ትከሻቸው ላይ ጣል ባደረጉት ሻርፕ በአንድ እጃቸው ዓይናቸውን አበስ የሚያደርጉት እናት በሌላኛው ደግሞ ፌስታል ሙሉ የሰነድ ማስረጃዎችን ይዘዋል። ማስቀመጫ እንደሌላቸው የሚያመላክተው አያያዛቸው ለሚመለከታቸው ምነው ጎናቸውን ከሚያሳርፉበት ቢያስቀምጡት? የሚል ጥያቄ አዘል ሐሳብን ማጫሩ አያጠራጥርም። ቀረብ ብዬ ምን እንደገጠማቸው ባወጋኋቸው ጊዜም ለም ሆቴል ፊት ለፊት ከነበረው ቤታቸው ወጥተው በአሁኑ ወቅት የካ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ተጠልለው እንደሚገኙ በሐዘን ነገሩኝ። እኛም ለዛሬ የጉዳዩን መነሻ ከተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችና ከኮርፖሬሽኑ ምላሽ ጋር አቀናብረን ዘገባውን እንዲህ ይዘንላችሁ ቀርበናል።
የቅሬታው መነሻ
ወይዘሮ አየለች ሸማመኔ በቀድሞ ወረዳ 16 ቀበሌ 11 በአዲሱ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት የቤት ቁጥር 794 ነዋሪ ሲሆኑ፤ ባለቤታቸው ሻምበል በቀለ ካሣዬ ከመንግስት ቤቶች ኮርፖሬሽን በሥማቸው በተከራዩት ቤት ውስጥ በጋራ ይኖሩ እንደነበር ያስታውሳሉ። ሆኖም የማይቀረው ሞት ውሃ አጣጫቸውን ሕዳር 6 ቀን 2010 ዓ.ም ከጎናቸው ይወስድባቸዋል። ውስጥ ውስጡን እንደ ፍም እሳት የሚፈጃቸው የባለቤታቸው ሕልፈተ ሕይወት ሐዘን ሳይወጡም ሕዳር 22 ቀን 2010 ዓ.ም ሕጋዊ እንዳልሆኑ ተገልፆ ከቤቱ እንዲወጡ ደብዳቤ ይደርሳቸዋል። ታኅሳስ 09 ቀን 2010 ዓ.ም ደግሞ ቤቱ ድረስ በማምራት በ20 ቀናት ውስጥ ቤቱን እንዲያስረክቡ፤ በተሰጣቸው ቀነ ገደብ የማያስረክቡ ከሆነ ግን ኮርፖሬሽኑ አስለቅቆ እንደሚረከብ እንደተገለፀላቸው ያኔ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳሉ።
ቅሬታ አቅራቢዋ፤ ወሳኝ ኩነት ላይ እንደሌሉ በመግለጽ፤ የሟች ባለቤትነታቸው ተሽሮ ኮርፖሬሽኑ ከቤት አውጥቶ እንደወረወራቸው በብሶት ይገልፃሉ። የወረዳው አስተዳደርም ሆነ የተለያዩ የሕዝብ ቅሬታ የሚያስተናግዱ ተቋማት በቤቱ ላይ መወሰን የሚችለው የሚያስተዳድረው ኮርፖሬሽኑ በመሆኑ ምንም ሊያደርጉላቸው እንደማይችሉ እንዳሳወቋቸው ይናገራሉ።
ከሻምበል በቀለ ጋር የአብራክ ክፋይ የሆነ ማስታወሻ ልጅ ባይኖራቸውም ቤት ኪራይ የጊዜ ክፍያ ሳያልፍ ይከፍሉበት የነበረው ቤታቸውን እንደተቀሙም ይናገራሉ። በፍርድ ቤት ሚስትነታቸው እንደተረጋገጠ፣ የጡረታ መብት እንዳስከበሩ እንዲሁም የሠፈሩ ዕድርም ሚስትነታቸውን እንደመሰከረላቸው በመጠቆም፤ ኮርፖሬሽኑ ግን ውል እንዲዋዋሉ ቢጠይቁም ሚስት ባለመሆናቸው ሊያስተናግዳቸው እንደማይችል እንደተገለፀላቸው ነው ወይዘሮ አየለች የሚናገሩት።
ጉዳዩም እስከ ፍርድ ቤት ደርሶ ከኮርፖሬሽኑ ጋር ክርክር ሲያደርጉ ይቆያሉ። ፍርድ ቤቱ ያሳረፈው ውሳኔም ቤቱ ለኮርፖሬሽኑ ተመላሽ እንዲሆን የሚያስደርግ በመሆኑ ለከፍተኛ እንግልትና ከቤት አውጥቶ ለጎዳና ሕይወት እንደዳረጋቸው ይገልፃሉ። በውሳኔውም አምስት የቤተሰቡ አባላት እንደዘበት ተበትነዋል። ሰኔ ሰባት ቀን 2011 ዓ.ም ውሳኔው ፀንቶ ከቤታቸው ከመውጣታቸው አስቀድሞም የሚመለከታቸውን አካላት በጉዳዩ ላይ ቢያነጋግሩም ውል ስለሌላቸው ፍርድ ቤት ውሳኔ የሰጠው ጉዳይ በመሆኑ ቤቱን እንዲያስረክቡ እንደተነገራቸው ይናገራሉ።
ሰነዶች
ሻምበል በቀለ ከኮርፖሬሽኑ ጋር የገቡት የቤት ኪራይ ውል ከሰነዶቹ መካከል የሚገኝ ሲሆን፤ የቤተሰብ ብዛት በሚለው ቦታ አምስት እንደሆኑ ያመላክታል። የቤት ኪራይ የተከፈለባቸው ደረሠኝ ግልባጮችም ይገኛሉ። የሻምበል በቀለ ህልፈተ ሕይወት ተከትሎም ወይዘሮ አየለች ውል ለመዋዋል የኮርፖሬሽኑን ቅርንጫፍ አራት ጽሕፈት ቤት የጠየቁባቸው ማመልከቻዎችን መመልከት ችለናል።
በመዝገብ ቁጥር 10842 በቀን 05/04/2010 ዓ.ም በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የየካ ምድብ ችሎት ያሳለፈው ውሳኔ መዝገብ ግልባጭ ወይዘሮ አየለች በ25/03/2010 አቤቱታ ማቅረባቸውን ያትታል። በአቤቱታቸው መስከረም 15 ቀን 1992 ዓ.ም ጀምሮ በባሕላዊ መሠረት ጋብቻ ፈፅመው መኖራቸውን በመጥቀስ፤ ጥያቄያቸው ተረጋግጦ ማስረጃ ይጠይቃሉ።
ፍርድ ቤቱ የቅሬታ አቅራቢዋን አቤቱታ ከመረመረ በኋላ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ቁጥር 213/92 አንቀጽ 96 እና 97/1 መሠረት የሟች ሻምበል በቀለ ሚስት ነበሩ ሲል ውሳኔ እንደሰጠ የመዝገብ ግልባጩ ያሳያል። በተመሳሳይ በመዝገብ ቁጥር ፌ/ደ/ፅ/007/2009 በቀን 24/04/2010 ዓ.ም በወረዳ 16 ቀበሌ 11 የፈጥኖ ደራሽ ዕድር ለማህበራዊ ዋስትና ጽሕፈት ቤት የላከው ደብዳቤ ይገኛል።
በደብዳቤው፤ የዕድሩ አባል የነበሩት ሻምበል በቀለ ሕይወታቸው ማለፉንና ዕድሩም አስፈላጊውን እርዳታ እንዳደረገላቸው ባለቤታቸው ወይዘሮ አየለች ታኅሳስ 21 ቀን 2010 ዓ.ም ጠይቀዋል ሲል ያብራራል። በመሆኑም ባለቤታቸው ሕዳር 8 ቀን 2010 ዓ.ም የቀብራቸው ሥነ ሥርዓት በሆለታ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን መፈፀሙን አስፍሯል።
በመዝገብ ቁጥር የካ/ወ/8/ሴ/ህ/ጉ/ጽ/ቤት/458/11 በቀን 30/07/2011 ዓ.ም በየካ ክፍለ ከተማ የወረዳ ስምንት አስተዳደር ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የፃፈው ደብዳቤ ሌላው የተመለከትነው ሰነድ ነው። በደብዳቤው እንደተመላከተው፤ ወይዘሮ አየለች ምንም ዓይነት ገቢ እንደሌላቸው በሚኖሩበት በወረዳው ቀጣና ስድስት አደረጃጀት በመረጋገጡ ድጋፍ እንዲደረግላቸው መጠየቁ ይነበባል። በተያያዘ በነፃ ጥብቅና የሚቆምላቸው የሕግ ባለሞያ የጠየቁባቸውና ፍቃድ ያገኙባቸው ሰነዶችም ይገኛሉ።
ኮርፖሬሽኑ በቁጥር ቅ4/16-11-794/009 በቀን 3/11/2010 ዓ.ም ለቤቱ ተገልጋይ የላከው ደብዳቤ ሲሆን፤ ኮርፖሬሽኑ የሚያስተዳድረውን መኖሪያ ቤት ሕጋዊ ውል ሳይኖራቸው እየተገለገሉበት መሆኑ እንደተረጋገጠ ያሳያል። ስለሆነም ቤቱን ለመረከብ ሐምሌ 6 ቀን 2010 ዓ.ም ቤቱን ለመረከብ ፕሮግራም እንደተያዘ በመጥቀስ፤ በቤቱ ውስጥ የሚፈለግ የቤቱ ኪራይ የውሃ፣ የመብራትና ሌላ የጎደለ ንብረት ቢኖር በመክፈል ቤቱን እንዲያስረክቡ ያሳስባል። በዕለቱ የፖሊስ ተወካዮች በተገኙበት ኮርፖሬሽኑ ቤቱን እንደሚረከብና ንብረታቸውን የማያወጡ ከሆነ ወደ ኮርፖሬሽኑ መጋዘን በማስገባት ለጉልበትና ትራንስፖርት የወጣውን ወጪ እንደሚያስከፍል ለወይዘሮ አየለች ማሳወቁ በደብዳቤው ይታያል።
የፍርድ ሒደት
በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የኮ/መ/ቁ259107 በቀን 23/04/2010 ዓ.ም ከሳሽ ወይዘሮ አየለች ተከሳሽ ደግሞ የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን እንደሆነ የመዝገብ ግልባጩ ያሳያል። በዚህ መዝገብ ሌላ ተለዋጭ ትዕዛዝ እስከሚሰጥ ቤቱን ወይዘሮ አየለች እንዳይለቁ ትዕዛዝ መስጠቱ ይታያል። ትዕዛዙም ለክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ እንዲደርስ እንደተደረገ ሰነዶች ያመላክታሉ።
ጉዳዩ በፍርድ ቤት ተይዞ ሲታይ ከቆየ በኋላ መዝገብ ቁጥር 214737 ሐምሌ 6 ቀን 2010 ዓ.ም ወይዘሮ አየለች ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ባይ ሆነው ቀርበው እንደነበር ያሳያል። በዚህም ይግባኝ ባይ በቀን 05/10/2010 ዓ.ም በተፃፈ አቤቱታ በስር ፍርድ ቤት በተሰጠ ፍርድ ቅር ተሰኝተው ይግባኝ አቅርበው ጉዳዩ ለምርመራ ተቀጥሮ ውሳኔ ከማግኘቱ በፊት የስር ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 259107 ግንቦት 09 ቀን 2010 ዓ.ም የሰጠውን ፍርድ ተከትሎ ኮርፖሬሽኑ ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ቤት እንዲያስረክቡ ሐምሌ 6 ቀን 2010 ዓ.ም ማስጠንቀቂያ እንደሰጣቸው እንዳቀረቡ ያስነብባል። ጉዳዩ ውሳኔ እስኪሰጥበት ድረስም ቤቱን እንዲያስረክቡ የተሰጠው ትዕዛዝ ታግዶ እንዲቆይላቸው መጠየቃቸውን ያትታል።
ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ ሳያጠናቅቅ በስር ፍርድ ቤት ውሳኔ መሠረት ወይዘሮ አየለች ቤቱን ለኮርፖሬሽኑ ቢያስረክቡና ምርመራው ሲጠናቀቅ የቀድሞውን ውሳኔ ቢሽረው ወይንም ቢያሻሽለው በይግባኝ ባይ ላይ ሊካስ የማይችል ጉዳት ሊደርስባቸው እንደሚችል ችሎቱ ግንዛቤ መውሰዱ በመዝገብ ግልባጩ ይታያል። በመሆኑም በፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ትዕዛዝ እስኪሰጥ ድረስ ታግዶ እንዲቆይ ያዛል።
በመዝገብ ቁጥር 214737 በቀን 25/03/2011 ዓ.ም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለልደታ ምድብ ችሎት 13ኛ ፍትሐብሔር ችሎት ወይዘሮ አየለች ይግባኝ እንዳሉ የሚያሳይ ሰነድ ነው። ይህን ተከትሎም መጋቢት 9 ቀን 2011 ዓ.ም የኮ.መ.ቁ 214737 የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ባይ ወይዘሮ አየለች፤ መልስ ሰጪ ደግሞ የኮርፖሬሽኑ ቅርንጫፍ አራት ጽሕፈት ቤት እንደሆነ መዝገብ ግልባጩ ያሳያል።
በመዝገብ ግልባጩ፤የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 259107 ግንቦት 9 ቀን 2010 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠው ውሳኔ ወይዘሮ አየለችን ቅር በማሰኘቱ ይግባኝ ለማለት ምክንያት እንደሆነ ያስቀምጣል። በስር ፍርድ ቤት ባቀረቡት ክስ ማመልከቻ ንብረትነቱ የኮርፖሬሽኑ የሆነውን ቤት
ባለቤታቸው ሻምበል በቀለ በሥማቸው የኪራይ ውል ገብተው ይኖሩ እንደነበር በመግለጽ፤ ከባለቤታቸው ሞት በኋላ የኪራይ ውሉ በሥማቸው እንዲሞላ ኮርፖሬሽኑን እንደጠየቁ ያሳያል።
ኮርፖሬሽኑ፣ ከሳሽ ሚስት ባለመሆናቸው ቤቱን ለቅቀው እንዲያስረክቡ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ በመስጠት የሁከት ተግባር እንደፈፀመባቸው በክሳቸው አቅርበው እንደነበር መዝገቡ ያመላክታል። ለዚህም የሚረዳቸው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የካ ምድብ ችሎት የሻምበል በቀለ ሚስት መሆናቸውን በማረጋገጥ የሰጠው ውሳኔ፣ ለቤቱ ኪራይ ገንዘብ የተከፈለበት ደረሰኝ እንዲሁም የሠው ምስክሮች አቅርበው ነበር ይላል።
ለክርክሩ ምክንያት የሆነው ቤት ተከራይ የነበሩት ሻምበል በቀለ ሕይወታቸው በማለፉ ውሉ እንደተቋረጠ ኮርፖሬሽኑ ለቀረበበት ክስ በሰጠው ምላሽ ማሳወቁን መዝገቡ ያሳያል። የተሰረዘ ውልን መነሻ በማድረግ ከሳሽ ክስ ማቅረብ አይችሉም። በቤቱም ላይ መብትም ሆነ ጥቅም የላቸውም በማለትም ተከራክረዋል። ሟችም ተከራይተው ሲኖሩ በኪራይ ውሉ ላይ ሚስት የሌላቸው መሆኑን ያረጋገጡ በመሆኑና ለመጨረሻ ጊዜ የኪራይ ውል ሲያድሱ ሚስት የሌላቸው መሆኑን ከየካ ክፍለ ከተማ ወሳኝ ኩነት ጽሕፈት ቤት የተረጋገጠ ማስረጃ አያይዘዋል ሲል ኮርፖሬሽኑ ያብራራል።
ወይዘሮ አየለች ሚስት እንደሆኑ ያቀረቡት አቤቱታ የማይገባቸውን የኪራይ ውል ለማግኘት በመሆኑ ክሳቸው ተገቢነት የለውም በሚል ውድቅ እንዲደረግ ኮርፖሬሽኑ መከራከሩ ይነበባል። የስር ፍርድ ቤቱ በግራ ቀኙ የቀረበውን ክስና የሰነድ ማስረጃ ከመረመረ በኋላ ሟች በሕይወት እያሉ ሚስት የሌላቸው መሆኑን በመግለጽ የኪራይ ውል የሞሉ ከመሆኑም በላይ ጥቅምት 21 ቀን 2009 ዓ.ም ከኪራይ ውሉ ጋር ሚስት እንደሌላቸው የሚያረጋግጥ ከወሳኝ ኩነት ጽሕፈት ቤት የተሰጣቸውን ማስረጃ ማያያዛቸውን ያሳያል።
ከፍርድ ቤት ለከሳሽ የተሰጣቸው የሚስትነት ማረጋገጫ ተራ ማስረጃ እንጂ አግባብነት ባለው የምስክር መስማት ሒደት ታልፎ ተረጋግጦ የተሰጠ ባለመሆኑ ግለሰቧ የሻምበል በቀለ ሚስት ስለመሆናቸው አያስረዳም። በመሆኑም በቤቱ ላይ መብት ወይም ጥቅም ያላቸው ስለመሆኑ ያላረጋገጡ ስለሆነ ክሳቸው ተቀባይነት የለውም በማለት በብይን ውድቅ እንዳደረገው መዝገብ ግልባጩ ያሳያል። በውሳኔው ቅር በመሰኘት ወይዘሮ አየለች ይግባኝ ያሉ ሲሆን፤ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የስር ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ብይን፣ ከይግባኝ ባይ ቅሬታና ግራ ቀኙ ካቀረቡት ክርክር እንዲሁም አግባብነት ካለው ሕግ ጋር በማገናዘብ እንደመረመረ ያትታል።
ይግባኝ ባይ ከሟች ጋር በአገር ባህል ጋብቻ መሠረት ተጋብተው አብረው እንደኖሩ በምስክሮች ፍርድ ቤት እንዳረጋገጡና ሚስት ስለመሆናቸው ውሳኔ እንደተሰጣቸው በመግለጽ፤ ይህ ከሆነ ደግሞ ከባለቤታቸው ሞት በኋላ ቤቱን የመከራየት መብት ቢኖራቸውም ኮርፖሬሽኑ ግን ማስረከብ እንዳለባቸው ያነሳው ሐሳብ የሁከት ተግባር ነው በማለት መከራከራቸውን ሰነዱ ያሳያል። ወይዘሮ አየለች ሚስት ስለመሆናቸው እንዲረጋገጥላቸው ለፍርድ ቤት ክስ ያቀረቡት ሟች ከሞቱ በኋላ በመሆኑም ሚስት ናቸው በሚል የቀረበውን አቤቱታ ለመካድ ወይንም ለማመን ዕድል አልነበራቸውም።
ውሳኔውም በአንድ ወገን ብቻ የቀረበውን ምስክር ቃል በመስማት ብቻ ነው የተሰጠው። በሌላ በኩል ደግሞ ሟች በሕይወት እያሉ በኪራይ ውሉ ላይ ሚስት ያላቸው ስለመሆኑ አለመሙላታቸውና ሚስት እንዳሌላቸው በ2009 ዓ.ም ውላቸውን ሲያድሱ ከወሳኝ ኩነት የተሰጣቸው ማስረጃ ለኮርፖሬሽኑ ማቅረባቸው ሚስት እንዳሌላቸው የሚያሳይ ነው ይላል።
ይግባኝ ባይ በአንድ ወገን የቀረበውን ማስረጃ ብቻ መሠረት አድርጎ በተሰጠ ውሳኔ መነሻነት ለክርክሩ ምክንያ ሆኖ በቀረበው ቤት ላይ መብት እንዳላቸው በመግለጽ የሁከት ይወገድልኝ የዳኝነት ጥያቄ ማቅረብ እንደማይችሉ መዝገብ ግልባጩ ያስነብባል። ሁከት እንደተፈጠረበት የዳኝነት ጥያቄ የሚያቀርብ አካል ሁከቱን ፈጥሯል ከተባለው አካል የተሻለ መብት ያለው ስለመሆኑ ማስረዳት እንደሚጠበቅበት ሕጎችን በማጣቀስ በማብራራት ግለሰቧ የተሻለ መብት እንዳላቸው ባላስረዱበትና መብት ወይም ጥቅም በሌላቸው ሁኔታ ላይ ተመስርቶ የቀረበ በመሆኑ ውድቅ ሆኗል በሚል የስር ፍርድ ቤት የሰጠው ብይን አግባብ ስለመሆኑ ያብራራል። በዚህም የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 259107 ግንቦት 9 ቀን 2010 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠው ብይን ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት እንዳፀናው መዝገብ ግልባጩ ያትታል።
የሰ/መ/ቁ.173508 በቀን 23/07/2011 ዓ.ም ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ወይዘሮ አየለች የዕግድ ጥያቄ ማቅረባቸውን መዝገብ ግልባጩ ያሳያል። በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ችሎት በመ/ቁ 214737 በቀን 09/07/2011 ዓ.ም የተሰጠው ውሳኔ አፈፃፀሙ ታግዶ ይቆይ በማለት መጠየቃቸውን ያብራራል። አንድ ጉዳይ ለሰበር ችሎት ሊቀርብ የሚችለው ቅሬታ የቀረበበት ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተገኘበት እንደሆነ ብቻ መሆኑንም በመጥቀስ፤ የቀረበው የዕግድ ጥያቄና የሰበር አቤቱታ መነሻ በማድረግ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ተፈፅሞባቸዋል የተባሉትን ውሳኔዎች አግባብ ካለው ሕግ ጋር በማገናዘብ መርምሯል። በዚህም በስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔዎች ላይ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ተሰርቷል ለማለት ባለመቻሉ የቀረበው የዕግድ ጥያቄ እንዳልተቀበለውና ጉዳዩም ለሰበር ችሎት አያስቀርብም በማለት ትዕዛዝ መስጠቱን መዝገብ ግልባጩ ያሳያል።
ኤጀንሲው ምን ይላል?
በፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የቅርንጫፍ አራት ጽሕፈት ቤት የቤት አስተዳደርና ደንበኞች አገልግሎት ቡድን መሪ አቶ ዘሪሁን አፈወርቅ፤ አንድ ግለሰብ ከኤጀንሲው ቤት ሲከራይ በቅድሚያ ሕጋዊ ሆኖ ውል እንዲገባ ይደረጋል በማለት አሠራሩን ያብራራሉ። በውሉ ላይም የቤተሰብ አባላቱ በቅጽ ላይ ይመዘገባሉ። የጋብቻ ሠርተፊኬት ማቅረብ ካለባቸውም ያቀርባሉ። በየዓመቱም ውሉን ያድሳሉ። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ግዴታቸውን ካልተወጡና ውል ካላደሱ ግን ኮርፖሬሽኑ በመመሪያው መሠረት ውሳኔ ይሠጣል። የቤት ቁጥር 794 በፍርድ ቤት ውሳኔ ያገኘ ጉዳይ እንደሆነም አያይዘው ይናገራሉ።
ፍርድ ቤቱ በኮርፖሬሽኑና በሕጋዊ ነኝ ባይ ቅሬታ አቅራቢዋ መካከል ሲደረግ የነበረውን ክርክር ግራ ቀኝ ካደመጠ የሰነድ ማስረጃዎችንም አገላብጦ ከመረመረ በኋላ ግለሰቧ ማሟላት ያለባቸው ያልተሟሉ ጉዳዮች በመኖራው እንደማይገባቸው ወስኗል። ለቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱም የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ደርሷል። ኮርፖሬሽኑም ለጽሕፈት ቤቱ በጽሁፍ አሳውቋል። በዚህ መሠረት ቤት ፈልገው እንዲወጡና ቤቱን ለኮርፖሬሽኑ እንዲያስረክቡ ሥርዓትና ሕጉን በጠበቀ ሁኔታ አሳውቋል።
ሥራው ሲሠራ የፖሊስ ኃይል፣ የፍትሕ አካላት እንዲሁም የኮርፖሬሽኑ ተወካዮች በተገኙበት ቤቱን የመረከብ ሥራ እንደተሠራ ያስታውሳሉ። ግለሰቧ ሕጋዊና ትክክለኛ ቢሆኑ ኖሮ ፍርድ ቤቱ ተመልክቶ ኮርፖሬሽኑ ሁከቱን አስቁሞ ሊወስን ይችል ነበር። ነገር ግን ኮርፖሬሽኑ ትክክል በመሆኑ በክርክሩ ኮርፖሬሽኑ የፍርድ ባለመብት ሊሆን ችሏል። በዚህም መሠረት ቤቱን በመረከብ አብዛኛውን ጊዜ በኮርፖሬሽን ደረጃ ውሳኔ አግኝተው ቤቱን የሚዋዋሉት የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በመሆናቸው ሌላ ተዋዋይ መብት ተፈጥሮለት ውል ተዋውሎ እየኖረበት ይገኛል ይላሉ።
ከውል ተዋዋይ ወገኖች መካከል ባል ወይንም ሚስት ሕይወታው ካለፈ ከሁለት አንዳቸው ወይንም ልጆች በፍርድ ቤት ወራሽነታቸውን ካረጋገጡ በኋላ ይስተናገዳሉ። ነገር ግን ይህን ሳያደርጉ ከቀሩ የወረዳውን አስተዳደር ይጠየቃል። በቤቱ ይኖሩ እንደነበር ከተረጋገጠ በኋላ ወራሽነታቸው ጋር በማመሳከር ወደ መስመር እንዲገቡና ሕጋዊ እንዲሆኑ ይደረጋል። ይህ ከሆነም ከቤቱ በምንም አግባብ እንዲወጡ አይደረግም በማለት አቶ ዘሪሁን ያረጋግጣሉ። ይሁን እንጂ ቅሬታ አቅራቢ ግለሰቧ ማሟላት የሚገባቸውን መረጃዎች ባለማሟላታቸው ፍርድ ቤቱም ውሳኔውን ሊያሳርፍ ችሏል።
መንግስት በከተማዋ የሚስተዋለውን ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ችግር ለማቃለል የተለያዩ ሥራዎችን እንደሚሠራ ይታወቃል። ከሚያሠራቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች በተጨማሪ በቀበሌ ቤት ውስጥ በጥገኝነት ይኖር የነበረ ዜጋ ከአምስት ዓመት በላይ ከኖረ የቀድሞ ውል ተዋዋይ ሕይወቱ በሚያልፍበት ወቅት በዛው ቤት እንዲኖር ያደርጋል። ከዚህ አንፃር ግለሰቧን ከቤት አውጥቶ ለሌላ ግለሰብ ቤት መሥጠትስ ተገቢ ነውን ? ለአቶ ዘሪሁን ያቀረብንላቸው ጥያቄ ነበር። አንድን ግለሰብ አስወጥቶ ሌላ ግለሰብ ማስገባት እንደ ሠው ሲታሰብ ሊከብድ ቢችልም በመመሪያና በሕጉ መሠረት ግን ምንም ማድረግ አይቻልም በማለት ምላሻቸውን ሰጥተውናል። ሕግና ደንብን ጠብቆ ማስወጣትም ይገባል። ኮርፖሬሽኑም በዚህ መሠረት በሕጋዊ መንገድ በመመሪያው መሠረት ነው ሥራውን የሠራው ቤቱንም የተረከበው።
በመመሪያው መሠረት በተዋዋሉት ውል መሠረት በአግባቡ የማይፈጽም ተከራይ ቤቱን እንዲያስረክብ ይደረጋል። ሥራውን ሲሠራም መመሪያውን ማዕከል በማድረግ እንጂ ግለሰብንና ፍላጎትን መነሻ በማድረግ ብቻ የማስወጣትም ሆነ የማስገባት ሥራ አይሠራም ሲሉም አቶ ዘሪሁን ያስረዳሉ። በአሁኑ ወቅት ኮርፖሬሽኑ ሰፊ ግንባታዎችን እያካሄደ መሆኑን በመጠቆም፤ በቀጣይ የሚስተዋሉ የቤት ችግሮችም እንደሚቃለሉ ያላቸውን ዕምነት ይገልፃሉ። ነገር ግን ተከራዩ ሕግና ደንብን አክብሮ መሄዱ ወሳኝ ነው። በግለሰቧ ጉዳይ ላይ ግን ፍርድ ቤት ኮርፖሬሽኑ የወሰደው እርምጃ ትክክል ነው ብሎ የወሰነበት በመሆኑ ወደኋላ በመሄድ እንዲሻር አይደረግም። የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ማክበርም ግዴታ ነው በማለት ዳግም ሊታይ እንደማይችል ያመላክታሉ።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሀሴ 29/2011
ፍዮሪ ተወልደ