አዎን ስለአገራዊ ሰላማችን ሲባል ሁላችንም “ለምን?” እንበል።
ብዙዎቻችን “ከእጅ ያለ ወርቅ…” ሆኖብን ነጋ ጠባ አገራዊ ሰላማችንን ሊያሳጣን የሚችል የክፋት ጠጠር በየፊናችን እንወረውራለን። አውቀንም ይሁን ሳናውቅ። ሳናውቅ ላደረግነውና ለምናደርገው የማወቅ ቀናችንን ዛሬ አድርገን ከእኩይ ድርጊታችን ለመታቀብ ጊዜው አልረፈደብንም። ከመጣነው የጥፋት መንገድ ይልቅ የምንሄደው የሰላም መንገድ ይበልጣልና ለሰላማችን ዘብ እንቁም።
አሁን ላይ ትልቁ ችግር አውቆ፣ አስልቶና ጊዜና ቦታ ጠብቆ የሚያጠፋው ነው። ብሂሉም “አውቆ የተኛን…” እንዲል ባለሁለት አገሮችና ባለሁለት አጀንዳዎች የአገራችንን ሰላም ከእጃችን ሊነጥቁን ጠዋት ማታ ሲሯሯጡ ይታያሉ። እነዚህ ከሰላም ፈላጊው ህዝብ ቁጥር አንጻር ኢምንት የሆኑ ግለሰቦችንና ቡድኖችን አይተን እንዳላያን የምናልፈው ግን እልፍ አዕላፍ ነን። ብዙዎች በጥቂቶች አጀንዳ ተወስደናል። አውቀንም ሳናውቅም አይተን እንዳላየን የምናልፈው እኩይ ተግባር በዝቷል።
ለምን?
አዎን! ስለ አገራችን ሰላም ሲባል ለምን ብለን ልንጠይቅ ይገባናል።
ለምን ማለት ምክንያታዊነት ነው። እንደ አለመታደል ሆኖ ግን የአገራችን ሰላም ነቀዞች “ለምን” የሚለውን ጥያቄ አብዝተው ይጠሉታል፤ ይሸሹታልም። ለምን የሚላቸውን ግለሰብም ይሁን ቡድን አንዳች ስያሜ በመስጠት ያውግዙታል፤ ያስወግዙታል። ባስ ሲልም ደብዛውን ያጠፉታል።
የእያንዳንዳችንም ሆነ የአገራችን ሰላምን በእጃችን ነው። ይሄንን እውነት እውነት ነው ካልን የሚወረወርልንን አጀንዳ ሁሉ እንዳለ ከመቀበልና ከመቀባበል ልንታቀብ ይገባናል። ለዚህ ደግሞ መድኃኒቱ “ለምን” ብሎ መጠየቅ ነውና ለምን ባዮች እንሁን። ለምን ማለታችን ሰለማችንን ያጠናክርልናል፤ አገራችንንም ያሰነብትልናልና።
ከለውጡ ወዲህ በአገራችን ያገኘነውን ቱሩፋት ካጣነው ስንመዝነው በብዙ መልኩ ያገኘነው ይልቃል። ነገር ግን ልናጣው እየተንደረደርን ያለንበት መንገድ ያሳስበናል። ሁሉም አዋቂ፤ ሁሉም እኔ ትክክል ነኝ ባይ፤ ሁሉም ቦታና ሁሉም አጀንዳ ላይ ትክክል እንደሆነ አድርጎ ይሰብካል፤ ያሰብካል። መደማመጥ ብዙ ርቆናል። የጎዳና እና የማህበራዊ ድረ ገጽ ዎችና አጀንዳና አጀንዳዎች በጊዜ ወደ አዳራሽ ካልገቡ ኢትዮጵያ እንደ ሶሪያ እና የመን የምትሆንበት እድል ሰፊ ነው። ይህንን አገር እና ህዝብ የማይመጥን አጀንዳ እና አንጃዎች ከመካከላችን ሰርገው ገብተዋል። እነዚህን
እኩያን ነቅሶ ማውጣት የመንግስት ስራ ብቻ አድርገን እንመልከት። መንግስት የሚባለው አካል ሁሉን የሚያውቅ አራት አይና አድርገንም መመልከት የለብንም። ለራሳችን ሰላም ያለነው ራሳችን ነን በሚል ስሜት የጋራ አገራችንን በጋራ እንጠብቅ።
ከፊት ሆነው በዚህ ሂዱ፤ በዚያ አትሂዱ፤ ይህንን ያዙ፤ ያንን ልቀቁ የሚሉንን ሁሉ ነብይ አድርገን አንመልከት። አገራዊ መንገዳችን “ያለፈውን ክፉ ክፉ ረስተን በጎ በጎውን ይዘን በመደመር ወደፊት እንጓዝ፤ ወደብልጽግና እንሻገር” ከሆነ አንድ አመት አልፎናል። ይሁን እንጂ ቀን ቀን ተደማሪ ማታ ማታ ጉድጓድ ቆፋሪ በሆኑ ግለሰቦች እና ቡድኖች አማካኝነት ወደማንፈልገው ምናልባትም ወደማንወጣበት ችግር ለመግባት እየተንደረደርን ነን።
መንግስት ይህን ችግር አስቀድሞ በመረዳት ሚኒስቴር መስሪያቤት በማቋቋም ጭምር ስለሰላም እየሰራ ይገኛል። ይህ ለአገራችንም ለአለምም አዲስ የሆነ ተቋም የተፈጠረው ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት መሆኑን መንግስት ስለተረዳ ነው ብለን እናምናለን። ነገር ግን ይህ በራሱ ወይንም ብቻውን አገራዊ ሰላማችንን ያረጋግጣል፤ ያስጠብቃል ማለት የዋህነት ነው። ስለሆነም የአገራችንን ሰላም መጠበቅ ማስጠበቅ የሰላም ሚኒስቴር ጉዳይ ብቻ አድርገን መመልከት የለብንም። የአገራችን ሰላም በእያንዳንዳችን እጅ ውስጥ መሆኑን መረዳት አለብን።
አገራዊ ልብ ኖሮን ልብ ካልን በአገራችን መዲና አውራ ጎዳናዎች ላይ ፈስሰው የምንመለከታቸው የሶሪያ ስደተኞች ብዙ ያስተምሩናል። ትናንት ለሰው አገር ዜጎች ይተርፉ የነበሩ ሶሪያዊያን እንደ ቀልድ ከእጃቸው በወጣው ሰላም ሳቢያ ዛሬ ራሳቸው ስደተኛ ራሳቸው ተመጽዋች ሆነው እየተመለከትናቸው ነው። ከዚህ ተምረንና ሰላማችን በእጃን መሆኑን ተረድተን የሚጠበቅብን ማድረግ ካልቻልን እኛም ነገ በሱዳን፣ በኬንያ አሊያም በሌላ አገሮች ጎዳናዎች ላይ “አገር ነበረን…” በሚል ለምጽዋት ላለመፍሰሳችን ምንም ዋስትና የለንም።
ተወደደም ተጠላም የሰላም እጦት የመጨረሻው እውነታ ይሄ ነው። ሁሉም ወገን ዙሪያ ገባውን መመልከትና ነቅቶ መጠበቅ አለበት። ህዝብ ለሚቀርብለት በማር የተለወሰ አጀንዳ ሁሉ እጁን መዘርጋትም የለበትም። ሁሉም ለሁሉም ጥያቄና ግብዣ ሳይታክት ለምን ይበል። ለምን ማለት ምክንያታዊነት ነው። ሁለት አገርና ሁለት ዜግነት ያላቸው አንድ አንድ ጸረ ሰላም ሀይሎች ነጋ ጠባ የሚያቀርቡትን የ”ተነስ ዝም አትበል” ጥያቄና “አጀንዳችንን ፈጽም” ውትወታ እንዳለ ተቀብሎ ከመፈጸም በፊት “ለምን” እንበል። “ለምን” ማለት የምንወዳት አገራችን ሰላም ማጽኛ አንዱ መንገድ ነው ብለንም እንመን። ነውናም።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 28/2011