
አዲስ አበባ፡– ለግብርና ምርቶች የመልክዓ ምድር ጥበቃ ሥርዓት በመዘርጋት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትታቸውን ማሳደግ የሚያስችል ረቂቅ መመሪያ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን አስታወቀ።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ወልዱ ይመስል ከግንቦት 26 እስከ 27 ቀን 2017 ዓ.ም የሚካሄውን ዓለም አቀፍ የመልክዓ ምድር አመላካች ጥበቃ ሥርዓት ጉባዔን አስመልክተው ትናንት በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ምርቶች የተሚመረቱበት መልክዓ ምድር በተለምዶ የሚገለፅ ቢሆንም፤ አእምሮዊ ንብረት ጥበቃ ስላልተደረገላቸው የሌላ ሀገር ምርቶችን የኢትዮጵያ ምርት አስመስሎ የመሸጥ ወይም ከሌላ ሀገር ምርት ጋር ቀላቅሎ የመሸጥ ሁኔታ ይታያል፡፡
እስካሁን የምርቶች መልክዓ ምድር በሕጋዊ መንገድ አለመመዝገቡ የምርት ተወዳዳሪነት ላይ ማነቆ እንደነበር በማንሳት፤ በኢትዮጵያ የሚመረቱ የግብርና ምርቶች የምርት ቦታቸው በአእምራዊ ንብረት ተምዝግቦ ጥበቃ እንዲደረግላቸው እና ምርቶቹ ወደ ውጭ በሚላኩበት ወቅት መለያቸው ተለጥፎ እንዲላክ የሚያስችል ረቂቅ መመሪያ መዘጋጀቱን ይፋ አድርገዋል፡፡
የመልክዓ ምድር አመልካች ሥርዓት ላይ የግንዛቤ እጥረት እና የተነሳሽነት ችግር በመኖሩ ወደ ተግባር ሳይገባ መቆየቱን አንስተው፤ ከዚህ በፊት የነበረው የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ሥርዓት ዝግ መሆንም ለመዘግየቱ እንደ ምክንያት የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡
አቶ ወልዱ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት መፈረሟን፤ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ጫፍ ላይ መድረሷን እንዲሁም አጠቃላይ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረጓን በማንሳት፤ የመልክዓ ምድር አመልካች ጥበቃ ሥርዓት መዘርጋት ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚሠሩ ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት የአባልነት ስምምነት ከተደረገ በኋላ የኢትዮጵያን ምርቶች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ በሚደረገው እንቅስቃሴ የመልክዓ ምድር አመልካች ጥበቃ ሥርዓት ወሳኝ እንደሆነ ገልጸው፤ ይህን ማድረግ ካልተቻለ የሌሎች ሀገራት ምርት ተቀባይ ብቻ ሆነን ነው ምንቀረው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት፤ የፊታችን ማክሰኞ እና ረቡዕ የሚዘጋጀው ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ ለረቂቅ መመሪያው ተጨማሪ ልምድ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ረቂቅ መመሪያው ከቻይና፤ ከአፍሪካ እና ከሌሎች ሀገራት በመጡ ባለሙያዎችም ይገመገማል፡፡
ለሶስት ቀናት ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት የዓለም አእምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዳሬን ታንግ ጉባዔው ላይ እንደሚሳተፉ ጠቁመው፤ ይህም ትብብር ለመፍጠርና አዲስ አሠራሮችን ለመዘርጋት እድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳሉ ሞሲሳ በቡኩላቸው፤ ለሁለት ቀናት የሚካሄደው ጉባዔ በመልክዓ ምድር አመልካች ጥበቃ ሥርዓት ለመመዝገብ የታጩ ምርቶች ለማስተዋወቅ፤ ተሞክሮዎችን ለማግኘት፤ ለሚዘጋጀው መመሪያ ግብዓት ለማግኘት እና ባለድርሻ አካላትን ለማሳተፍ እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡
በጉባዔው ላይ ከዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ከፌዴራል እና ከክልል አጠቃላይ 130 ያህል ሰዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ የሚጠበቅ ሲሆን፤ 15 የግብርና ምርቶች ለኤግዚቢሽን እንደሚቀርቡ ተመላክቷል፡፡
ዓመለወቅ ከበደ
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 24 ቀን 2017 ዓ.ም