ከውል ውጭ የሚመጡ ኃላፊነቶችን በወፍ በረር
እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
ከስያሜው በቀላሉ ለመረዳት እንደሚቻለው ከውል ውጭ የሚመጣ ኃላፊነት በሰዎች መካከል ምንም ዓይነት የውል ግንኙነት ሳይኖር በሌላው ሰው ላይ ለሚደርስ ጉዳት ተጠያቂነትን የሚያስከትል የፍትሐብሔር ግዴታ ነው። ኃላፊነቱ በስምምነትና ሃሳብ ለሃሳብ በመግባባት ላይ የተመሰረተ አይደለም። ይልቁንም በውል ባልሆነ ግንኙነት ሰዎች ወደውና ፈቅደው ባልፈጸሙት አድራጎት ጉዳት ለደረሰበት ሰው ተጠያቂ የሚሆኑበት ፍትሐብሔራዊ ኃላፊነት ነው። (የወንጀል ጥፋት ያልሆነ ማለት ነው)
በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2027 እንደተደነገገው ከውል ውጭ የሚደርስ ኃላፊነት ከሶስት ሁኔታዎች ይመነጫል። እነዚህም በራስ ጥፋት በሌላ ሰው ላይ ጉዳት በማድረስ፤ አጥፊ ሳይሆን ኃላፊ ስለመሆን ማለትም የራስ ጥፋት ባይኖርም እንኳን በአንዳንድ በሕግ ተለይተው በተጠቀሱ አድራጎቶች ወይም ንብረቶች አማካኝነት በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ሲደርስ እንዲሁም በሌሎች ሰዎች ጥፋት በሌላው ሰው ላይ ጉዳት ሲደርስ ኃላፊ መሆን ናቸው።
አንድ ሰው በራሱ ጥፋት በሌላ ሰው ላይ በሚያደርሰው ጉዳት ከውል ውጭ የሚመጣ ኃላፊነት እንዳለበትና ካሣ ሊከፍልም እንደሚገባው ሕጉ አስቀምጧል። እዚህ ላይ መሰረታዊው ነጥብ ታዲያ “ጥፋት” ምንድን ነው የሚለው ነው። በፍትሐብሔር ሕጉ በስፋት ተደንግጐ እንደምናነበው ጥፋት ሰፊ አንድምታ ያለው ጉዳይ ነው። አንድ ሰው አስቦ ወይም በቸልተኝነት በሚሰራ ተግባር ጥፋት ሊያደርግ ይችላል። በሌላ በኩል አንድ ተግባርን መፈጸም ወይም አለመፈጸም ጥፋት ይሆናል።
ይህ ብቻ ሳይሆን አንድ ሰው ሕሊናን ወይም መልካም ጠባይን ተቃራኒ በሆነ መልኩ የማይገባውን የሰራ ወይም የሚገባውን ሳይሰራ የቀረ እንደሆነ ጥፋት አድርጓል ይላል ሕጉ። በተጨማሪም ሕጉ በሙያ ሥራ ላይ ስለሚደረግ ጥፋት ሲደነግግ በልዩ ሙያው አንድ ሥራ የሚፈጽም ሰው ወይም በዚህ ሙያው የሥራ ተግባሩን የሚያካሂድ ሰው የሙያ ስራው የሚመራበትን ደንብ መጠበቅ እንደሚገባው ግዴታ አስቀምጧል። አገርና ሕዝብን እንዲያገለግልበት በተሰጠው ሥልጣን ለግሉ ወይም ለሌላ ሰው ጥቅም የሰራ ሹመኛም (ሰራተኛም ቢሆን) ለጥፋቱ ኃላፊ ነው።
ከውል ውጭ ለሚደርስ ኃላፊነት ሁለተኛው ምንጭ አጥፊ ሳይሆን ኃላፊ መሆን ነው። ይኸውም አንድ ሰው በራሱ ጥፋት ባይሰራም እንኳን በአንዳንድ በሕግ ተለይተው በተጠቀሱ አድራጎቶች ወይም በንብረቶቹ አማካኝነት በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ቢደርስ ጥፋተኛ ሆኖ የሚጠየቅበት ሁኔታ ነው። አንድ ሰው አጥፊ ሳይሆን በህጉ ላይ እንደተመለከተው ተለይተው በተቀመጡ አድራጎቶች ወይም ንብረቶች አማካኝነት በሌላ ሰው ላይ ለሚደርስ ጉዳት ተጠያቂ የሚሆነው በሕግ ተለይተው በተቀመጡት የተወሰኑ ጉዳዮች ማለትም አስፈላጊ ሁኔታ፣ የአካል ጉዳት፣ ሕንጻዎች፣ መኪናዎች፣ አደገኛ ስራዎች፣ ሞተር ተሽከርካሪዎች እና የተፈበረኩ እቃዎች ለሚደርስ ጉዳት ነው።
ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑትን በምሳሌ እንመልከት። አስፈላጊ ሁኔታ የሚለውን ሕጉ ሲደነግግ አንድ ሰው ራሱን፣ ሌላን ሰው፣ ሃብቱን ወይም የሌላውን ሰው ሃብት በእርግጥ ሊደርስበት ከሚችል አደጋ ለማዳን ሲከላከል በሌላው ሰው ላይ ሆነ ብሎ ጉዳት ካደረሰ (በተጎጂው ጥፋትና ምክንያት ካልሆነ በቀር) ተጠያቂ ነው ይላል። መኖሪያ ቤቱ በእሳት ሲቃጠልበት በድንገት የደረሰ ሰው የጎረቤቱን በር ገንጥሎ በመግባት የእሳት ማጥፊያ መሳሪያ አውጥቶ እሳቱን ቢያጠፋ በጎረቤቱ ንብረት ላይ ላደረሰው ጉዳት ኃላፊ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ የሚፈነዱ ወይም መርዛማ ነገሮችን በመጠቀም፣ በማከማቸት እንዲሁም የኤሌክትሪክ መስመር የሚዘረጋ ወይም የመሬትን የተፈጥሮ አቀማመጥ መቀየርን በመሳሰሉ አደገኛ ስራዎች ላይ የተሰማራ ሰው በሥራው ሳቢያ ጉዳት ካደረሰ ካሣ የመክፈል ኃላፊነት አለበት።
ከዚህ የኃላፊነት ዓይነት መረዳት እንደሚቻለው ታዲያ ኃላፊነቱ ያለጥፋት የሚመጣ ሲሆን፤ ካሣ እንዲከፍል የሚከሰሰው ሰው ጥፋተኛ አለመሆኑን በማስረዳት ከኃላፊነት አይድንም። ካሣ ለማግኘት ደግሞ ጉዳት መድረሱንና መንስኤውን ማስረዳት ብቻ በቂ ነው።
ሶስተኛው ከውል ውጭ የሚደርስ ኃላፊነት ምንጭ በሌላ ሰው ጥፋት ተጠያቂ መሆን ነው። አንድ ሰው በራሱ ምንም ጥፋት ባይፈጽምም ወይም በሚያከናውናቸው ተግባሮች ወይም በንብረቶቹ ምክንያት ጉዳት ባይደርስም ሌላ ሰው በፈጸመው ተግባር ለሚመጣ ጉዳት ኃላፊ የሚሆንበት የህግ አግባብም አለ።
ይኸውም አንደኛው አካለ መጠን ያላደረሰ ልጅ ለሚፈጽመው ጥፋት ወላጆች ወይም ሞግዚትና አሳዳሪዎቹ ኃላፊ የሚሆኑበት ነው። ሁለተኛው መንግስትም ሆነ ሌሎች ቀጣሪዎች ሰራተኞቻቸው ወይም ወኪሎቻቸው የተቀጠሩበትን ስራ በሚያከናውኑበት ወቅት ለሚያደርሱት ጥፋት ኃላፊ የሚሆኑበት ሁኔታ ነው። ሶስተኛው ሁኔታ ደግሞ በፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 2135 ላይ ተደንግጐ እንደምናነበው የአንድ ጽሁፍ ደራሲ፣ የጋዜጣ መሪ፣ የበራሪ ማስታወቂያ (ፓምፍሌት) አታሚ ወይም የመጽሐፍ አውጪ (ፐብሊሸር) በጽሁፍ ውስጥ ለተፈጸመ የሥም ማጥፋት ኃላፊዎች የሚሆኑበት ነው።
ከሕክምና ሙያ የሚመነጭ ከውል ውጭ ኃላፊነት
ከሕክምና ሙያ ጋር በተያያዘ የሚመጣውን የፍትሐብሔር ኃላፊነት ብቻ እንደ ሰበዝ መዝዘን በዚህ ጽሁፍ ለመመልከት ወደድን እንጂ በጠቅላላው የሙያ ጥፋት የሚባለው ጉዳይ በራሱ በጣም ሰፊ ጽንሰ ሃሳብ ነው። የሙያ ጥፋትን ለመመልከት የሙያን ምንነት አስቀድሞ መረዳት ጠቃሚ ነው። በሙያ ስራ የሚደረግ ጥፋትን የተመለከተው የፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 2031 እንደሚደነግገው በልዩ ሙያው አንድ ስራ የሚፈጽም ሰው ወይም በዚህ በሙያው የሥራ ተግባሩን የሚያካሂድ ሰው የዚሁ የሙያ ሥራው የሚመራበትን ደንብ መጠበቅ ይገባዋል። ይህ ሰው ታዲያ በደንቡ መሰረት ያሉበትን ግዴታዎች አለመከተሉ ሲታወቅ ባለመጠንቀቁ ምክንያት ወይም በቸልተኝነቱ ጥፋተኛ ሆኖ በተገኘ ጊዜ ለሚያደርሰው ጉዳት ኃላፊ ይሆናል።
“ከውል ውጭ ኃላፊነትና አላግባብ መበልጸግ ሕግ” በሚል ንጋቱ ተስፋዬ ባሰናዳው መጽሐፍ ውስጥ ሙያ የሚለው ቃል Profession ወይም Trade በሚሉ ሁለት አንድምታዎች ተብራርቷል። Profession የሚለው ቃል የሚያመለክተው በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ገብቶ በመማር የሚገኘውን እንደ ሕክምናና ምህንድስና የመሳሰለውን ሙያ ነው። Trade የሚለው ቃል ደግሞ ባለሙያዎች በሥራ ላይ የሚያከናውኑትን እየተመለከቱ ዕውቀት የሚቀስሙበትን እንደ ግንበኝነት፣ አናጢነት፣ አሽከርካሪነት እና ለዕለት ጥቅም ማግኛ የሚከናወኑትን ሥራዎች ሁሉ ይጨምራል።
ንጋቱ ተስፋዬ ከላይ በተጠቀሰው መጽሐፉ ውስጥ የሙያ ጥፋት የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ከውል ውጭ ኃላፊነት ይልቅ ከውል ለሚመነጭ ኃላፊነት ይበልጥ አስፈላጊ መሆኑን ያስረዳል። አያይዞም የሙያ ደንቦችን ባለማክበር በሚፈጸሙ ተግባሮች ላይ የሚመሰረቱ ብዙ የካሣ ክርክሮች የሚነሱት ከውል ግንኙነቶች እንጂ ከውል ውጭ ኃላፊነት አይደለም ሲልም ያብራራል። የሐኪሞችን ተጠያቂነት አስመልክቶ ትንታኔውን ሲቀጥልም የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2647 የሙያ ደንቦችን ባላከበሩ ሐኪሞች ላይ የውል ኃላፊነትን ከሚጥል ውጭ በሆስፒታሎች ተቀጥረው ለሚያገለግሉ ሐኪሞች ከውል ውጭ ኃላፊነት በፍጹም ሊደርስ አይችልም ይላል። ምክንያቱን ሲያስቀምጥ ደግሞ ግንኙነቱ በውል ላይ የተመሰረተ ስለሆነ በማለት ይደመድማል።
በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተሰጠን አንድ ውሳኔ ከዚህ ድምዳሜ አንጻር እንመልከተው። አንዲት ነፍሰጡር እናት በአዲስ አበባ በሚገኝ አንድ የግል ሆስፒታል የቅድመ ወሊድ ክትትልና ምርመራ ስታደርግ ትቆያለች። የመውለጃዋ ጊዜ ሲደርስም በዚያው ሆስፒታል ውስጥ በአዋላጅ ሐኪም እርዳታ ትወልዳለች። ይሁንና የተወለደችው ሕጻን ጤናዋ የተጓደለ ሆነ።
በዚሁ መነሻ የህጻኗ እናት ሆስፒታሉንና ሐኪሙን በአንድነት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፍትሐብሔር ክስ መሰረተችባቸው። በክሷም በወሊድ ወቅት አዋላጅ ሐኪሙ በትክክለኛ የማዋለድ ሥርዓት የሙያ ግዴታቸውን መፈጸም ሲገባቸው ይህንን ባለማድረጋቸው በቸልተኝነት በፈጸሙት ድርጊት የወለድኳት ልጅ ለከፍተኛና ቋሚ የአካል ጉዳት ተዳርጋለች። የጡንቻዎች መስነፍ፣ የብራኳ አጥንት መስለል፣ የቀኝ እጅ መስነፍና መታጠፍ መዘርጋት አለመቻል ጉዳት አጋጥሟታል። በመሆኑም ሕጻኗ ወደ ውጭ ሔዳ መታከም እንዳለባት በሐኪሞች በመወሰኑ ለዚሁ የህክምና ወጪ የሚሆን፤ በእድሜ ልኳ ለሚረዳት ሰራተኛ የሚሆን፤ ለጸጉር መሰሪያ፣ ለተሽከርካሪ ሾፌር ደመወዝ፣ ወደፊት ለምትወልዳቸው ሶስት ልጆች ተንከባካቢ እንዲሁም ለጂምና ለፊዚዮቴራፒ የሚሆን ወጪ እና የሞራል ካሳ ከሕጋዊ ወለድ ጋር እንዲከፍሉ አመለከተች።
አዋልደዋል የተባሉት ሐኪም በጋዜጣ ሳይቀር ተጠርተው ሊቀርቡ ባለመቻላቸው ሆስፒታሉ ብቻ ነበር ክርክሩን ያደረገው። ሆስፒታሉ በሰጠው መልስም በቂ መሳሪያዎችና ስፔሻሊስት ሐኪሞችን በማቅረብ አገልግሎት የሚሰጥ ስለሆነ ለደረሰው ጉዳት የራሱ ጥፋት እንደሌለበት፤ ሐኪሙም በስፔሻሊስት ደረጃ የተመረቁ በሙያ ሥነ ምግባራቸውና ጠንቃቃነታቸው መልካም ሥም ያተረፉ ናቸው በማለት የተጠየቀው ካሣም የተጋነነ ነው ሲል መልሱን ሰጥቷል።
ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የመዳኘት ስልጣኑ የተመለከተው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሆስፒታሉ በገባው የወሊድ ውል መሰረት ጤናማ ሕጻን እንድትወለድ አላደረገም በማለት ጥፋተኛ ነው ሲል ወስኖበታል። ሐኪሙ ደግሞ የማዋለድ ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት የወሰዱትን የሕክምና ሂደት (ፕሮሲጀር) ያልመዘገቡ በመሆኑ ይህም በሙያ ምስክሮች ጥፋት መሆኑ የተረጋገጠ ስለሆነ፤ ሕጻኗ ስትወለድ አራት ነጥብ ሶስት ኪሎ ግራም የምትመዝን በመሆኗ ከትልቅነቷ አንጻር ምጥ የሚያፋፍም መድኃኒትና የማዋለጃ መሳሪያ (የብረት መጎተቻ መሳሪያ) ከመጠቀም ይልቅ ሌሎች የጥንቃቄ ዘዴዎችን መከተል ይገባቸው እንደነበር፤ መሳሪያውንም ሲጠቀሙ የነፍሰ ጡሯን ፈቃድ አለመጠየቃቸው፤ በዚህም በወሊድ ጊዜ ከውጭ በኃይል ጉተታ በደረሰ ጉዳት ምክንያት የሕጻኗ ነርቭ ተጎድቶ ጉዳት ላይ መውደቋን በመግለጽ ከውል ውጭ ኃላፊነት አለባቸው ሲል ወስኗል። ይግባኝ የቀረበለት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ውሳኔውን አጽንቶታል።
ሆስፒታሉ ታዲያ ለሰበር ባቀረበው አቤቱታ የህክምና ታሪክ አለመመዝገብ እና የነፍሰጡሯን ፈቃድ አለመጠየቅ በሕይወት ማዳን ጥድፊያ ወቅት ሊዘነጋ እንደሚችል በመግለጽ ሐኪሙ ተገቢውን ወስኖ ከመፈጸሙ ውጭ ቸልተኝነት ወይም ስህተት አልፈጸመም ሲል ተከራክሯል።
ሰበር ሰሚውም እናት የተሻለ የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ወደ ሆስፒታሉ ያቀናችው ቅድመ ወሊድ ክትትል እየተደረገላት ለመቆየትና በወሊድ ወቅትም ተገቢውን ሕክምና በማግኘት በሰላም ለመገላገልና ጤናማ ልጅ ለመውለድ ስትል መሆኑን አትቷል። እናም ሆስፒታሉ መሳሪያዎችን ከማቅረብም በላይ ባለሙያዎች እውቀትና ክህሎታቸውን ተጠቅመው የማዋለድ አገልግሎቱን እንዲፈጽሙት በማድረግ ግዴታውን የመፈጸም ኃላፊነት አለበት።
ይህ የሆስፒታሉ ኃላፊነት ከውል የሚመነጭ ሲሆን፤ ተቀጣሪ ሐኪሙ በሚያዋልድበት ወቅት የሚወስዳቸውን እርምጃዎችና ለምን ሊወስድም እንደቻለ ሳይመዘግብ ሲቀር ተከታትሎ ማስተካከል ነበረበት። አዋላጅ ሐኪሙ ደግሞ እውቀትና ክህሎቱን እንዲሁም ሙያው የሚጠይቀውን አሰራር ሁሉ ተጠቅሞ ያለምንም ጥፋት፣ ስህተት ወይም ቸልተኝነት በሰላም ማዋለድ እንደነበረበት በመግለጽ የስር ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ አጽንቶታል።
ከዚህ የምንረዳው ታዲያ አንድ የህክምና ባለሙያ በመስኩ የሚሰራባቸውን የሙያ ደንቦችና መመሪያዎች ሆነ ብሎ ወይም በቸልተኝነት ሳያከብር በመስራቱ ምክንያት በታካሚው ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ ከውል ውጭ የሚመነጭ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን ነው። ይህም በፍትሐብሔር ሕጉ 2031 እና 2647 በግልጽ ተደንግጐ እናገኘዋለን። እነዚህ የሙያ ደንቦችና መመሪያዎች ደግሞ በሕግ የተደነገጉ (ቁጥር 2035) አልያም በሕግ ሳይደነገጉ በሙያው የተሰማሩ ሰዎች የሚገለገሉባቸው የመልካም ልማድ አሰራሮች የሚመነጩ (ቁጥር 2030) ሊሆኑ ይችላሉ።
ከላይ በተመለከትነው ጉዳይም ፍርድ ቤት ቀርበው የመሰከሩት የሙያ ምስክሮች በጽሁፍ ተደንግጐ ባይገኝም አንድ ሐኪም በህክምና ወቅት የሚወስዳቸውን የህክምና ሂደቶች መመዝገብና ለምን እንደወሰዳቸውም ማስፈር እንዳለበት አረጋግጠዋል። ይህ የሕክምና ተቋማት እና የሐኪሞች ልማድም የሙያው የአሰራር ደንብ ሆኖ ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን፤ ይህን አለመፈጸም ደግሞ ጥፋት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። ለዚህም ነው አዋላጁ ሐኪም ምጥ የሚያፋፍም መድሃኒትና የብረት መጎተቻ መሳሪያ ለምን እንደተጠቀሙ እና በማዋለድ ሂደቱም የወሰዷቸውን የሕክምና ሂደቶች አለመመዝገባቸው የተለመደውን የሙያ ደንብ መጣስ በመሆኑ የሙያ ጥፋተኛ ያሰኛቸውና ከውል ውጭ ለደረሰው ጥፋትም ኃላፊ ያደረጋቸው።
ከሙያ ጥፋት ጋር በተያያዘ በመጨረሻ ግንዛቤ ሊያዝበት የሚገባው ሌላው ጉዳይ ከፍትሐብሔር ተጠያቂነት በተጨማሪ የወንጀል ቅጣትንም እንደሚያስከትል ነው። በወንጀል ሕግ አንቀጽ 559 ስር እንደተደነገገው ማንም ሰው በቸልተኝነት በሌላ ሰው አካል ወይም ጤንነት ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ ይልቁንም ጉዳት አድራሹ የሌላ ሰውን አካል ወይም ጤንነት የመጠበቅ የሙያ ወይም የሌላ ግዴታ ያለበት እንደ ሕክምና ባለሙያ ወይም አሽከርካሪ ያለ ሰው እንደሆነ የእስራትና የገንዘብ ቅጣት ይጠብቀዋል።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሀሴ 29/2011