ሀኪም አበበች ሽፈራው የዘርፈ ብዙ ዕውቀት ባለቤት ናቸው።የስነ ፈለክ፤የባህላዊ ህክምናና የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያና ተመራማሪ ናቸው።በእነዚህ ዘርፎችም ላለፉት 40 ዓመታት ምርምር በማድረግ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገራት በርካታ ሽልማቶችን አግኝተዋል።በሙያቸውም ከሀገር ውስጥ አልፎ የውጭ ሀገራት ዜጎችንም ረድተዋል።ለአፍሪካ፤ ለአውሮፓና ለአሜሪካ ተመራማሪዎች በሀገር በቀል ዕውቀቶች ዙሪያ ስልጠና ሰጥተዋል፤ ልምዳቸውንም አካፍለዋል።
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ከእኒህ የሀገር በቀል ዕውቀቶች ጠቢብ ጋር ቆይታ አድርጓል።መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን ፤- የስነ ፈለክ ጠበብት፤ የባህል ሀኪምና የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ ኖዎት፤የነዚህ ሁሉ ሙያ ባለቤት እንዴት ሊሆን ቻሉ?
ሀኪም አበበች፤- ተፈጥሮ የራሷ የሆነ ጥበብ አላት።የምትመራውም ውስጧ ያሉት ሃብቶች በሚያደርጉት መስተጋብር ነው።እርስ በእርስ የተያያዙ የተሳሰሩ ናቸው።ስነፈለኩ ከአካባቢ ጥበቃው፤ የአካባቢ ጥበቃው ከባህላዊ ህክምናው ጋር የተቆራኘ ነው።አካባቢ ካልለማ እጽዋቱ የሚመገቡት አያገኙም፣ መድሃኒትም አይኖርም።ስለዚህ ተያያዥ ናቸው።ስነ ከዋክብቱ፤ ለዕጽዋቱ ዕድገት፤ ዕጽዋቱ ደግሞ ለመድሃኒቶቹ ፍቱንነት ተፈጥሯዊ የሆነ ቁርኝት አላቸው።አንዱ ያለአንዱ ሊበለጽግ ሊያድግ አይችልም።በተፈጥሮ ብቻውን ቆመ ነገር የለም።ስለዚህም ሀገር በቀል ዕውቀቶችን የሚያጠና ሰው እነዚህን ተያያዥና ዘርፈ ብዙ ዕውቀቶችን አብሮ ይቀስማል።ለዚህ ነው እኔም በነዚህ ዕውቀቶች ዙሪያ እየሰራሁ ያለሁት፡
አዲስ ዘመን፤- በሀገር በቀል ዕውቀቶች ዙርያ ያለውን የኢትጵያዊያንን ስልጣኔ እንዴት ይመለከቱታል?
ሀኪም አበበች፤- ስነፈለክን የጀመረችው ኢትዮጵያ ትመስለኛለች።ስልጣኔውም ከናምሩድ ይጀምራል።ከናምሩድ በኋላ ኢትኤል ቀጥሎበታል።ኤትኤል ስነፈለክ ተመራማሪ ብቻ ሳይሆን ዘርፈ ብዙ እውቀት ያለው ኢትጵያዊ ተመራማሪ ነው።ከኢትኤል ቀጥሎ ያለው ደግሞ ደሸት ሲሆን አሁን እየተጠቀምንበት ያለውን እውቀት መዝግቦ ያስቀመጠውም እሱ ነው፤ ቀደም ሲል የነበሩ አባቶችም እህልን ለመዝራትና ፍሬ በጥሩ ሁኔታ እንዲያፈራ ይህንን የስነፈለክ እውቀት ይጠቀሙበት ነበር።
አዲስ ዘመን ፤- ጥንታዊ ኢትዮጵያውያን በስነፈለክ እውቀት የተራቀቁ ናቸው ነው የሚሉኝ?
ሀኪም አበበች፤-ምንም ጥርጥር የለውም።ለምሳሌ ካሶፕያንና አንድሮሜዳን ካየን ኢትዮጵውያን ነገስታት ናቸው።እነዚህ ኢትዮጵያውያን በዘመኑ ከፍተኛ ሆነ የስነ ፈለክ ዕውቀት የነበራች ነበሩ። እኛ የእነዚህን ኢትዮጵያውን ታሪክ በአግባቡ ለዓለም ስላላስተዋወቅን ግሪኮች እንደደረሳቸው ታሪክ አድርገው ሲያአስነግሩ ኖረዋል።ይሁን እንጂ በተደረጉ ጥናቶች እነዚህ ነገስታት ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ተደርሶበታል።በነዚህን ነገስታት ስምም ከዋክብቶች ተሰይመው እናገኛለን።ለምሳሌ አንድሮሜዳን በሰማይ ላይ የወርቅ ቀሚስ ለብሳ አክሊል ደፍታ እናያታለን።በተለይ ሀምሌ ላይ ጎልታ ትወጣለች።ካሶፕያ ደግሞ ቁጭ ብላ ትታያለች።እነዚህና መሰል ከዋክብቶችን በመመልከት የትናንት አባቶች በስነ ፈለክ ምርምር ዙሪያ የጠለቀ ዕውቀት እንዳላቸው መረዳት ይቻላል።እኛ በወጉ ባንረዳውም ቀሪው ዓለም ግን ይህንን ከተረዳው ውሎ አድሯል።በቅርቡ እንኳ ብንመለከት አዳዲስ ፕላኔቶችን ኢትዮጵያ ስያሜ እንድትሰጥ መጠየቁ ከዚሁ ታሪካዊ ሁነት ጋር የሚያያዝ ነው ብዩ አምናለሁ።እኛ ብንዘነጋውም አለም ኢትዮጵያን ቀደምት የስነፈለክ እውቀት ባለቤቶች መሆናቸውን መመስከሩን ያስረዳል።
አዲስ ዘመን፤- ካሶፕያና አንድሮ ሜዳ የሚባሉ ነገስታት ኢትዮጵያ ውስጥ ነበሩ ማለት ነው?
ሀኪም አበበች፤- ካሶፕያና አንድሮ ሜዳ የዛሬ 4 ሺ ዘመን አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ነገስታት ነበሩ።አነዚህ ኢትዮጵያውያን በነበራችው ዕውቀት ከመካከለኛው ምስራቅ አልፈው ቬትናም ደረስ ግዛት የነበራቸውና ዛሬም ድረስ በስነፈለክ ምርምሩ ዘርፍ ስማቸው የሚነሳ ነው።
አዲስ ዘመን፤- የታሪክ መዛግብት አሉ ይህንን የሚያረጋግጡ ?
ሀኪም አበበች፤- በርካታ የጽሁፍ ማስረጃዎች አሉ አለምም ይህንኑ እውነታ ዛሬም ድረስ የሚመሰክረው ነው።በሀገራችንም ሆነ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የነዚህን ኢትዮጵያውያን ጥንታዊ ታሪክ የሚያስረዱ ሰነዶች አሉ።ኢትኤል የሚባለው ንጉስ ኢትዮጵያ ውስጥ መግዛት የጀመረው የዛሬ 5 ሺ ዓመት ገደማ ነው።ቀጥሎ ደሸት፤ ካሰፕያና አንድሮሜዳን የመሳሰሉ ነገስታ ኢትዮጵያን አስተዳድረዋል።የእነዚህ ነገስታት ታሪክ በርካታ አሻራዎችን ትቶ ያለፈ ነው።ቅድም እንዳልኩህ በከዋክብት ጭምር ስማቸው ተሰይሞ መገኘቱ የዚህ እውነነታ አንዱ ማሳያ ነው።ይሁን እንጂ የእነዚህን ታላላቅ ኢትዮጵያውያን እውቀት ለትውልድ ማሻገር ባለመቻሉ ኢትዮጵያ የዛሬ 3 ሺ ዓመት ገደማ ከነበረችበት ማማ ልትወርድ ችላለች። ቀድሞ የነበረው እስከ መካከለኛው ምስራቅ ድረስ የሚሻገረው ግዛቷም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያነሰ ሄዷል።ዕውቀት ከትውልድ ወደ ትውልድ ካልተላለፈ መምከኑ አይቀርም።ዛሬ እነዚህን ድንቅ ኢትዮጵያውያን ታሪክ የሚያውቅ ትውልድ
እጅግ በጣም ትንሽ ነው።ኢትዮጵያውያን ከየትኛውም ሀገር ቀድመው በዕውቀት ቢራመዱም እነዚህን ዕውቀቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሻገሩ ባለማድረጋቸው ሀገር በቀል ዕውቀቶች ተመናምነዋል።
አዲስ ዘመን፤- በተፈጥሮ ሀብት ረገድስ ኢትዮጵያ የሚጠቀስ የጎላ ነገር ኣላት?
ሀሳብና ዕውቀት እየተመናመነ መጣ እንጂ ኢትዮጵያ የበርካታ የተፈጥሮ ሃብቶች ባለቤት ነች።ይሁን እንጂ ያሉንን የተፈጥሮ ሃብቶች በአግባቡ ተጠቅመን ሀገራችንን መለወጥ እንዳንችል ዕውቀት አጥሮናል።ቀደም ሲሉ የነበሩ ኢትዮጵያዊ እውቀቶች ዋጋ ስላልተሰጣቸው የዕውቀት ደሃ ሆነናል።ባሉን ሃብቶች እንዳንጠቀም ዕውቀት አንሶናል።ኢትዮጵያ ውስጥ የማይገኝ የዕጽዋትም ሆነ የማዕድን ሃብት የለም።እኒህን ሃብቶች መንግስትም ሆነ ትውልዱ አላወቋቸውም። በምዕራቡ አስተሳሰብ ተውጠናል። ሀገራዊ ዕውቀቶችን ንቀን የምዕራቡ አለም አድናቂ ሆነናል።ሌላው ቢቀር 85 በመቶ የሚሆነው የሃገራችን ህዝብ ህክምና የሚያገኘው ከባህል ህክምና ነው። የባህል ህክምና ዕውቀት በሀገራችን የረጅም ዘመናት ታሪክ ያለውና ሌሎችም ሀገራት ይህንን ዕውቀት ወስደው ከዘመናዊ ህክምና ጎን ለጎን በትኩረት እየሰሩበት ይገኛሉ።ዕውቀቱንም ፈልገው ዛሬ ድረስ በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎችና ትላልቅ ተቋሞቻቸውና ዩኒቨርሲቲዎቻቸው ሳይቀሩ ወደ ኢትዮጵያ በስፋት ይመጣሉ።በየዱር ገደሉና በየጫካው ዕውቀት ያላቸውን አባቶች አፈላልገው ዕውቀቱን ለመቅሰምና ወደ ሀገራቸው ለማሸጋገር ይታትራሉ። እኛ ግን ‹‹በእጅ ያለ ወርቅ›› እንደሚባለው ለባህላዊ ዕውቀቶቻችን ዋጋ አልሰጠናቸውም።በየዘመናቱ የነበሩ የሀገራችን ገዢዎችም ቢሆኑ ይህን ዕውቀት እንዲያድግ ከመደገፍ ይልቅ ውድቀቱን የተመኙለት ይመስላል።በዚሁ ምክንያትም በርካታ ጠቢባን እንኳን ለሩቅ ሰው ይቅርና ለቅርብ ልጆቻቸው እንኳን ዕውቀታቸውን ለማስተላለፍ ፍላጎት አጥተዋል።በርካታ የሀገር በቀል ዕውቀት ጠቢባን ድጋፍ አጥተውና ተስፋ ቆርጠው የያዙትን ዕውቀት እንደያዙት ወደ መቃብር ወርደዋል።
አዲስ ዘመን፤- እነዚህ ባህላዊ ዕውቀቶች ድጋፍ ያጡበት ምክንያት ምንድን ነው?
ሀኪም አበበች፤- በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል።በዋነኝነት ግን ሁለት ናቸው።አንደኛው ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩልህ ቀደም ሲሉ የነበሩን ሀገራዊ እውቀቶች በአግባቡ ከትውልድ ወደ ትውልድ ባለመተላለፋቸው በትውልዱ መካከል ክፍተት ሊፈጠር ችሏል።ቀደምት አባቶች የነበራቸው ዕውቀት ዓለምን ያስተዳድር የነበረና ለሃገሪቱም ገናናነትን ያተረፈ ነበር።ይህ ዕውቀት አንድ ቦታ ተገትቷል።ስለሆነም ትውልዱ ባህላዊ ዕውቀቶቻችን ያን ያህል ጠቃሚ ነው ብሎ እንዳያስብ የሚያደርገው ነገር የለም።በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ እንኳን የሀገር በቀል ዕውቀቶችን የተመለከተ አንድም ክፍል የለም። በርካታ ሀገራት ሀገር በቀል ዕውቀቶችን በትምህርት ስርዓታቸው ውስጥ አካተው ዜጎቻቸው ዕውቀት እንዲቀስሙ እያደረጉ ይገኛሉ።ይህ በመሆኑም ለበርካቶቹ የዕድገት መሰረት ሊሆኑ በቅተዋል።የእኛ ሀገር ግን ሀገር በቀል ዕውቀትን ችላ በማለት ከምዕራባውያን የተገለበጠ የትምህርት ስርዓት የሙጥኝ ብለን ዕድገታችን ወደ ኋላ እንዲገታ አድርገናል።በምዕራባውያን የትምህርት ስርዓት ያደገ ደግሞ አንድም ሀገር የለም።
ሀገር በቀል ዕውቀቶች ድጋፍ ያጡበት ሌላኛው ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያለው ምክንያት ደግሞ ምዕራባዊያን በዘረጓቸው ልዩ ልዩ ስልቶች አማካኝነት የእኛን ነባር ዕውቀት ትተን የእነሱ አምላኪዎች እንድንሆን ማድረጋቸው ነው።ለዚህ ሰለባ የሆነው ደግሞ ህዝቡ ብቻ ሳይሆን መንግስትም ጭምር በመሆኑ ባህላዊ እውቀቶችን ለመደገፍ ተነሳሽነቱ ጠፍቷል።አንድ ሀገር ሀገር በቀል እውቀቱን ከተጠቀመ በቀላሉ ማደግ እንደሚችል ምዕራባውያን ያውቁታል።ይህ እንዳይሆን ደግሞ ዘመን የማያሻግር፤ ችግር የማይፈታ፤ በዕርዳታ ላይ ብቻ የተመሰረተ ኑሮን የሚያበረታታ ዕውቀት እንድንጨብጥ አድርገውናል።የእኛም መንግስታት ይህንን ችግር የተረዱት አይመስለኝም።
አዲስ ዘመን ፤- ነባር ዕውቀቶቻችንን ባለመያዛችን ያጣነውን ነገር በተጨባጭ ሊያስረዱኝ ይችላሉ?
ሀኪም አበበች፤- የምዕራባዊያን ዕውቀት ለብዙ ሰው ጠቃሚ መስሎ ሊታየው ይችላል።ከጥቅሙ ግን ጉዳቱ ያይላል።ለምሳሌ ቀደምት አባቶቻችን እርሻ የሚዘሩት ያለማዳበሪያ ነበር።ምርታማ ከመሆኑም ባሻገር የሚመረተው ምርት ለጤናም በጣም ተስማሚ ነው።አሁን ማዳበሪያ ከመጣ በኋላ የአብዛኛው ህዝብ ጤና ተቃውሷል፡፤ በየመንገዱ በኩላሊትና በልብ ህመም የሚሰቃዩ ዜጎች ቁጥር ጨምሯል።በካንሰር ብዙ የማትታወቀው ሀገራችን በርካታ የካንሰር ህመምቶኞች ያሉባት ሀገር እየሆነች ነው።ይህንን ሀቅ ደግሞ በየሆስፒታሉ ሄዶ በቀላሉ ማረጋገጥ ይቻላል።
በግብርና ምርምር ማዕከሎችም ልዩ ልዩ ሰብሎችን፤ እጽዋቶችንና ፍራፍሬዎችን የማዳቀል ስራዎች ይሰራሉ።በዚህ ሂደት ያልተበረዙት ሀገራዊ ሰብሎቻችን ተፈጥሯዊ ባህሪያቸውን እንዲያጡና ወደ በሽታ አምጪ ዝርያነት እንዲቀየሩ ምክንያት እየሆነ ነው።የእጽዋት፤ የሰብልና የፍራፍሬ ዳይቨርሲቲያችን እንዲመናመን ምክንያት እየሆነ ነው።ላለፉት አስራ ስድስት ዓመታት ከአርሶ አደሩ ጋር በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሰራሁበት ወቅትም የተረዳሁት ነገር ይህንኑ ሃቅ ነው።በተቻለኝ አቅምም አርሶ አደሩ ሀገር በቀል የሆኑ ሰብሎችን እንዲያለማ ሳበረታታ ቆይቻለሁ።የእንስሳት ሃብቶቻችንም ተመሳሳይ ችግሮች እያጋጠሙት ነው።ስለዚህም የራሳችንን ነባር እውቀት ማክበር ከበርካታ ችግሮች ይታደገናል።
አዲስ ዘመን፤- በሀገራዊ ዕውቀት ብቻ ማደግ እንችላለን ነው የሚሉኝ?
ሀኪም አበበች፤- ሀገርን የሚያሳድገው ሀገራዊ እውቀት እንጂ ከምዕራቡ ዓለም የተኮረጀው የእኛ ያልሆነው እውቀት አይደለም።በነባር ዕውቀቶቻችን ከምድር አልፈን የሰነፈለክ ምርምር ድረስ ደርሰናል።ሌላኛው ዓለም የምድሩን ዕውቀት እንኳን በቅጡ ሳይረዳው እኛ ስለከዋክብት ተጠበናል።ሌላው ቅጠል ሲያገለድም እኛ ሸማ ሰርተን ለብሰናል።ዛሬም የተለየ ነገር የለም፤ ወደ ነባር ዕውቀቶቻችን ከተመለስን እያጋጠሙን ያሉትን ችግሮች ተሻግረን ወደጥንቱ ልዕልናችን መመለስ እንችላለን።የሚገርመኝ ደግሞ የምዕራባውያኑን ዕውቀት ኮርጀንም እኮ አላደግንም።ይልቁንም ችግሮቻችን ተበራከቱ እንጂ።
አዲስ ዘመን ፤- አንድ ጊዜ ላቋርጦትና..ቀደም ሲልም ያደግንባቸው ወደፊትም እናድግባቸዋለን ብለን የምናስባቸው ነባር ዕውቀቶች ተሰንደው ይገኛሉ?
የሚገርምህ ነገር ቀደምት ኢትዮጵያውያን በጣም ጠንቃቆች ናቸው።ሁሉንም ሀገራዊ ዕውቀት በአግባቡ ሰንደው አስቀምጠውልናል።ህንዶች እኮ ገና በቅርቡ ነው በሰነድ መልክ ለማዘጋጀት እየጣሩ ያሉት።ሜክሲኮም በተመሳሳይ።ልምድ ለመቅሰም እኮ ኢትዮጵያ ነው የሚመጡት።ስለዚህ ሰንዶ በመያዝ ረገድ ኢትዮጵያ ብዙም ችግር የለባትም።በየገዳማቱ፤ አድባራቱና በየገጠሩ በርካታ ሀገራዊ ዕውቀቶች በሰነድ መልክ ተቀምጠው ይገኛሉ።ይሁን እንጂ እነዚህ ዕውቀቶች ዝም ብለው ከመቀመጥ ውጪ ጥቅም ላይ አልዋሉም።ቀደም ብዬ እንደነገርኩህ ከሀገራዊ ዕውቀቶች ይልቅ የፈረንጅ ዕውቀት ያሳድገናል ብለን አምነናል።ግን ለበርካታ አመታት ያህል ማየት እንደሚቻለው የምዕራባውያን ዕውቀት ለችግሮቻቸን ፍቱን መድሃኒት ከመሆን ይልቅ እራሱ
ችግር ሆኖብናል።ያሉንን ነባር ዕውቀቶች ብንጠቀምባቸው ዛሬ የት በደረስን።
አዲስ ዘመን፤- ለምሳሌ እርስዎ ጋር ምን አይነት ሰነዶች ይገኛሉ?
ሀኪም አበበች፤- እኔ ጋር በርካታ ሰነዶች አሉ። በቃል ብቻ ሲተላለፉ የነበሩ የመድሃኒት ስርዓት ተመዝግቦ ይገኛል።በሀገሪቱ የትኛው ዕጽዋት የት እንደሚበቅልና የሚሰጠውም ጥቅም ጭምር ተሰንዷል።የስነ ፈለግ ምርምርም በርካታ ሰነዶች በእጄ ይገኛሉ።በተለያዩ አድባራትና ገዳማት እንዲሁም በሀገር በቀል ዕውቀት ጠበብት ዘንድ በርካታ የሰነድ ሀብቶች አሉ።
አዲስ ዘመን፤- እርስዎም ጋር ሆነ በሌሎች ቦታዎች የሚገኙ ሀገራዊ እውቀቶች በሂደት ሊጠፉ ይችላሉ የሚል ስጋት የለዎትም?
ሀኪም አበበች፤- ሙሉ በሙሉ ይጠፋሉ የሚል ስጋት የለኝም።ሆኖም ግን ሊመናመኑ የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው።በተለይም በየዘመናቱ የሚመጡ መንግስታት ሀገራዊ ዕውቀቶችን ለመደገፍ ምንም አይነት ፍላጎት አለማሳየታቸው ስጋቱ እንዲያድርብኝ አድርጎኛል።በእኔ እንኳን የደረሰውን ብነግርህ ባህላዊ ዕውቀቶችን ለማስፋፋት ደረጃውን የጠበቀ የሀገር በቀል ዕውቀት ማስፋፊያ ማዕከል ለመክፈት የጠየቅኩት ጥያቄ በጎ ምላሽ አላገኘም።ይህ ማዕከል ዕውን ቢሆን ደግሞ ርካታ ኢትዮጵያውያንን በሀገር በቀል ዕውቆች ዙሪያ በማሰልጠን ዕውቀቱን ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ ያስችል ነበር።ሆኖም ግን ማዕከሉን ለመገንባት ከመንግስት ፍቃድ አላገኘንም።
አዲስ ዘመን፤- የተከለከሉበትን ምክንያት አውቀውታል?
ሀኪም አበበች፤- ያው ቅድም እንዳልኩህ ዕውቀት የሚመስለን የምዕራባውያኑን ስንከተል ብቻ ነው።ይህ የሀገር በቀል ዕውቀት ማዕከል የትምህርት ካሪኩለም ውስጥ ስለሌለ ፍቃዱን ሊሰጡኝ አልቻሉም።እርግጠኛ ነኝ ሌላ ትምህርት ቤት ልክፈት ብል ግን ይሄ ሁሉ ውጣ ውረድ አይገጥመኝም ነበር።
አዲስ ዘመን፤- ሌሎች ሀገሮች እኮ ከዘመናዊ ዕውቀት ጋር እያስተሳሰሩ ዜጎቻቸውን ተጠቃሚ እያደረጉ ይገኛሉ፤
የእኛ እንዲህ እንዴት ሊሆን ቻለ?
ሀኪም አበበች፤- የአፍሪካ ባዮ ዳይቨርሲቲ ኔት ዎርክ (Africa Biodiversity Network) በሃገር በቀል ዕውቀቶች ዙሪያ ለአፍሪካ ሀገራት በኢትዮጵያ የስልጠና ዕድል አመቻችቶ ነበር።ይህ ስልጠና የተሰጠው በእኔ ቤት ውስጥ ነበር።አንዷም አሰልጣኝ እኔ ነበርኩ።ከአፍሪካም አልፎ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ተደርጎ የስልጠናው አስፈላጊነት ስለታመነበት ኩባ፤ ሜክሲኮ፤ እንግሊዝ፤ፈረንሳይ፤ጃፓን የመሳሰሉት ሀገራት ስልጠናውን ከአንድም ሁለት ጊዜ ኢትዮጵያ መጥተው ወስደዋል።ደብረዘይት የነበረኝን ዕጽዋት ማዕከልም ‹‹የአፍሪካ የባዮ ዳይቨርሲቲ ማዕከል›› በሚል ስያሜ በመሰየም ከ53 የአፍሪካ ሀገራት የመጡ የሀገር በቀል ዕውቀት ተመራማሪዎች ልዩ ልዩ ዕጽዋቶችን ተክለውበታል።ይህ እንግዲህ ከእኔም አልፎ ለሀገርም ኩራት ነው።ነገር ግን አለም በዚህ ደረጃ የሚጓጓለትን እውቀት በእኛ ሀገር ብዙም ቦታ አልተሰጠውም።ጭራሽ ደብረዘይት የሚገኘው ይኸው የባዮ ዳይቨርሲቲ ማዕከል በመንግስት ትዕዛዝ እንዲዘጋ ተደርጓል።
አዲስ ዘመን፤- የተዘጋበት ምክንያት ምንድን ነው?
ምክንያቱን አላውቅም። የተለያዩ የመንግስት ተቋማትን ብንጠይቅም መፍትሄ አላገኘሁም።በማዕከሉ ውስጥ ከ1400 በላይ ለመድሃኒትነት የሚያገለለግሉ ዕጽዋቶችም ከማዕከሉ መዘጋት ጋር ተያይዞ ለአደጋ ተጋልጠው ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን፤- ወደ ህክምናው ልመለስና ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ የውጭ ሀገር ዜጎች እርስዎ ጋር ይታከማሉ ይባላል?
ሀኪም አበበች፤- የእኔን ህክምና ፈልገው ከበርካታ ሀገራት የሚመጡ ታካሚዎች አሉ። ከአሜሪካ፤ ከካናዳ ከመሳሰሉት ሀገራት መጥተው ይታከማሉ። የሚወስዱትም ህክምና የተለያየ ነው።አንድ ታካሚ ለአስር ቀናት ታክመው ይሄዳሉ።የካንሰር፤ የኩላሊት፤ የጉበት መሳሰሉት ህክምናዎችን መጥተው ይወስዳሉ።እኔ ግን ደስታ የሚሰጠኝ ድሃውን ኢትዮጵያዊ ሳክም ነው።በተለይ በአሁኑ ወቅት ከአመጋገብ ጋር በተያያዘ በርካታ ኢትዮጵያውያን ለችግር እየተጋለጡ ነው።ጄሶና ሰጋቱራ ቀላቅለው እንጀራ መሳይ ነገር የሚጋግሩ ሰዎች ተበራክተዋል።ለህጻናት የሚቀርበው ወተት በኬሚካል የተሞላ ነው። ስግብግብ ነጋዴዎች ትርፋቸውን እንጂ የሰው ጤና የሚያሳስባቸው አይደሉም።የሚመለከተውም የመንግስት አካል በቂ ቁጥጥር ስለሚያደርግ ህብረተሰቡ የጤና ችግር ውስጥ ወድቋል።በየመንገዱ ውጭ ሀገራት ለመታከም ዕርዳታ የሚጠይቀውም የበሽተኛ መጠን እጅግ ከፍተኛ ነው።እኔም የእነዚህ ኢትዮጵያውን ችግር ስለሚያሳስበኝ ባ፤ኝ አቅም ሁሉ በሙያዬ ብረዳቸው ደስተኛ ነኝ።
አዲስ ዘመን፤- በሀገር በቀል ዕውቀቶች ላደረጉት አስተዋጽኦ ያገኝዋቸው ሽልማቶች አሉ?
ሀኪም አበበች፤- በሀገር አቀፍ ደረጃ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እጅ የምስክር ወረቀት አግኝቻለሁ።ኢትዮ ኦርጋኒክ የሚባል ደርጅትም አርሶ አደሩ ኦርጋኒክ ምርት እንዲያመርት ለ16 ዓመታት ያህል ላደረግኳቸው ጥረቶች ተመሳሳይ እውቅና ሰጥቶኛል።በውጭ ሀገራትም ተመሳሳይ ግብዣዎች ተደርገውልኝ ልምድና ተሞክሮዬን አካፍያለሁ።በዓለም ባንክ ጋባዥነት አሜሪካን ሀገር በሜሪላንድ እና ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ሄጄ ልምዴን አካፍያለሁ።ወርቅና 200‚000 ዶላር ሽልማትም አግኝቻለሁ።ባገኘሁት ገንዘብም የሀገር በቀል ዕጽዋቶችን ለማስፋፋት ተጠቅሜበታለሁ።
አዲስ ዘመን፤- ኢትዮጵያ ቀድሞ ሰፊ ሀገር ነበረች፤ አሁን ብልቃጥ አክላለች ሲሉ ይደመጣሉ ምን ለማለት ፈልገው ነው?
ሀኪም አበበች፤- ኢትዮጵያ የሰፊ ግዛት ባለቤት ነበረች።ከመካከለኛው ምስራቅ አልፋ በርካታውን የአፍሪካ አህጉር በግዛትዋ ስር አድርጋ ነበር።ዛንዚባር ላይ ቅርንፉድ እናመርት ነበር።ህንድ ላይ ደግሞ እርድ እናመርት ነበር።ዛሬ በአስተሳሰብም በስፋትም ጠበን መንደርተኛ ሆነናል።
አዲስ ዘመን፤- ዛሬ ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ያሳስቦታል?
በጣም ያሳስበኛል። አፍሪካን መካከለ ኛውን ምስራቅ አልፈን ስናስተዳድር የነበርን፤ ከምድር አልፈን ስለክዋክብት ስንጠበብ የቆየንና በነገስቶቻችን ስም ከዋክብቶች የተሰየሙልን ልዕለ አያል የነበርን ህዝቦች ዛሬ አንሰን በመንደርና በጎጥ ስንጣላና ስንገዳደል ከማሳሰብም አልፎ ያሳዝነኛል።ለበርካታ ሀገራት ዜጎች መጠለያና መሸሸጊያ የነበርን ህዝቦች ዛሬ ሰው በሀገሩ ከአካባቢዬ ውጣ፤ አትድረስብኝ የሚባልበት ዘመን ላይ ደርሰናል።ይህ ሁኔታ ኢትዮጵያን ወዴት ይወስዳት ይሆን ብዬ እጨነቃለሁ።
አዲስ ዘመን- ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ
ሀኪም አበበች- አኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጳጉሜ 2/2011
እስማኤል አረቦ