በእርግጥ የሥነ አዕምሮና ሥነ ልቦና ሊቃውንት እንደሚሉት እንደ ጭንቀት፣ ድብርትና ከመሳሰሉ ሌሎችም አዕምሮ በሽታዎች ለመዳን ተመራጩ መንገድ ራሳችንን በሥራ ውስጥ መደበቅ ነው። ይሁን እንጅ “ሰውም ሊሚት አለው” እንዳሉት ጓድ መንግስቱ ኃይለማርያም ድካም የተፈጥሮ ባህሪያችን ነውና እረፍት ማድረግም ከሥራ እኩል ለጤና አስፈላጊ ነው። ሁሌም በእረፍት ላይ መኖር ለጭንቀትና ድብርት መንስኤ እንደሚሆነው ሁሉ እንደዚሁ ያለ እረፍት መስራትም ከሰው ተፈጥሯዊ ባህርይ ተቃራኒ በመሆኑ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናልና። እኛም ለዛሬው ከደረቅ ነገሮች ወጣ እንበልና ዘና እያልን እረፍት እናድርግ። ታዲያ በዚህ ከተስማማን እርስዎ ሳምንቱን ሙሉ በሥራ ተጠምደው ሰንብተው ቅዳሜና እሁድ ሲመጣ በሥራ የዛለ አካልዎን ዘና ለማድረግ ወደ የት ነው የሚሄዱት?
ምናልባት ከጓደኞችዎ ጋር ሰብሰብ ብለው ሻይ ቡና እያሉ ጥሩ ጊዜ ሊያሳልፉ ወደሚችሉባቸው መናፈሻ ቦታዎች ሊያመሩ ይችላሉ። አለያም ከከተማ ወጣ ብለው ነፋሻውን አየር ተመግበው፤ ጋራ ሸንተረሩን ቃኝተው፣ የዛፎቹ ጥላ ሥር አርፈው የወፎቹን ዜማ አዳምጠው፣ በአበቦች መዓዛ ረክተው ተፈጥሮን በማድነቅ ራስዎን አዝናንተው ሊመለሱ ይችላሉ። ምናልባትም እርስዎ መጠጣት ላያስደስትዎት ይችላል (መጠጣት ሲባል ውሃ አለመሆኑ ልብ ይባልልኝ። ያችን ሞቅ የምታደርገንንና የሆድ የሆዳችንን የምታስወራንን የመጠጥ ቤቷን ወዳጃችን ማለቴ ነው) መጠጣት የሚያዝናናቸው ግን ብዙ ሰዎች አሉ። ብቻ መዝናናት ወይም መዝናኛ እንደየሰው ፍላጎትና ስሜት ይለያል። እርስዎን የሚያዝናናዎ ሌላውን ላያዝናናው ይቻላል። እናም መዝናናት ልክ እንደ ውበት ነው። ውበት እንደ ተመልካቹ፤ መዝናኛም እንደ ተዝናኝው ነው።
ብዙውን ጊዜ ግን መዝናናት ሲባል ቀድሞ ወደ አዕምሯችን የሚመጣው በሥራ የደከመ አካላችንን ዘና የሚያደርግልን ነገር ነው። ሆኖም የሚደክመው አካላችን ብቻ አይደለም። ያለ ምንም እረፍት በርካታ ጊዜያትን በሥራ ተወጥረን በምናሳልፍበት ጊዜ አካላችን ብቻ ሳይሆን አዕምሯችንም ድካም ይሰማዋል፤ የምንሰራቸው ሥራዎች የሚሰሩት በአካል ብቻ ሳይሆን በአዕምሮም ጭምር ነውና። ስለሆነም መዝናናት ያለበት አካላችን ብቻ ሳይሆን አዕምሯችንም ጭምር መሆን አለበት። ሰው አካላዊም አዕምሯዊም ፍጡር ነውና። ለምሳሌ እርስዎ በስራ ብዛት የደከሙ ጡንጫዎችዎችን ዘና ለማድረግና እንደገና በአዲስ ኃይል ለመሙላት ማሳጅ ሊያደርጉ (ሰውነትዎን ሊታሹ) ይችላሉ።
በውጥረት የደከመ (የተሰላቸ) አዕምሮዎን ዘና ለማድረግ ቢፈልጉስ? ምን ያደርጋሉ? ለዚህማ የአዕምሮ ማሳጅ ቤት ያስፈልግዎታል። አዕምሮ ከድካሙ የሚታደሰውና እንደገና አዲስ ኃይል የሚያገኘው ከመሰልቸትና ከተስፋ መቁረጥ ስሜት ተላቅቆ ስለ ስኬትና ድል አድራጊነት ማሰብ ሲጀምር፣ በህይወት ጉዞ ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በፅናት ታግሎ ሲያሸንፍና መሰናክሎችን በብቃት አልፎ ያሰበበት መድረስ ሲችል ነው። ይህ እንደሚቻልም ማወቅና ማመን ነው የአዕምሮ ማሳጅ የሚባለው። ደጉ ነገር ደግሞ የአዕምሮ ማሳጅ ለማግኘት እንደ አካላዊው ማሳጅ ብዙም ከባድ አለመሆኑ ነው።
በእርግጥ አካላዊ ማሳጅ ለማድረግ የሚከፈለው ክፍያም ያን ያህል ውድ ሆኖ አይደለም (ለእኔና የእኔ ቢጤ ጓደኞቼ ግን ለማሳጅ የሚከፈለው የወር አስቤዛችን ሊሆን ስለሚችል አቅማችንን እንድናውቅ ብዬ ነው)። ለማለት የፈለግኩት የአዕምሮ ማሳጅ ለማድረግ በእርግጥም ብዙ የሚያስወጣ አይደለም ነው። በተለይ መረጃ እጅዎ መዳፍ ላይ በሆነበት በአሁኑ ዘመን አዕምሮዎን ለማነቃቃትና በአንዳች ደስ የሚል የአሸናፊነት ስሜት ለመሙላት ጥቂት ሳንቲሞችን አውጥተው ስለ ስኬት የተጻፉ መጽሃፎችን ማንበብ (በተመሳሳይ እጅዎ ላይ የሚገኘውን ተንቀሳቃሽ ስልክዎንም ለዚህ ተግባር ሊጠቀሙበት ይችላሉ) አለያም ንግግሮችን ሊያዳምጡና ቪዲዮዎችን ሊመለከቱ ይችላሉ። እንግዲያውስ እኛም ለዛሬው እጅግ በርካታ ተስፋ አስቆራጭ ችግሮችን አሸንፎ በመጨረሻም አስደናቂ የስኬት ማማ ላይ በደረሰው ቻይናዊ የስኬት ሰው ቢሊየነር ጃክ ማ ህይወት ጥቂት አዕምሯችንን ማሳጅ እናድርግ።
ጃክ ማ በአሁኑ ሰዓት የሃምሳ ሦስት ዓመት አዛውንት ነው። መሰረቱን በሃገረ ቻይና ሻንጋይ ከተማ ውስጥ ያደረገው ይህ ሰው የዝነኛው የኢንተር ኔት ንግድ ኩባንያ የአሊባባ ግሩፕ መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ነው። አሊባባ ግሩፕ በገንዘብ ቢተመን 519 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው ግዙፍ የንግድ ኩባንያ ነው። ታዲያ ሚስተር ጃክ ማ እዚህ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፏል። በተደጋጋሚ ተስፋ አስቆራጭ ፈተናዎች ቢያጋጥሙትም፣ ብዙ ሰዎች ወላጅ እናቱ ሳይቀሩ እንደማይሆንለት ቢነግሩትም “አምቢ ተስፋ አልቆርጥም አንድ ቀን ይሳካልኛል” በማለቱ ከበርካታ እልህ አስጨራሽ የመከራ ዓመታት በኋላ በስተመጨረሻ የአሸናፊነቱን ካባ ተጎናጽፏል።
ስለ ጃክ ማ ሲነሳ አስገራሚው ነገር ሰላሳ ዓመት እስኪሞላው ድረስ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ህይወትን እንኳን በአግባቡ ለመምራት የሚያስችለው ሥራ እንኳን ያልነበረው መሆኑ ነው። ከ30 በላይ በሚሆኑ ድርጅቶች ስራ ለመቀጠር ተወዳድሮ በአንዱም ተቀባይነትን ሳያገኝ ቀርቷል። አሁን ለእራሱ ሥራ ከማግኘት አልፎ ለሚሊዮኖች ሥራ ያስገኘው ያኔ ቀጣሪ ያጣው ወጣት ወቅቱን እንዲህ ሲል ያስታውሰዋል፤ “በርካታ ጊዜያት ወድቄያለሁ። ሥራ ለማግኘት ብዙ ጊዜ ተወዳድሬ ሁሉም ሳይሳካልኝ መቅረቱን ሰዎች ያውቃሉ። 30 ጊዜ አመልክቼ በአንዱ እንኳን ማለፍ አልቻልኩም፤ እንድወዳደር እንኳን ዕድሉን አልሰጡኝም”። የሚገርማችሁ ነገር ይላል ጃክ ማ …“አንድ ጊዜ አንድ ሥራ ለመቀጠር ሃያ አራት ሰዎች አመልክተን ሁላችንም ለቃለ መጠይቅ ቀረብን። ሃያ ሦስቱንም ቀጠሯቸው፤ እኔን ብቻ ነው ያባረሩኝ”። በሌላ ጊዜ ደግሞ እንደዚሁ ከሌሎች አምስት ሰዎች ጋር ሆኖ ለፖሊስነት ተወዳድሮም አብረውት ያመለከቱት ሁሉም ተወዳዳሪዎች ፈተናውን አልፈው ሲቀጠሩ እርሱ ተቀባይነትን ሳያገኝ ቀርቷል። ምን ይሄ ብቻ በአንድ ወቅት ከአጎቱ ልጅ ጋር ሆነው ለሆቴል አስተናጋጅነት አመልክተው የአጎቱ ልጅ ሲቀጠር ዕድል ፊቷን ያዞረችበት ማ ግን አሁንም እንደገና ማመልከቻው ውድቅ ተደርጓል። በዚህም ህይወት በጣም አስቸጋሪ ሆኖበት እንደነበርና ወላጅ እናቱ እንኳን ሳትቀር ችሎታ እንደሌለውና ለስቃይ የተፈጠረ ከንቱ ዕድለ ቢስ ሰው አድርጋ ትቆጥረው እንደነበር ማ ወደ ኋላ ተመልሶ ያሳለፈውን የችግርና የመከራ ዘመን ያስታውሳል።
ይሁን እንጅ ይላል ማ፤ “… ያን ያህል መከራና ውድቀት ቢበዛብኝም፣ ሰዎች እርባና ቢስ አድርገው ቢቆጥሩኝም እኔ ግን ለወደፊት ህይወቴ አስፈላጊ የሆኑ ትምህርቶችን እየተማርኩ እንደነበረ አውቅ ነበር። ይሄ ነው እንግዲህ እጅግ አስፈላጊውና በዓለም ላይ ምርጡ የአዕምሮ ማሳጅ፤ በተስፋ አስቆራጭ ችግር ውስጥ ሆኖም ሽንፈትን ድል መንሳት– እምቢ ተስፋ አልቆርጥም ማለት! በመሆኑም ጃክ ማ ዛሬ 519 ቢሊዮን ዶላር የሚያንቀሳቅስ ግዙፍ ኩባንያ ባለቤት ነው።
ከቁሳዊው ሃብትና ንብረት ባለፈም ለብዙዎች በመመሪያነት የሚያገለግልና ለስኬት የሚያበቃ አስተሳሰብና ዕውቀትም ባለቤት ነው። ለዚህም ነው በቅርቡ ስዊትዘርላንድ ዳቦስ ላይ በተካሄደው የዓለም መሪዎችና ታላላቅ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ምሁራን በተገኙበት የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ ተጋብዞ አስተሳሰቡንና ልምዱን ሲያካፍል የተመለከትነው። በፎረሙ ላይ ተገኝቶ አስደናቂ ንግግር ያደረገው ጃክ ማ፤ “ስኬታማ መሆን ከፈለጋችሁ ከሰዎች ስኬት ሳይሆን ከስህተታቸው ተማሩ” ብሏል።
በተለይም ወጣቶች በተሰማሩበት የሙያ መስክ ስኬትን ለመቀዳጀት ምን ማድረግ እንደሚገባቸው ለጠየቁት ከተለያየ አገር የመጡ ወጣት መሪዎች፤ “ከ20 እስከ 30 ዓመት ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ የምትገኙ ወጣቶች ከሆናችሁ ነገሮችን በምን መልኩ መስራት እንዳለባችሁ ትማሩ ዘንድ ጥሩ ድርጅት ውስጥ ተቀጥራችሁ ከጥሩ አለቆች ጋር ሥሩ፣ እነርሱ የሚሏችሁንም ተከተሉ” ብሏቸዋል።
እንግዲህ ጃክ ማን ለዚህ ሁሉ ስኬት ያበቃው ዋነኛው ምክንያት የ“እምቢ ተስፋ አልቆርጥም” አስተሳሰቡ ነው። ይሄንን አስተሳሰብ ነው በርካታ ውስብስብ ችግሮች በሞሉባት በዚህች ውጥንቅጥ ዓለም ውስጥ ሆነን በሃሳብ ብዛት አዕምሯችን ለደከመው፣ ተመሳሳይ በሆነና ለውጥ በሌለበት የተሰላቸውን ህይወታችንን እንደገና የሚያነቃቃልን፣ የሚያክምልን፣ ትኩስ ኃይል የሚፈጥርልን ዘና የሚያደርግልን ምርጡ የአዕምሮ ማሳጅ ያልነው። ያኔም ልክ እንደ ጃክ ማ መከራና ችግር ከበዛበት የውድቀት ህይወት ተላቅቀን የተስፋ መቁረጥና የእርባና ቢስነት ስሜትን አሸንፈን ወደእምንፈልገው የደስታና የሙላት ህይወት የምንደርሰው።
ሁሌም በልቶ ከማደር ያልዘለለውን ከእጅ ወደ አፍ መናኛ ህይወታችንን ለማቃናት ሌት ተቀን ከመዳከር ባለፈም የተፈጠርንለትን ዓላማ ማሳካት የምንችለውና ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የሚተርፍ ትርጉም ህይወት መኖር የምንችለው አዕምሯችን በእዚህ የአልሸነፍ ባይነት አስተሳሰብ የተሞላ ሲሆን ነው።
ሌላው ውድ አንባቢያን ሩጫና ጥድፊያ በሞላበት በእዚህ የድካም ዓለም በሃሳብና በሥራ የተወጠረ አዕምሮን ዘና ለማድረግ ምንም የማይከፍሉበትን ነገር ግን ብዙ የሚያተርፉበትን ምርጥ የአዕምሮ ማሳጅ ልጠቁምዎ። ይህም መንፈስን በማደስና ደስታን በመለገስ ረገድ ወደር ያልተገኘለት ፍቱን የአዕምሮ ማሳጅ ሰው በመሆንዎ ብቻ ተፈጥሮ በነጻ የለገሰችዎ ፈገግታዎ ነው። ፈገግታ ብዙ ሚስጥሮችን የያዘ ለሰው ልጆች ብቻ የተሠጠ (በፈገግታ የተሞላ በሳቅ የሚፍለቀለቅ እንስሳ አይቼ አውቃለሁ የሚል ካለ ገጠመኙን ሊያጋራን ይችላል) ውድ ተፈጥሯዊ ስጦታ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ምክንያቱም ፈገግታ የደስታ ምንጭ ነው። ለራስም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ፈገግታ የሚሰጠው በረከት ብዙ ነው። ፈገግታ ለጤንነት፣ ለጓደኝነትና ለማህበራዊ ግንኙነት አልፎ ተርፎም በንግድ ሥራ ለተሰማሩ ሰዎች ደንበኞችን ለመሳብና ገበያን ለማድራት የሚያስችል ልዩ ኃይል እንዳለው ሳይንስ ይመሰክራል። በአንድ ወቅት ጃፓን አገር ውስጥ የሚገኙ ትልልቅ የንግድ ኩባንያዎች ለሽያጭ ሰራተኞቻቸው ስለ ፈገግታ ስልጠና እንደሚሠጡ ማንበቤ ትዝ ይለኛል።
በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ጊዜያት ስለ ፈገግታ የተባሉ አስደናቂ አባባሎችም ይህንን ተዝቆ የማያልቅ የፈገግታ በረከት የሚገልጹ ናቸው። ጥቂቶቹን ብቻ ጨልፌ ላቃምሳችሁ። አንድ ያልታወቀ ደራሲ ስለ ፈገግታ ተዓምረኛነት የሚከተለውን ብሏል።
‹‹ፈገግታ የሚቆየው አንድ አፍታ ነው የሚፈጥረው ትዝታ ግን እስከ ዘላለም የማይጠፋ ነው። ፈገግታ ምንም ወጭ የማያስወጣ ግን በጣም ውድ የሆነ ነገር ነው። ሰጭውን አያደኸይም ተቀባዩን ግን ያበለፅጋል። ፈገግታ አያስፈልገኝም የሚል ሐብታምና ጉልበታም የለም፤ ምንም ስለሌለኝ መስጠት አልችልም የሚል ደሃም የለም።
‹‹ ፈገግታ በቤተሰብ ውሥጥ ደስታን ይፈጥራል፤ በሥራ ቦታ ደግሞ መተማመንን ያመጣል። ለጓደኝነት ዋስትና ነው። ለደከመ ደግሞ ብርታት ይሆናል። መከራ ለዋጠው ፍቱን ማርከሻ ነው። ፈገግታ አይገዛም፣ በልመናም አይገኝም። በውሰት አይሰጥም፤ ደግሞም በስርቆት አይገኝም፤ ምክንያቱም በንጹህ ልብ ካልለገሱት በስተቀር ማንንም አይጠቅምምና።
‹‹ አንዳንዶች ፈገግታቸውን ለመስጠት ይሰንፋሉ፤ ግዴለም የናንተን ስጧቸው። ምክንያቱም ፈገግታውን ለሌሎች መስጠት የሚቸግረውን ሰው ያህል ፈገግታ የሚያስፈልገው ሰው የለምና!››
“እስካሁን ድረስ በፈገግታ ውስጥ ሆኖ ቆንጆ ያልሆነ ፊት አይቼ አላውቅም” ኒው ዮርከር
“ከእያንዳንዱ ዶፍ በኋላ ፀሐይ ፈገግ ትላለች፤ ለእያንዳንዱ ችግርም የራሱ መፍትሄ አለው። የእኛ ሥራ የሚሆነው ለነፍሳችን ጥሩ ፈገግታን መለገስ ነው” ዊሊያም አር. አልገር
“ሰላም የሚጀምረው ከፈገግታ ነው፤ አንተ ታላቅ ፈገግታ ከለበስክ ሰዎች አሮጌ ልብስ መልበስህን እንኳን ላያስተውሉት ይችላሉ” ሊ ሚልደን
“በእያንዳንዷ ሰዓት የሆነ ሰው ስታይ ፈገግ ልትል ትችላለህ፤ ይህ የፍቅር ድርጊት ነው፤ ይህ ለዚያ ሰው ስጦታ ነው፣ ውብና ደስ የሚል ነገር” ማዘር ቴሬሳ
“ወደ ሰዎች ስመለከት እነሱም አይተውኝ ፈገግ ካሉ እንደተወደድኩና እንደተፈቀርኩ ይሰማኛል። ይህም ከጭንቀትና ከችግር ነጻ የምሆንበት ጊዜ ነው” ኢታ ጀምስ
“እሱ ከመቆጣት ይልቅ ፈገግታን የሚመርጥ ሁል ጊዜም ጠንካራ ሰው ነው፤ አንዳንድ ጊዜ ደስታዎ የፈገግታዎ ምንጭ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ፈገግታዎም የደስታዎ ምንጭ ሊሆን ይችላል” ቲሂች ንሃት ሃንህ
እስቲ ስለ ፈገግታ ይሄን ያህል ካልን የሚከተለውን ስለ ሁለት መንትዮች የሚያወራ ቀልድ እንንገርዎትና ፈገግ ይበሉ። በልሁና አጥናፉ መንትያ ወንድማማቾች ናቸው። በልሁ አሮጌ የዓሳ ማጥመጃ ጀልባ አለችው። አጋጣሚ ሆኖ የአጥናፉ ሚስት በሞተችበት ዕለት የበልሁ ጀልባም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሃይቅ ውስጥ ሰምጣ ቀረችበት። ከጥቂት ቀናት በኋላ ሁለቱንም ወንድማማቾች የሚያውቁ የሰፈራቸው አንዲት አሮጊት በልሁን ያገኙትና አጥናፉ መስሏቸው በኃዘን ስሜት እየተመለከቱት “እንዴት ነህ ልጄ? ለመሆኑ በረታህ? ምን ዓይነት ክፉ አጋጣሚ ነው ያገኘህ? አዬዬ…”አሉት።
በልሁም ስለሰጠመችው ጀልባ የሚጠይቁት መስሎት በጣም በማዘናቸው እሱም አዝኖላቸው “አይ አይ እማማ አረ እንዲያውም ተገላገልኳት! ድሮም ቢሆንኮ በስብሳ አርጅታለች። የተበላሸ ዓሳ፣ ዓሳ እየሸተተች ነበር። ከፊትም ከኋላም ተበሳስታ ነበር። ቆይ ዛሬ ቆይ ነገ እቀይራታለሁ ስል ነው ለአራት አጥማጆች አከራይቻት የገላገሉኝ። አረ ትሂድ ደስ ብሎኛል….” እያለ ሊቀጥል ሲል አሮጊቷ የሚያወራው ነገር አስደንግጧቸው …. አጥወልውሏቸው ዓይናቸው ተስለምልሞ እግራቸው ሸብረክ ብሎ ሊወድቁ ሲሉ ደግፎ ያዛቸው።
“ከፍትፍቱ ፊቱ” የሚለው አገርኛ ፈሊጥስ የሚናገረው ፈገግታ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አይደል። በዚያ ላይ ምንም ወጭ የማያስወጣ ቀላል ነገር ነው። እንዲያውም ከዚህ ጋር ተያይዞ ሳይንሱ ያረጋገጠውን አስገራሚ ነገር ልንገራችሁ። አንድ ሰው ፊቱን ለማኮሳተር አርባ የሚደርሱ ጡንቻዎችን ማዘዝ የሚኖርበት ሲሆን ፈገግ ለማለት ግን ከዚህ አራት እጥፍ የሚያንሱ ጡንቻዎቹን ብቻ ነው አገልግሎት ላይ የሚያውለው። ታዲያ ያለምንም ልፋት በቀላሉ በርካታ ትሩፋቶችን ይዞልን የሚመጣውን ብዙ ጉልበት የማይጠይቀውን ፈገግታ በመምረጥ አዕምሯችን በቀላሉ ማሳጅ ማድረግና ልባችንን በደስታ መሙላት ይቻላል። አዕምሮዎ እንዲነቃቃ ስለ ስኬት ያስቡ፣ ይናገሩ፣ ያንብቡ፤ መንፈስዎ እንዲታደስ፣ ልብዎ በደስታ እንዲሞላ ፈገግ ይበሉ፤ አካልዎን ብቻ ሳይሆን አዕምሮዎንም ማሳጅ ያድርጉ፤ ዘና ይበሉ የሚለው የሳምንቱ መልዕክቴ ነው። ዘና የሚሉበት መልካም ሳምንት እየተመኘሁ የዛሬውን በዚሁ አበቃሁ።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሀሴ 29/2011
ይበል ካሳ