ዘወትር አዲስ ዓመት፣ በአዲስ ሰማይ ኩል ሲኳል የሰው ልጅ በየተገናኘበት ፈርጅ፣ “እንኳን አደረሰህ”፣ “እንኳን አደረሰሽ” መባባሉ የኖረ ብሒል ነው። መላሹም፣ “እንኳን አብሮ አደረሰን “ ማለቱ የተለመደ ዘይቤው ነው።
ድሮ ዘመን በቁጥር ሳይታሰር በፊት ሰው ዝም ብሎ ሳይቆጥር ተወልዶ ሳያስቆጥር ነበር፤ የሚሞተው ይባላል። ቁጥርስ ለምን ያስፈልጋልና። ራሳቸውስ ሁለት አንድ አልነበሩ ምን መቁጠር ያስፈልጋቸዋል። በወቅቱ ሁሉ ነገር የእነርሱ ስለነበረ (እንኳንስ በሬና ዶሮው ውሻና ድመቱ ነብሩና አንበሳው ሁሉ የእነርሱና የእነርሱ ታዛዦች ነበሩና) እናም ሰው እየበዛ ሲመጣ ቁጥርና ቋጠሮ አስፈለገ። በርና በረት ሁሉ ተሰሩ፤ ሌሎቹ እንስሳት የሚያስፈልጋቸው፤ ይሰጣቸው ነበር እንጂ የፈለጉትን እያደኑ የሚያበላሹ አልነበሩም።
ጥንቃቄና ቁጥጥር ፣ ጥበቃና ቁጥር የመጣው ዘግይቶ ዘግይቶ ሰው እጅግ ግላዊነት ሲያጠቃውና አውሬ ወደመሆን ባህሪ ሲለወጥና ማስፈራቱ ሲያይል ነው፤ ይባላል። ሙሴም በቁጥር የተደነገጉ የማይታለፉ ትእዛዛት ይዞ መምጣት ያስፈለገው ለዚህ ነበረ። እናም ከዚያ በፊት መልካምና ክፉ ድርጊቶች በመባል የሚታወቁ የስነ ምግባር ወጎች እንጂ ሌላ አልነበረም ፤ እነዚህንም የመልካምነት ዘንጎች ህሊና በሚባለው አምላካዊ ህልው ላይ አትሞ ነበር፤ ለሰው የሰጠው።
የሆነው ሁሉ ሆኖ ዘመን ከተሰፈረ ጊዜ ከተቆጠረ ወዲህ፣ ስለአዲስ ዘመን ስናስብ ዘመን በአበቅቴ (ወቅታት) አንጓ ተከፍሎ ነው ፤ የሚታሰበው። በልግ፣ ፀደይና መፀው፣ ከክረምት ጋር እየተጎናጎኑ ይለኩታል። አንዳንዴም ክረምትና በጋ ብቻ ተብለው ለሁለት ተከፍለው ዓመቱን ይገልጹታል።
በዚህ የክረምት ወራትም የሚወዳትን ያጣ እጅግ በአዘነ ጭፍንና የሐምሌ ጨለማ ውስጥ ሆኖ….
ምነው ተለየሽኝ መስከረም ሳይጠባ ፤
እንቁጣጣሽ እያልን ሳናጌጥ በአበባ። እያለ ያንጎራጉራል።
አዲስ ማለዳና አዲስ ሰማይ፣ አዲስ ዘመንና አዲስ ሐሙስ ፤ አዲሱን ዓመት ይዞ ብቅ ይላል። ሁሉም አዲስ ነው …. እውነት ነው፤ ዘመን ራሱን አድሶ ብቅ ብሏል…የሰው ልጅ ግን አዲስ ዓመት መጥቶ በባተ ጊዜ ሁሉ ፣ እርጅናን ወደ ራሱ እየጋበዘ መሆኑን ይዘነጋዋል ፤ ራሱ የታደሰ ይመስል!!
“በዘመን ግስገሳ ልባችን ተማርኮ፤
ያለፍነው እኛ ነን ጊዜ አይደለም እኮ።”
ሲሉ፣ ደራሲውና ባለቅኔው ከበደ ሚካኤል ….. አዲስ ዘመንን በማወደስ የሰው ልጅን እጣ ፈንታ በልዩ ሁኔታ ገልጸውታል።
ዘመንን ለማስቆጨት ለማሳሰብ ፣ ለማስታወቅ ለማስደሰት በየጊዜው የተለያዩ ገጣሚያን የራሳቸውን አሻራ በዘመንና ጊዜ ላይ አሳርፈዋል ። ይሁንናም ቀጥሎ ያለውን ነባር ህዝባዊ ግጥምም በደስ ደስ ሁነት እንመልከተው።
“ካልተሳፈሩበት ቶሎ ተሽቀዳድሞ፤
ጊዜ ታክሲ አይደለም አይጠብቅም ቆሞ!!” (ህዝባዊ ግጥም)
የዚህ ግጥም ትርጓሜ ወርቃ ወርቅ ነው። ሁሉን ነገር በጊዜ ካላከናወኑት ጊዜ ከቶውንም መጓዙንና ማለፉን ለአፍታ አያቆምም፤ ማለት ነው። የአሁኗ ሰከንድ ለቅድሟ ሰከንድ አምናዋ ነው። የቅድሟ ደቂቃ ለአሁኗ ደቂቃ እንዲሁ ናት፤ በሰዓታትም ብናየው አንዱ ለሌላው እንዲያ ነው። አናስብበትም እንጂ እያንዳንዱን ሰኣት ብንኖረው ቀናችን ይባረካል።
ለዚህ ነው ፈረንጆቹ አንተ ሰዓትህን ተቆጣጠር ቀኑ ራሱን ይቆጣጠራል ፤ የሚሉት። አንተ ሳንቲሞቹን ተቆጣጠር ብሩ ራሱን ይጠብቃልም ይላሉ። ባለንበት ሁኔታ ውስጥ ሰዓቱን በምን መልክ እንዳሳለፍነው ማስተዋል ከቻልን እኛ የጊዜያችን መሐንዲሶች እንሆናለን ። ካለዚያ ባለፈ ቀንና ሰዓት ያለፈ ትዝታ ታስረን መቆዘም ዕጣችን ይሆናል።
ጊዜን አንዳንዶች አለቃ ሲሉት አንዳንዶች ፈራጅ ሌሎች ደግሞ ፍትሃዊ ይሉታል። ሁሉም እንደየብጤቱ ጊዜን ይመዝነዋል። ጊዜን አለቃ ነው የሚሉት በጊዜ ውስጥ ጊዜን የሚያስጠብቀውንና የሚያከናውነውን ነገር የሚያሰማራውን ሰው በማየት ሲሆን ፈራጅ የሚያደርጉት ደግሞ የሰው ልጅ በጊዜ ውስጥ ወደከፍታ ተነስቶ በቆይታው ወይም ከፍ ባለበት ወቅት ለሰራው ክፉ፣ ጊዜ የራሱን ዳኝነት ይሠጣል ብለው ስለሚያምኑ ነው።ፍትሐዊ ነው፤ ሲሉም ከዚሁ ጋር ፍርድ እንደ ዋሽንት ቅኝት የሰመረለትና በአግባቡ የተወሰነለት ሲሆን አይተው አድራጊውን “ጊዜ” አድርገው ስለሚያስቡ ነው።
ይሁንናም በሁሉም ውስጥ ዳኛው የሰው ልጅ መሆኑን ማስተዋል አያቅትም። ሰያሚው ሰው፣ አለቃ፣ ፈራጅና ፍትሐዊ ያደረገው ራሱ ነውና ።
ጊዜን ደግሞ እቃና መጠቀሚያ አድርገው የሚያስቡ ደግሞ በ”ጊዜህ ሥራ” በ”ጊዜው አድርግ” ለሚሉት ነገር፣ የሚሰጡትን ስያሜም እናያለን።
“አደባባይ ቆሞ አበጀሁ ቢላችሁ፣
ይህን ባለጊዜ ምን ትሉታላችሁ። “(መርስዔኃዘን ወልደቂርቆስ)ይላሉ።
ጊዜው የፈቀደለት ፣ ጊዜ የስልጣን እርካብ ያቆናጠጠውና ግብዝነት ከዕብሪት ጋር ሰውነቱን የወረሱት ሰው ፣ ሲገኝ “ባለጊዜ” ይባላል። በተለይ የተረሳ ፣ የተናቀና የተተወ የመሰለው ትንሽነት አለቅጥ የሚሰማው ሰው ስልጣን ሲይዝ በፊት ገዝተውኛል፤ አስረውኛል፣ አሳንሰውኛል ፣ ብሎ የሚላቸውንና ከእነርሱም ጋር የተባበሩ ናቸው፤ ብሎ የሚያስባቸውን ሁሉ ስልጣን ተጠቅሞ ያዋርዳቸዋል። ትንሽነት ክፋቱ ይኼ ነው።
ከኢዲ አሚን የስልጣን ዘመን ታሪኮች ጥቂቱን ላቃምሳችሁ። የዚህ ክፉ የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ትልቅ ልጅ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነበርና አባትየው በጣም በማዘኑ ልጄ ጭንቅላቱ ለ8ኛ ክፍል አይደለም፣ ከ11ኛ በላይ ነው፤ ብሎ ወዲያው የ12ኛ ክፍልን ትምህርት እንዲከታተል ትምህርት ቤቱን ያዝዛል። ትምህርት ቤቱም “የዕብዱን መሪ” ትዕዛዝ ተቀብሎ ተግባራዊ ያደርጋል። ልጁ በክፍል ውስጥ የሚያመጣው ውጤት አስቂኝ ነበረ። በነፍሳቸው የቆረጡ መምህራን ትክክለኛውን የቴስት ውጤት ይሰጡ ነበረና። የመጣበትን የክፍል ደረጃ የሚያውቁ የክፍል ልጆች ደግሞ ያላግጡበት ገቡ፤ ይህንን በቁጣ ሄዶ ለአባቱ የተናገረው ልጅም ወዲያውኑ ከአባቱ ፕሬዚዳንታዊ ሁሉን አድራጊነት ስልጣንገምሶ ከወታደሮቹ ጋር ያለገደብ ይሰጠዋል። በልጆቹም ህይወት ላይ ያሻውን ማድረግ እንዲችልም ይፈቅድለታል።
ልጅም ከትምህርት ቤት ሲወጡ ጠብቆ ልጆቹን አስለቅሞ፣ ወደ ቤተመንግስት እስር ቤት አስወሰዳቸው። ይሄ “የባለጊዜ ልጅም”፣ የክፍል ጓደኞቹን በቤተመንግስቱ ምድር ቤት ውስጥ ካሳሰራቸው በኋላ እየተመላለሰ ይሰድባቸው፣ ያላግጥባቸው ፣ ይመታቸው ነበረ። በዚህ ሊረካ ስላልቻለ የምድር ቤቱን ጣራ አስከፍቶ ከላይ ቆሞ ይፀዳዳባቸው ነበረ። (ጸዳ ይልባቸው ነበር፤ እንዲል የአራዳ ልጅ) አባቱ በሙሴቬኒ ተዋጊዎች ካምፓላን ለቅቆ ወደ ሳውዲ አረቢያ በፍርሃት ፣ ሲፈረጥጥ ከንብረቶቹና ቤተሰቦቹ ጋር ከኡጋንዳ ይዞ ያልፈረጠጠው ነገር ቢኖር “ባለጊዜነትን” ብቻ፣ ነው። ዛሬም ኡጋንዳን ላለፉት 30 ዓመታት ያለቅያሬ እየመሯት ያሉት የዚያን ጊዜው የለውጥ ተዋጊና “አምባገነንነት ለሃገራችን አያስፈልግም” ባዩ ፣ የዛሬው “ባለጊዜ” ዩዌሪ ሙሴቬኒ ናቸው።
ወደእኛ ሐገር የአዲስ ዘመን በዓል ልመልሳችሁና፣ ዘመን ማጣቀሻው ብዙ ነው፤ በእኛ ሐገር አዲስ ዘመን ከአደይ አበባ ጋር፣ አዲስ ዘመን ከአደስ ጋር፣ አዲስ ዘመን ከእንቁጣጣሽ ጭፈራ እና ከኢዮሐ አበባዬ ጋር መጋመዱና መዛመዱ አለምክንያት አይደለም ።
ልጃገረዶች “አበባየሽ ወይ ለምለም” ሲሉ ጎረምሳዎቹ ደግሞ “እዮሃ አበባዬ መስከረም ጠባዬ፣ መስከረም ሲጠባ ወዳገሬ ልግባ” ፣ እያሉ የክረምቱን ማብቃት የፀደዩን ወር መምጣት ያበስራሉ። ያ፣ ብቻ ሳይሆን ያደጉበት ሐገር ፣ የኖሩበት ቀዬና ዘመድ አዝማዱ የሚጠየቅበት፤ ምድር በአደይ አበባ የምትደምቅበት ጊዜም ስለሆነ ነው።
በዚህም ሁላችንም በቡሔ የጀመርነውን ደማቅ የባህል አሻራ፣ በአሸንድዬ ድልድይ እስከ እንቁጣጣሽ እንዘልቅበታለን። ብዙዎቻችንም እንዲህ አልፈንበታል፤ መልካም የባህል ውርስ ነው፤ ሰውን የማሰባሰብ ፣ ለበዓል የማስተባበርና በመጠያየቅ የማስተጋበር መልካምነት ስላለው በቀላሉ የማይረሳ ነው። ሁሉም በጊዜው ሲሆን ነገር ሁሉ ውብ ይሆናልም።
ታዲያ ፣ የአዲስ ዓመቱን መንፈስ ብዙ ሰዎች ከተለያዩ ደባል ሱሶቻቸው ለመላቀቅ፣ የጀመሩትን ክስ በአሸናፊነት ለመወጣት፣ አዲስ ሥራ ለመጀመር ፣ የጀመሩትን ፕሮጀክት ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ ወዘተ… ቃል የሚገቡበት ሰበብ ነው። ይሁንናም ኪዳን መግባታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሥራን ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገር ከሚለው ሐሳብ በስተቀር ብዙዎቹ ቃል የሚገቡባቸው ነገሮች በእያንዳንዱ አዲስ ቀን ሊከናወኑ የሚገባቸውን ድርጊቶች መሆናቸውንና አንዳንዱም ያልተገባ ሂደት መሆኑን ማጤን ስለሚያቅተን እንስታለን።
ከዚህ በተጨማሪ ግን ብዙዎች የማናስተውለውና ቃል የማንገባበት ነገር አለ። ለአብነት ያህልም ዳግመኛ በተከፋሁበትም ነገር ሆነ ሰውን ባስከፋሁበት ምክንያት፣ በጥላቻ ሌላውን ላለማየት፣ የጠላሁትንም ሰው ይቅር ለማለት ፤ የጠላኝንም ይቅር ለማለት ተዘጋጅቻለሁ ፤ የሚል ቃልኪዳን ለመግባት ምን ያህሎቻችን እንደተዘጋጀን አላውቅም።
ምክንያቱም በይቅርታ ውስጥ ስብራት ይጠገናል፤ በይቅርታ ሃይል የጥላቻ ደመና ይገፈፋል፤ በይቅርታ ጥበብ የመንግስተ ሰማያት በር ይከፈትና የሲኦል በር ይጠረቀማል። ይቅር ስትሉ አሸናፊዎች ትሆናላችሁ፤ ይቅር ስትሉ ጉልበት ታገኛላችሁ። ይቅር ስትሉ መንገዳችሁ በብርሃን ይሞላል፤ ህይወትም ቅልል ትላለች። ቂም የያዘና የተቆጣ ሰው ብርሃኑ የጨለመበት የሞቀበት የሚበርደው ነው።
ሁላችንም ከዚህ በመለስ ሳይባል ይቅር ልንባባል ያስፈልገናል ። ልጆች ትኩረት ነፍገውናል፤ አልተንከባከቡንም የሚሏቸውን ወላጆች ይቅር ሊሉ፣ እንደሚገባ አልታዘዙንም፣ አላከበሩንም፣ ራሳቸውንም ክፉኛ ጎድተው አሳዝነውናል፤ የሚሏቸውን ልጆች ይቅር ሊሉ ይገባል። በቤት ውስጥ የሚፈጠር ስንጥቅ አንዳንዴ ከራስ ይልቅ ቤተሰባዊ ሞትንም ያመጣልና። ባሎች፣ አትሰማኝም፣ አትታዘዘኝም የሚሏቸውን ሚስቶች ይቅር ሊሉ ይገባል፤ ሚስቶች ይቅርታ የሌለው በደል በባል ተፈጽሞብኛል ብለው አኩርፈው ተቀምጠው ከሆነም ይቅር ይበሏቸው፤ የሁለቱ ይቅርታ ሊፈርስ ያለ ቤትን ይገነባል፤ የተዛነፈ ጎጆን ያቀናልና።
መሪዎች፣ ሰራተኞችን በይቅርታ ልብ ሊመሩ ይገባቸዋል፤ ሰራተኞችም መሪዎችን ሰው መሆናቸውን ተቀብለው የሚፈጥሯቸውን ስህተቶች ለማረም የሚችሉበት ዕድል ሊሰጧቸውና በይቅርታ ልብ ሊመለከቷቸው ይገባል። አገልጋዮች፣ በሚመሩት ምዕመን አዝነው ከሆነ በይቅርታ ልብ ሊምሯቸውና ሁሌ በሚመችም በማይመችም ሁኔታ ፍቅርን መመገብ ይጠብቅባቸዋል። ምዕመናንም የቤተ-እምነት መሪዎችን ስህተት፣ የቤተ- እምነት ስህተት አድርጋችሁ ከመውሰድ ታቅባችሁ መሪዎችን በይቅርታ ልብ እንድታዩዋቸው አስፈላጊ ከሆነም ይቅርታ ብትጠይቋቸው መልካም ነው፤እላለሁ።
ለራሱ ክብር ያለው ሰው ሌላውንም ያከብራል፤ ራሱን የሚወድ ሰው፣ ሌላውንም ይወዳል። ለራሱ ይቅርታን የሚፈልግ ሰው ሌላውንም ይቅር ሊል ይገባዋል። በሌላ አንጻር በራሱ ሊፈጸምበት የማይወደውን ክፉ በሌላው ላይ አያደርግም ።
የዚህ የይቅርታ ህይወት አስፈላጊነት የይስሙላ አይደለም፤ ይልቅስ በእውነት መኖርን አመልካች ነው እንጂ። ይቅርታ ሰብሳቢ ነው፤ ይቅርታ ሁሉም ወገን አሸናፊ ሆኖ የሚወጣበት ክስተት ፤ ግብዝነት በሌለበት ህይወት የመመላለሳችን ምልክት፣ ፍቅርን የመግለጫ ምስክርነት ነው።
ይቅርታ አልባ የሆነ ህይወት የሚመራ ሰው ህይወት የለውም ፤ ዕድሜውን ይቆጥራል ግን ከሞቱት በላይ ካሉት በታች የሚኖር ነው። ይቅርታን ገንዘቡ ካላደረገ፣ ዛሬም የለውም ፣ ነገም የለውም፤ ያለው ትናንት ብቻ ነው ፤ ማለት ነው።
እንዲህ ማለትም በመቆዘም የሚኖር ሰው፣ ዛሬውን እያጠፋ ነገውን በቁዘማ የሚቀበል በትናንትና ላይ የሚኖር ነው። ሁልጊዜ እንዲህ ተበድዬ ፣ እንደዚህ ተጎድቼ፣ እንደዚያ ኮንነውኝ ያለጥፋቴ ከስሰውኝ፣ ያለስህተቴ ወቅሰውኝ፣ እያለ በወቀሳና ክስ የሚኖር ግለሰብ ዛሬን በቅጡ የማይኖር ነው፣ ማለቴ ነው።
ስለዚህ በይቅርታ እንደመኖር ያለ ነጻነት የለም። ይቅር ባይ ሰው ይቅርታውን ካደረገ በኋላ በነጻነት የሚመላለስ ፍጡር ነው ። ከነብሒሉም ይቅርታ ተቀባዮች ጀግኖች ሲሆኑ ጠያቂዎቹ ምስጉን ናቸው!!
ስለዚህ አዲሱን ዓመት በአዲስ ሰማይ ሥር በአዲስ ልብስ ሳይሆን በአዲስ ልብና በይቅርታ ተሞልተን ልንቀበለው እንዘጋጅ። ያኔም ምድራችን ትባረካለች፤ የህዝቧ ህይወት ቀሊል ይሆናል። ባገኘነው ምቹም ሆነ የማይመች መድረክ ላይ ተገናኝተን፤ እንተራረቅ!!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጳጉሜ 2/2011
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ