ዓመት ሲለወጥ ሁልጊዜ ተስፋችን ይታደሳል፡፡ አዲስ ነገርም ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ነገር ግን ሁኔታውን በደንብ ከተረዳነው የዓመቱ ወሮችና ቀኖች በራሳቸው አዲስ አይደሉም፡፡ ያለእኛ አስተዋፅኦ በራሳቸው ምንም ሊያደርጉልን አይችሉም፡፡
ያው ሰኞ፣ ማክሰኞ፣ ረቡዕ፣ ሐሙስ፣ ዓርብ፣ ቅዳሜና እሁድ ናቸው፡፡ የዓመቱ ወራቶችም በተመሳሳይ መስከረም፣ ጥቅምት፣ ህዳር፣ ወዘተ… እያለ ያንኑ የዓመቱን ወራት ይደግማል፡፡ ታዲያ አዲሱ ነገር ምንድነው? ብሎ በአዲስ ዓመት ማሰብና አንድ ነገር ላይ መድረስ ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም ጊዜው አዲስ አይደለም፤ አዲስ ዓመት አዲስ የሚያደርገው አዲሱን ዓመት ለመቀበል እድሜና ጤናውን የተቸረን ሰዎች በአስተሳሰብና በሰብዓዊነት ልኬታችን ታድሰን ስንገኝ ነው ዓመቱ አዲስ የሚሆንልን፡፡
2012 ዓ.ምን አዲስ የሚያደርገው ትናንትን በሚገባ ፈትሸን መጥፎውን ተግባርና ምግባራችንን ከጥሩው ለይተን ስናበቃ የትናንቱን ክፉ ነገር በአዲስ ዓመት ውስጥ ካልደገምነው እውነትም ዓመቱ አዲስ ይሆናል፤ አለበለዚያ ግን ያን መጥፎ ምግባራችንን እና ስራችንን መስከረም ሲጠባ የምንደግመው ከሆነ አዲስ የሚባል ዓመት አይኖረንም፡፡ በመሆኑም አሁን እያንዳንዳችን ቆም ብለን አሮጌው እንዴት አለፈ? አዲሱ ዓመትንስ እንዴት እንቀበለው በማለት ጊዜ እንስጥ፡፡
ከተነሳንበት መስፈርት አኳያ አሮጌው ዓመት ላይ ቆመን እንደ ሀገር ምን ሰራን? ብለን ስንፈትሽ ሁላችንም ተመሳሳይና የጋራ የምንላቸው ጉዳዮች አሉን፡፡ እነሱን በጋራ እናስታውስ፣ እንመርምርና በሰብዓዊነት ልክ መዝነን የቱን ይዘን ወደ አዲስ ዓመት እንሻገር? የቱንስ እንኮንን? የሚሉት ሁሉ አሁንም የጋራችን ናቸው፡፡
በ2011 ዓ.ም መባቻ ልክ የዛሬ ሳምንት እንደምንጀምረው አዲስ ዓመት አሮጌውን ዓመት የተለመደ መልካም ምኞታችንን በመግለፅ ጀመርን፡፡ ይሁን እንጂ ሙሉው ዓመት ግን እንዳሰብነው ሳይሆን ብዙ ፈተና ያየንበት፣ ብዙ ወገኖቻችን የተፈናቀሉበት፣ የሞቱበትና የተሰቃዩበት ለመሆኑ ከእኛ በላይ የሚናገርና የሚመሰክር ሊኖር አይችልም፡፡ ብቻ ዓመቱ እንደ ህዝብ እና እንደ ሀገር ብዙ የተፈተንበት ሆኖ ሊገባደድ የስድስት ቀናት እድሜ ብቻ ቀርተውታል፡፡
በመሆኑም ዓመቱ በተለይ በአንዳንድ አካባቢዎች የግጭት፣ የደም መፋሰስ የመፈናቀል፣ የሞትና የስደት እንዲሁም የሴራ ሰለባ ጭምር ሆኖ ብዙ ሀብትና የሰው ህይወትን ነጥቆናል፡፡ በተለይ ደግሞ በእነዚሁ አካባቢዎች የሚፈጠሩ አለመግባባቶችና ግጭቶችን ብሄር ተኮር በማድረግ ግጭቶቹን የከፋ መልክ በማስያዝ አላስፈላጊ ዋጋ አስከፍለውናል፤ በእነዚህ መራራ ችግሮች ቂም እና በቀል የቋጠረ በመብዛቱ የዓመቱ ድባብ በአንድ አካባቢ የተወሰነ እንቅስቃሴ ብቻ እንዲኖረን አድርጎናል፡፡ የቆየው የአብሮነት እሴታችንም ሳይቀር የተፈተነበት ነበር፡፡
እየተሰናበትነው ባለው ዓመት ሰላም በከፍተኛ ሁኔታ አጥተው ከሰነበቱ አካባቢዎች ውስጥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትላልቆቹ ማሳያዎቻችን ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተውጣጥተው እውቀት የሚቀስሙባቸው ናቸው፡፡ በእነዚህ ተቋማት ውስጥ የተሰባሰቡት ተማሪዎች ግን ሰው በመሆናቸው የተዋወቁ አይመስሉም ነበር፤ ይልቅ በአካባቢ፣ በጎጥና በብሄር በዘር ጭምር መቦደናቸው በቀዳሚነት የራሳቸውን ህይወት ሲያስከፍል፤ አገርን ክፉኛ በመጉዳት ገፅታዋ ላይ ጥቁር ጠባሳ አስ ቀምጧል፡፡
ችግሮቹ በተጨባጭ በተከሰቱባቸው አካባቢዎች ገፈቱን ሙሉ በሙሉ የተጎነጩት ወገኖቻችን፣ ነብስ አድን ብለው የኖሩበትን ቀዬ ትተው የተሰደዱ፣ የእነርሱም ዘመዶችና ቤተሰቦች በአጠቃላይ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ወሬውን ስንሰማ የነበርነው ሳይቀር የውስጥም የውጭም ሰላም አጥተን ሰንብተናል፡፡ ስሜቱ እንዲያውም ‹‹በእነዚህ ወገኖቻችን ላይ የደረሰው የግፍ ተግባር በእኔም ላይ ይደርስ ይሆን?›› እያልን በስጋት ውስጥ ሆነን ነው 2011 ዓ.ም ለመሸኘት፤ አዲስ ዓመትን ለመቀበል እየተዘጋጀን ያለነው፡፡
እውነት ነው እየሸኘነው ባለው ዓመት ከላይ አጋጠሙን ብለን ከገለፅናቸው ችግሮች በላይ በርካታ የግጭት ውጤቶችን መዘርዘር እንችላለን፡፡ ትልቁ ቁም ነገር የችግሩ ፈጣሪዎች፣ ገፈት ቀማሾች እና አባዝቶ በታኞች ሌሎች ሳይሆኑ እኛው ራሳችን ነን፡፡ ምክንያቱም የሆነው ሁሉ ወንድም በወንድሙ እንጂ ጠላት መጥቶብን አይደለምና፡፡
‹‹ነገር ቢበዛ…›› እንዳይሆን እኛ ኢትዮጵያውያን በዚህ ታሪካዊ ወቅት ላይ ሆነን ማሰብ እና ለመጪው ትውልድ ጭምር ማስቀመጥ የሚገባን፤ መፈፀምም ያለብን አንዱና ትልቁ መፍትሄ ችግሩን በጥልቀት መረዳት ነው፡፡ ለዚህ ችግር ደግሞ ዋናው መፍትሄ አገራዊ እርቀ ሰላም ማውረድ ብቻ ነው፡፡
እርቅ ስናወርድ በመጀመሪያ ውስጣችን ይፀዳል፤ ይህንን ስናደርግ ደግሞ እውነትም አዲሱ ዓመት አዲስ ይሆንልናል፡፡ ነገር ግን ዛሬም እንደትናንቱ ከሆንን አዲስነቱ ምኑ ላይ ነው? ወራቱ ወይስ ቀናቱ? እነዚህ ሁሉ ያው ናቸው፤ አዲስ አይደሉም፤ እኛ ግን ለነበረን ምግባር እና ስራችን አዲስ እንሁን፡፡ ይህ ሲሆን አዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ ይኖረዋል፡፡ መጪው አዲስ ዓመት አዲስ እንዲሆንልን ከትናንት ጥፋታችን እንታቀብ፤ በአስተሳሰብ እና በሰብዓዊነት ልኬት ራሳችንን መዝነን እንታደስ፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 30/2011