱ የሆነውን የህዝብን ክንድ በመያዝ በንፁህ ህሊና እና ገለልተኛነት ጠንክሮ በመስራት ለወጡ ህጎች ተግባራዊነት ሊታትር ግድ ይላል።
የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ህጎችን በማውጣት ብቻ መጠመዱ ትርፍ እንደሌለውም በመረዳት የዜጎች ሰብዓዊ መብት ተጥሶ በየፍትህ ተቋማት ደጅ ሮሮ ከመደመጡ በፊት ከህዝቡ ጋር በመሆን ለህግ ተገዢነታችሁን በተግባር አሳዩ። የእናንተ ግንባር ቀደም መሆን ሌሎቹንም የሚያነሳሳ ነውና ለተግባራዊነቱ ፊት አውራሪ በመሆን የተጣለባችሁን ኃላፊነት ተወጡ፣ ህዝብም በዚሁ ልክ የድርሻውን ይወጣ!
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 5/2011