
አዲስ አበባ፡- በክልሉ በዘንድሮ የክረምትና የበልግ ወቅቶች በሰባት ሺህ ሄክታር መሬት ላይ 117 ሚሊዮን የሻይ ቅጠል ችግኞች ሊተከሉ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለፀ።
የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የቡናና ሻይ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ መሐመድሳኒ አሚን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ ክልሉ ለሻይ ልማት ችግኞች በጀት በመመደብ፣ አስፈላጊ ግብዓቶችን በማቅረብና አርሶ አደሩን በማሳተፍ ችግኝ አዘጋጅቷል፤ በተያዘው በጀት ዓመትም 117 ሚሊዮን የሻይ ቅጠል ችግኞች በሰባት ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ለመትከል ጉድጓድ ተቆፍሯል፤ ዝናብ ተደራሽ በሆነባቸው ስፍራዎችም የመትከል ሥራም ተጀምሯል ።
በሀገራችንም ይሁን በኦሮሚያ ክልል የሻይ ልማት ለማካሄድ ትልቅ አቅም እያለን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ብዙም ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቷል ያሉት ኃላፊው፤ በአሁኑ ጊዜ የክልሉ መንግሥት ሻይ ልማትን እንደ አንድ የትኩረት አቅጣጫ ይዞ ወደ ሥራ ገብቷል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ አንድ ወረዳ ኢሉ አባቦራ ውስጥ ብቻ በሚድሮክ ኢንቨስትመንት የሻይ ልማት ለበርካታ ዓመታት እንደሚከናወን ገልጸው፤ ይህን የሻይ ልማት ወደ አርሶ አደሩ እና ወደ ሌሎች አካባቢዎች የማስፋፋት ሥራ ሳይሠራ ቆይቷል፤ በአሁኑ ወቅት ግን አርሶ አደሩ ማሳ ላይ በስፋት በማልማት ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በውስን አካባቢ ብቻ ይለማ የነበረው የሻይ ልማት በአሁኑ ወቅት ኢሉ አባቦራን ጨምሮ በደሌ እና ጅማ፤ በሶስቱም ዞኖች በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን አመልክተው፤ በቀጣይ ሶስት ዓመታት እስከ ሰላሳ ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡
ለአርሶ አደሩ የሻይ ምርት አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የግንዛቤ እና በሥልጠና በመስጠት የውጭ ሀገር ልምድ በመቅሰም ባለሙያውና አርሶ አደሩ አብሮ እየሠራ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
በክልሉ በቀጣይ ጊዜ ለሻይ ልማት 300 ሺህ ሄክታር መሬት ገደማ ለማልማት የተጠና መሆኑን ጠቅሰው፤ በኢሉ አባቦር፣ ጅማ፣ ቄለም ወለጋ፣ ሁሩጉድሩ፣ እና ምዕራብ ወለጋ እንዲሁም ምስራቅ ወለጋ ላይ ሰፊ አቅም እንዳለ በመረዳት ልማቱን ለማስፋፋት ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት፡፡
መንግሥት ለሻይ ልማት ትኩረት መስጠቱ አመቺ ሁኔታ ፈጥሮልናል ያሉት ኃላፊው፤ የአካባቢው ሰፊ ቦታ እና ምቹ አየር ንብረት እንዲሁም ሰፊ የሰው ኃይል ምርታማነትን ለማሳደግ ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የፋይናንስ እጥረት፣ የልምድ ማነስ እንዲሁም ልማቱን ለማዘመን ፋብሪካ በማስፋፋት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በማስተካከል ወደፊት ማጠናከር ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
በሻይ ልማት ያለውን አቅም አሟጦ በመጠቀም ሻይን ቡና የሚያስገኘውን የውጭ ምንዛሬ መጠን ጋር የተቀራረበ በማድረግ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሠራም አመልክተዋል፡፡
ሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 24 ቀን 2017 ዓ.ም