ኢትዮጵያ “ሃይማኖተኛ ሕዝቦች” ካሉባቸው ሀገራት መካከል ተቀዳሚ መሆኗን የሚያረጋግጥ መረጃ በአንድ ዓለማቀፋዊ ተቋም በቅርቡ ለዓለም ሕዝቦች መበተኑን ብዙዎቻችን ሳናነብ የምንቀር አይመስለኝም። እንዲህ ዓይነቱ መረጃ በየጊዜው ይፋ ቢሆንም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እጅግም ቀልቤን አይስበኝም ነበር። ዛሬ ግን በመረጃው መሳብ ብቻ ሳይሆን ብዙ ተጓዳኝ የጎንዮሽ ጉዳዮችንም እንዳገናዝብ ጭምር ምክንያት ስለሆነኝ ጉዳዩን መዳሰሱ አስፈላጊ መስሎ ታይቶኛል።
ማንኛውም ጤነኛ ሃይማኖት ለምዕመኑ በብዙ መልኩ ጠቃሚ ስለመሆኑ እየተነተንኩ ማረጋገጫ ለመስጠት አልሞክርም። ቦታው ስላይደለ። ለመንደርደሪያ እንዲሆን ግን አጠቃላይ ሃሳብ ሰንዝሮ ማለፉ አይከፋም። ሁሉንም ሃይማኖቶች ከሚያማክሏቸው የጋራ መርሆዎች መካከል ይቅርታና ንስሃ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ በግልም ሆነ በቡድን፣ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ተፈጽሟል ለሚባል ግላዊም ሆነ ማኅበራዊ በደልና ጥፋት በስውር ብቻ ሳይሆን በግልጽና በአደባባይ ጭምር በፈጣሪና በሰው ፊት ይቅርታ እንዲጠይቅ ማዘዙ የእምነቶች ሁሉ ማዕከላዊ ቀኖና ነው። እውነትም በንስሃ እንደመታደስ ውስጥን የሚፈውስ ሌላ ኃይል ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም። አስፈላጊነቱን ባልክድም ከይቅርታ በተጓዳኝ በቅጣት፣ በካሣና በተለያዩ ሕጋዊ ውሳኔዎች በደል የሚካስበት አካሄድ እንኳ ቢሆን ኑዛዜና ንስሃ የሚፈውሰውን ያህል አቅም ይኑረው አይኑረው እርግጠኛ አይደለሁም።
የጠቀስኩት ስታትስቲክስ ሀገራችንን “የሃይማኖተኞች ሕዝቦች ቁንጮ” አድርጎ በዓለም ፊት ሊያስጨበጭብላት ወይም ሊያዘምርላት አለያም ሊያዘይርላት የቻለው በምን መስፈርት መዝኖ እንደሆነ ዝርዝር ምክንያቶችን አላቀረበም። በሃይማኖቶቹ፣ በመሪዎቹም ሆነ በተከታዮቻቸው መካከል በረጂሙ ሀገራዊ ታሪካችን ውስጥ አንዳንድ ታሪካዊ ስህተቶች አልተፈጸሙም ብሎ መከራከር ባይቻልም ክርስቲያኑ ከሙስሊሙ፣ ይሁዲው ወይንም ባህላዊዎቹን ጨምሮ የተለያዩ እምነት ተከታይ ወገኖቻችን እርስ በእርስ ለዘመናት ተከባብረውና ተጋምደው መኖራቸው ግን እውነት ነው።
ዓለም አቀፉ ተቋም የሰሞኑን መረጃ ይፋ ያደረገው የሀገራችንን ስታትስቲክስ ማቀነባበሪያ ተቋም ወይንም ይመለከተናል የሚሉ አካላት የሰጡትን ሪፖርት ብቻ ዋቢ በማድረግ ተዳፍሮ ከሆነም ገበናችንን ሳይፈትሽ “የሰነፍ ጥናት” እንደወረወረልን ቆጥረን የሌለንን ሰሞንኛ ጽድቅና ሞገስ በማጎናጸፉ “አይመለከተንም!” ብለን እንዳላየን ማለፉ ይበጅ ይመስለኛል። ይህንን የግል አቋሜን በድፍረት የምገልጸው ሃይማኖቶቻችን ለሚያዙት ተግባሮች ጀርባችንን እየሰጠን በቁጥሮች ስሌት መፅደቅ ተገቢነቱ ስለማይታየኝ ብቻ ነው። የቁጥር ቁጥርማ እንኳንስ የውጭ ባዕዳን ቀርተው የሀገራችን ቤተ እምነቶች ራሳቸው የአማኒያናቸውን ቁጥር እየገለፁልን ያለው በሚሊዮኖች እያጋነኑም አይደል? መረጃዎቹ ራሳቸው አንዳንዴ ከሕዝቡ ከራሱ ቁጥር ባይበልጡ ብዬ እጠይቃለሁ።
በዚህን መሰሉ ጠቅላይ መንደርደሪያ ብዕሬን ያጀገንኩት ያለምክንያት አይደለም። አብዛኞቹ የየሃይማኖቶቹ መሪዎችም እንሁን ምዕመናን ነን የምንል ዜጎች “የአምልኮ መልክ እንጂ ለተመላኪው ፈጣሪ ትዕዛዝ እጅግም ቁብ ያልሰጠን” እስክንመስል ድረስ በዕለት ተዕለት ሕይወታችንና ሀገራዊ ታሪኮቻችን ላይ የማይጠቅም እድፍ ስንለጥፍ መዋላችን የአደባባይ ምሥጢር ነው። ደግሜ እላለሁ ስታትስቲክሱን ያሰራጨው ተቋም ይህንን ገበናችንን ገልጦ ስለማየቱ እርግጠኛ አይለሁም።
የሃይማኖቶቹ ክብር እንደተጠበቀ ሆኖ አማንያን ተብለን የምንጠራው ዜጎች ለሥልጣን፣ ለክብር አለያም ለጊዜያዊ ጥቅማ ጥቅሞች ስንል የምንፈጽማቸው ተግባራት እንደምን አሸማቃቂ እንደሆኑ ነጋ ጠባ የምናስተውለው ሐቅ ነው። ውሎ አድሮ የዓለም መሳቂያ መሳለቂያ እንደምንሆን መጠርጠሩም አይከፋም።
ሀገራዊ ባህልም እንበለው ባህርይ ብቻ በግል በቡድንና በማኅበረሰብ ደረጃ እንደ ሀገር መመሰጋገን ባዕድ የሆነብን፣ የኋለኛውን ትውልድ ኃጢያት እያገዘፍን መልካም ተግባራትን እየነቀስን በዛሬው ጥረታችን ላይ ከማከል ይልቅ አብዛኞቻችን የሚቀናን መሠረት መናድና ምሰሶዎችን ማፍረስ ነው። ከታሪክ መሰዊያ ላይ አመዱን አንገዋለን ፍሙን ከመጫር ይልቅ የምንሽቀዳደመው “የትችት መጫሪያ ገል” ይዞ በመቅረብ ለምስጋና ሳይሆን ለትችት መወዳደር ይመስላል። ሺህ ዓመታትም ይሁን መቶ ዓመታትን ወደ ኋላ አፈግፍገን በተፈጥሮ ሞትም ይሁን በተለያዩ ምክንያቶች ያሸለቡትን መሪዎቻችንንና የዘመናቸውን አፅም እረፍት እየነሳን ሙት ወቃሽ ስንሆንም ጥቂት አይፀፅተንም።
በክፋታቸው የምናወግዛቸውን ተቀዳሚ ትውልዶች ዜና መዋዕል በታሪክ መዝገብ ላይ አስፍረን “ነበርን” ከማቆየት ይልቅ ራሳቸውን በማይከላከሉበትና ሊከራከሩ በማይችሉበት ሁኔታ የዘመን ርቀት አቆራርጦን እያለ “ነፍሳቸውና መንፈሳቸው እንዳያርፍ” ነጋ ጠባ በአንደበታችን ዲስኩርና በወልጋዳ ብዕራችን ጥቁር ቀለም እየጠቀስን ስብዕናቸውንና ታሪካቸውን ማጨለሙን እንደ ጀብድ የቆጠርነው ምኑ ቢያስደስተን ነው? እያልኩ እጠይቃለሁ።
ወደ መነሻዬ ልመለስና የሩቁን ታሪካችንን ለጊዜው አቆይቼ የቅርብ በሚሰኙ ጉዳዮቻችን ላይ አፅንኦት በመስጠት ጥቂት ምልከታ ላድርግ። “ያ ትውልድ”፣ “ይሄ ትውልድ”፣ “ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ”፣ “የ60ዎቹ ትውልድ” ወዘተ… የሚሉ አገላለጾችን ደጋግመን ሳናነብና ሳንሰማ የቀረን አይመስለኝም። በግል አመለካከቴ “ያ ትውልድ” የሚለው መጠሪያ ይበልጥ ጎልቶ የወጣው የቀድሞው የኢህአፓ ሁነኛ ሰው የነበሩት አቶ ክፍሉ ታደሰ “ያ ትውልድ” በሚል ርዕስ በተከታታይ ቅጾች የጻፏቸው መጻሕፍት ለንባብ ከበቁ በኋላ ይመስለኛል። አባባሉ እንደ አዲስ ተፈጠረ ለማለት ሳይሆን ገኖ መውጣቱን ለማመልከት መሆኑን ልብ ይሏል።
“ያ ትውልድ” ወይንም “የ60ዎቹ ትውልድ” የሚለው አገላለጽ በዋነኛነት እንዲወክል የተመረጠው ከሃሳብ ልዩነት ይልቅ እስከ ሆሄ በሚዘልቅ ልዩነት ሳይቀር “እናሸንፋለን” እና “እናቸንፋለን” በማለት የተጠፋፋውን የዘመኑን አሳዛኝ ወጣት ለማመልከት ነበር። እነዚህ የቀይና የነጭ ሽብር ሰለባ ወንድሞቻችን፣ ልጆቻችንና ተስፋዎች “ዓላማዬ ያሉትን መርህ ሳይፈትሹ” መገዳደልን ምርጫ አድርገው ጥለው የወደቁት ወይንም እየወደቁ ለመጣል የጨከኑት ለምን ዓላማና ትርፍ ነበር በማለት እጠይቃለሁ። እንኳንስ “ትናንት በደመ ሙቅነት” አፍላ እድሜ ላይ እያሉ ቀርቶ ዛሬም ድረስ እድሜ አስክኗቸው እንኳ የጥሞና ጊዜ ወስደው ወደ ህሊናቸው ለመመለስ ለምን እንደሚያመነቱ ግራ ይገባል። ማስረጃዬ የምለው ትናንትም ሆነ ዛሬ መድረክ ባገኙ ቁጥር የሚደሰኩሩትንና በየጽሑፋቸው የሚሟገቱባቸውን ያረጁ ሃሳቦች ዋቢ በማድረግ ነው።
“አትነሳም ወይ! የዘውድ አገዛዝ አይበቃህም ወይ!” እያለ በመዘመር የአብዮትን ቋያ ያቀጣጠለውና “መሬት ላራሹ”ን አየፈከረ ወደ ውጤት ተቃርቦ የነበረው “ያ ትውልድ” በንግግር መተማመን፣ በሃሳብ ልዕልና መቀራረብ ተስኖት በሰይፍና በሰደፍ እየተፋለመ በመጠፋፋት ደርግን አፋፍቶ እርሱ ግን በምድረ በዳ ባክኖ መቅረቱ አንዱ የታሪካችን መራራ እውነታና ምድሪቱን ከል ያለበሰ የወቅቱ ክስተት ነበር። ዝርዝሩን ለታሪክ ፍርድ እተዋለሁ።
“ያ ትውልድ” እያለ ለራሱ ስም የሰጠውን የማኅበረሰባችን “ጠፍ ትውልድ” የሚወክሉት ወጣቶች ብዙዎቹ የተወለዱት በተቀራራቢ ግምት በ1930ዎቹ መጨረሻና በ1940ዎቹ ዓመታት ውስጥ ነበር። ያ ዘመን ደግሞ ሀገሪቱ ከፋሽስት ወረራ ነፃ ከወጣች ገና የአስርና የአስራ አምስት ዓመት ዕድሜ የድል በዓሏን ብታከብር ነው። ስለዚህም “ያ ትውልድ” የኖረው እነእከሌ የሚላቸው ተምሳሌትና መልካም አርአያዎች (Role Models) ያላገኙበት፣ የፈራረሰው ሀገራዊ ሥርዓተ መንግሥት፣ የትምህርት አቋም፣ የባህል፣ የማኅበረሰብና የኢኮኖሚ አውታሮች ገና እየተጠገኑና መልክ እየያዙ በነበሩባቸው የጦርነት ማግሥት ነበር። በእዚህን መሰሉ ዘመን ተፈጥረው ነውጠኛ ቢሆኑ መች ይፈረድባቸዋል እንደማይባል ተስፋ አደርጋለሁ።
ስለዚህም ያ ትውልድ በ20ዎቹ ዕድሜው ውስጥ እስከ ዩኒቨርስቲ ትምህርት ዘልቆ “በቼጉቬራ፣ በሆችሚኒ፣ በማኦ ዜዱንግ፣ በሌኒን፣ በስታሊንና በማርክስ” ስምና አይዲዮሎጂ ሲማማልና ሲቋሰል ሀገሪቱ ገና በሁሉም ዘርፍ በፊውዳላዊ ሥርዓተ መንግሥት አገዛዝ ዳዴ እያለች የምትድሄበት ወቅት ነበር። የ1953ቱ የጄኔራል መንግሥቱ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራና ከዚያ በፊት የተደረጉ አንዳንድ የአመፅ እንቅስቃሴዎችም የተሞካከሩት በ”ያ ትውልድ” ታዳጊነት ዘመን ነበር። ራሱ ትውልዱ፤
“ነቅናቂው ነቅንቆ ቢያነቃንቀው፣
የተነቃነቀው ነቅንቆ ጣለው።”
በማለት በእነጄኔራል መንግሥቱ አመፅ ክሽፈት ላይ መሳለቁ ውሎ ሳያድር የእርሱ ንቅናቄም በደርግ “ተነቅሎ” የሀገሪቱና “የያ ትውልድ” ታሪክ በደም ተጨማልቆ ማለፉን ልብ ይሏል። ከደርግ መልዓከ ሞት የተረፉት ጥቂቶች ከፊሉ በቦሌ፣ ያልቀናውም በባሌ ከፊሉ ወደ በረሃ ተሰዶ የተፈጠረው የትራዤዲና የኮሜዲ ፖለቲካዊ ክፉ ውጤትና የጠለሸ ሀገራዊ ጉዳይ ገና ተዘርዝሮ አላበቃለትም።
ደርግ የልቡን ጭካኔ ፈጽሞ ለተረኛውና “ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ” የሚል ስያሜ ለራሱ ለሰጠውና የሥርዓቱ ግፍና መከራ እስከዚህች ደቂቃ ገና ተተርኮ ላላለቀውና እስካሁንም ሊቆም ላልቻለው የበረኸኞች ሥርዓት ከተላለፈ በኋላ የተፈጸሙት ሀገራዊ እፍረቶች ገና ፈውስ አላገኙም። አንዳንድ ግፎችም የካንሰር ያህል ለመፍትሔ የሚያስቸግሩ ስለሆኑ ከሀገራዊ ህመማችንና ጥዝጣዜያችን እፎይ ብለን ልናርፍ አልቻልንም።
በቀይም ሆነ በነጭ ሽብርተኝነት እጃቸው ያደፈው የ“ያ ትውልድ” አባላት በልባዊ ፀፀት መንፈሳቸው ተነክቶ ከራሳቸው፣ ከሕዝባቸውና ከፈጣሪ ጋር እርቅ በመፍጠር በንስሃ መታደስ የተራራ ያህል ከብዷቸው ባገኙት መድረክና በጻፏቸው መጻሕፍት ሳይቀር የትናንት ድርጊታቸውን እንደ ፅድቅ በመቁጠር “በአራራይ ዜማ” ሲያንጎራጉሩ ማድመጥ ለትዝብት ይዳርጋል። አልፎም ተርፎ “ስህተተኛ የነበሩት የፖለቲካ ቡድኖች የእነእንቶኔ እንጂ የእኛማ ድርጅት የአርነት ተሟጋች፤ የሰላም ጠበቃ ነበር” እያሉ ሲሟገቱ ማድመጥ የተለመደ ክስተት ነው። አንዳንዶቹም የአርባ ዓመት የፖለቲካ ቅኝታቸውን በዘመን ወለድ ምት አስተካክለው “ሪ ሚክስ የፖለቲካ ጨዋታ ሲቆምሩ” ማስተዋልም ውስጥን ያሳምማል።
ሕጋዊ ፍርዳቸውን አጠናቀው ከበደሉት ሕዝብ ጋር የተቀላቀሉ የደርግ ሹማምንትም ቢሆኑ ለራሳቸው የጥሞና ጊዜ ወስደው ወደ ህሊናቸው ከመመለስ ይልቅ አልፎ አልፎ በየመድረኩና በየመጻሕፍታቸው ውስጥ ፅድቃቸውን ሲያውጁ ይስተዋላሉ። ይህም ከህሊና እውነታ አፈግፍጎ ራስን መሸንገል ይመስለኛል።
“ተራራውን እንቀጥቅጫለሁ” ባዩ ትምክህተኛ ትውልድም ዛሬም ድረስ ለተፈጸመው ሀገራዊ ግፍና በሕዝብ ህሊናና ሀብት ላይ ስለተፈጸመው በደል በኑዛዜና አጥፊውን አሳልፎ በመስጠት ከትውልድና ከታሪክ ወቀሳ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከመዳን ይልቅ እነሆ በየቀኑ አጀንዳና “ጠብ ያለሽ በዳቦ” መናከሻ እየፈበረከልን ሀገሪቱ በገበቴ ላይ እንደሚዋልል ውሃ በነውጥ እንድትናጥ ግፋ በለውን እየፈከረ ያባላናል።
“ይሄም ትውልድ” ቢሆን ካለፉት ትውልዶች ለመማር ተስኖትና ለመስከን አቅም አጥቶ በነጋ በጠባ የሚፈጠሩለትን አጀንዳዎች አጥልሎ ከማንገዋለል ይልቅ በጥፋት አውሎ ነፋስ ወዲያና ወዲህ እየተንገላታ የመከራችንን እድሜ እንድናራዝም ምክንያት እየሆነ እንዳለ ለማስተዋል አይገድም። በሀገርና በሕዝብ ላይ እልቂት የሚደግሱ ክፉዎች በቀይ ምንጣፍ ላይ እየተራመዱ ግፋ በለውን ሲዘምሩለት “ይሄ ትውልድ” በእሾህና በቆንጥር ላይ እየተራመደና “በዘራፋቸው ቀረርቶ” ወኔው እየገነፈለ ራሱን ለመከራ፣ ሕዝቡን ለሰቆቃ ታሪኩን ለውርደት እየዳረገ ይገኛል።
ትውልድ ሆይ! በዚህን መሰሉ ውጥንቅጥ ታሪካዊ ወቅት ላይ እያለን ነው የበቀደሙ ዓለማቀፋዊ ተቋም “በዓለም ላይ ሃይማኖተኛ ሕዝቦች ካለባቸው ሀገራት መካከል የመጀመሪያ ረድፍ ላይ የተሰለፋችሁት እናንተ ናችሁ ብሎ” እየተሳለቀ አጨብጭቦ፤ ያስጨበጨበልን። ንስሃን መች አውቀን። ፀፀትንስ መች ተምረን።
እናስ ምን ይሁን? ቂምና ቁርሾን እንዳረገዝን ኖረን መሞት ወይንም ሞተን መኖር – ምርጫ አንድ። ወደ ህሊናችን ተመልሰን በንግግር፣ በውይይትና በመግባባት ተቀራርበን የተላኩብንን መጥፎ ባህሪይዎች በይቅርታና በንስሃ ማደስ – ምርጫ ሁለት። ምርጫ ሦስት – ሀገርና ሕዝብን፣ ታሪክና ትውልድን የሀዘን ማቅ አልብሰን . . . ሃሳቡን መጨረሱ በራሱ ይጎፈንናል። ወገኔ ሆይ ቢመረንም፣ ቢጎመዝዘንም እርስ በእርስ እንፈዋወስና ከመከራችን እንዳን! መልካም ዘመን! ሰላም ይሁን።
ይህ ዓምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ አስተያየታቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሑፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሀሴ 29/2011
(በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ)