እነሆ የዓመቱ ማጠቃለያ ላይ ደርሰናል። 2011 ዓ.ምን ሸኝተን አዲሱን 2012 ዓ.ም ልንቀበል በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ቀርተውናል። ለመሆኑ 2011 ዓ.ም እንዴት አለፈ? ምን በጎ ነገሮች ነበሩ? ምን ተግዳሮቶችስ ገጠሙን? በወፍ በረር አለፍ አለፍ ብለን እንቃኛለን።
2011 የለውጥ ጉዞው አንድ ዓመት የደፈነበት ነው። ለውጡ ተቋማትን በመገንባትና በማሻሻል አጠናክሮ በመቀጠሉ የማይናቅ ስራዎች ተከናውነዋል። በዚህ ዓመት የምርጫ ቦርድ እና የሲቪል ማህበራት ሕጎችን ከማሻሻል ጀምሮ አዲስና ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ ለማቋቋም የተሄደበት ርቀት በቀላሉ የሚይታይ አይደለም። የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም እንዲሁ የማወዳደሪያ መስፈርት አውጥቶ ለቦታው የሚመጥን ሰው በማስቀመጥና ሥራዎች በተሻለ ሁኔታ እንዲራመዱ የጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ አስተዳደር የተሳካ ሥራ አከናውኗል።
በዓመቱ ካስተናገድናቸው ግጭቶች እና አለመግባባቶች ጥቂቶቹን ብቻ አለፍ አለፍ ብለን እንቃኛለን።
መስከረም 5 ቀን 2011 ዓ.ም ለኦነግ አመራሮች በመስቀል አደባባይ ደማቅ አቀባበል ፕሮግራም ተዘጋጅቶ ነበር። ከዚህ ፕሮግራም መልስ በቡራዩ ያልታሰበ ግጭት ተቀሰቀሰ። ንጹህ ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመው ግፍ ብዙዎችን ያሳዘነ ክስተት ነበር። በወቅቱ 15 ሺህ 86 ዜጎች በግጭቱ መፈናቀላቸው፣ በጥቅሉ በቡራዩና በሌሎች አካባቢዎች በዕለቱ ከ23 በላይ ሰዎች መሞታቸውን በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን መዘገቡ የሚታወስ ነው።
መስከረም 14 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዙሪያ የተፈጸመውን ጥቃት በመቃወም ለተቃውሞ ሰልፍ በርካቶች አደባባይ ወጡ። ሰልፈኞቹ ከፖሊስ ጋር ተጋጭተው የአምስት ሰዎች ህይወት አለፈ። ብዙ ወጣቶችም በወቅቱ ለእስር መዳረጋቸውን እናስታውሳለን።
በመጋቢት ወር 2011 ዓ.ም
በሰሜን ሸዋ ዞን አጣየ፣ ካራቆሬ፣ ማጀቴ እና ሌሎችም አካባቢዎች” የተደራጁ” በተባሉ ቡድኖች በከፈቱት ተኩስ የሰዎች ህይወት ማለፉን የየአካባቢዎቹ ነዋሪዎችና የፀጥታ አካላት ተናግረዋል። “የተደራጀው ቡድን” ቤተ እምነቶችንና የግለሰቦችን መኖሪያ ቤቶች ማቃጠሉን የሚዘነጋ አይደለም።
ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም
ያልታሰበ ጥቃት በባህርዳር እና በአዲስአበባ በሰዓታት ልዩነት ተሰከተ። በባህርዳሩ ጥቃት የክልሉ ርዕሰ መስተዳዳር የነበሩት ዶ/ር አምባቸው መኮንን፣ የአደረጃጀት ዘርፍ አማካሪቸው አቶ እዘዝ ዋሴ እና የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ምግባሩ ከበደ መገደላቸው የሚታወስ ነው። የቀብር ስነስርዓቱም በባህርዳር ቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክ ረቡዕ ሰኔ 19 ቀን 2011 ዓ.ም ተፈጽሟል።
ይህን የመፈንቅለ መንግሥት ወንጀል አቀነባብረው እንደመሩ የተነገረላቸውና ሊያመልጡ ነበር በሚል በጸጥታ ኃይሎች የተገደሉት የክልሉ የሠላምና ጸጥታ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ብ/ጀኔራል አሳምነው ጽጌ የቀብር ስነስርኣትም በተወለዱበት በላሊበላ ቤተክርስቲያን በዕለቱ ተፈጽሟል።
ከባህርዳሩ ግድያ በሰዓታት ልዩነት በአዲስአበባ የኢፌዲሪ መከላከለያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማጆር ሹም የነበሩት ጀኔራል ሰዓረ መኮንን እንዲሁም ጡረተኛው ሜጀር ጀኔራል ገዛኢ አበራ መገደላቸውን የምናስታውሰው በከፍተኛ ሐዘን ነው። ከዚህ ክስተት ጋር በተያያዘ 13 አመራሮችና የጸጥታ ኃይሎች ሕይወት ማለፉም የሚዘነጋ አይደለም። የእነዚህ ጦር መኮንኖች የቀብር ስነስርዓትም በመቀሌ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ሰኔ 19 ቀን 2011 ዓ.ም መፈጸሙ የሚታወስ ነው።
ከዚህ ወንጀል ጋር ተያይዞ በአዲስአበባ 45 በባህዳር ደግሞ የክልል የልዩ ጸጥታ ኃይል አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ተፈራ ማሞ እና የክልሉ የጸጥታ ሠላም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኮሎኔል አለበል አማረ ጨምሮ 178 ሰዎች በወቅቱ ተጠርጥረው መታሰራቸው የሚታወስ ነው።
ሐምሌ 2011- የሲዳማ ግጭት
በሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም በሲዳማ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች እና ከተሞች በተከሰተው ግጭት ሀኪም ቤት ሳይደርሱ በየአካባቢው የተቀበሩትን ሳይጨምር 53 ሰዎች ሲሞቱ ሌሎች 54 ሰዎች ደግሞ መጎዳታቸውን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አረጋገጠ። በወቅቱ ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘም እስካሁን 935 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የሲዳማ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል። የመምሪያው ዋና አዛዥ ምክትል ኮማንደር ዳኛቸው ደምሴ በተለይ ለጀርመን ድምጽ እንደገለፁት የግጭቱ መነሻ ሐምሌ 11 ቀን 2011ዓ.ም በሐዋሳ ከተማ የሲዳማ ብሔር በክልል የመደራጀት ጥያቄን እናውጃለን የሚሉ ወጣቶች ከፀጥታ አካላት ጋር መጋጨታቸው ነው። በመቀጠልም ግጭቱ ሲዳማ ዞን ውስጥ ወደሚገኙት ሁላ፣ ይርጋዓለም፣ ማልጋ፣ ሞሮቾ እና አለታ ወንዶ ወረዳ እና ከተሞች መዛመቱን ተናግረዋል። በተጠቀሱት ከተሞችና ወረዳዎች ከሞቱትና ከቆሰሉት ወገኖች በተጨማሪ፤ የዱቄት ፋብሪካዎችና የመዝናኛ ሎጆችን ጨምሮ በሚሊየን ብሮች የሚገመት ንብረት በቡድን ሲንቀሳቀሱ በነበሩት ወጣቶች መውደሙና መቃጠሉም የሚታወስ ነው።
ይህም ሆኖ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይህንኑ ደም አፋሳሽ የሲዳማዎች ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል በመጪው ዓመት ህዳር ሦስት ቀን 2012 ዓ.ም ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ መወሰኑን አስታውቋል።
በደቡብ ክልል የሕዝቦች የክልልነት ጥያቄ ለመመለስ ይረዳ ዘንድ በገለልተኛ አጥኚ ቡድኖች ጥናት መከናወኑ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ሰንብቷል። የጥናቱ ፍሬ ሃሳብ የሚከተለውን ይመስላል።
የደቡብ ክልል የሕዝብ ብዛት በኢትዮጵያ ሶስተኛ (3ኛ) ደረጃ ማለትም 25 ሚሊዮን ገደማ መሆኑ ይታወቃል። እንደሚታወቀው የደቡብ ክልል መንግስት ከመመስረቱ በፊት በኢትዮጵያ ሽግግር መንግስት ወቅት ማለትም ከ1983-1987 ዓ/ም ድረስ አምስት ክልሎች የነበሩና ከፌደራሉ መንግስት ምስረታ ወቅት እነዚያ አምስት ክልሎች በኃይል ተጨፍልቀው የደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልል የሚል መንግስት መስርተው ለ24 ዓመታት ከነጥያቄያቸው የተለያዩ በደሎችን ከመንግስትና ከመሪው ድርጅት ሲያስተናግዱ እጅግ በትዕግስት እልህ አስጨራሽ ትግል ሲያካሂዱ ቆይተዋል።
በደቡብ ክልል ከመንግስት ምስረታ ጀምሮ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ከልክ በላይ እጅግ የተጎዱ አካባቢዎች እንዳሉና ፍትሃዊነት የጎደለው የሐብትና የሥልጣን ክፍፍል መኖሩን አንዳንድ ይፋ ያልተደረጉ ጥናቶችና የፖለቲካ ተንታኞች ይጠቁማሉ። በመሆኑም ከ27 ዓመታት የኢህአዴግ ዘመነ መንግስት በኋላ አገሪቷን የሚመራው ድርጅት ራሱን በጥልቀት ከመረመረና ካደሰ በኋላ የለውጥ መንግስቱም ከአንድ ዓመት በፊት መተካቱን ተከትሎ በተለያዩ አገሪቱ ክልሎች የተለያዩ ጥያቄዎች መነሳት ጀምረዋል።
ይህም የሆነው በፌደራል ደረጃ የለውጥ መንግስት የቀድሞ ሕወሃት መራሹ ኢሕአዴግ መንግስት ያልመለሳቸውን የዴሞክራሲና የፖለቲካ ብሎም የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ፍትሃዊነት ጥያቄዎችን በሆደ ሰፊነትና በቁርጠኝነት ለመመለስ ያሳየውን በጎ እንቅስቃሴ መሰረት በደቡብ ክልል ሕዝቦች የዘመናት ራስን በራስ የማስተዳደር ሕገ-መንግስታዊ የክልልነት ጥያቄ ይዘው መነሳት ጀመሩ።
ይህም በሕገመንግስት አንቀፅ39 እና 47 መሰረት ትክክለኛ ጥያቄ መሆኑን ራሱ መሪ ድርጅት ደኢሕዴንም ሆነ ኢሕአዴግ ብሎም የፌደራል መንግስት ጭምር በተለያዩ መግለጫዎች እምነታቸውን ገልፀዋል። የዚህ ጥናት መነሻ የሕዝቦች ጥያቄ ራስን በራስ ማስተዳደር ያለው ፍላጎት ምክንያትና ቀጣዮችን ዘመናት በየትኛው መንግስት ስር በመሆን መተዳደር እንደሚፈልጉ ለማወቅ የተደረገ ነው።
በጥናቱ ከደቡብ ክልል መንግስት ስር ቢቆዩ ምን ይጠቀማሉ፤ ምንስ ይጎዳሉ ደግሞም የራስን ክልል በመመስረት ምን ይጠቀማሉ ምንስ ይጎዳሉ የሚሉ ጥያቄዎችን ጭምር ያካተተ ነው። ጥናቱ ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ተሳትፎን ያማከለ ነበር። የጥናቱ ውጤት እንደሚያሳየው በጥናቱ ይሳተፋሉ ተብሎ ከሚጠበቀው 3567 ተሳታፊዎች መሃከል 98 በመቶ ምላሽ ሰጥቷል።
አብዛኞቹ ጥናቱ የተካሄደባቸው አካባቢዎች ራሳቸውን በራስ ማስተዳደር ፍላጎት ያሳዩ ሲሆን፤ የተወሰኑ አካባቢዎች በደኢህዴንና በደቡብ ክልል ስር ለመተዳደር ፍላጎታቸውን ገልፀዋል። የራስ ክልል አስተዳደር ለመመስረት ፍላጎት ያሳዩ አካባቢዎች በዋናነት በደኢህዴን መራሹ ደቡብ ክልል መንግስት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት መጓደልና የመልካም አስተዳደር ጉድለትና የዴሞክራሲ ግንባታ ክፍተት አካባቢያቸውን በክፉ እንደጎዳባቸው ገልፀዋል። በተጨማሪ ታሪክ ባህልና ቋንቋ ለማሳደግና ያለሌላ የፖለቲካ ዕርከን ተፅዕኖ ከፌደራል መንግስት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ለመፍጠር እንደሚያስችላቸው ጭምር አረጋግጠዋል። ጥናቱ የሚያሳየው ከሌሎች ሀገሮች ማለትም ከሕንድ፤ ናይጄሪያና አሜሪካ መሰል ሀገሮች በፌደራል መንግስት የሚተዳደሩ ብዙ ግዛቶች አንፃር አዳዲስ በሚጨመሩ ክልሎች ምክንያት ለፌደራል መንግስት አባል የሚሆኑ ክልሎች ቁጥር ያነሰ መሆኑን ያሳያል። የጥናቱ ውጤት ከአገሪቷ ሕገ መንግስት ጋር የሚጣጣም መሆኑን ገለልተኛ አጥኚ ቡድኑ አረጋግጧል።
በተቃራኒ በጥናቱ ላይ የደቡብ ክልል እንዲቀጥል የሚፈልጉ አካባቢዎች መኖሩን አጥኚዎቹ የደቡብ ክልል መንግስት እንዳይፈርስና እንዲቀጥል የሚፈልጉ በክልሉ ብሎም በአካባቢያቸው ከፍተኛ ልማት እና የሥልጣን ክፍፍል በብዛት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጧል።
በተጨማሪ ብቻቸውን ክልል መመስረት ብዙ ለውጥ አያመጣም የሚያምኑ እንዳሉ ሁሉ ይበልጥ በደቡብ ክልል ወደፊት እንጠቀማለን የሚል አመለካከት ያላቸው መሆኑ ተረጋግጧል።
በሌላ በኩል ጥናቱ ሁሉንም አካባቢዎችን ያላካተተ መሆኑን ጭምር ገለልተኛ አጥኚዎቹ አረጋግጠዋል።
አሁን የራስን ክልል መንግስት መመስረት ለሚፈልጉ በሕገ-መንግስቱ መሰረት ብቻ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ ነው በአጥኚዎቹ የተገለፀው።
ነገር ግን በተለይ ከደቡብ ክልል ጋር አብሮ ለመቆየት በሚፈልጉ አካባቢዎች ወደፊት ተጨማሪ ጥናቶች እንዲካሄዱ አጥኚዎቹ ጠቁመዋል።
የፍኖተ ካርታ ጉዳይ
በ2012 የትምህርት ዘመን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፍሬሽማን መርሃ-ግብር ሊጀመር መሆኑ የተነገረው በያዝነው ነሐሴ ወር ነው። በተካሄደው የስርዓተ-ትምህርት ክለሳ መሰረት በ2012 የትምህርት ዘመን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመጀመሪያ ዓመት (የፍሬሽማን) መርሃ-ግብር ሊጀመር መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም እንዳሉት በመጀመሪያው ዓመት የሚሰጡት ኮርሶች በተማሪዎች ዘንድ የሚስተዋሉትን ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ለመቅረፍ ያስችላሉ። ኮርሶቹም 15 መሆናቸውን ፕሮፌሰር ሂሩት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎች ሲስፋፉ የትኩረት መስኮችን ከመለየት ይልቅ አጠቃላይ ዩኒቨርሲቲዎች እየሆኑ ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ የልህቀት ማዕከልነትን ለማጎልበት ይሰራል ብለዋል።
ይህ የፍኖተ ካርታ ጉዳይ ከተነገረ በኋላ አማርኛ ቋንቋ እንደግዴታ ውሰዱ ተብለናል በሚል በአንዳንድ ክልሎች ቅሬታ መነሳቱም የሚታወስ ነው።
የኑሮ ውድነት ጫና መባባሱ
2011 የዋጋ ንረት አልቀመስ ብሏል። ይህን ያህል በመቶ ደርሷል፣ አድጓል፣ ወርዷል ከሚሉ ስሌቶች ይልቅ የሰው ኑሮ ብዙ ይናገራል። የሸቀጦች ዋጋ ንረት ሰዎች በተለይ በወርሀዊ ደመወዛቸው ሊኖሩ የማይችሉበት ደረጃ አድርሷቸዋል። የአንድ ኪሎ ሥጋ ዋጋ በአዲስ አበባ ከ 400 ብር ከፍ ብሏል። የሌሎችም ሸቀጦች ዋጋ ንረት መክፋቱ ሰዎች በቂና ተመጣጣኝ ምግብ ቀርቶ የተገኘውን መቅመስ እንዳይችሉ እያደረገ ነው።፡
ከምንም በላይ ደግሞ የዋጋ ንረቱ ሕዝብን ለከፋ ድህነት በሚጋለጡ ማህበራዊ ትስስሩ እንዲላላ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ስለመሆኑ የዘርፉ ምሁራን የሚናገሩት ጉዳይ ነው። እንኳንስ ራቅ ያለን ቀርቶ በቅርብ ካለ ወዳጅ ዘመድ ጋር ለመጠያየቅ ወጪን መፍራት ተጀምሮአል። ማህበራዊ መሰረትን በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና ያላቸው ሰርግ፣ ክርስትና…ደግሶ ሰውን ማብላት አልተቻለም። ጥሪው እንኳን ቢኖር ከአቅም ማነስ ጋር ተያይዞ ሰዎች ለመገኘት የማይችሉበት ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑ የሚያሳስባቸው ወገኖች አሉ።
ለማንኛውም ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴም ከሞላ ጎደል ዓመቱን ገምግሟል። የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ግንቦት ስምንት ቀን 2011 ዓም ባካሄደው ስብሰባ ባለፈው አንድ ዓመት የለውጥ ጉዞ ውስጥ የተከናወኑ የብሔራዊ ደህንነት ስኬታማ ስራዎችን እንዲሁም እያጋጠሙ ያሉትን ተግዳሮቶችን መገምገሙ ተሰምቷል።
ባለፈው አንድ ዓመት በአጠቃላይ በጸጥታው ዘርፍ ጠንካራ ስራዎች ቢከናወኑም በርካታ ተግዳሮቶች እያጋጠሙ መሆናቸው ኮሚቴው ገምግሟል። ተግዳሮቶቹ በዋነኛነት ከጽንፈኛ ብሔርተኝነት፣ ከኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ወይም ደቦዎች፤ ከህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር እንዲሁም ከማህበራዊ ሚዲያ ሀሰተኛ ዜናዎች ተጽዕኖ ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ተመልክቷል። እነዚህ ተግዳሮቶች ለዜጎች ሞት፣ መፈናቀልና የደህንነት ስጋት ምክንያት መሆናቸውንም አስምሮበታል።
ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ በጥልቀት ከተወያየ በኋላ ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል። በዚህም ብሔራዊ ደህንነትን ማረጋገጥና የህግ የበላይነትን ማስከበር የመንግስት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆናቸውን አፅንኦት በመስጠት የዜጎችን የሰላም ዋስትና የሚያረጋግጡ ስራዎች ላይ መረባረብ ይገባል ብሏል።
እንደመሰናበቻ
መጪው አዲስ ዓመት 2012 ዓ.ም 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሚካሄድበት አመት ነው። አዲሱ ዓመት ሠላማዊ ነጻና በሕዝብ ዘንድ ተአማኒ የሆነ ምርጫ የምናካሂድበት፣ ከአካባቢያዊ ቀውስ የምንወጣበት፣ አለመግባባቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ የምንፈታበት፣ የዋጋ ግሽበት የሚረጋጋበት፣ ሠላምና ፍቅርና ብልጽግና የሚናኝበት ዓመት እንዲሆንልን እመኛለሁ።
ይህ ዓምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ አስተያየታቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሑፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሀሴ 29/2011
ፍሬው አበበ