የአቃቂ ቃሊቲ ስታዲየም ግንባታ በመጪው ዓመት ይጠናቀቃል

አዲስ አበባ፦ በተለያዩ ምክንያቶች የግንባታ ሂደቱ ሲጓተት የቆየው የአቃቂ ቃሊቲ ስታዲየም ግንባታ በመጪው ዓመት እንደሚጠናቀቅ የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች የልማት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ባዩ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በ2010 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው የአቃቂ ቃሊቲ ዞናል ስታዲየም በአሁኑ ጊዜ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ደረጃን (ስታንዳርድ) ባሟላ መልኩ እየተገነባ ነው።

ስታዲየሙ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ደረጃን (ስታንዳርድ) ያሟላ ለማድረግ ከሁለት ዓመት በፊት አዲስ ዲዛይን ተሠርቶ ወደ ሥራ መገባቱን የገለጹት አቶ ብርሃኑ፤ ስታዲየሙን በዞናል ደረጃ ለመገንባት ሲታሰብ 500 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞ ነበር። ነገር ግን በተደረገው የዲዛይን ማሻሻያ የተያዘው በጀት ወደ አንድ ቢሊዮን ብር ከፍ እንዲል ተደርጓል ብለዋል።

የዚህም ዋና ዓላማ ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ እና የአትሌቲክስ ውድድሮችን ለማከናወን እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ብርሃኑ፤ ይህን መሠረት በማድረግ የግንባታውን አፈፃጸም ከ85 በመቶ በላይ ማድረስ ተችሏል። አሁን ላይ ጣሪያ ገጠማ ሥራ እየተከናወነ ሲሆን በቀጣይ የሜዳና የመሮጫ ትራክ ሥራ እንደሚከናወን ገልጸዋል።

የስታዲየም ግንባታውን ሂደትን ከዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና ከዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተውጣጡ ባለሙያዎች የክትትል ሥራ እንደሚያከናውኑ የጠቆሙት አቶ ብርሃኑ፤ በሚሰጠው ምክረ ሃሳብ መሠረት የስታዲየሙ ግንባታ በቀጣይ ዓመት ሙሉ ለሙሉ የሚጠናቀቅ ይሆናል። ይህም ልምድ ባላቸው የውጭ ኩባንያዎች የሚሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ስታዲየሙን እኤአ ለ2029 የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጁ ለማቅድረግ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አመልክተው፤ በዚህም ከ20 ሺህ በላይ ተመልካቾችን ማስተናገድ እንደሚቻል እና ለሚዲያዎች፣ ለቪ. አይ.ፒ እና ለቪ.ቪ.አይ.ፒ እንግዶች የተዘጋጀ ልዩ ቦታ መኖሩንም ተናግረዋል።

ስታዲየሙ ከሁለት ሺህ በላይ መኪናዎችን በአንድ ጊዜ ማቆም የሚቻልበት ቦታ እንዳለው እና ተመልካቾች በቀላሉ ወደ ውጪ መውጣት እንዲችሉ የስታዲየሙ መግቢያ በሮች ሰፋፊ ተደርገው እንዲገነቡ መደረጉን ገልጸዋል።

ሌላው ዝናብ ሲዘንብ ሜዳ ውስጥ የሚገባውን ውሃ በአምስት ደቂቃ ውስጥ መምጠጥ እንዲችል የሚያደርግ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ የሳር ሜዳ በስታዲየሙ እንደሚኖር ጠቁመው፤ ቢሮዎች፣ ሱቆች፣ የሳይክል መንገድ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ደረጃ (ስታንዳርድን) መሠረት ያደረጉ ግንባታዎች የተካተቱበት እንደሆነ አመልክተዋል።

ከዚህ ባሻገርም ሥራ ሲጀምር ቲኬት በዲጂታል ሥርዓት መቁረጥ የሚቻልበት አሠራር እንደሚኖር እና በግንባታው የተቆረጠውን ቲኬት ስካን ማድረጊያ ቦታዎች እንዲኖሩት ይደረጋል ያሉት አቶ ብርሃኑ፤ ግንባታው ሲጠናቀቅ በአካባቢው ያለውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ለወጣቶች የሥራ ዕድል አማራጭ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You