የአዲስ ሌላው አዲስ ገጽታ

እንደ ንስር ራሷን እያደሰች የውበት ብርሃኗን መፈንጠቅ ጀምራለች። አዲስ አበባ እንደ ስሟ አበባ እየሆነች ነው። የኮሪዶር ልማቱ የአዲስ አበባን ውበት እየገለጠ፣ ዘመናዊነትን እያለበሳት፣ ሳቢነቷን እየጨመረ፣ የበርካቶችን ቀልብ እንድትገዛ እና ድምቀቷ እየፈካ እንድሄድ አድርጓታል። በአሁኑ ጊዜም በርካታ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎችንም አዘጋጅታለች። እያዘጋጀችም ነው። ከተማዋ የበለጠ ለመድመቅ

በአሁኑ ጊዜ ሁለተኛው ዙር የኮሪዶር ልማት ምዕራፍን በማገባደድ ላይ ትገኛለች።በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪዶር ልማት የካዛንቺስ፣ የፒያሳ፣ የሜክሲኮ፣ የቦሌና የሰሚት መስመሮች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል። እየተከናወኑ ያሉ የኮሪዶር ልማቶችም ወደ መጠናቀቁ እየተቃረቡ ነው። ለአብነትም የአራት ኪሎ – ሽሮ ሜዳ መስመር ተጠቃሽ ነው።

ወጣት ረታ ዱጋሳ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሲሆን አራት ኪሎ ከኮሪዶር ልማቱ በፊት ለዓይን የማይማርክና ለመዝናኛ የማይመች እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የትራፊክ መጨናነቅ ያለበት አካባቢ እንደነበር ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተናግሯል።

የኮሪዶር ልማቱ አራት ኪሎን ከተጨናነቀና ንፁህ ካልሆነ አየር አውጥቶ ተስማሚና ውብ እንዲሆን አድርጎታል። በተለይ የአካባቢውን ገፅታ ያበላሹ አሮጌ ቤቶች አሁን የሉም፤ ለተሽከርካሪም ሆነ ለእግረኛ ምቾት የማይሰጡ ጠባብ መንገዶችም እንዲሁ ደረጃውን በሚመጥን መልኩ ሰፋ ብለው መሠራታቸው እግረኛ መንገድ ባለፈ የእግር ጉዞ ለማድረግም ምቹ ሁኔታን የፈጠረ መሆኑን ገልጿል።

ዘመናዊና አዳዲስ የመንገድ መብራቶችም አካባቢውን ልዩ ገፅታ በማላበስ አካባቢውን ውብና ለኑሮ ተስማሚ እያደረጉ ነው። ይህም ብዙሃኑ ለሚጠቀምበትና ተስማሚ የጋራ ከተማ ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን በጉልህ የሚያረጋግጥ እንደሆነ ተናግሯል።

“የኮሪዶር ልማቱ ለከተማዋ ልዩ የሆነ ውበት የሰጠ በመሆኑ እጅጉን ደስተኛ ነኝ። አስፓልት ዳር የሚስተዋሉ ቆሻሻዎች ተወግደው በዚህ መልኩ ለዓይን ማራኪና ሳቢ መሆኑ ብቻም ሳይሆን ለህብረተሰቡም ለጤና ጠንቅ የሆኑ ቆሻሻዎች ተወግደው በማየቴ ደስተኛ ነኝ” ብሏል።

ከዚህ በፊት በከተማው የሚስተዋለው የጎዳና ላይ የንግድ እንቅስቃሴ የውበት ሥራዎች ላይ ክፍተት የነበረው ሲሆን አሁን ግን በኮሪዶር ልማት አማካኝነት ከተማው አረንጓዴ በመላበስ ነፋሻማ እና ንፁህ አየር እንደፈጠረለትም ገልጿል።

ሌላኛው የአዲስ አበባ ነዋሪ አቶ ፍስሃ ማስረሻ በበኩላቸው፤ በአራት ኪሎ የነበረው የፅዳት ሁኔታ እና ያልተመቹ መንገዶች በቱሪዝም ዘርፉ ላይ አሉታዊ ተፅኖ ሲያሳድሩ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ ከአራት ኪሎ እስከ ሽሮ ሜዳ የተከናወነ ያለው የኮሪዶር ልማት ሥራ ትርጉሙ ጥልቅ መሆኑን ተናግረዋል።

የኮሪዶር ልማቱ ምቹ የእግረኛ መንገዶች እንዲኖሩ በማስቻል ከተማዋን ለኑሮ ምቹ ከማድረግ ባሻገር ጽዱና ውብ ገጽታ በማላበስ እግረኞች ከአደጋ ስጋት ነፃ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ ማስቻሉን ገልፀው፤ በተለይ የኮሪዶር ልማቱ አካል በሆነው የአረንጓዴ ልማት ሥራ ለአቅመ ደካሞች እና ነዋሪዎች የተመቹ የመዝናኛ እና ማረፊያ ስፍራዎች መገንባታቸውን እንዳስደሰታቸው ይገልጻሉ።

በኮሪዶር ልማት ሥራው የተመዘገበው ውጤት አዲስ አበባን በእንግዶች ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን ማስቻሉንም ገልጸው፤ የልማት ሥራዎቹን በመጠበቅና በመንከባከብ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

በአራት ኪሎ እስከ ሽሮ ሜዳ መስመር ቀድሞ የነበሩ መንገዶች ጠባብ እና ለእግረኞች ብሎም ለተሽከርካሪ ፍሰት እምብዛም ያልተመቹ ዜጎችን ለትራፊክ አደጋ ተጋላጭ ያደርጉ እንደነበር የገለፁት ደግሞ የራይድ ሹፌር የሆኑት አቶ ዘሪሁን ኦጂ ናቸው።

አሁን ግን ኮሪዶሩ የትራፊክ ፍሰቱን በማሳለጥ ይከሰቱ የነበሩ የትራፊክ አደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ከፍተኛ አበርክቶ ይኖረዋል ያሉት አቶ ዘሪሁን፤ የኮሪዶር ልማቱ የተሻለና ምቹ የእግረኛና የተሽከርካሪ መንገድን በማካተት በጥራት እየተሠራ በመሆኑ ለአካባቢውም መልካም ገፅታን እያላበሰ ነው ይላሉ።

የኮሪዶር ልማቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መነቃቃቶችን እንደሚፈጥር ገልጸው፤ ለአካባቢውም ጭምር የመልማት እድልን የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

ሳሙኤል ወንድወሰን

አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You