ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ካስመዘገበቻቸው ዘርፈብዙ ስኬቶች ውስጥ አንዱ በትምህርት ዘርፉ የተገኘው እድገት ነው፡፡ በተለይ የትምህርት ተደራሽነትን ለማሳደግ በተከናወኑ ስራዎች በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በርካታ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ የተማሪዎች ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል፡፡
ከዚህ አንጻር 4 ሺህ የነበሩትን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቁጥር ወደ 39 ሺህ፣ 278 የነበሩትን የሁለተኛ ደረጃ ትምህር ቤቶች ቁጥር ወደ 3300 እንዲሁም ከ2 ሚሊዮን ያልበለጡ ተማሪዎችን ቁጥር ከ28 ሚሊዮን በላይ ማድረስ ተችሏል፡፡ የቴክኒክና ሙያ ትምህርና ስልጠና ተቋማትንም ቁጥር ከ16 ወደ 1546፣ 2 የነበሩትን የመንግስት ዩኒቨርሲዎች ቁጥር ወደ 46 ማሳደግ ተችሏል፤ እንዲሁም 178 የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ተፈጥረዋል፡፡
ያም ሆኖ ግን በክልሎች መካከል ያለው የአፈጻጸም ልዩነት መኖርና ፍትሐዊነቱ የሰፋ መሆኑ፣ ደረጃውን የጠበቀ ሥርዓተ-ትምህርት አለመኖር፣ ከአለም አቀፍ(ዩኒስኮ ስታንዳርድ) እና ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች አንጻር ሲታይ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆኑ፣ በየደረጃው ያለው አመራርም የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ በእውቀትና በቅንጅት መምራት አለመቻሉ የዘርፉ ዋነኛ ችግሮች እንደሆኑ ተለይቷል፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት (1ኛ-8ኛ ክፍል) ፕሮግራም ፍትሐዊነትን ሙሉ በሙሉ ያላረጋገጠ ፕሮግራም መሆኑ፣ አሁንም ቢሆን ከትምህርት ገበታ ውጪ ያሉ ሕጻናት መኖር፣ በአንዳንድ ክልሎች የተሣትፎው ሁኔታ ወደ ኋላ የመመለስ አደጋ መኖር፣ በጾታ መካከል የተሳትፎ ልዩነት አሁንም መኖሩ፣ ልዩ ፍላጐት ያላቸው ሕጻናት ተገቢውን አገልግሎት አለማግኘት፣ ከብቃት አኳያ መጠነ ማቋረጡ አደጋ መሆኑ አሁንም በዘርፉ ያልተፈቱ ችግሮች ናቸው፡፡
በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፍም የተደራሽነት ችግር መኖር፣ ከኢንዱስትሪው ፍላጐት ጋር ያልተሳሰረ የሙያ ደረጃ ምደባ መኖሩ፣ ኢንዱስትሪው በእምነት ያልተቀበለው የትብብር ስልጠና እና ባለቤት ያልሆነበት የብቃት ምዘና መካሄድ፣ የሥልጠና ጥራትን ማረጋገጥ ያልቻለ የአሠልጣኝ ምልመላና ዝግጅት መኖር፣ በበቂ እውቀት ላይ ያልተመሠረት የቴክኖሎጂ ሽግግር ፣ ቅንጅት የጐደለው የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት፣ በተለያዩ ችግሮች የተወሳሰበ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና አደረጃጀትና አመራር ዘርፉን ቀይደው የያዙ ማነቆዎች ናቸው፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም የጥራት ተደራሽነት ችግሮች ያሉባቸው ናቸው፡፡ በመሆኑም እነዚህን ችግሮች መፍታት በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታትና ደረጃውን የጠበቀ የትምህርትና ስልጠና ፕሮግራምን ለመገንባት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ እነሆ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል፡፡
ይህ የፍኖተ ካርታ ዝግጅት በዋናነት በዘርፉ በሚገኙ አንጋፋ ባለሙያዎች የተመራ ሲሆን ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል ተቋማትና የስራ ኃላፊዎችም ግብዓት የሰጡበት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ጥናቱ የተካሄደው በ36 ተመራማሪዎች፣ በ73 ተባባሪ ተመራማሪዎችና በ11 የትምህርት ቢሮ አስተባባሪዎች ሲሆን የትምህርትና ሥልጠና ሴክተር አመራሮችና ባለሙያዎች፣ የክልል ትምህርት ተቋማት፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ አባገዳዎች፣ ወላጆች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የመገናኛ ብዙኃን እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮችም ጋርም በተዘጋጁ የጋራ መድረኮች ሰፋፊ ግብዓት ተሰብስቦበታል፡፡
ፍኖተ ካርታው በመልካም እሴቶች የታነፁ፤ መልካም ሥነ-ምግባርና ብቃት ያላቸው ኢትዮጵያውያንን ማፍራት፤ ከሀገሪቱ የትምህርትና ሥልጠና ፍልስፍ እና ከተማሪውና ከማህበረሰቡ ፍላጐት ጋር የተጣጣመ ስርዓተ ትምህርት መፍጠር፣ ሣይንስና ቴክኖሎጂን ማስፋፋትና ማጠናከር፤ ትምህርትና ሥልጠና ከችሎታ፣ ከፍላጐት እና ከአቅም ጋር በማጣጣም አካታችና ፍትሐዊ እንዲሆን ማድረግ፣ የመምህራን ብቃትና ተነሳሽነት በማጐልበት መምህርነት ተመራጭ የሙያ መስክ እንዲሆን ማድረግ፤ ትምህርት ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ ትምህርት ቤቶችን እንዲሁም ከፍተኛ የትምህርትና ሥልጠና ተቋማትን አቅም ማጐልበት እና ተጠያቂነትን የተላበሰ ጠንካራ ሀገር አቀፍ የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ማረጋገጫ ሥርዓት የመዘርጋት ዓላማን ያነገበ ነው፡፡
አገራችን አሁን ካለችበት የድህነት አዘቅት ወጥታ የበለፀገችና ለዜጎቿ ምቹ የመኖሪያ ስፍራ እንድትሆን የተማረ የሰው ኃይል ወሳኝ ነው፡፡ ይህ ኃይል ደግሞ የሚፈለገውን ግብ እንዲመታ ጥራት ያለው ሊሆን ይገባል። በተለይ አሁን ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ እያደረገ ከመጣው የቴክኖለጂ እድገትና ስልጣኔ ጋር አብሮ የሚጓዝ ትውልድን መፍጠር ካልተቻለ ተወዳዳሪ መሆን አዳጋች ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ለትምህርትና ስልጠና ዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ወቅቱ የሚጠይቀው መሰረታዊ ጥያቄ ነው፡፡
በመሆኑም በአገራችን በሚገኙ ከፍተኛ የዘርፉ ምሁራን የሌሎች አገራት ተሞክሮን ከግንዛቤ በማስገባት የተዘጋጀው የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ለዘርፉ እድገት የሚያበረክተው አስተዋፅኦ የላቀ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ሁሉም ባለድርሻ አካል ሊረባረብ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 27/2011