የሀገርን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ጽንፈኛ ኃይሎች በቃችሁ ይባሉ!

በየትኛውም ሁኔታ ሕዝብን በተሳሳተ ፕሮፓጋንዳ እና ትርክት ዘላቂ ተጠቃሚ ማድረግ አይቻልም። በዚህ የተሳሳተ የጥፋት መንገድ ተጠቃሚ እሆናለሁ ብሎ ማሰብ እና መንቀሳቀስ አንድም ከአላዋቂነት / ከድንቁርና ከዚያም ባለፈ የሕዝብን ወድቀት እና ጥፋት ከመመኘት የሚመነጭ የሴራ መንገድ ነው።

በሀገራችን የዛሬ ስድስት ዓመት መላው ሕዝባችንን ከዳር እስከዳር ያነሳሳ የለውጥ መነቃቃት ተፈጥሯል። በዚህም እሱን የማይነቀነቅ አድርጎ ሲቆጥር የነበረውን የቀድሞ ሕወሓት መራሹ የኢህአዴግ መንግሥት ያለ አንዳች የጥይት ድምጽ ዘመኑን በሚዋጅ የፖለቲካ ትግል ተወግዷል። የትግሉ ተሞክሮም በሀገሪቱ አዲስ የለውጥ የታሪክ ምዕራፍ መፍጠር አስችሏል ።

በወቅቱ ሀገር እንደ ሀገር የነበረችበትን የለውጥ መነቃቃት ፣ መነቃቃቱ የፈጠረው የለውጥ ተስፈኝነት፣ መላው ሕዝባችንን አንድ ከማድረግ ባለፈ ፣ ለለውጥ በቁጭት በጋራ እንዲነሳ አድርጎታል። ስለ ሀገር እና ስለ ትውልድ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ አደባባዮችን በጋራ ዜማ አድምቆም ታይቷል።

መዋቅራዊ በሆነ መንገድ ሳይቀር ለሦስት አስርት ዓመታት ከተሰበከ የነጠላ ትርክት ወጥቶ አንድነቱን በሚያጸና የጋራ መንገድ ላይ ቆሞም ተስተውሏል። ይህም ብዙ ትውልድ ተስፋ አድርጎ ከሩቅ የተሰናበተው የሀገሪቱ ትንሳዔ ስለመቃረቡ ምልክት ተደርጎ የተወሰደበትም ሁኔታ ሰፊ ነበር ።

በዚህ የታሪክ ክስተት ውስጥ ፤ እንደቀደሙት የለውጥ ዘመናት ከለውጡ የግል ተጠቃሚ እንሆናለን ባሉ ግለሰቦች እና ቡድኖች ፤ ከሁሉም በላይ ራሳቸውን በዘመናት መካከል በሥልጣን መንበር ላይ አስቀምጠው ፤ ሥልጣን በእነሱ እና የእነሱ የመገበያያ ሸቀጥ አድርገው ሲያስቡ በነበሩ ኃይሎች ግልጽ እና ስውር የጥፋት ተልዕኮ ለውጡ በብዙ መንገጫገጮች ውስጥ ለማለፍ ተገድዷል።

እነዚህ ኃይሎች ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በገዥው የቀድሞ ሕውሓት መራሹ የኢህአዴግ መንግሥት የሀገሪቱን የፖለቲካ መድረኮች ባጣበቡ የተዛቡ ትርክቶች እና የአልቃሽ አስለቃሽ የፖለቲካ ዲስኩሮች የለውጡን አደባባዮች በማጣበብ የሥልጣን ፍላጎቶቻቸውን በግርግር ተጨባጭ ለማድረግ ረጅም መንገድ ተጉዘዋል።

በሴራቸው የንጹሃንን ደም በአደባባይ አስፈስሰዋል ፤ ሚሊዮኖችን ከቤት ንብረቶቻቸው አፈናቅለዋል። ለዘመናት በክፉም በደጉም አብሮ የኖረው ሕዝብ ፤ አንዱ በአንዱ ለይ እንዲነሳ ለማድረግ ሞክረዋል። ከሀገራዊ የሰላም እጦት አትራፊ ለመሆን ፤ በየጎጡ በመንቀሳቀስ የሕዝባችንን የለውጥ ተስፋ አደብዝዘዋል።

ከታሪካዊ ጠላቶቻችን የጥፋት ተልዕኮ በመቀበልና ከሀገር እና ከሕዝብ ዘላቂ ጥቅሞች ላይ ተቃርኖ ቆመው የባንዳነትን ተግባር ያለ እረፍት በአደባባይ ሲከውኑ ፤ ይህንንም እንደክብር ሲያወሩ ተስተውሏል። በዚህም ለጌቶቻቸው ሀገር የማፍረስ ተልዕኮ ሌት ተቀን ያለዕረፍት ሲሠሩም መታዘብ ተችሏል።

በሐሰት ፣ በጥላቻ እና በጽንፈኞች ፕሮፓጋንዳ እንወከለዋለን የሚሉትን ሕዝብ ብዙ ዋጋ አስከፍለዋል፤ ልጆቹን ትርጉም ለሌለው መሥዋዕትነት ፤ ሀብት ንብረቱን ለውድመት ዳርገዋል። ትውልዱ የትምህርት ብርሃን እንዳያገኝ የመማር ማስተማር ሂደቱን በማወክ ሚሊዮኖችን ከትምህርት ገበታ አስቀርተዋል።

ከትናንት የተሻለ ዛሬን እና ነገን ለመፍጠር በለውጡ ተስፈኛ የነበረውን ሕዝብ ዛሬን በብዙ አበላሽተውበታል። ማኅበረሰባዊ ማንነቱን በማይመጥን መንገድ አንገቱን እንዲደፋ አድርገውታል። ጊዜ ባለፈበት የነጻ አውጪነት ስም ሰላማዊ ሕይወቱን ነጥቀው ፣ የጥፋት ተልዕኮው ግዞተኛ አድርገውታል።

በፉከራ እና በቀረርቶ ፤ በተሳሳተ የጥፋት ትርክት ዘላቂ የሕዝብ ጥቅም እውን ይሆን ይመስል ፤ ተራሮችን እና ሸለቆዎችን ፤ በረሃዎች እና መንደሮችን በፉከራ እና ቀረርቶ፤ አየሩን በተሳሳተ ፕሮፓጋንዳ እና ትርክት ሞልተው ፣ እንወክለዋለን ያሉትን ፣ በስሙ የሚምሉ እና የሚገዘቱበትን ሕዝብ ለከፋ መከራ ዳርገውታል።

እነዚህ ኃይሎች አሁን ላይ ፍጥረታዊ ሞታቸውን እየሞቱ ያሉበት ሁኔታ እየተስተዋለ ቢሆንም ፤ “እኔ ከሞትኩ ወዲያ ሰርዶ አይብቀል” የሚለው ከውልደታቸው ጀምሮ ይዘውት የኖሩት የአስተሳሰብ ስንኩልነት ሀገር እና ሕዝብን ተጨማሪ ዋጋ ሊያስከፍል ስለሚችል መላው ሕዝብ ከእያንዳንዷ እንቅስቃሴያቸው ጀርባ ያለውን ጥፋት ዓይኑን ከፍቶ ሊመለከተው ይገባል።

በተለይም የሀገርን እና የሕዝብን ዘላቂ ጥቅሞችን ከዚያም አልፎ የሀገርን አንድነት እና ሀገረ መንግሥቱን አደጋ ውስጥ የሚጨምሩ ጽንፈኛ ኃይሎች ከታሪካዊ ጠላቶቻችን እና ለሀገራችን እድገት ሁሌም ቀና አስተሳሰብ ከሌላቸው ኃይሎች ጋር እየሄዱበት ያለው የጥፋት መንገድ ለማንም የሚበጅ አይደለምና መንግሥት እና መላው ሕዝብ በቃ ሊሏቸው ይገባል!

አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You